የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office @eotcpatriarichate Channel on Telegram

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

@eotcpatriarichate


የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office (Amharic)

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የሚለው ቡና በበሽታዋ አዳዲስ ተሳትፎ እና አስተያየቶችን በእርስዋ ስልክ እንዳለ ይፈልጋል። ይህ ባለስራ አስፈላጊ ሪፖርት ነው ውስጥ በየቦታው ምን ለመጠን ይረዳል። በቡናዋ ከተጠቓሚነት፣ ከክንፉ፣ ከመከላከያው እና ከሌሎች አካል የሚሆኑ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት አማርኛ እና የቋንቋ ሀገር ይገኛል። ከፍተኛ ውይይት እና ሀሳብ ምን ለመድላት እንደሆነ የቡናቋን በብዛት ይመልከቱ።

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

06 Feb, 16:44


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ መግለጫ
ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው፡፡

ጥር 29ቀን 2017ዓ.ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተላለፈ የምህላ ሱባዔ፡-
‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ አስተጋብኡ ሕዝበ ሊቃውንተ ሕዝብ፤ ጾምን ቀድሱ፣ጉባኤውንም አውጁ፤ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ኣምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ (ኢዩ ፩÷፲፬)
    ሁላችንም እንደምናውቀው ያለንበት ዓለም የመከራ ዓለም ነው፣ መከራው በኛ ስሕተትና ክፋት የመጣና እየሆነ ያለ መሆኑም ይታወቃል፤ እኛ የምንፈጽመው ጥቃቅንና ትላልቅ ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን እንደሚያስቈጣ በቅዱስ መጽሐፍ ተረጋግጦ ያደረ ነው፤ ለዚህም ከነነዌ ነዋሪ ሕዝብ የበለጠ ማስረጃ የለንም፤ የነነዌ ከተማ ነዋሪዎች በፈጸሙት ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን አስቈጥተዋል፤ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ ቢሆንም እሱ ምሕረቱን ማስቀደም ስለፈለገ በዮናስ በኩል አስጠንቅቆአቸዋል፤ የነነዌ ነዋሪዎችም በዮናስ በኩል የደረሳቸውን የንስሓ ጥሪ ወዲያውኑ ተቀብለው በምህላ፣ በጾም፣ በጸሎት ንስሓ ስለገቡ እግዚአብሔር ፍጹም ይቅርታ አድርጎላቸዋል፤
•  የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን !
እኛ ሰዎች ዛሬም በየሰዓቱ ብቻ ሳይሆን በየደቂቃው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ አበሳ እንደምንፈጽም ማወቅ ኣለብን፣ አበሳውና ኃጢኣቱ ሲበዛ እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነውና ወደ ዳኝነት ተግባሩ ይገባል፤ይህ ደግሞ በሰብአ ትካት በሰዶምና በጎሞራ ያስተላለፈውን ዳኝነት ያስታውሰናል፤ አሁን ያለንበት ዘመን ዓመተ ምሕረት በመሆኑ እግዚአብሔር ለጊዜው ቢታገሠንም በኃጢኣታችን የምንጠየቅበት ጊዜ አዘጋጅቶአል፤ ዛሬም ቢሆን የማናስተውለው ሆነን ካልሆነ በስተቀር እግዚአብሔር ተግሣጹን ማስተላለፍ አላቆምም፤ በምድራችን ላይ በምናደርሰው የተዛባ ተግባር በጐርፍ፣ በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በአየር መዛባት እየገሠጸን እንደሆነ ማስተዋል አለብን፤
እግዚአብሔር ከጥንቱ ከጠዋቱ ጀምሮ ምድርን እንድንከባከባት፤ እንድናበጃት፣ እንድናጠብቃትና እንድናለማት አዞናል፤ ሆኖም ይህን ትእዛዙን ገሸሽ አድርገን በኬሜካልና በመርዛም ጋዝ ምድርን በመበከል፣ደንዋን በመመጠርና ራቁቷን በማስቀረት በምናደርገው ድርጊት አበሳ እየፈጸምን እንደሆነ ያወቅነው አይመስልም፤ በዚህም ምክንያት በጐርፍ፣ በድርቅ ለሰው ልጆች በማይመች የኣየር ፀባይ ወዘተ . . . ስጋት ውስጥ እየወደቅን ነው፤

   በሌላም በኩል በምናወሳስበው የአስተዳደር ርእዮትና መሳሳብ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭና ያላስፈላጊ አደጋ ላይ እንድወድቅ እያደረግን ነው፤ በዚህም ጠንቅ ሰላም እየደፈረሰ፣ ፍቅርና አንድነት እየላላ የሃይማኖት ክብርና ልዕልና እየተነካ ራሳችንንም እየጐዳን ነው፤በዚህ ሁሉ ተግባራችን  እግዚአብሔርን እያሳዘንን ነው፤ ይህ ሊገባንና ሊቈረቁረን ይገባል፤
  የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ አላቸው፤ መፍትሔውም የሚገኘው ከእግዚአብሔርና ከእኛ ነው፤ ከእኛ በንስሓ ተመልሰን ከልብ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅና ከክፉ ተግባራችን በእውነት መጸጸት ይጠበቃል፤ እግዚአብሔር ደግሞ ይህንን ዓይነቱ ንስሓ ከኛ መኖሩ ሲመለከት ምሕረትና ይቅርታን ይለግሰናል፤በዚህም መፍትሔና ፈውስ ይገኛል፤ ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ ለሀገራችንና ለዓለማችን ስጋት የሆኑ የጦርነት ክሥተቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የአየር መዛባት፣የድርቅ መከሠት፣የጎርፍ መጥለቅለቅ የሰላም መደፍረስ፣ የሰላማውያን ወገኖች መጎዳት፣ የፍቅርና የአንድነት መላላት ወዘተ. . . . ከምድራችን ተወግደው ፍጹም ምሕረትና ሰላም እናገኝ ዘንድ በኃጢኣታችን ተጸጽተን በምህላ ንስሓ መግባት አለብን፤ ከዚህ አኳያ ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ የሚጾመው ጾመ ነነዌ ለዚህ አመቺ ጊዜ ስለሆነ ከየካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ  ለሦስት ቀናት ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ሁላችንም ጠዋትና ማታ በየቤተክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት እየተገኘን በንስሓ በዕንባ በጸሎት በምህላ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ እንድንጠይቅ፤ እንደዚሁም በሀገራችንና በውጭ ያላችሁ ሊቃውንተ ሕዝብ ቀኖናውን ጠብቃችሁ ይህንን በማስፈጸም ምህላውን በቀኖናው መሠረት እንድታከናውኑ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን ይቅርታውንና ሰላሙን ለሀገራችንና ለዓለማችን ይስጠን፤ ምህላችንንም ይቀበልልን፤
   “እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

01 Feb, 12:03


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የግብፅ  ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ልዑካንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ጥር 24 ቀን 2017.ዓ.ም.
=================
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በብፁዕ አቡነ አምባ ቢመን  የሚመራውን የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ልዑካንን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል ።ልዑካኑ  ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ  የተላከ የሰላምታ መልእክት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በማቅርብ  በሁለቱ ተቋማት መካከል  የነበረውን የጋራ ትብብር በማጠነከር ላይ ውይይት አድርጓል። እንደ ልዑካኑ ገለጻ ከዚህ በፊት በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የሚገኙ የጋራ የመገልገያ ሥፍራዎችን  በጋራ መጠቀም የሚያስችል አንድነት  የነበረን በመሆኑ አሁንም የተለመደውን ሥራ ማለትም  የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  በምትገኝበት  ቦታ ሁሉ የኮፕቲክ ቤተክርስቲያን  እንድትገለገል የኮፕትክ ቤተክርስቲያን ባለችበት ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  መገልገል እንድትችል የሚያስችል ሁኔታን ማስቀጠል ነው ብለዋል ። 
ልዑካኑን በጽሕፈት ቤታቸው ያነጋገሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ይዘውት የመጡት ሐሳብ የነበረና በመገልገያ ሥፍራ በማጣት የሚቸገሩ ምእመናን  የሚታደግ ሐሳብ ነውና በአድናቆትና በደስታ   ተቀብለነው እየተገበርነው ያለ ቢሆንም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስም ይህንን የሰላም መልእክተኛ እና በሁለቱም ተቋማት ውስጥ የሚገለገሉ ምእመናን ችግርን የፈታ ሐሳብ በልዑካኑ በኩል የማጠናከሪያ ሐሳብ እንድንሰጥበት ስላደረጉ እናመሰግናለን ብለዋል።
በመቀጠልም ልዑካኑ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ  የግብፅ ኮፕቲክ  ፓትርያርክ የተላከውን ስጦታ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ያስረከቡ ሲሆን ቅዱስነታቸውም  ስለ ስጦታው አመስገነዋል። በመጨረሻም ልዑካኑ ስለተደረገላቸው መልካም አቀባበልና ይሁንታ መደሰታቸውን ገልጸው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በኢትዮጵያውያን ምእመናን ትከሻ ተሠርቶ ማለቁ እጅግ ደስ እንዳሰኛቸው በመግለጽ የግብጽ ኮፕቲክ እንደተለመደው በካቴድራሉ መገልገል የሚችሉበት  መንገድ ስለ ተመቻቸላቸው አመስገነው የውይይቱ ፍጻሜ ሆኗል።

©የ/ኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

29 Jan, 16:03


የአስተርእዮ ማርያም በዓለ ንግሥ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም  በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ተከበረ ።
        
በየዓመቱ ጥር 21 ቀን በከፍተኛ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚከበረውን የአስተርእዮ ማርያም  በዓለ ንግሥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ የመምሪያ ኃላፊዎች ፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሽህ የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት ዛሬ ጥር 21 ቀን 2017 ዓ,ም በመንበረ  ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በድምቀት ተከብሯል።
ታቦተ ሕጉን  ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሥርዓተ ዑደት ተደርጓል፣ በገዳሙ ሊቃውንትና ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት  ወረብ ቀርቧል ፣ 

በመጨረሻም  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሰፊ ትምህርት፣ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ተሰጥቷል፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ቅዳሴ ከተከናወነ በኋላ
የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል ።

++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2.  ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

19 Jan, 11:49


ስለሆነም የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆናችን ልዩ ምልክታችን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የፍትሕና የእኩልነት ሰዎች ሆነን እንድንገኝ ነውና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያላችሁ ልጆቻችን ሁሉ በሃይማኖት ጸንታችሁ ለሰላምና ለአንድነት ከምንጊዜውም በላይ የበኩላችሁን ጥረት ታደርጉ ዘንድ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

በዓለ ጥምቀቱን የሰላምና የበረከት ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣

ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2. ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

19 Jan, 11:49


#መልእክተ_ቅዱስ_ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
ክቡራን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣
ክቡራን አምባሳደሮችና የኮር ዲፕሎማቶች፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣
በአጠቃላይ በቅርብና በሩቅ ሆናችሁ የ2017 ዓ.ም በዓለ ጥምቀት እያከበራችሁ የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያኖች በሙሉ፣
በመጠመቁ የክዋኔ ልጅነቱን አስመስክሮ የጸጋ ልጆች እንድንሆን ያበቃንን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓመት ምሕረት የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

ወመጽአ ቃለ እግዚአብሔር ኀበ ዮሓንስ ወልደ ዘካርያስ፤የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሓንስ መጣ (ሉቃ ፩÷፪፤)
የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ሆኖ እንዲያገለግል በእግዚአብሔር ዘንድ ከዘመናት በፊት የተመረጠው ዮሓንስ ወልደ ዘካርያስ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነበር፤ ቅዱስ ዮሓንስ በዮርዳኖስ በረሃ በብሕትውና ሕይወት በነበረበት ወቅት የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ፤ ወደ እርሱ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፣ዓዘቅቱ ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን ፤ሸካራውም መንገድ ይስተካከል፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ››፤

መጥምቁ ዮሓንስ ይህንን የድኅነት መልእክት ከእግዚአብሔር የመጣለት በገዳመ ዮርዳኖስ ባሉ ከተሞች እያስተማረና ሕዝቡን ለንስሐ እያዘጋጀ በነበረበት ጊዜ ነው፤ የትምህርቱ ዋና ይዘትም የጌታ መንገድ የሰው አእምሮ መሆኑን በማስገንዘብ ጌታ በዚህ መንገድ እንዲጓዝበትና እንዲመላለስበት በደንብ ይዘጋጅ የሚል ነው፤

የዝግጅቱም ሁናቴ በዝርዝር ሲገለጽ ተስፋ በመቁረጥ እንደ ዓዘቅት የጐደጐደውና የጨቀየው አእምሮ በተስፋ ድኂን ቀና ይበል፤
በሥልጣን፣ በዕውቀት፣በሀብትና በወገን ከሁሉ የላቀ እንደሆነ የሚያስብም እንደማንኛውም ሰው መሆኑን ተረድቶ እኩልነትን ተቀብሎና ኣክብሮ ይኑር፤ በክፋትና በምቀኝነት፣ በተንኮልና በሴራ አተርፋለሁ የሚል ጠማማ አእምሮም ወደ ቅን አስተሳሰብ ይመለስ፤ በቂም፣ በበቀልና በጥላቻ ተዘፍቆ የሚኖር ልብም በሰላም በፍቅርና በስምምነት ወደሚገኝ የተስተካከለ ጣዕመ ሕይወት ይግባ ማለት እንደ ሆነ እናስተውላለን፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!

እግዚአብሔር ምድርና ሰማየ ሰማያት የማይችሉት ምሉእ፤ረቂቅና ስፉሕ ነው፤

ይሁን እንጂ በቅዱሳን ሰዎች አእምሮ ውስጥ ማደርና ማረፍ በእጅጉ የሚሻ አምላክ እንደሆነ ደጋግሞ ገልጾአል፤መመላለሻውም በሰው ኅሊና፣ በሰው ልቡና እና አእምሮ ውስጥ እንደሆነ አልሸሸገም፤ያም በመሆኑ መንገዱና ጥርጊያው የሆነ የእኛ አእምሮ ቀጥ ያለና ይማይጐረብጥ እንዲሆንለት ያዘናል፤

መጥምቁ ዮሓንስም ይህ ዓይነቱ ዝግጅት በሰው አእምሮ ውስጥ እንዲኖር ለመቀስቀስ ተልኮአል፤
ዝግጅቱ የጠቅላላ ስራው መቋጫ አልነበረም፤ የዝግጅቱ ዋና መቋጫ ሰው ሁሉ እንደ ስምዖን የእግዚአብሔርን ማዳን በዓይኑ አይቶ በአእምሮው አስልቶ በልቡ ኣምኖ የድኅነቱ ባለቤት መሆን ሲችል ነው፤ የእግዚአብሔር ፈቃድና ፍላጎትም ይኸው ነው፤ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኛን ሰውነት በመዋሐድ አምላክና ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም እንዲገለጥ ያስፈለገበት ዓቢይ ምክንያትም ይኸው ነው፤ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ዕለት በፈለገ ዮርዳኖስ የፈጸመው ምስጢረ ጥምቀት ሰው የሚያድንበት ዕድል ምን እንደሆነ ለማስረዳት ነው፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!

ሰው በራሱ ዘላቂ ሕይወት የለውም፤ የሕይወት ምንጭ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ሰው ዘላቂ ሕይወትን ማግኘት የሚችለው የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነት ሲኖረውና በግንኙነቱ አማካኝነት ዘላዓለማዊ ሕይወት ከእግዚአብሔር ሲቀዳጅ ነው፤ ይህንንም ልዩ ግንኙነት የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ሲወለድ ነው፤ ለመወለድ ደግሞ በእግዚአብሔር የማዳን ስራ ማመንና መጠመቅ ሲቻል ነው፤ ሰው ሲጠመቅ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፤
እግዚአብሔርም በልጁ አእምሮ ውስጥ በሃይማኖት በአምልኮና በምስጋና ይመላለሳል፤ ያድራል፤ ያርፋልም፤ ሥጋ የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ የተባለውም ይህንን ልጅነት ነው፤

በዚህ ልጅነት ምክንያት ሰው የዘላለም ሕይወት ባለቤት ሆኖ ይኖራል፤ ጥምቀት ለሰው ልጆች የሚያስገኝልን ጸጋ ይኸው ነው፤

ታዲያ የእግዚአብሔር የዝግጅት ጥሪ ዘላዓለማዊ ሕይወትን ለማደል ሆኖ ሳለ የተጠበቀው ዝግጅት ግን ከሰው እየታየ ኣይደለም፤

ዛሬም እኛ ሰዎች አእምሮችን ጐድጓዳ ዓዘቅት ሆኖ በመቀጠሉ ለጉዞ አልተመቸውም፤
ዛሬም ልባችን ከተራራና ኮረብታ ባልተናነሰ ሁናቴ ትዕቢት እንደተሞላ ነው፤ ከቅንነት ይልቅ ጠማማነት፤ ከእውነት ይልቅ ማሴር የየዕለት ተግባር አድርገነዋል፤

በዚህም እግዚአብሔር ከኛ እንዲርቅ አድርገናል እሱም በኣጸፋው ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጥቶናል፤ ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ ያላት ምስል ይኸው ነው፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!

ዓለማችን አሁን ያለችበት ምስል ለሰው ልጅ ሁሉ በጣም አሳሳቢና አስፈሪ ነው፤ ለእግዚአብሔር አልታዘዝም ብሎ በነውረ ኃጢአት መጋለብና ለጦርነትና ለዕልቂት የሚሆን መሳሪያ በማምረት መሽቀዳደም የሚበጅ አይደለም፤

ከዚህ ይልቅ ዓለማችን አሁንም ቆም ብላ ብታስብና ሕይወት ወደ ሆነው እግዚአብሔር እንድትመለስ በእግዚአብሔር ስም እንመክራለን ፤

በሰው ልጆች የሚታይ መሠረታዊ ችግር ከእግዚአብሔር መለየትና ለእሱ ያለመታዘዝ እንጂ የሀብት ዕጥረት አይደለም፤

ምድሪቱ ኁልቈ መሥፈርት የሌለው ሀብት በውስጥም በውጭም አጭቃ ይዛለች፤ እሱን በፍቅርና በስምምነት ብናለማው ከበቂ በላይ ነው፤

እሱም ቀርቶ ያለውን ለጦርነትና ለዕልቂት ከምናውለው ለልማት ብናውለው ችግርና እጦት ከምድራችን በጠፋ ነበር፤

አሁንም ራሳችንን በራሳችን ከማጥፋት ተቆጥበን የምድራችንን የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሥነ ምኅዳር በመጠበቅ ግጭትንና ጦርነትን በማስቆም ለተመደበልን ሰላማዊ ሕይወት ልንተጋ ይገባል፣

በመጨረሻም

በዓለ ጥምቀቱ ከእግዚአብሔር የምንወለድበትን ዕድል የከፈተ ነው፤ በዚህም ዕድል የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን በቅተናል፤

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

10 Jan, 14:04


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ 
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት  ወቅታዊ  ጉዳዮችን አስመልክተው  አባታዊ የሰላም ጥሪ አስተላለፉ።
ጥር 02 ቀን 2017 ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ ኢትዮጵያ 


++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2.  ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

06 Jan, 10:10


መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
•በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
•ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
•የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
•በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
•እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፤
በምሉእ ፍቅሩ ሰውን ከባርነት ወደ ነጻነት ለመመለስ በሥጋ ሰብእ የተወለደው ጌታችን  ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓመተ ምሕረት የልደት በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ለዘሠምሮ ለሰብእ፤ ክብር በሰማያት ለእግዚአብሔር ይሁን›› በምድርም እጅግ ለወደደው የሰው ልጅ ሰላም ይሁን” (ሉቃ ፪÷፲፬)
ይህ ቃለ ሰላም በጌታችን ዕለተ ልደት የተነገረ ነው፣ ቃሉ የተነገረው እንዲሁ እንደ ተራ ነገር ሳይሆን በቃለ መዝሙር እየተደጋገመ ነው፡፡ የተዘመረውም በምድራውያን ደራሲዎች ሳይሆን በሰማያውያን መላእክተ እግዚአብሔር ነው፣ የያዘው መልእክትም ሰማያውያንና ምድራውያንን ሁሉ ያካለለ ነው፡፡ የመልእክቱ ገዢ ሓሳብም አምላክ ከሰውነታችን ጋር ባለመለያየት፣ ባለመጠፋፋት፣ ባለመቀላቀል፣ ባለመዋዋጥ፣ ባለመለዋወጥና ያለባዕድና አንድ አካል፣ አንድ ክዋኔ፣ አንድ ጠባይ ሆኖ በተዋሕዶ ተገልጾኣልና እግዚአብሔር ይክብር ይመስገን፡፡ የተዋሕዶውም ምስጢር ሰላምን ያሰፍናልና እግዚአብሔር ሰውን በእጅጉ መውደዱ ከዚህ ተዋሕዶ ዓውቀናል የሚል ነው፡፡

በእርግጥም እግዚአብሔር ሰውን ለመውደዱ ከዚህ የበለጠ ማሳያ ወይም ማስረጃ የለም፤ እንከን የለሽ ንጹህ አምላክ የእኛን ኃጢአተኛ ሰውነት አካሉ አድርጎ ተወለደ ሲባል ላስተዋለው ሰው ምንኛ ቢወደን ነው የሚለው ጥልቅ አድናቆትን ያጭራልና ነው፡፡ይህ ብቻም አይደለም በዚህ ነገረ ተዋሕዶ ምክንያት ሰውነታችን አምላክ ሆኖ በመንበረ ጸባኦት እንዲቀመጥ መብቃቱ የድኅነታችንና የክብራችን ከፍታ ምን ያህል አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደደረሰ መንፈሳችን በአንክሮ ይረዳዋል፡፡ድምር ውጤቱም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ፍጹምና አስተማማኝ ሰላም መፈጠሩን ያስረዳናል፤ ሰማያውያኑ መላእክተ እግዚአብሔር በመዝሙራቸው ያበሰሩን ይህንን የምስራች ነው፡፡

•የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ እግዚአብሔር በእጅጉ ይወደናል ስንል እንዲሁ ከሜዳ ተነሥተን ኣይደለም፡፡ በበደላችንና በኃጢአታችን ሳይጸየፈን ሰውነታችንን በረድኤት ወይም በኅድረት ያይደለ በኩነት ተዋሕዶ ወደ አምላክነት ደረጃ ከፍ ስላደረገው  ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ፍጹምና ምሉእ ፍቅሩ ሰውነታችንን በመበረ ጸባኦት ኣስቀምጦ መላእክት ሳይቀሩ ፍጥረታትን በሙሉ እንድንገዛ አድርጎናል፤ ምክንያቱም መላእክት በዕለተ ልደት የዘመሩለት በተዋሕዶ አምላክም ሰውም ለሆነ ለቤተ ልሔሙ ሕፃን እንጂ ለመለኮት ብቻ ኣይደለምና ነው፡፡ የዕለተ ልደት መዝሙር ዛሬም በሰማያትም ሆነ በምድር በተዋሕዶ ሰውም ኣምላክም የሆነ አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመለክበታል፣ ይመሰገንበታል፡፡የሰማዩና የምድሩ ዕርቅ ወደ ኋላ ላይመለስ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ተከናውኖኣል፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሰውም አዋጭ ምርጫ ይህ ዕርቅ ተጠብቆ እንዲኖር ነው፣ ያለ ዕርቅ ሰላም ሕይወት የለውምና፡፡

•የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የእግዚአብሔር ክብርና ሰላም በእጅጉ የተሳሰሩና የተቆራኙ ናቸው፤ እኛ እግዚአብሔርን ካከበርነው፣ ካዳመጥነው፣ ከታዘዝነውና ከተከተልነው ሰላም አለ ማለት ነው፡፡ ለሱ ካልታዘዝንና እሱን ካላከበርን ግን ዘላቂ ሰላምን ማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፤ ምክንያቱም ሰላምን ጨምሮ መልካም ነገር ሁሉ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነውና፡፡ ዛሬ በሁሉም የዓለማችን ማዕዘን የሚታየው የሰላም መደፍረስ እግዚአብሔርን ካለማክበራችንና ለሱ ካለመታዘዛችን የተነሣ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ዓለም ከእግዚአብሔር ቃል ርቃ ለመሄድ በእጅጉ እየኳተነች ነው፤ በዚህ እኩይ ተግባርዋ ደግሞ እግዚአብሔር ለስጋትና ለጉስቁልና አሳልፎ እየሰጣት ነው፡፡ እግዚአብሔር በምስጢረ ሥጋዌው ቢታረቃትም ዕርቁን ማክበር አቅቶአታል፤ ይህንን የእግዚአብሔር ጸጋ ቸል ብላ የምታደርገው ሩጫ የትም ሊያደርሳት እንደማይችል ብታውቅና በንስሓ ብትመለስ እግጅ ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡
•የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
የእግዚአብሔር ቃል “እናንተስ ከማይጠፋ ዘር ተወለዳችሁ” ብሎ ተስፋውን እንደነገረን ምድባችን ከማይጠፋ ዘር እንዲሆን ክርስቲያኖች የሆን ሁላችን በአእምሮ ጐልብተን፣ በሥነ-ምግባር ኣምረን፣ ጤናማ ሕይወትን ልንመራ ይገባናል፡፡

የአምላካችንን በዓለ ልደት ስናከብር ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ፍቅርን፣ ነገረ ዕርቅንና ነገረ ሰላምን በማኅበረሰባችን የማሥረጽ አጀንዳ ይዘን ልናከብር ይገባል፡፡
ጠቡ ፣ ጥላቻው፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ለወንድሜ  ከማለት ይልቅ ለኔ ለኔ ማለቱ ሲጎዳን እንጂ ሲጠቅመን ኣላየንም፡፡ አሁንም ወደ ልባችን እንመለስና በፍቅር፣ በዕርቅና በእኩልነት፣ በስምምነትና በወንድምነት ወደሚገኝ አንድነት እንምጣ፤ የልደቱ መዝሙር ያስተማረን ይህና ይህ ብቻ ነውና፡፡ በሌሎቹ ክፍለ ዓለማት እንደሆነው ሁሉ በሀገራችን የተከሠተው አላስፈላጊ ግጭት ብዙዎችን አሳጥቶናል፤ ብዙዎችንም ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ሜዳ ላይ ፈሰው የሰቆቃ ኑሮ እንዲገፉ አድርጎብናል፡፡ የሀገር ሀብት እንዲወድም ሆኖአል፤ ልጆቻችን ምናለ ከእንግዲህ ወዲህ ቢበቃንና ምድሪቱን የሰላም አየር እንድትተነፍስ ብንፈቅድላት፤ ይህ የወቅቱ የቤተክርስቲያናችን ዋነኛ መልእክትና ጥሪ ነው፡፡    
                         በመጨረሻም፡-
በዓለ ልደት የእግዚአብሔር በዓል ነውና፣ እግዚአብሔር በምድራችን ሰላምን ያወርድ ዘንድ ካለን ከፍለን ለተፈናቃዮች፣ ለነዳያን እና ለአካል ጉዳተኞች በመለገስ በዓሉን በመንፈሳዊ ደስታና በሰላም እንድናከብር አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፤
መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር  አሜን!

  አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ


++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2.  ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

31 Dec, 09:47


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር የ2025 አዲስ ዓመትን በማስመለክት ለመላው የዓለም ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።

ቅዱስነታቸው ለመላው የዓለም ማኅበረሰብእ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት የአማርኛ ትርጉም ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ለመላው የዓለም ሕዝብ የተላለፈ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ 
አባታዊ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
‹‹ወሰላም በምድር ለዕጓለ እመሕያው ሥምረቱ:-
ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ ።” ሉቃ. 2፡14

ከሁሉ በማስቀደም በመላው ዓለም ለምትገኙ፤ የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ላከበራችሁና አዲሱን ዓመት 2025 ዓ.ም. ለምትቀበሉ ልጆቻችን የመልካም ምኞታችንን ለመግለጽ እንወዳለን ። 

ዘመን ከቊጥር ያለፈ ትርጉም ያለው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ በዘመን ውስጥ ያጣነውን እናገኛለን ፣ ያገኘነውን እንመልሳለን ። በዘመን ውስጥ ሕፃናት ሲጠነክሩ ፣ ሽማግሌዎች ይደክማሉ ። አንዱ ዘመን ላንዱ ልደት ለሌላው ሞት ሆኖ ይውላል ። እግዚአብሔር አምላካችን ከጊዜ ውጭ ቢሆንም እኛን በጊዜ ሰሌዳ ውስጥ አስቀምጦናል ። ዘመን ሳያደክመው በዘመን ውስጥ በሚለዋወጥ ማንነት እንድናልፍ ተሠርተናል ። ከጠዋት እስከ ማታ ያለው ሂደት ከልደት እስከ ሞት ያለውን ረጅም ጉዞ የሚገልጥ ነው ። በየቀኑ ዕለቱን ብቻ ሳይሆን መላው ዘመናችንን እንኖራለን ። የሰው ልጅ በዚህ ዓለም በጊዜ የተለካ በሚመጣው ዓለም ከጊዜ ውጭ የሚኖር ፍጡር ነው ። በሚሞት ሥጋ የማይሞት ነፍስን ተሸክሟል፣ በሚያልፍ ጊዜም የማያልፍ ዘለዓለማዊነትን ይጠባበቃል ። በታሪክ ውስጥ ከፍታና ዝቅታ ቢፈራረቁም ፣ ሥልጣኔዎች መጥተው ቢሄዱም ፣ አንዱ ፍልስፍና ሌላውን ቢሽረውም የዘመናት መፈራረቅ ግን ቋሚ ሕግ ሁኖ ይኖራል ። የሰው ልጆች ከመከራ ቀናት የተነሣ መኖራቸውን የሚጠሉበት ጊዜ ቢገጥምም አዲስ ዓመትን መናፈቃቸው መኖርን እንደሚፈልጉ ማሳያ ነው ። ትልቅ የምስጋና ርእስ ቢኖር እርሱም አዲስ ዘመንን ማየት ነው ። አሮጌነትን እየተውን አዲስን ዓመት የምንቀበለው ፣ ያለፈውን አሮጌ ብለን ይህን አዲስ የምንለው በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ መሆንን ስለምንፈልግ ነው ። 


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ የዓለምን ታሪክ ለሁለት ከፍሎታል ። ከክርስቶስ ልደት በፊትና ከክርስቶስ ልደት በኋላ እየተባለም ይጠራል ። በሃይማኖታችንም ዓመተ ፍዳና ዓመተ ምሕረት ተብሎ ለሁለት ይከፈላል ። ዓለምን ለመለወጥ ብዙዎች ወደ ዓለም መጥተዋል ። ጌታችን ግን የሰውን ሕይወት ለመለወጥ ወደ ዓለም መጥቷል ። አሁን ያለነው በጌታ ዓመት ፣ በምሕረት ዘመን ነው ። ፍርድ በሙሉነት መፈጸሙ ለዓለም ሰላም ወሳኝ ቢሆንም ምሕረት ግን እውነተኛውን የልብ ሰላም ታመጣለች ። ከእኛ ወደሚያንሱት የምናደርገው ጉዞ ፣ ራስ ወዳድነትን አሸንፈን ሌሎችን ለመርዳት የምንከፍለው መሥዋዕትነት ዓለምን የሚለውጥ ነው። ከተሞቻችን በማያቋርጥ ዕድገት ውስጥ ላያልፉ ይችላሉ ። ዕድገትም የሚቆምበት ጊዜ አለ። የሰው ልጅ የሞራል ከፍታ ግን መቆሚያ የለውምና አዲሱ ዘመን ክፉ ተግባር የሚወገድበት፤ መልካም ተግባራት የሚከናወኑበት ሊሆን ይገባዋል ። 
የተወደዳችሁ የዓለም ሕዝቦች! 
ያለፈው ዓመት 2024 ዓ.ም. እንደ ዓለም ብዙ ነገሮችን ብናተርፍም የከሰርንበትም ጭምር ነው ። ከተፈጥሮ አደጋዎች ይልቅ ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች ዓለምን እስር ቤት ውስጥ ቆልፈንባት ይታያል ። ሲጀመር በቀናት ውስጥ የሚያበቃ ይመስል የነበረው የራሽያና የዩክሬን ጦርነት ዓመታትን እያስቆጠረ ነው ። በመላው ዓለምም ለኑሮ ውድነትና ጫና ምክንያት ሆኗል ። ከሁሉ በላይ ሁለቱ ኦርቶዶክሳውያን ሕዝቦች የሰላም ረሀብተኛ ሆነዋል ። መካከለኛው ምሥራቅም በየዕለቱ በሚሰፋ ጦርነት ተውጦ ይታያል ። የዓለም የስበት ማዕከል በመሆኑም ብዙ ጫናዎችን እያሳደረ ይገኛል ። ስልጣኔው ይዞት የመጣው የግለኝነት ኑሮ ለብዙ የሰው ልጆች በጭንቀት ውስጥ ማለፍ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ። መፍትሔን ከመፈለግ፣ እሳትን ከማጥፋት ይልቅ ችግሮችን የሚያባብሱ ነገሮች የዓለማችን መገለጫ ሆነዋል። ለይስሙላ የሚደረጉ የሰላም ስብሰባዎችም ተናግረን ነበር ለማለት ካልሆነ በቀር ቁርጥ ውሳኔ ያላቸው አይደሉም ። 
ምድራችን ሰላምን በጣም ተርባለች ። እንስሳትና አራዊት ያለምርጫቸው በመከራ ውስጥ እያለፉ ነው ። የዓለማችን ብርቅዬ እንግዶች የሆኑት ሕፃናት እየታወኩ ነው ። ራሳቸውን መከላከል ያልቻሉ ሴቶች ልጆቻችን በፍርሃት ውስጥ አሁንም አሉ ። ይህች ዓለም አስተማሪ ቅጣት እንደሚያድናት ስታምን ብትኖርም አሁን ግን አስተማሪ ምሕረት እንደሚያስፈልጋት ግልጽ እየሆነ ይመስላል ። ስለዚህ በዚህ የልደተ ክርስቶስ መታሰቢያና የ2025 ዓ.ም. መቀበያ ላይ ቆመን ይቅር መባባል፣ ለጋራ ቤታችን መሥራትና በሰዎች አለመግባባት የታወከችውን ዓለም በሰዎች ቁርጥ ውሳኔ እንድትረጋጋ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል ።

በመጨረሻም አዲሱን ዓመት እየተቀበላችሁ ያላችሁ፤ አዲሱን ዓመት ከክርስቶስ ልደት ጋር አብራችሁ የምታከብሩ ወገኖቻችን ልደተ ክርስቶስ ትሕትና የተገለጠበት ነውና በትሑት ሰብእና ቆማችሁ የነደደውን እሳት እንድታጠፉ፤ ጦርነትን በሰላም ለመለወጥ የራሳችሁን ድርሻ እንድትወጡ ስንል አባታዊ የተማኅጽኖ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡ 

እግዚአብሔር አምላክ መላውን ዓለም በሰላም ይጠብቅልን፤
ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥር 1 ቀን 2025 G.C.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

29 Dec, 12:37


#ብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ማትያስ_ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አባቶች ጋር ለቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የነበራቸውን አገልግሎት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ በሰላም ተመልሰዋል ።

የቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ከሁላችን ጋር ይሁን !

++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2. ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

26 Dec, 15:05


ቅዱስ ፓትርያርኩ በድሬዳዋ  ገብረ
መንክራት ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን
የተሰራውን ሁለገብ ሕንጻ መረቁ።
******

ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻፲ ወ፯ ዓ.ም
*****
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የድሬዳዋ ገብረ መንክራት ቅዱስ ዑራኤል ወባዕታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ያሰራውን ሁለ ገብ ሕጻ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ከጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች ጋር በመሆን መረቁ።

በቤተክርስቲያኑ ቅጽረ ጊቢ የተገነባው ሕንጻ ባሁለት ወለል ሲሆን ለሁለገብ  አገልግሎት እንዲውል ታስቦና ሙሉ ወጪውም በዲያቆን ኢንጂነር መላኩ ተስፋዬ ተሸፍኖ የተሰራ መሆኑ በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የድሬዳዋ ሐዋርያዊ ጉዞ በነገውም ዕለት የሚቀጥል ይሆናል ።


++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2.  ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

26 Dec, 09:38


በቡፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራየኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንየልዑካን ቡድን
ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
+++++++++++++++++++++++++++++++++++

ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
""""""""""""""""""""""
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚመራ ፲ የልዑካን ቡድን ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓል ለማክበር ፣በበዓሉ ላይ ለሚገኙ ምዕመናንን ትምህርተ ወንጌል፣ቃለ በምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ለመስጠት ዛሬ ማለዳ ድሬዳዋ ገብተዋል።

የልዑካን ቡድኑም፦
1- ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የዳውሮ ኮንታ ከንባታ ሐላባና ጠምባሮ አህጉረ ስብከት ጳጳስ
2- ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የኢትዮ ሶማሌ ጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
3- ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ጳጳስ
4- ክቡር ንቡረእድ ኤልያስ አብርሃ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ መንፈሳዊ ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ
5-መ/ሕ ቆሞስ አባ ኃይለገብርኤል ነጋሽ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ኀላፊ
6- መ/ካ ዕንቈባሕርይ ተከስተ የመ/ፓጠ/ቤ/ክ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኀላፊ
7- መ/ር አካለወልድ ተሰማ (ደ/ር) የመ/ፓጠ/ቤ/ክ አስተዳደር መምሪያ ኀላፊ
8- ሊ/ስ እስክንድር ገ/ክርስቶስ የመ/ፓጠ/ቤ/ክ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኀላፊ
9-ሊቀ ነብያት ሙሴ ኀይሉ የቅዱስ ፓትርያርኩ ፕሮቶኮል ተጠሪእና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተጉዘዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ እና የልዑካን ቡድኑ ድሬዳዋ አውሮፕላን
ማረፊያ ሲደርሱ በብፁዕ አቡነ በርተሎሚዎስ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በአቶ ከድር ጁዋርና በካቢኔ አባለቱ፣ በሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ በካህናትና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለቅዱስነታቸውና ለልዑካን ቡድኑ ደማቅ አቀባበል ያደረጉለት የድሬዳዋ ከንቲባ አቶ ከድር ጅዋር በክብር ዘብ፣በፖሊስ የማርሽ ቡድንና በፈረሰኛ የታጀበ ደማቅና የክብር አቀባበል አድርጎላቸዋል።

++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2. ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

04 Nov, 13:42


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት #የሰላም_ሚኒስቴር ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ መልእክት አስተላለፉ።

የቅዱስነታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፦

#ቃለ_በረከት_ዘብፁዕ_ወቅዱስ_ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ክቡር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም
የኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር፤
ክቡራን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት፤
ክቡራን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች፤
ክቡራን ታሪካዊ በሆነው ዓለም ዐቀፍ የሃይማኖት ጉባኤ ለመሳተፍ በዚህ የተገኛችሁ በሙሉ፤

"#ሰላምየ_አኀድግ_ለክሙ_ወሰላመ_አቡየ_እሁበክሙ፡- ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፡፡" ዮሐ. ፲፬፥ ፳፯

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሥጋ ለብሶ በሚታይ ሰውነት የተገለጠው ሰላምን ለማምጣት ነው፡፡ የማዳን ተግባሩን አከናውኖ፤ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አድርጎ ባረገ ጊዜም ዓለም እንደምትሰጠው ሰላም ያይደለ ልቡናን የሚያሳርፍ፣ መንፈስን የሚያረጋጋ እውነተኛ ሰላምን ሰጥቶናል፡፡ ልዑል አምላክ ትሑት ሥጋን በመዋሐዱም ታላላቆች ለይቅርታ ዝቅ በማለት የሰላም ምክንያት መሆን እንደሚችሉ በተግባር አስተምሮናል።

ሰላም የሰው ልጆች ፍላጎት፣ የብዙ ምንዱባን የየዕለት ናፍቆት ነው። የበርካታ ዘመናት ቅርሶች፤ ጊዜ፣ ገንዘብ እና የሰው ጉልበት የፈሰሰባቸው ግንባታዎች በሰላም ማጣት በቅጽበት ይፈርሳሉ። ሰላም ካለ የዓለም ሀብት ለሁሉም በቂ ነው። ሰላም ማጣት ግን ብዙ ሠራዊት፣ ብዙ የጦር መሳሪያ እንዲዘጋጅ እያደረገ ሀብትን ያወድማል። ጦርነት ማለት ሀብትና ሕይወትን ወደሚነድ እሳት ውስጥ መጣል ነው። የአንደኛና የሁለተኛ ዓለም ጦርነት፣ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ጠባሳው አሁንም የዓለምን መልክ አበላሽቶታል። ሰላም በውስጥዋ ገራምነት፣ ትዕግሥት፣ ታዛዥነትና በትህትና ዝቅ ማለት ስለሚገኙ መራራ ትመስላለች፤ በውጤቷ ግን ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከመከራ ማትረፍ የሚቻል በመሆኑ ዋጋዋ ከፍ ያለ ነው።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላም የሆነው ክርስቶስ የሚሰበክባት፣ የሰላም መልእክተኞች በውስጥዋ የሚመላለሱባት፣ በግብረ ኃጢአት የወደቁት በንስሓ ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቁባት የሰላም ድልድይ ስለሆነች በሥርዓተ ቅዳሴዋ ሰላምን ደጋግማ ታውጃለች፤ በጸሎቷ ለመላው ዓለም ሰላምን ትለምናለች፤ በጉልላትዋ ላይ የሰቀለችው መስቀልም ሰላምን የሚሰብክ ነው፤ የመስቀሉ ቅርፅ ወደ ላይና ወደ ጎን መሆኑም ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ሰላም መሆን እንዳለብን የሚያስገነዝበን ነው። ታሪካችን እንደሚነግረን ወንድማማቾች ሲጋደሉ፣ በሕዝብ መካከል መተላለቅ ሲመጣ ቤተ ክርስቲያን ታቦት አክብራ፣ በእሳት መካከል ገብታ ሰላምን ስታወርድ የኖረች ናት። በሀገር ውስጥ ግጭቶች በተፈጠሩበት ጊዜም የሰላም ጥሪን ያላስተላለፈችበት ቀንና ሰዓት አይገኝም፡፡

ክቡር ሚኒስትር
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራንና ክቡራት የዚህ ታላቅ ጉባኤ ተሳታፊዎች

ሰላምን የመወያያ ርእስ አድርገን ስንሰባስብ በጦርነት መካከል የተጨነቁ ሕዝቦች፣ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እና ምን እየተደረገ እንዳለ በውል የማይገነዘቡ ደካሞች ተስፋ ያደርጉናል። ስለዚህ ሰላም ከአንገት በላይና ዝም ላለማለት ያህል የምንናገረው ሳይሆን ዋጋ ከፍለን የምናመጣው ስለሆነ ይህ ጉባኤ ከውይይት ባሻገር በተግባር ጭምር የሰላም ተምሳሌት መሆን እንደሚገባው ለማሳሰብ እንወዳለን።

ዓለም በዚህ ወቅት አስጊ በሆኑ ጦርነቶች ውስጥ እያለፈች ነው፡፡ በሩሲያና በዩክሬን ያለው ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚ አናግቷል፤ ከሁሉ በላይም ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት እየቀጠፈ ነው። በእስራኤል፣ በፍልስጤም እና በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ያለው አለመረጋጋት ሁሉንም የሚነካ ነውና በጦርነቱ የሚሳተፉት በሙሉ ወደ ሰላም እንዲመለሱ፤ የዓለም መሪዎችም ልበ ሰፊ ሆነው ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም በሀገራችን ውስጥ ያሉት ግጭቶች የመቆሚያ ድንበራቸውን ያገኙ ዘንድ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከ ጉባኤ ያድርግልን!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፳፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

31 Oct, 14:14


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ከጥቅምት 11 እስከ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ልዑል እግዚአብሔርን አጋዥና መሪ በማድረግ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት፣ ስለምጣኔ ሀብት እድገት፣ በሀገራችን እየተከሰቱ ስላሉት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች፣ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ሐዋርያዊ ተልእኮ ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነት በስፋት በመወያየት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
ከጥቅምት 4 ቀን እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ 43ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተሳታፊዎች የቀረበው ቃለ ጉባኤና የአቋም መግለጫ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት የበጀት ዓመቱ የሥራ መመሪያ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እየተከሰተ ባለው የሰላም እጦት፣ የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ፣ አካል እየጎደለ፣ ማኅበራዊ ትሥሥር እየተናደ፣ ሰብአዊ ክብር እየተጎዳ፣ መብት እየተጣሰ፣ በዜጎች ላይ ሥጋትና አለመረጋጋት እየበዛ ሀብትና ንብረት እየወደመ ስለሆነ ጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልገው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስለሆነም በጦርነትና በግጭት የመጣ ሰላም፣ የተገነባ ሀገር የለምና በሀገራችን እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ካለፈው በመማር በጥበብ፣ በማስተዋልና በሰለጠነ አካሄድ በሰላማዊ መንገድ በመወያየት ችግሩ በእርቅ እንዲፈታ ለሁሉም ወገኖቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ጥሪውን በአጽንኦት ያቀርባል፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሥሩ ባሉ ገዳማትና አድባራት ውስጥ እየቀረቡ ያሉ መጠነ ሰፊ የአስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ በክፍላተ ከተሞችና ችግር አለባቸው ተብለው በጥናት በሚለዩት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የማጣራት ሥራ እንዲሠራና ውጤቱ ለውሳኔ እንዲቀርብ በሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡
የኦሲኤን ቴሌቪዥን ስርጭት የተቋረጠ በመሆኑ በአዲስ መልክ ሁሉንም የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች ማህበረሰብ ባቀፈ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአፋን ኦሮሞ ኔትወርክ በሚል ስያሜ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ውል ተፈርሞ በአዲስ መልክ የሳተላይት ግዥ እንዲፈጸም ሆኖ አስተዳደሩን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ጋር በአንድ ሊቀ ጳጳስና ቦርድ ራሱን በቻለ ሥራ አስኪያጅ እየተመራ አገልግሎቱ ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለደቀ መዛሙርት የሚሰጠው የምስክር ወረቀት አድቫንስ ዲፕሎማና ዲግሪ እንዲሆን፤ ሥርዓተ ትምህርቱ ለሚሰጠው የትምህርት ማስረጃ በሚመጥን መልኩ ተሟልቶ፣ ሊኖረው የሚገባው የሰው ኃይል በየዘርፉ ተጠናክሮ ወደ ትግበራ እንዲገባ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፣
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሥነ ሕንጻና በኪነ ጥበብ በዓለም ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትና ክብር የሚሰጠው ከመሆኑ በተጨማሪ በመዐርገ ጵጵስና ፕትርክና የሚሾሙ አባቶች ሥርዓተ ሲመት የሚፈጸምበት፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ካቴድራል መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ለዕድሳት ሥራው የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግለት ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤ በተጨማሪም ምእመናን እስከ አሁን እንደሚያደርጉት ሁሉ ለእድሳት ሥራው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዐቢይ ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥልና በንቃት እንዲሳተፍ ሁሉንም አህጉረ ስብከት ባቀፈ ሁኔታ የአጀንዳ መረጣና ተሳታፊ የመለየት ሥራ እንዲከናወን ሆኖ ዐቢይ ኮሚቴው የሥራ ዕቅዱንና አፈጻጸሙን ለቋሚ ሲኖዶስ እያቀረበ በማስወሰን እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ላለፉት ተከታታይ ቀናት በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ተገቢውን ውሳኔ በማስተላለፍ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቅቋል፡፡ መሐሪና ሁሉን ቻይ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ፍቅሩንና አንድነቱን ይስጥልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፳፩ ቀን !)0፯ ዓ.ም.
ኢትዮጵያ አዲስ አበባ

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

22 Oct, 08:36


መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ብፁዕ አቡነ አብርሃም 
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጐጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ዓመቱን ጠብቆ ስለ አጠቃላይ ተልእኮአችን ለመወያየት በዚህ ጉባኤ የሰበሰበን አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤ 
“ወይእዜኒ ግብኡ ኀበ ኖላዊሃ ወዓቃቢሃ ለነፍስክሙ፤ አሁንም ወደ እረኛችሁና ወደ ነፍሳችሁ ጠባቂ ተመለሱ” (1 ጴጥ 2÷!5)
ሁሉን የሚችል አምላካችን እግዚአብሔር በፍቅሩና በፍቅሩ መነሻነት ብቻ ፍጥረታትን በሙሉ እንደፈጠረ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፤ ከፈጠረም በኋላ የክብሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ወዶ ክብሩን አድሎአቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ለፍጡራኑ ካደላቸው ነገሮች አንዱ በየዓይነታቸው ጠባቂና መሪ እያደረገ በፍጡራን ላይ ፍጡራንን መሾሙ ነው፤ ይህ ስጦታ በሰማይም ሆነ በምድር ላሉ ፍጥረታት የተሰጠ የሱታፌ መለኮት ስጦታ ነው፡፡
ይህም በመሆኑ ሁሉም ፍጡራን አራዊትም ሆኑ እንስሳት ይብዛም ይነስ ጠባቂና መሪ እንዳላቸው እናስተውላለን፤ በተለይም የፍጥረታት ቁንጮ የሆኑ መላእክትና ሰዎች መሪና ሹም እንዳሏቸው የማንክደው ሓቅ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሓፍም ይህንን ደጋግሞ ያስረዳል፤ የእነዚህ ሁሉ ላዕላዊ ጠባቂና መሪ ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በፍጡራን ላይ ፍጡራንን ጠባቂዎች አድርጎ ሲሾም ፍጡራንን የክብሩ ተሳታፊ ለማድረግ እንጂ የእሱ ጥበቃ አንሶ ወይም ድጋፍ ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ፍጹምና ላዕላዊ የሆነ ጥበቃው ሁሉንም ያካለለ ነውና ከእሱ ቊጥጥርና ጥበቃ ውጭ አንድም ነገር እንደሌለ የምንስተው አይደለም ፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
በአምሳለ እግዚአብሔር በተፈጠረውና በክብር መልዕልተ ፍጡራን በሆነው ሰው ላይ በዚህ ዓለም የተሾሙ ሁለት አካላት አሉ፤ እነሱም የመንፈስና የዓለም መሪዎች ናቸው፡፡  በተለይም የመንፈስ መሪዎችና ጠባቂዎች የተባሉት በመንፈስ ቅዱስ ተሹመን በዚህ ክርስቶሳዊ ጉባኤ የተሰበሰብነው እኛ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ነን፡፡ 
ይህ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መሪና ጠባቂ ነው፤ ከዚያም ባሻገር እንደ ቃሉ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ቃሉን በመስበክ ፍጥረተ ሰብእን በሙሉ የመጥራት ተልእኮ ለእኛ የተሰጠ የቤት ስራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተሰጠን ኃላፊነት እጅግ በጣም ታላቅ እንደመሆኑ የሚጠበቅብን ውጤትም በዚያው ልክ ትልቅ ነው፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለግበታል ያለው የጌታችን አስተምህሮም ይህንን ያስታውሰናል፡፡ 
ሁላችን እንደምንገነዘበው አሁን የምንገኝበት ዘመን የጸላኤ ሠናያት መንፈስ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከምንም ጊዜ በበለጠ ጦሩን ሰብቆ የተነሣበት ጊዜ ነው፤ አሁን ያለው ዓለም በሀገራችንም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን ከባድ ፈተና ደቅኖብናል፡፡ ክፉው መንፈስ የሰውን አእምሮ በማዛባት ምእመናንን በቅዱስ መጽሐፍና በሕገ ተፈጥሮ ከተመደበላቸው የጋብቻ ሕግ በማስወጣት እንስሳት እንኳ የማይፈጽሙት ነውረ ኃጢአት እንዲፈጽሙ በመገፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ በአማንያን ልጆቻችን ላይም በረቀቀ ስልት ግድያ፣ እገታ፣ አፈና፣ የመብት ተጽዕኖ እና አድልዎ በማድረግ እንደዚሁም በአስመሳይ ስብከትና አምልኮ ጣዖትን በማለማመድ ሕዝቡ ሳይገባውና ሳይጠነቀቅ ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዲወጣ እያደረገ ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ክፉው መንፈስ በተራቀቀና በተራዘመ ስልት ሊውጠን በተነሣ ልክ እኛም ከእሱ እጥፍ በሆነ መለኮታዊ ኃይል ልንመክተው ካልቻልን በፈጣሪም ሆነ በትውልድ እንደዚሁም በታሪክ ፊት በኃላፊነት መጠየቃችን አይቀርም፡፡ መከላከል የምንችለውም ችግሩን በውል ከመረዳት አንሥቶ ሕዝቡን በደምብ በማስተማርና በመጠበቅ እንደዚሁም ለመሪነታችን ዕንቅፋት ከሚሆኑን ዓለማዊ ነገሮች ራሳችንን በማራቅ ነው፡፡ ሕዝቡም በዚህ ዙሪያ ሊያደምጠንና ሊከተለን የሚችለው መስለን ሳይሆን ሆነን ስንገኝለት ነው፡፡ ሕዝቡ ሊከተለን የሚችለው እሱን በብቃት ለመጠበቅ ዓቅሙም ተነሣሽነቱም ቁርጠኝነቱም እንዳለን ሲመለከት፣ እንደዚሁም ከዕለት ተዕለት ተግባራችንና አኗኗራችን የሚያየው ተጨባጭ እውነታ ኅሊናውን ሲረታ እንደሆነ አንርሳ፡፡ 
የምናስተምረው ሌላ የምንሰራው ሌላ ከሆነ ግን ከሕዝቡ አእምሮ መውጣታችን እንደማይቀር መገንዘብ አለብን፤ በመሆኑም በሰብእናችን፣ በአስተዳደራችን፣ በአመራራችንና በጥበቃችን ሁሉ እንደቃሉና እንደቃሉ ብቻ ለመፈጸም መትጋትና በቁርጥ መነሣት ጊዜው አሁን ነው እንላለን፡፡ ይህ ሲሆን በምእመናንና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝና እንከን የለሽ ይሆናል፤ ይህ ከሆነ እውነትም የመሪነት፣ የእረኝነትና የመልካም ተምሳሌነት ኃላፊነታችንን በትክክል ተወጥተናል ማለት እንችላለን፡፡ 
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
  የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ሲኖሩ የተሟላ ሰላምና ጣዕመ ሕይወት ሊኖራቸው የሚችለው በመንፈሳዊ ኑሮአቸው የተሻለ ነገር ስላገኙ ብቻ አይደለም፡፡ ሰዎች ከሥጋዊ ክዋኔም ጭምር የተፈጠሩ እንጂ እንደመላእክት ሥጋ የሌላቸው መንፈስ ስላይደሉ ለኑሮአቸውና ለሥጋዊ ክዋኔአቸው የሚሆን ነገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህም ዓለማዊው አስተዳደር የተመቻቸ መደላድል ሊፈጥርላቸው ግድ ነው፤ ዓለማዊው አስተዳደርም የመለኮትን ተልእኮ ለመፈጸም የተሾመ ሹመኛ እንደመሆኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በትክልል መምራት ይጠበቅበታል፡፡ ምንም ቢሆን የተቀበለው ኃላፊነት የእግዚአብሔር ነውና በሚሰራው ሁሉ በሿሚው አምላክ ከመጠየቅ አያመልጥም፡፡
እኛም በዚህ ዓለም የእግዚአብሔር ወኪሎች ስለሆንን ቢሰሙንም ባይሰሙንም ዓለማውያን ሹማምንትን  የማስተማርና የመምከር ኃላፊነት አለብን፡፡ ይህ የሁለታችን ኃላፊነት እንደ እግዚብሔር ፈቃድ ስንፈጽም የሕዝብ ሰላምና በረከት፣ ፍቅና አንድነት፣ ዕድገትና ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ ይረጋገጣል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በአካባቢያችን እየሆነ ያለው ይህ አይደለም፤ አለመግባባት በዝቶአል፣ ማኵረፍና መቀያየም ሰፍቶአል፤ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባና የተመሰቃቀለ ሆኖ ይታያል፡፡ ችግሩ ከሕዝብ አልፎ የአምልኮ ስፍራዎችንና የአምልኮው ፈጻሚዎችን ዒላማ ያደረገ እግዚአብሔርን መዳፈር እየተለመደ መጥቶአል፤ ይህ ለአንድ ሀገር ወይም ሕዝብ የውድቀት ምክንያት ከሚሆን በቀር ከቶውኑም የዕድገት ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ 
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ክፉ ድርጊት እየተፈጸመ ያለው በእኛው ልጆች በኢትዮጵያውያን መሆኑ ነው፤ ስለሆነም በከተማም፣ በጫካም፣ በገጠርም በየትኛውም ስፍራ የምትገኙ ልጆቻችን ምንም ይሁን ምን ሀገርንና ሕዝብን ከመጉዳት ተቆጠቡ፡፡ በተለይም ከቤተ ክርስቲያንና ከሀገር እንደዚሁም ሕዝቡን ከሚያገለግሉ ካህናትና ሲቪል ሰራተኞች እባካችሁ እጃችሁን አንሡ፤ ቤተ ክርስቲያን እኮ የእናንተና የሕዝቡ ሁሉ እናት ናት፤ በእናታችሁ ላይ መጨከንን እንዴት ተለማመዳችሁት? አሁንም ንስሐ ግቡ ያለፈው ይበቃል፡፡ ልብ በሉ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት አይበጅም፤ ሰውን መጉዳትና እግዚአብሔርን መዳፈር አቁሙ፤ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሥርዓተ አምልኮም ያለቦታው አታውሉ፤ ጥያቄአችሁን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዕድል ስጡ፡፡ በእግዚአብሔር ስም ለመላው ኢትዮጵያውያን

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት / His Holiness Patriarch Office

22 Oct, 08:36


ወገኖቻችንና ልጆቻችን የምናስተላፈው ወቅታዊ መልእክታችን ይህ ነው፡፡  
በመጨረሻም
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎትና የስራ አፈጻጸም ላይ ለመምከርና ለመወሰን ኃላፊነት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት መደበኛና ዓመታዊ ጉባኤውን የጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበስራለን፡፡
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን::

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፤

++++++++++++++++++++++++++++
#የቅዱስ_ፓትርያርኩ_ሓዋርያዊ_አገልግሎቶች እና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን_ለማግኘት:-
ከታች ያለውን link #share, Like & #follow ያድርጉ።
👇👇👇👇
1. ቴሌግራም:- https://t.me/EOTCPatriarichate
2.  ፌስቡክ ;- https://www.facebook.com/EotcpatriarchateOffice?mibextid=ZbWKwL

1,438

subscribers

2,484

photos

2

videos