አዳምን ለማዳን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ፣ ሥጋዋን ለብሶ በፍጹም ተዋሕዶ ሰው በመሆን ማደሪያው ትሆን ዘንድ ቅድመ ዓለም የመረጣት፣ ከኢያቄምና ከሐና ልጅ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ፣ ዳግመኛም ሕማምና ደዌ የሌለበት፣ የሰላምና የደስታ ሀገር የምትሆን ወደቀደመ የክብር ቦታው ወደ ገነት በሰላም ያገባው ዘንድ በገዳም የተፈተነ፣ በሥጋው የታመመ፣ የሞተ፣ የተቀበረ፣ ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ግሩም በሚሆን በመለኮቱ ኃይል በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በእግዚአብሔር ወልድ በተለየ ስሙ ለዘላለሙ በእውነት እናምናለን፡፡
በባሕርይው መጉደል ወይም መጨመር ሳይኖርበት በመንግሥቱ ከአብ ከወልድ ጋር ትክክል የሚሆን፣ በሃምሳኛው ቀን በደብረ ጽዮን በጉባኤ አዳራሽ የወረደ፣ በእጅ የማይዳሰስ ነበልባላዊ መጠጥ ይጠጡ ዘንድ ልማድ ያይደለ ነገር ግን የክርስቶስ አፍራሰ መንግሥቱ ወይም ደቀ መዛሙርቱ ጠጥተውት በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ እንዲናገሩ እውቀትን የገለጠላቸው የአብና የወልድ የባሕርይ ሕይወታቸው በሚሆን መንፈስ ቅዱስ በተለየ ስሙ ለዘላለሙ በእውነት እናምናለን፡፡ አሁንም እንደዚሁ በስም ሦስት ሲሆኑ በመለኮት፣ በባሕርይ፣ በሕልውና ወይም በአኗኗር፣ በፈቃድ አንድ አምላክ ብለን እናምናለን፡፡››
እስከመጨረሻው በአምልኮተ ሥሉስ ቅዱስ ያጽናን። ሥሉስ ቅዱስ ከበዓላቸው ረድኤት በረከት ይክፈሉን!