[ 🕊 ገ ድ ለ ቅ ዱ ሳ ን 🕊 ]
▬▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬▬
[ የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ የተጋድሎ ሕይወቱና ትምህርቱ ]
[ ክፍል ሃያ ስድስት ]
💛
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
[ እግዚአብሔር የአባ መቃርዮስን ጩኸት እንደ መለሰለት ]
🕊
❝ በአንድ ወቅት ታላቁ አባ መቃርዮስ ከአስቄጥስ ወደ ግብፅ እየሄደ ሳለ ትንሽ ቅርጫቶች ተሸክሞ ነበር፡፡ እርሱም በደከመው ጊዜ ቁጭ አለ፡፡ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ ፦ " ጌታ ሆይ ፣ ምን ያህል እንደ ደከመኝና እንደዛልኩ የምታይ አንተ ነህ " አለ፡፡ ይህን ካለ በኋላ ወዲያውኑ ራሱን ከቅርጫቶቹ ጋር በዓባይ ወንዝ ዳር ላይ ደርሶ አገኘው፡፡
የቅዱስ መቃርዮስ ደቀ መዝሙር የነበረው አባ በብኑዳ እንዲህ አለ ፦ " አንድ ቀን ቅዱስ መቃርዮስ ቆሞ ሲጸልይ ሳለ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረው ፦ ' መቃራ ሆይ ፣ እገሌ በምትባል ሀገር ያለማቋረጥ በትጋት የሚያገለግለኝንና የሚያመሰግነኝን አንድ ገበሬ ምሰል፡፡ ' ይህን በሰማ ጊዜ ከመጀመሪያዎቹ አርድእት አንዱ የሆንኩትን እኔን በብኑዳን ፦ ' ተነሥና ምርኩዝህን ይዘህ ከእኛ ጋር እገሌ ወደምትባል ሀገር እንሂድ ' አለኝ፡፡ ወደዚያ ሄደን ከወንዙ ሐይቅ ዳር ደረስን ፣ የሚያሻግረን በፈለግን ጊዜ አላገኘንም ነበርና ስፋቱን እየተመለከትን ሁላችንም ዝም ብለን በዚያ ተቀምጠን ነበር፡፡ ቅዱስ መቃርዮስ ግን በተመሥጦ ሆኖ ራእይን እያየ ነበር፡፡
እኔም አባታችን ፣ እግዚአብሔር ጸሎትህን እንደሚሰማ አውቃለሁና ይረዳን ዘንድ ጸልይ አልኩት፡፡ ያን ጊዜም እየማለደ ጸለየ፡፡ ወዲያውኑ ታላቅ አዞ ከባሕሩ ወጣ ፤ ቅዱሱም ' እግዚአብሔር ከወደደና አዝዞህ ከሆነ አሻግረን ' አለው፡፡ ያ አዞም ተሸከመንና ወደ ማዶ አሻገረን፡፡ ቅዱስ መቃርዮስም ያንን አዞ ' እግዚአብሔር ዋጋህን እስከሚሰጥህ ድረስ ወደ ውኃው ግባ ' አለው፡፡ እርሱም እራሱን ወደ ውኃው አጠለቀ፡፡
ወደ ሀገሩ በወጣንና ወደዚያ በደረስን ጊዜ በሀገረ ገዢው እርሻ ላይ ተሰማርተው የሚሠሩ ብዙ ገበሬዎችን አገኘን፡፡ አረጋዊው መቃራም እነዚያን ገበሬዎች እያንዳንዳቸውን እየተመለከተ በበሩ አንጻር ተቀመጠ፡፡ እግዚአብሔር ስለ እርሱ ያመለከተው ያ ገበሬ በመጣ ጊዜ በዙሪያው ከብባው ያለችውን ጸጋ እግዚአብሔር ተመለከተ ፣ በትዕግሥት የተከደነ መሆኑንም አየ፡፡ ሰላምታ ሰጥቶ የተቀደሰች መሳምን ሳመው፡፡ ከዚያም እርሱን ይዞ ለብቻው ገለል አደረገውና ፦ 'እግዚአብሔርን የምታገለግልበት ሥርዓተ ተልእኮህ ምንድን ነው ? ' አለው፡፡ ያ ገበሬም ፦ ' እኔ በዚህ ዓለም ለቀሲስ [ ለካህን ] እላላካለሁ ፣ ጌታዬ ሰማያዊ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስም ዋጋዬን ይሰጠኛል፡፡ ስለዚህም ይህን ያህል ዘመን ሁሉ ዘወትር አገለግላለሁ ፣ እኔም ልቤ የቀና ነው ' አለው፡፡
መቃርዮስም ፦ ' ይህን ሃሳብ ከየት አገኘኸው?' አለው፡፡ እርሱም ፦ " ሠራተኞቹን አምጧቸውና ደመወዛቸውን ስጧቸው " ካለው ከጌታ ቃል ነው ' አለው፡፡ ቅዱስ መቃርዮስም ይህን ነገር ከእርሱ በሰማ ጊዜ ሳመውና መከረው ፣ በላዩም ላይ ማሕየዊ በሆነ በትዕምርተ መስቀል ባረከው፡፡ ከዚያም ሲመለስ ነፍሱን ፦ ' መቃራ ሆይ ወዮልህ ፣ የዚህን ዓለማዊ ወንድም ያህል እንኳን አእምሮ የለህም ፣ ብታውቅበትና በምግባርህ እግዚአብሔርን ብታገለግል እርሱ ዋጋህን ይሰጥሃል' እያለ በመንገድ ላይ ሁሉ ታላቅ ለቅሶን ያለቅስ ነበር፡፡ "
" ወደ ወንዙ በደረስን ጊዜ የሚያሻግረን ስላጣን አባት መቃርዮስ በዚያ ጸለየ፡፡ እኛንም ፦ ' ልጆቼ ሆይ እግዚአብሔር እስኪረዳን ድረስ ተቀመጡ ' አለን፡፡ እኔም በዚያ ትንሽ ተኛሁና በነቃሁ ጊዜ እኔና እርሱን በበኣታችን በር ፊት ቆመን አገኘሁት፡፡ እኔም 'ይህ ነገር እንዴት ሆነ? አልኩት፡፡ እርሱም ፦ 'ልጄ ሆይ ነቢዩ እንባቆምን ከይሁዳ ምድር ወስዶ ባቢሎን ከነቢዩ ዳንኤል ዘንድ እንደ ዓይን ጥቅሻ አድርሶ እንደ ገና ወደ ቦታው የመለሰው እርሱ ነውና እግዚአብሔርን አመስግን ፤ እኛንም ከዚህ ያደረሰን እርሱ ነው' አለው፡፡ ❞
የአባታችን የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃና ጸሎቱ አይለየን፡፡
ይቆየን !
† † †
💖 🕊 💖