******
ህዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛ ትምህርትና ስልጠና ባሻገር የፖሊስ አመራርና አባላት ሙያው የሚጠይቀውን የፖሊስ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በረጅም ጊዜ እና በአጫጭር ስልጠናዎች የፖሊስ ሰራዊቱን አቅም የሚያሳድጉ ስልጠናዎችን በመስጠት የተሰጠውን ታላቅ ሀላፊነት በብቃት እየተወጣ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በአፖስቶ ካምፓስ የሚያሰለጥናቸውን የ25ኛ ዙር መደበኛ ሰርተፊኬት ዕጩ መኮንኖች የሪኩሪቲ ጊዚያቸውን ጨርሰው በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በስነ-ምግባር የትክሻ ማዕረግ (ስትራይፕ) ለመልበስ የሚያስችለውን መስፈርት ለአሟሉ ሰልጣኞች በዛሬው ዕለት የትክሻ ማዕረግ (ስትራይፕ) የማልበስ ፕሮግራም ተከናውኗል።
በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት የስራ መመሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ም/ፕሬዝዳንት ረ/ኮሚሽነር ተሻለ ሚቆሬ ዕጩ መኮንኖቹ ከስልጠናው ባሻገር በልማት ስራ ያከናወኗቸውን ስራዎች ተዘዋውረው በመጎብኘት በዚህ የአጭር ጊዜ ቆይታችሁ የሰራችሁት ስራ በናንተ ውስጥ ሰባዊነትን፣ ሙያዊ ብቃትና ምልዑነትን ያየንበት ስራ መሰራቱን ያየንበተት ነው ብለዋል።
አያይዘውም በዚህ የስልጠና ቆይታችሁ ማዕረግ ብቻ ሳይሆን ለማዕረጉ የሚመጥን እውቀት ይዛቹህ መውጣት ይገባል ሲሉ ለዕጩ መኮንኖቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሌላ በኩል የስልጠና ሪፖርት ያቀረቡት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአፖስቶ ካምፓስ ተወካይ ሀላፊ ረ/ኮሚሽነር ካሳሁን ተስፋዬ በአፖስቶ ካምፓስ 925 ዕጩ መኮንኖች በስልጠና ላይ እንደሚገኙ ገልጸው የተቀመጠውን መስፈርት ያሟሉ 920 ዕጩ መኮንኖች የትክሻ ማዕረግ ለመልበስ እንደደረሱ ተናግረዋል።