- ሀሩን ሚዲያ፣ ጥር 14/2017
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአፋር ክልል በርዕደ መሬት የተጓዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን ገልጿል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት እንዲሁም ከውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጣ ቡድን ይህን ያለው በአፋር ክልል በርዕደ መሬት የተጎዱ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ መመልከቱን ተከትሎ ነው።
የምክር ቤቱ አባላቱ ከሰብአዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ የመጠለያ፣ የምግብና ውሃ አቅርቦት እንዲሁም የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከተመለከቱ በኋላ፤ በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች አመላክተዋል ተብሏል።
ለዜጎች የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትና በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራር ለጉዳዮ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የቡድኑ አባላት ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ ጉዳቱ ቅፅበታዊ ድርጊት ቢሆንም በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በአፋር ክልል በተደጋጋሚ እየተከሰተ ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ58 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወቃል።
© ሀሩን ሚዲያ