የካቲት ፰/፳፻፲፯ ዓ.ም
በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ አማካኝነት በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጀው ፲፫ተኛው የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር ከየካቲት 21 እስከ የካቲት 23/6/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበበ በዳዳ ገልጸዋል።
ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት የመርሐ ግብሩ ዓላማ በከፍተኛ የት/ት ተቋማት የሚማሩ ኦርቶዶክሳዊያን ተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን አሁናዊ ሁኔታና በማኅበረ ቅዱሳን በአጠቃላይ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ዙሪያ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ግንዛቤ የማስጨበጥና የበለጠ ለማገልገል እንዲተጉ ለማድረግ የተዘጋጀ እንደሆነ አስታውቀዋል።
አክለውም ከ43 ማእከላት የተወጣጡ 450 የግቢ ጉባኤ አገልግሎት ዋና ክፍል አባላትና ተሳታፊዎች እንዲገኙ እንደ ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታና በበጀት እጥረት ምክንያት ከ300 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል ብለዋል።
ሴሚናሩ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን ማኅበሩ በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ላይ እያከናወነ ያለውን ተግባር ለመገምገም እና ለወደፊት የተሻሉ አቅጣጫዎች ለማስቀመጥ እንደሚያግዝ ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
ማኅበረ ቅዱሳን ወጣቶች መንፈሳዊ አገልግሎትን እና ቤተ ክርስቲያንን እንዲያውቁ በግቢ ጉባኤያት በኩል እያስተማረ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አበበ አያይዘውም የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን ለከፍተኛ ት/ት ተቋማት ሲልኩ ወደ ግቢ ጉባኤያት መሄድና መማር እንዲችሉ በማድረግ በሁለቱም በኩል እንዲጠነክሩ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው መልእክት አስተላልፈዋል።