የኢየሱስ ሞት ከፍተኛ ዋጋ አለው
የአዳም ሞት ምንም ዋጋ አልነበረውም። ለሠራው ኃጢአት መሞት ይገባው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሞተው ኃጢአት ሳይኖርበት በመሆኑ የእርሱ ሞት ከፍተኛ ዋጋ አለው። ስለዚህ ይሖዋ አምላክ ታዛዥ ለሆነው ለኃጢአተኛው የአዳም ዘር ቤዛ ሆኖ የተከፈለው የኢየሱስ ፍጹም ሕይወት ያለውን ዋጋ መቀበል ይችላል። እንዲሁም የኢየሱስ መሥዋዕት ዋጋ ላለፉ ኃጢአቶች ይቅርታ በማስገኘት ብቻ የተወሰነ አይደለም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ምንም ዓይነት የወደፊት ተስፋ አይኖረንም ነበር። በኃጢአት የተወለድን በመሆናችን እንደገና ኃጢአት መሥራታችን አይቀርም። (መዝሙር 51:5) የኢየሱስ ሞት ይሖዋ አምላክ በመጀመሪያ ለአዳምና ለሔዋን ልጆች አስቦት ወደነበረው ፍጽምና የመድረስ አጋጣሚ ስለሚሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል!
አዳም ፈጽሞ ልንከፍለው በማንችለው ከፍተኛ ዕዳ (ኃጢአት) ውስጥ ከትቶን ከሞተ አባት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በሌላው በኩል ግን ኢየሱስ፣ ከተዘፈቅንበት ዕዳ ነፃ የሚያወጣንን ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ለመኖር የሚያስችለንን በቂ ሃብት አውርሶን እንደሞተ አባት ነው። የኢየሱስ ሞት ያለፈ ኃጢአታችንን የሚያስተሰርይ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ሕይወታችን የተደረገ አስደናቂ ዝግጅት ጭምር ነው።
ኢየሱስ ለእኛ ብሎ የሞተ በመሆኑ ያድነናል። የኢየሱስ ሞት ምንኛ ዋጋ ያለው ዝግጅት ነው! ይህ ዝግጅት የአዳም ኃጢአት ያስከተለውን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት አምላክ ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አድርገን ከተመለከትነው በይሖዋና ነገሮችን በሚያከናውንባቸው መንገዶች ላይ ያለን እምነት ይጠነክራል። አዎን፣ የኢየሱስ ሞት “በእርሱ የሚያምን ሁሉ” ከኃጢአት፣ ከህመም፣ ከእርጅና እና ከሞት ጭምር መዳን የሚችልበትን አጋጣሚ ከፍቷል። (ዮሐንስ 3:16) አምላክ እኛን ለማዳን እንዲህ ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት በማድረጉ አመስጋኝ አይደለህም?