በጤናው ዘርፍ ረዘም ላለ ጊዜ ስሠራ አንዳንድ በጣም የተጨነቁ ታካሚዎች የምርመራ ውጤታቸው ምን እንደ ሆነ ሲጠይቁኝና ውጤታቸውም normal ሲሆን ከጭንቀታቸው እንዲላቀቁና ዘና እንዲሉ "ጤና በዝቶቦታል" እላቸዋለሁ። የእኔ ምርመራም አብዛኛውና ዋና ዋናው ጉዳይ እንዲያ የሚያስብል ነበር። ግን... አንድ ሕመም አለብህ ተባልኩ። ደነገጥሁ።
ከፊት ለፊቴ ተቀምጣ ከምታወራኝ ሐኪም ጋር እያወራሁ ሁለት ነገሮችን በጥልቀትና በመረበሽ አስብ ጀመር። የመጀመሪያው ሞት ነበር። በዚህ ጥልቀት ስለ ሞት አስቤ አላውቅም። ለካስ እሞታለሁ! ይህን እውነት ባውቅም በዚያች ቅጽበት እንደ ተሰማኝ ሆኖ አስቤው አላውቅም። ታሞ የማያውቅ ሰው ሆኜ ለትንሿ ነገር ደነበርሁ። የሐኪሟ አነጋገር እኔ ካለሁበት ሁኔታ አንጻር እንክብካቤን የተሞላ እንዳልሆነ በራሴ ሚዛን መዝኜ አዘንሁባት። ታዘብኳት!
ደግሞ ሌላ ትዝብት... ለካስ በሐኪም ቤት ውስጥ ሰው ታሞ ሲመጣ ከዚህ ዓይነት ስሜት ጋር ነው። ለእኛ ሆስፒታሉ የሥራ ቦታችን ነው። የምንውልበትም እንደ ሥራ ቦታችን ነው። ለታካሚው ግን ጤናውን የሚሻበት፣ የሚታከምበት፣ የሚፈወስበትም ነው። የታመመ ሰው ለካ የሚያክመውን ሐኪም፣ የጤና ባለሙያን ብቻ ሳይሆን ከሜዲካል ሳይንሱ በላይም የሚያጽናናውን ወዳጅም ይፈልጋል። ለካስ የጤና ባለሙያ የሚዳብስ ወዳጅም መሆን ይገባዋል። እንዲህማ ከሆነ ለንስሐ አባቴ የምነግረው ገና ብዙ በደል አለብኝ። ይህ ሙያ ለእኔ ከባድ በመሆኑም ብዙ እንደማልገፋበትም ማሰብ ጀመርኩ።
ደግሞ እንደ ገና ራሴን ታዘብኩ። ድንጋጤዬን "ሞት ወደ ላይኛው ዓለም የምንሻገርበት ድልድይ ነው" ብዬ በተደጋጋሚ ከመስበኬ ጋር አነጻጽሬ ራሴን ታዘብኩ። "አበው ራሳቸውን የሚጎሽሙበት በሽታን እንዲሰጣቸው ይጸልያሉ፤ ፈጣሪ ጤናን ብቻ ሳይሆን በሽታንም በመስጠት ይጎበኛል" ብዬም አስተምሬ ነበር ለካ! እንዲህ መርበድበዴን አንድ ከሥሬ የተማረ ምእመን ቢያይ ምን ይል ይሆን? እኔን ብሎ መምህር! (በርግጥ እንዲህ ብለው ሲጠሩኝ ሁሌም ይከብደኛል)። ለካስ ሲናገሩትና ሲኖሩት አንድ አይደለም። (ታሞ የማያውቅ ሰው ችግር ነው፤ ለሚያልፍ ነገር እንዲህ መረበሽ። እግዚኦ!)
ወደ አእምሮዬ የመጣው ሌላኛው አሳብ ደግሞ "የጀመርኳቸውን እነዚያን ሁሉ ሥራዎች ማን ሊጨርሳቸው ነው? ሞት ሊቀድመኝ?" አልኩ። በቅድሚያ ያሰብኩት መጽሐፎቼን ነው። የመጨረሻ መጽሐፌ አውግስጢኖስ ከታተመ 6 ዓመት ሊሞላው ነው። ከዓመታት በፊት የተጀመሩ የተወሰኑ ወጥና የትርጉም ሥራዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ ለመገባደድ ከጫፍ ደርሰው የተተዉ፣ አንዳንዶቹ የተጋመሱ፣ አንዳንዶቹ የተጀመሩ፣ የተቀሩት ደግሞ ቅድመ ዝግጅታቸው ተጠናቆ መጻፍ ብቻ የሚቀራቸው ነበሩ።
(ምናልባት ይህች አጋጣሚ እነዚህ የዘነጋኋቸውን ሥራዎች እንዳስታውስ መልአኩን ልኮ ጎኔን የጎሸመባት ትሆናለች)
የዘኆኅተ ብርሃን ሚዲያን ስናስጀምር በሥሩ ያሉትን አገልጋዮች ሁልጊዜም "እንደሚሞት ሰው ሥሩ" እላቸው ነበር። እኔም በዚህች ቀን ሞቱ እንደ ተቆረጠለት ሰው መፍጠን እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ። ከሥራና ከሌሎች አገልግሎቶች (በተለይም ከዘኆኅተ ብርሃን ሚዲያ) በሚተርፈኝ ጊዜ እነዚህ ሥራዎች ላይ አተኮርኩ።
(በነገራችን ላይ የሕመሙን ጉዳይ ለመንደርደሪያነት አነሣሁ እንጂ አሁን ጤና በጤና ነኝ - ለነገሩ ያኔም ሕመም አለብህ አሉኝ እንጂ እኔ አልታመምሁም ነበርኮ)
ያሰብኳቸውን ወጥ ሥራዎች ከመሥራቴ በፊት እጄ ላይ ያሉት ጅምሮች ማለቅ እንዳለባቸው ተሰማኝ። በቅድሚያ የተመለስኩበት ሥራ መምህር ገብረ እግዚአብሔር ኪደን የመሰሉ ወዳጆች "ከምን ደረሰ?" እያሉ ዘወትር ከሚያስታውሱት ሥራ ነው። የሴባስቲያን ብሮክ - የቅዱስ ኤፍሬም - Luminous Eye - ብርህት ዓይን።
፩- ብርህት ዓይን
ይህችን የትርጉም ሥራ ያጋመስሁት የዛሬ 5 ዓመት ነበር። ሕንዳዊው የቲዎሎጂ የዶግማ መምህራችን ፋዘር ጆሲ ጄኮብ ይህን መጽሐፍ እንተረጉም ዘንድ ደራሲው መፍቀዱን ከነገረኝ በኋላ ዘግይቼ ብጀምረውም ካጋመስኩት ኋላ ግን ትቼው ነበር። የቅዱሱ ሊቅ ወዳጆችና ሥራው መጀመሩን የሚያውቁት ጥቂቶች "ከምን ደረሰ" ሲሉኝ እያፈርኩ መለስ እልበትና መልሼ እተወው ነበር። ይኸው አሁን እርሱ ፈቅዶ ከእጄ ሊወጣ ነው መሰል!
ዛሬ - የካቲት 3 የቅዱስ ኤፍሬም በዓል ነው። በዚህች ዕለት መጽሐፏ ኅትመቷን ጨርሳ ከእጃችሁ ባትገባም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በዐቢይ ጾም ውስጥ እንድትደርስ የሚቻለንን እያደረግን ነው። ስለ መጽሐፉ በበቂ ሁኔታ ስለ ተነገረ ብዙ አልልበትም። ብቻ ሴባስቲያን ብሮክ ለቅዱስ ኤፍሬም እንዳደረገው ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስም እንዲህ ዓይነቱን ሥራ የሚሠራላቸውን "አንድ ሴባስትያን ብሮክን ቢያስነሣላቸው" ብዬ የምመኝበት ዓይነት ግሩም ሥራ ነው።
ጥቂት እርማት ተደርጎባትና ሴባስትያን ብሮክን የማናገር ሥራችንን እንደ ጨረስን ወደ ኅትመት ትገባለች።
፪- ወደ ሙስሊሞች የተላኩ መልእክታት
ይህኛውም እግዚአብሔር ከረዳኝ ከዐቢይ ጾም አይዘልም። ወደ መገባደዱ ነው። በውስጡ ሁለት መልእክታትና አንድ ደግሞ የታሪክ ማስረጃዎች (historical apologetics) ስብስብን የያዘ ነው። ይህም ተጋምሶ ለዓመታት ቢቆይም በመጨረሻ የኅትመት ፀሐይን ሊያይ የቀረበ ነው። ያድርሰን!
፫- ሦስተኛው የሦስት ሰዎችን ታሪክ የያዘ ነው። የአንዱን ብቻ ለመናገር ያህል ይህችን ልበል:- በግርድፉ የዛሬ ስድስት ወይም ሰባት ዓመት አካባቢ አለርት ሆስፒታል ውስጥ እየሠራሁ አንድ አባት ቢሮዬ ድረስ መጡ። ብሩክ ሰለሞን ይባላሉ (በነገራችን ላይ አሁን ያሉበትን ለሚጠቁመኝና ለሚያገናኘኝ ምስጋናዬ ከልብ ነው)። የሚኖሩት በስዊዘርላንድ ሲሆን ለአጭር ጊዜ ዕረፍት ሲመጡ ፈልገው እንዳገኙኝ ነገሩኝ። ያን ጊዜ አጫጭር ጽሑፎችን አዘውትሬ እየጻፍኩ የተለያዩ የቫይበር ግሩፖች ላይ ለጥፍ ነበር። እነዚያን ጽሑፎች እርሳቸው እየወሰዱ በስዊዘርላንድና በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ውስጥ ላሉ ግሩፖች ይልኩ እንደ ነበርና በዚያ እንደሚያውቁኝ ነገሩኝ።
ማርቲን ፍላድ የተባሉ ለ60 ዓመታት በኢትዮጵያ የኖሩ አንድ ሰው ነበሩ። በፈረንሳይኛ የተጻፈ የኢትዮጵያ ቆይታቸውን የተመለከተ ግለ ታሪካቸውን ወደ አማርኛ እንድመልሰው ፈልገው ነበር። ግለ-ታሪኩ ያልታተመና ተጽፎ በረቂቅነት የተቀመጠ ነበር። ፈረንሳይኛን ከሰላምታና ከትውውቅ በሚያሻግር ሁኔታ እንደማልችል ብነግራቸውም ኃላፊነቱን ወስጄና በተለያዩ አካላት ታግዤ ራሴ እንድሠራው ተማጸኑኝ። በጎዶሎ ልቤ ተማጽኗቸውን ተቀበልኩ።
(በነገራችን ላይ የማርቲን ፍላድ ታሪክ ከጊዜያት በኋላ ወደ እንግሊዝኛ ተመልሶ በአማዞን የግብይት መድረክ ላይ አይቼዋለሁ። ዋጋው ግን አይቀመስም፤ ከ1ሺህ ዶላር ያልፋል።)