❤ #ኅዳር ፲፪ (12) ቀን።
❤ እንኳን #ለሰው_ወገን_ለሚያዝንና_ለሚራራ በእግዚአብሔር ጌትነት ፊት ሁልጊዜ በመቆም ለፍጥረት ሁሉ ለሚማልድ #ለመላእክት_አለቃ_ለቅዱስ_ሚካኤል_እስራኤልን_ከግብፅ_ባርነት ሲወጡ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋር በሆነ ሕዝብ በመንዳቸው ሁሉ እየመራ የኤርትራ ባሕር ለከፈለበት፣ #ለነዌ_ልጅ_ለነቢዩ_ለቅዱስ_ኢያሱ ለተገለጠለት፣ #ዱራታዎስና_ሚስቱን_ቴዎብስታ_ለረዳበት_ዓመታዊ_በዓልና #ለኢትዮያዊው_ንጉሥ #ለጻድቁ_ለዐፄ_በእደ_ማርያም_ለዕረፍቱ መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከመጥምቀ_መለኮት_ቅዱስ_ዮሐንስ ራሱ በደብረ ማህው ከታየችበት፣ ከእስክድርያ ስልሳ ሦስተኛ ሊቀ ጳጳስ ከቅዱስ አባት #ከአባ_ፊላታዎስ ዕረፍት ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ በዚች ቀን #ለሰው_ወገን_የሚያዝንና_የሚራራ #በእግዚአብሔር_ጌትነት_ዙፋን_ፊት_ሁልጊዜ በመቆም #ለፍጥረቱ_ሁሉ_የሚማልድ_የመላእክት_አለቃ በሰማያትም ለሚኖሩ ኃይሎች ሁሉ አለቃቸው ለሆነ #ለቅዱስ_ሚካኤል_የበዓሉ መታሰቢያ ነው።
❤ ይህም በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በታላቅ ክብር ሁኖ የነዌ ልጅ ኢያሱ ያየው ነው "ከእኛ ሰዎች ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?" አለው። "እኔስ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ አሁንም ወዳንተ መጥቻለሁ" አለው። ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደለትና "በእኔ በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል?" አለው። የእግዚአብሔር የሠራዊቱም አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን "የቆምክባት ምድር የከበረች ቦታ ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ" አለው ኢያሱም እንዳለው አደረገ። እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው "በውስጧ ያለውን ንጉሷን ከኃያላኑና ከአርበኞቹ ጋር በእጃችሁ ኢያሪኮን እነሆ አስገባታለሁ"።
❤ ይህም የከበረ መልአክ ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋር በመሆን ገድላቸውን እስከ ሚፈጽሙ የሚያጽናቸውና የሚያስታግሣቸው ነው። ስለዚህም ስለ ልዕልናውና ስለ አማላጅነቱ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ለመታሰቢያው በዓል ተሠራለት እርሱ ስለ እኛ የምድሩን ፍሬ ይባልክልን ዘንድ ዝናሙንም በጊዜው እንዲወርድልን የወንዙንም ውኃ እንዲመላልን ነፋሱንም የምሕረት ነፋስ እንዲአደርግልን ሁሉንም የተስተካከለ እንዲአደርግልን ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ይማልድልናልና።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_ሚካኤል_ያደረገው_ተአምር_ይህ_ነው፦ እንዲህም ሆነ እግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው እነርሱም ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢ ያደርጉ ነበር ከዚህም በኋላ በአገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ ለዚህም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉት አጡ ዱራታዎስም ሽጦ ለበዓሉ መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱን ልብስና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሔደ። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኰንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለት ወደ ባለ በጎች ሒዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ ሁለተኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ሒዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ግን መልአኩ ወደ ቤቱ ሳይደርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ ወደ ባለ ሥንዴም እንዲሔድና የሚሻውን እንዲሁ በርሱ ዋስትና እንዲወስድ አዘዘው ዱራታዎስም ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዘው አደረገ። ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ በረከትን ሁሉ ቤቱ ተመልቶ አገኘው። እጅግም አደነቀ የዚህንም የከበረ መልአክ የበዓሉን መታሰቢያ እንዳስለመደ አደረገ። የተራቡ ድኆችን ሁሉንም ጠርቶ መገባቸውና ወደየቤታቸው አሰናበታቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው። ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሠነጥቅ አዘዘው። በሠነጠቀውም ጊዜ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ተገኘ። ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስንና ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው "ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ ለባለ ዓሣውና ለባለ ሥንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ። በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል" አላቸው።
❤ እነርሱም ሲሰሙ ስለዚህ ነገር ደነገጡ እርሱም "ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ መሥዋዕታችሁና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም" አላቸው። ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት ወጣ። እነርሱም ሰገዱለት ተአምራቱም የማይቈጠር ብዙ ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ መልአክ በቅዱስ ሚካኤል ጸሎትና አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ፊላታዎስ፦ በእስክንድርያ ከተሾሙ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ ሦስተኛ ነው። በሹመቱ ወራት የኢትዮጵያ ንጉሥ ወደ ኖባ ንጉሥ ወደ ጊዮርጊስ እንዲህ ብሎ የመልክት ደብዳቤ ጻፈ "ወንድሜ ሆይ ከሊቀ ጳጳሳት ቆዝሞስ ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ጳጳስ ስለ ሌለን እኛ በታላቅ ችግር ውስጥ እንዳለን ዕወቅ። ይህም የሆነው ተንኰለኛው ሚናስ በተንኰልና በሐሰት ነገር የከበረ ጳጳሳችንን ጴጥሮስን ከሹመቱ ወንበር እንዲሰደድ ስለ አደረገው ነው። ስለዚህ አምስት ጳጳሳት እስቲአልፉ ለአገራችን ጳጳስ አልተላከም። አሁንም ስለ እግዚአብሔር ብለህ ስለ ቀናች ሃይማኖትም በድካም ከእኛ ጋር አንድ በመሆን ስለእኛ ወደ ግብጽ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ ፊላታዎስ ጳጳስ ይልክልን ዘንድ ከራስህ ደብዳቤ እንድትጽፍለት እለምንሃለሁ" የሚል ነበር።
❤ በዚያንም ጊዜ የኖባ ንጉሥ ጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስን ይሾምላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ ወደ አባ ፊላታዎስ ጻፈ ይህ ቅዱስ ፊላታዎስም ልመናውን ተቀብሎ ከአስቄጥስ ገዳም ስሙ ዳንኤል የሚባል አንድ ጻድቅ መነኰስ አስመጣ እርሱን ጵጵስና ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ አገር ላከው ወደ እነርሱም በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች በታላቅ ደስታ ተቀበሉት። በዚህም አባት ፊላታዎስ ዘመን ብዙ ተአምራት ተገልጠዋል ኅዳር 12 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ፊላታዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የኅዳር 12 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ ንጉሥ። ወብዙኀ ይትሐሠይ በአድኅኖትከ። ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ"። መዝ 20፥1-2። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ19፥11-28።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ዘነፈቃ ለባሕረ ኤርትራ ወከፈላ። እስመ ለዓለም ምሕረቱ። ወአውፆኦሙ ለእስራኤል እንተ ማዕከላ"። መዝ 135፥14-15 ወይም መዝ 33፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 9፥17-24 ይሁ 1፥9-14 እና የሐዋ ሥራ 20፥28-31። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥15-21 ። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።