“ተሓድሶና ቃሉ”
በአውሮፓ በ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረው ተሓድሶ፥ ቤተ ክርስቲያንን ከአደገኛ የሞት እንቅልፍ አባንኗታል ። አዳሽነት ባህሪው የኾነው አሐዱ-ሥሉስ አምላክ በደካማ ሰዎች በኩል ቤተ ክርስቲያኑን ጎብኝቷታል ። ክስተቱ ቁልፍ ነገረ መለኮታዊ ዕሳቤዎች የተነቀነቁበት ብቻ አልነበረም ። የአገሮቹን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ላይ ጭምር ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነበር ። የቤተ ክርስቲያን ተሓድሶ ያልነበረውን አላመጣም ፤ ዐዲስ ነገር አልጀመረም ። መሰረቱ ላይ የተከመረውን አቧራ አራገፈ እንጂ! ድንግዝግዝ ጭጋግ ላይ ብርሃን ፈነጠቀ እንጂ!
የቤተ ክርስቲያን ተሓድሶ በቀላል ቋንቋ እውነተኛውን የወንጌል ብርሃንና እርሱን የሚመጥን ኑሮ መልሶ መቀዳጀት ማለት ነው ። ወደ ቀደመው ርቱዕ መንገድ መመለስ ነው ።
እግዚአብሔር በደካማ ሰው በኩል የቤተ ክርስቲያኑን የፊት መጨማደድ በቃሉ ሂጶብ የሚያጸዳበት፥ በጸጋው ዘይት ዝገቷን የሚያራግፍበት ሂደትም ነው ። ምክንያቱም በጎሎጎታ የተመረቀው የሰማያዊው መንግሥት አብዮት ጥልቀቱና ኅይሉ መታወቅ ስላለበት ። የመስቀሉ ሥራ ሁሌም ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች ሞኝነት እንደሆነ መቀጠል አለበት ። ሰው በራሱ ሞራላዊ ጥረትና የአዕምሮ ልህቀት አምላክን ማወቅና ከኅጢአት በሽታው መገላገል እንደማይችል ሊገባው ያስፈልጋል ። ባጠቃላይ የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ !
ተሓድሶው ሲጀመር እጅግ አወዛጋቢ ነበር ። በክርስትና ስም በተደላደለው የሰው ሥርዐትና ወግ ላይ የተወረወረ ቦንብ ነው ። ፍንዳታው ከሩቅ ተሰምቶ በየቦታው ሲብላሉ የነበሩ ተመሳሳይ ጩኸቶች እንዲሰሙ አስችሏል ። እስከዛሬም ድረስ ‹ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት› የሚለው የተሓድሶ ጩኸት ለአንዳንዶች ጆሮ የማይስማማ እንግዳ ድምጽ ነው ። ጥቂቶችን ያስቆጣል ፤ በሌሎች ዘንድ ግርታንና ፌዝ ይፈጥራል ። አወዛጋቢነቱ በከፊል የሚመነጨው ሰው ጒረኛና ጥቅመኛ ስለሆነ ነው ። ትህትናንና ዝቅ ማለትን ፣ በየትኛውም ጉዳይ 'አስተዋፆ የለህም ወይም አትችልም' መባልን አይፈልግም ። ተሓድሶ ደግሞ የሰውን ጥበብና ችሎታ አሳንሶ የእግዚአብሔርን ጥበብ [መሲሑን] የማላቅ ፕሮጀክት ነው ።
በተሓድሶ ነገረ-መለኮት ውስጥ የሰው ትምክህት ቅንጣት ቦታ የለውም ። ተሓድሶን መናፈቅ ማለትም ይኼንን “መራራ”
እውነት ዐውቆና ፈቅዶ መቀበል ማለት ነው ። ሰው ድነቱን — ወይም ስለ እግዚአብሔር ያለውን ልከኛ እውቀትና ምልልስ — በራሱ ማስተዋል ፣ በመልካም ሥነ ምግባር ወይም በኅይማኖት ድርጅት አባልነት ማግኘት አይችልም ። ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚመሰክሩት የሰማዩ መንግሥት ጉዳይ ከሀ እስከ ፐ ከእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ነው ። ማንም በመልካም ሥራው እንዳይመካ!
ማዳን የእግዚአብሔር ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? እግዜሩ የሰውን ድነትና ዋስትና በተመለከተ ኪዳን የገባውም የፈጸመውም ብቻውን ነው እያልን ። ይኼም ዘላቂና አስተማማኝ አምላካዊ ኪዳን ነው ። በብሉይ ኪዳን ለአብርሃም የተገባለት የተስፋ ቃል የተፈጸመው በዐዲሱ ኪዳን በመሲሑ ደም ነው ። ከኅጢአት በሽታ መዳን ፣ በትንሣኤው ኅይል መጽደቅ ፣ ዐዲስ ፍጥረት መኾን ፣ መላ-ዐለሙን በሚያድስበት ድንቅ አሠራሩ ከርሱ ጋር አብሮ ሠራተኛነት ፣ በዐዲሱ ሰማይና ምድር ከንጉሡ ጋር በትንሣኤ አካል መክበር ... ተጀምሮ እስከሚያልቅ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ብቻ ከተመሠረተ - ክብሩም ምስጋናውም ለእርሱ ብቻ ይገባል ። “የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ” እንዲል ቃሉ!
ይኼን እውነት ሓዳሲያኑ ከየትም አላገኙትም ። ልዩ ፍጥረት አልሰበከላቸውም ፤ ልዩ መገለጥም አልመጣላቸውም ። በእጃቸው የነበረውን ቅዱሳት መጻሕፍትን አክብረው ሲገልጡትና ሲያጠኑ - እውነቱ በራላቸው ። ለአስተምህሮም ሆነ ለምልልስ ቃሉን ቀዳሚ ባለስልጣን አድርገው ሲሾሙ - ለእግራቸው መብራት ለመንገዳቸው ብርሃን ሆነላቸው ። ከቆየ የቤተ ክርስቲያን ልማድም ሆነ የሰው ወግ ቃሉን ሲያስበልጡ — የጸጋው ጉልበትና የሰው ድሽቀት ታያቸው ።
“ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ” ብለው ሲጸኑ — ሁሉም ጉዳይ ቦታ ቦታውን ያዘላቸው ።
በOctober 31, 1517 ፣ 95ቱን አንቀፆች በቪተንበርግ ካቴድራል ማስታወቂያ ሰሌዳ በመለጠፍ የተሓድሶን እሳት በመለኮስ ፈር ቀዳጅ የሆነው ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር፥ ስለተቀጣጠለው እንቅስቃሴ ሲናገር “I did nothing; the Word did everything. - እኔ ምንም አላደረኩም፤ ሁሉን ያደረገው ቃሉ (የእግዚአብሔር) ነው!” እንዳለው ነው!
ክብር ለአዳሹ ያሕዌ ይሁን!
#ተሓድሶው_ሲታወስ
#ቅዱሳት_መጻሕፍት_ብቻ
በፍጹማን ግርማ
@siloam4world
@siloam4world