መዝገበ ቅዱሳን @mezigebekidusan Channel on Telegram

መዝገበ ቅዱሳን

@mezigebekidusan


የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን

መዝገበ ቅዱሳን (Amharic)

የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መዝገበ ቅዱሳን ማንኛውም ቅዱሳን ከእግዚአብሔር በእምነት እንደሚመራ ሲሆን በመጨረሻው ላይ ያቀረባቸዋል። ሁሉም ለእግዚአብሔር በሚናገር ተስፋ ምክንያት እንደሆነ መቀበል ይመጣል። ከዚህ ግራም መዝገበ ቅዱሳን፣ ከሰኞ እስከ እሮብ ሕግ ላይ ጥንቃቄ፡፡

መዝገበ ቅዱሳን

20 Nov, 17:49


=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
2.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
3.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
4.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
5.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
6.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ
=>+"+ በሰማይም ሰልፍ ሆነ:: ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ:: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ:: አልቻላቸውምም:: ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ:: +"+ (ራዕይ. 12:7)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5

መዝገበ ቅዱሳን

20 Nov, 17:47


እንኩዋን ለሊቀ መላእክት "ቅዱስ ሚካኤል" እና "ለቅዱሳኑ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት

=>ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር: ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ: አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በ99ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል::

+ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያሕል ክብርና ርሕሩሕ የለም:: በምልጃውም: በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል:: "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው: ለምሕረት የሚፋጠን: ደግ መልአክ ነውና::

+በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ: ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እሥራኤልን 40 ዘመን በበርሃ መርቷል:: መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: (ዘፍ. 48:16, ኢያ. 5:13, መሳ. 13:17, ዳን. 10:21, 12:1, መዝ. 33:7, ራዕይ. 12:7)

+ደስ የሚለው ደግሞ ርሕሩሑ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን: በረከትን ያወርዳሉ::

+"+ ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ +"+

=>ዳግመኛ በዚህች ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን እንደ ረዳው ታስተምራለች:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ 5 ላይ እንደ ተጻፈው ቅዱሱ መልአክ ለኢያሱ ተገልጦለታል:: እሥራኤልን በምድረ በዳ የመራ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ሲያርፍ ታላቅ ሐዘንና ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር::

+እግዚአብሔር ግን ኢያሱን አስነስቶ አረጋግቷቸዋል:: ቅዱስ ሚካኤል 40ውን ዘመን እሥራኤልን ደመና ጋርዶ: መና አውርዶ: ክንፉን ዘርግቶ: ጠላትን መክቶ ከሙሴ ጋ እንደ መራቸው ከኢያሱ ጋርም ይሆን ዘንድ ከሰማይ ወረደ::

+በኢያሪኮ አካባቢም የተመዘዘ ሰይፉን ይዞ በግርማ ለኢያሱ ታየው:: ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ "አንተ ከእኛ ወገን ነህን? ወይስ ከጠላቶቻችን?" ሲል ጠየቀው:: ቅዱስ ሚካኤልም መልሶ "እረዳህ ዘንድ እነሆ የሠራዊት አለቃ ሆኜ ተሹሜ መጥተቻለሁ" አለው::

+ያን ጊዜ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ በግንባሩ ተደፍቶ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሰገደለት:: ቅዱሱ መልአክም አክሎ "ፍታሕ ቶታነ አሳዕኒከ እም እገሪከ: እስመ ምድር እንተ ትከይዳ ቅድስት ይዕቲ - የረገጥካት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውጣ" አለው::

+ኢያሱም የተባለውን አደረገ:: ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን "ለመላእክት የጸጋ (የአክብሮ) ስግደት ይገባል: በቅዱሳኑ ፊትም ጫማ ተለብሶ አይቆምም" የምትለው:: ያ መሬት ሊቀ መላእክት ቢቆምበት ተቀድሷል:: ዛሬም ቤቱ በታነጸበት: ታቦቱ በተቀረጸበት ቦታ ሁሉ ቅዱሱ መልአክ አለና ጫማን አውልቆ: ባጭሩ ታጥቆ መግባት ይገባል::

+ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከኢያሱ ጋር ሆኖ አማሌቅን ጨምሮ የእሥራኤልን ጠላት አጥፍቷል:: ጥቅመ ኢያሪኮን (ቅጥሩን) አፍርሷል:: ምድረ ርስትን አውርሷል:: በገባኦን ፀሐይን: በቆላተ ኤሎምም ጨረቃን ሲያቆም ከእርሱ ጋር ሆኖ ረድቶታል::

+"+ ዱራታኦስና ቴዎብስታ +"+

=>ቅዱሳኑ ዱራታኦስ (ዶርታኦስ) እና ቴዎብስታ (ቴዎብስትያ) የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ:: በድርሳነ ሚካኤልና በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፎ እንደምናገኘው 2ቱ ቅዱሳን በተቀደሰ ትዳር ተወስነው: ሕጉን ትዕዛዙን ፈጽመው: ለነዳያን ራርተው: ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው የሚኖሩ ነበሩ::

+ይልቁኑ ግን የጌታችን: የእመቤታችንን እና የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ያለማስታጐል ያደርጉ ነበር:: ከጊዜ በሁዋላ ግን ሐብት ንብረታቸው አልቆ ተቸገሩ:: ግን የጨነቃቸው መቸገራቸው ሳይሆን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ሊያቆሙ መሆናቸው ነው::

+አማራጭ ሲያጡ ተቀምጠው ተመካከሩ:: የቅዱሱ መልአክ ዝክር ከሚቀር ልብሳቸውን (ያውም የክብር ልብሳቸውን) ሊሸጡ ተስማሙ:: በዚህ መሰረት ቅዱስ ዱራታኦስ ወደ ገበያ ሲሔድ ወዳጁ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወረደለት::

+መንገድ ላይም የጦር መኮንን ሃገረ ገዢ መስሎ ተገናኝቶ አጫወተው:: ችግሩን ጠይቆም መፍትሔውን ነገረው:: "እኔ እዋስሃለሁና ለበዓል የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሁሉ ገዝተህ አሰናዳ" አለው::

+"እኔ ወደ ቤትህ መጥቼ ስለምስተናገድ አንድ አሣ አምጥተህ አቆየኝ:: እኔ ሳልመጣ ግን አትረደው" አለው:: ቅዱስ ዱራታኦስ የተባለውን ሁሉ ፈጽሞ ወደ ቤቱ ሲሔድ ድንቅ ነገርን ተመለከተ:: ሚስቱ ቅድስት ቴዎብስታ በቤቱ መካከል ሁና ቤቱ በበረከት ሞልቷል::

+ማሩ: ቅቤው: እሕሉ ሁሉ በየሥፍራው ሞልቷል:: ባልና ሚስቱ ደስ ብሏቸው:: ነዳያንን ሲያበሉ: እንግዳ ሲቀበሉ ዋሉ:: በሁዋላ ያ መኮንን (ቅዱስ ሚካኤል) በቤታቸው መጥቶ ተስተናገደ::

+በእርሱ ትዕዛዝ የአሣው ራስ (ሆድ) ሲከፈት በውስጡ 300 ዲናር ወርቅ (እንቁ) ተገኘ:: ቅዱሳኑ ይህን ተመልክተው ሲደነግጡ ቅዱስ ሚካኤል ክንፉን ዘርግቶ ራሱን ገለጸላቸው:: ደንግጠው በግንባራቸው ተደፉ::

+እርሱ ግን "በተገኘው ሃብት እዳችሁን ክፈሉ:: ከዚህ በሁዋላ ግን በምድር አትቸገሩም:: በሰማይም ክፍላችሁ ከእኔ ጋር ነው" ብሎ ባርኩዋቸው ወደ ሰማይ ዐረገ:: እነርሱም በሐሴትና በበጐ ምግባር ኖረው ዐርፈዋል:: ለርስቱም በቅተዋል::

+"+ ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ +"+

=>የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ::
*በሕጻንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ::
*በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ::
*በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ::
*ምጽዋትን ያዘወተረ::
*አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው::
¤አርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል::

+"+ አፄ በእደ ማርያም +"+

=>"በዕደ ማርያም" ማለት "በማርያም እጅ" እንደ ማለት ነው:: እኒህ ሰው የኢትዮዽያ ንጉሥ ሲሆኑ የነገሡትም በ1460 ዓ/ም ነው:: ደጉ አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሲያርፉ በመንግስቱ ተተክተው ሃገራችንን አስተዳድረዋል:: ድርሰት ደርሰዋል:: አብያተ መቃድስ አንጸዋል::

+በተለይ ለቅኔ ትምሕርት ማበብ ልዩ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገራል:: ልክ በነገሡ በ10 ዓመታቸው ግን መንግስተ ምድር በቃኝ ብለው በምናኔ በርሃ ገብተዋል:: በዙፋናቸውም አፄ እስክንድር ተተክተዋል:: ጻድቁ ንጉሥ ግን ቅዱስ ሚካኤልን ይወዱት ነበርና በዚህች ቀን ዐርፈዋል::

=>አምላከ ቅዱሳን በክንፈ ሚካኤል ከክፉው ሁሉ ይሰውረን:: ከበረከታቸውም አይለየን::

=>ኅዳር 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ
3.ቅዱሳን ዱራታኦስና ቴዎብስታ
4.አፄ በዕደ ማርያም ጻድቅ
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
6.ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
7.አባ ፊላታዎስ ሊቀ ዻዻሳት

መዝገበ ቅዱሳን

18 Nov, 16:33


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ ኅዳር 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

✞✞✞ ቅድስት ሶፍያ ወቅዱሳት አንስት ✞✞✞

✞✞✞ እስኪ ዛሬ በጥቂቱ የተባረኩ (ቡሩካት) እናቶቻችን እንዘክር:: "ቅድስት" የሚለው ቃል ለሁሉም ቅዱሳት እናቶች ቢሰጥም ቅሉ ለድንግል ማርያም ሲሰጥ ግን ትርጉሙ ይለያል:: እርሷ 'ቅድስተ ቅዱሳን: ንጽሕተ ንጹሐን: ቡርክት እምቡሩካን: ኅሪት እምኅሩያን ናትና::

+ከሰው ልጆችም ሁሉ ትበልጣለች:: ይቅርና የሰው ልጅን ንጹሐን መላእክትንም በንጽሕናና በቅድስና ትበልጣቸዋለች:: እርሷ እመ ብርሃን: የአምላክ እናቱ: የሰውነታችን መመኪያ ናትና::

+እመቤታችንን "ቅድስት" ስንል "ጽንዕት: ንጽሕት: ክብርት: ልዩ" ማለታችን ነው::
1."ንጽሕት" ትባላለች:: ሌሎች ሰዎች (ቅዱሳን) ቢነጹ ከገቢር: ከነቢብ ኃጢአት ነው እንጂ ከኃልዮ ኃጢአት አይደለም:: እርሷ ግን ከነቢብ: ከገቢር: ከኃልዮ ንጽሕት ናት::

"ለመኑ ተውኅቦ ተደንግሎ ኅሊና: ለመላእክትሂ ኢተክህሎሙ-ኃጢአትን ከማሰብ መጠበቅ ከሰው ልጆች ለማን ተሰጠው: ይህስ ለመላእክትም አልተቻላቸውም" እንዲል:: (ተአምረ ማርያም)

2."ጽንዕት" እንላታለን:: ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው እንጂ በኋላ በጊዜው ተፈትሆ አለባቸው:: እመቤታችን ግን ቅድመ ጸኒስ: ጊዜ ጸኒስ: ድኅረ ጸኒስ: ቅድመ ወሊድ: ጊዜ ወሊድ: ድኅረ ወሊድ ድንግል ናትና::

"ጽንዕት በድንግልና አልባቲ ሙስና" እንዳላት:: (ቅዱስ ያሬድ) ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም "ወትረ ድንግል ማርያም-ማርያም ዘለዓለማዊት ድንግል ናት" እንዳለ:: (መጽሐፈ ቅዳሴ)

3.ድንግልን "ክብርት" እንላታለን:: ሌሎች ሴቶች ቢከብሩ ጻድቃን ሰማዕታትን: ነቢያት ሐዋርያትን ወልደው ነው:: እመቤታችንን ግን የምናከብራት "ወላዲተ አምላክ-የአምላክ እናቱ" ብለን ነውና::

4.እመቤታችንን "ልዩ" እንላታለን:: ከእርሷ በቀር እናት ሁና ድንግል: እመቤት ሁና አገልጋይ የሆነች: በድንግልና ወልዳ ወተትን (ሐሊበ ድንግልናዌን) ያስገኘች ሌላ ሴት የለችምና::

+የእመ ብርሃን ይቆየንና ደግሞ ሌሎች ቅዱሳት እናቶቻችንን እንመልከት:: እናቶቻችን ስናከብር የምንጀምረው በቅድስት ሔዋን ነው:: ብዙ ጊዜ የእናታችን ሔዋን ጥፋቷ እንጂ በጐ ነገሯ: ደግነቷ: ንስሃዋ አይነገርላትም:: ሆኖም እናታችን ቅድስት ሔዋን ክብር የሚገባት ሴት ናት::

*ክርስቶስ ሰው የሆነ እርሷንና ልጆቿን ለመቀደስ ነውና:: "ከመ ይስዓር መርገማ ለሔዋን ዲበ ዕፅ ተሰቅለ" እንዲል:: (ድጓ)

+ቀጥሎ በብሉይ ኪዳን እነ ሐይከል: እድና: ሣራ: ርብቃ: አስኔት: ሲፓራ: ሐና: ቤርሳቤህን የመሰሉ እናቶቻችን በበጐው መንገድ ፈጣሪን ደስ አሰኝተዋል:: በዘመነ ሥጋዌም ቅዱሳቱ ሐና: ኤልሳቤጥ: ማርያም: ሶፍያ: ሰሎሜ: ዮሐና እና 36ቱ ቅዱሳት አንስት በጐነታቸው ያበራል::

+ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ለ2,000 ዓመታት የተነሱ አእላፍ ቅዱሳት እናቶቻችንን ግን ዘርዝረን አንዘልቃቸውም:: በቅድስናቸው አራዊትን ያሰገዱ: ነገሥታትን ያንቀጠቀጡ: አጋንንቸትን የረገጡ: በዘንዶ ላይ የተጫሙ ብዙ እናቶችን ቤተ ክርስቲያን አፍርታለች::

+ዛሬም ቢሆን በበርሃና በከተማ በጐውን ጐዳና የተከተሉ ብዙ እናቶች እንዳሉን እናውቃለን:: አንድም እናምናለን:: ግን ግን በከተሞች የምንመለከተው ሥርዓቱን የለቀቀው የበርካታ እህቶቻችን አካሔድ ለሃገርም ለቤተ ክርስቲያንም ትልቅ ስጋት ነው:: ክብርና ነውር የማይለይበት ዘመን ይመስላል::

+ይህንን እያነበባችሁ ያላችሁ እህቶቼ! አንድ ነገር ልንገራችሁ:: በመልካቸው ብዙዎችን ያጋጩ: አጊጠው በመታየታቸው ብዙዎችን ያሰናከሉ: ለብዙ ምዕመናንም የጥፋት ምክንያት የሆኑ ብዙ ሴቶች በታሪክ ነበሩ::

+የሚያሳዝነው ግን ዛሬ ያሉት ከመሬት በታች ነው:: አፈር በልቷቸዋል:: ስም አጠራራቸውም ጠፍቷል:: በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬ በዘለዓለማዊው እሳት እየተቃጠሉ በሲኦል: በጥልቁ ውስጥ አሉ::

+እናም ወገኖቼ! ይህን አውቀን እንንቃ:: ይህ ዓለም ጠፊም: አጥፊም ነውና:: እድሜአችን ቢረዝምና ከዚህ በኋላ ለ100 ዓመታት ብንኖርም እርሱም ማለቁ አይቀርምና:: ምርጫችን ዘለዓለማዊው ሕይወት ይሁን ትላለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን::

+" እለ ቅድስት ሶፍያ "+

+ቅድስት ሶፍያና አብረዋት በዚህ ዕለት የሚከበሩ ቅዱሳት አንስት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም የነበሩ ክረስቲያኖች ናቸው:: አብዛኞቹ መልክ (ደም ግባት) ከጠባይ ጋር የተስማማላቸው ነበሩ:: ነገር ግን ከምድራዊው ክብር ሰማያዊውን መርጠው ለመንፈሳዊው ሙሽርነት ወደ ገዳም ገቡ::

+ከእነዚህ ቅዱሳን መካከል በጸጋና በሞገስ: በትምሕርትም የምትበልጥ ቅድስት ሶፍያ ናትና እመ ምኔት አድርገው ሾሟት:: እርሷም ለገዳሙ በጐውን ሥርዓት ሠራች:: ሁሉም (ደናግሉም መነኮሳይያቱም) በአንድነት ይጾማሉ: ይጸልያሉ: ይሰግዳሉ: የቅዱሳንን ተጋድሎ ያነባሉ:: ሥጋውን ደሙን ይቀበላሉ::

+እርስ በርስ ደግሞ ፈጽመው ይፋቀራሉ:: በዚህ ሕይወት አንዳንዶቹ እስከ 70 ዓመት ቆዩ:: የቅድስናቸው ዜና ሲሰማ በሮም ግዛት ያሉ ወጣት ሴቶች እየመጡ ይቀላቀሏቸው ነበር:: ቅድስት ሶፍያም የሕይወትን መንገድ ታሳያቸው ነበር::

+ከዚህ ሁሉ በኋላ ከሐዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ለጦርነት ወደ ፋርስ ሲሔድ ስላያቸው ባንድነት ሰብስቦ ሁሉንም በሰይፍ አስመታቸው:: ቅድስት ሶፍያም አብራ ሰማዕት ሆነች:: ስለ ቅዱሳኑ የሚበቀል ጌታም ቅዱስ መርቆሬዎስን ልኮ በጦርነቱ መካከል በጦር ወጋው:: ዑልያኖስ ወደ ዘለዓለም ኩነኔ ሲሔድ: ቅዱሳት አንስት ወደ ገነት ሔደዋል::

+" ባሕረ ሐሳብ "+

+ዳግመኛ በዚህ ቀን: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ባሕረ ሐሳብ በዓለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን አግኝቷል:: ሊቁ ቅዱስ ድሜጥሮስ (የግብጽ 12ኛ ፓትርያርክ) መንፈስ ቅዱስ ቀመረ ባሕረ ሐሳብን ገልጾለት በዓለም ላሉ ሊቃነ ዻዻሳት ልኮላቸው በዚህች ዕለት በሮም ከተማ ተሰበሰቡ::

+ሊቃውንትም ሐዋርያት ካስተማሩት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ቢያገኙት በደስታ ተቀብለውታል:: እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ለ1,700 ዓመታት ቤተ ክርስቲያን እየተገለገለችበት ይገኛል::

+የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ ዛሬም እንደ እነርሱ ያሉትን አያሳጣን:: በጸሎታቸው ምሮ ከበረከታቸው ይክፈለን::

+ኅዳር 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
2.ደናግለ ሮሜ (ሰማዕታት)
3.ቅዱስ ዻውሎስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ
5.ጉቡዓን ኤዺስ ቆዾሳት

ወርኀዊ  የቅዱሳን  በዓላት

1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
7.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ

++"+ ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ:: +"+ (1ዼጥ. 3:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5

መዝገበ ቅዱሳን

18 Nov, 08:58


††† እንኳን ለአበው ቅዱሳን "318ቱ ሊቃውንት" ዓመታዊ የጉባኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ጉባኤ ኒቅያ †††

††† በዚህች ዕለት (ኅዳር 9 ቀን) በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት ተሰብስበዋል::

የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር: በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ: 2348 ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ::

ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዝያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት መስከረም 21 ቀን ነበር:: ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና: ምግባራቸው የጸና 318ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ::

እነዚህ አባቶች "ሊቃውንት" ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን:: 318ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::

እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ: ፍቅረ ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ: የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው:: እስኪ እናውቃቸው ዘንድ የጥቂቶችን ማንነት በስምና በመገለጫ እንመልከት:-
1.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ (በዘመነ ሰማዕታት ለ22 ዓመት ሲቆራርጡት ኖረው በጉባኤው ላይ የተገኘው ያለ እጅ: እግር: ጀሮ: ከንፈር: ቅንድብ ነው)
2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ (ስለ ቀናች እምነት ለ50 ዓመታት የተጋደለና ለ15 ዓመታት በስደት የኖረ ነው)
3.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ (ከሰማይ ብርሃን ይወርድለት የነበረ አባት ነው)
4.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ (በጸሎቱ አጋንንትን ያንቀጠቀጠ: ነፍሳትን ከሲዖል የቀማና ከከዊነ እሳት የደረሰ አባት ነው)
5.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ (ስለ ቀናች እምነት መጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ ለ15 ዓመታት ተጥሎ የኖረ ሰማዕት ነው)
6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሜራ (ከሕጻንነቱ የተቀደሰ: በበርሃ የተጋደለ: በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው)
7.ቅዱስ ያዕቆብ ዘንጽቢን (በደግነቱ ሙታንን ያስነሳ: ወንዝን በጸሎቱ ያቆመ: በንጽሕና የተጋደለ አባት ነው)
8.ቅዱስ ሶል ጴጥሮስ (ቅዱሱን ንጉሥ ያጠመቀ:
ቁስጥንጥንያን በወንጌል ያበራ ሊቅ ነው)
9.ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ (ስለ ቀናች እምነቱ ብዙ ግፍ የደረሰበትና በስደት ያረፈ አባት ነው)

ለአብነት እንዲሆኑን እነዚህን አነሳን እንጂ 318ቱም ሊቃውንት ስለ ቤተ ክርስቲያን ተግተው የተጋደሉ: ብዙ ዋጋም የከፈሉ አባቶች ናቸው::

በወቅቱ ታዲያ ቤተ ክርስቲያንን የበጠበጡ ብዙ መናፍቃን ቢኖሩም የአርዮስ ግን ከመጠኑ አለፈ:: የእርሱ ኑፋቄ (ፈጣሪያችንን ፍጡር ነው ማለቱ) መነሻው ከእርሱ በፊት ነው:: መናፍቃን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ መኖራቸው ግልጽ ነው::

በተለይ ደግሞ ቢጽ ሐሳውያንና ግኖስቲኮች የወለዷቸው እሾሆች አባቶቻችንን እንቅልፍ ነስተው ነበር:: የሚገርመኝ በዘመኑ እንደ ነበሩ መናፍቃን ኃይለኝነት የእኞቹ ከዋክብት ሊቃውንት ባይኖሩ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳስብ ነበር::

ግን እግዚአብሔር ለሁሉ እንደሚገባ ያዘጋጃልና አበው ብርቱ መናፍቃንን በብርቱ መንፈሳዊ ክንድ እያደቀቁ ከጐዳና አስወገዷቸው:: የዛሬውን ደካማ ትውልድ ደግሞ የአርዮስ ልጆች 2 (3) ጥቅስ ይዘው ሲያደናብሩት ይውላሉ::

ሐረገ መናፍቃን በርጉም ሳምሳጢ ጳውሎስ: በመርቅያንና በማኒ ይጀምራል:: በእርግጥ አርጌንስ እና የግብጹ ቀሌምንጦስም ተቀላቅለዋቸዋል:: ርጉም ሳምሳጢ ድያድርስን በኑፋቄ ወልዶታል:: ድያድርስ ሉቅያኖስን: ሉቅያኖስ ደግሞ አርዮስን ወልደዋል::

ይህ አርዮስ እጅግ ተንኮለኛ በመሆኑ ልክ እንደ ዘመኑ መሰሎቹ ግጥምና ዜማ እየጻፈ በየመንገዱ እያደለ: በየቤቱ እየሰበከ ብዙዎችን በኑፋቄው በከለ:: በመጀመሪያ ተፍጻሜተ ሰማዕት
ቅዱስ ጴጥሮስ (አስተማሪው) መከረው:: ባይሰማው ከአንዴም ሁለት ጊዜ አወገዘው::

ቆይቶ ሰነፉ ጳጳስ አኪላስ ቢፈታውም ሊቁ ቅዱስ
እለእስክንድሮስ እንደ ገና አወገዘው:: እንደ አርዮስ ሐሳብ መድኃኒታችን ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት!) ማለት ክርስትናን ከሥሩ ፈንቅሎ መጣል ነው::

ስለ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ብሉይም ሐዲስም እየመሰከሩ (ኢሳ. 9:6, መዝ. 46:5, 77:65, ዘካ. 14:4, ዮሐ. 1:1, 10:30, ራዕይ. 1:8, ሮሜ. 9:5) አርዮስና የዛሬ መሰሎቹ አንዲት ጥቅስ ይዘው ክርስትናን ከመሠረቱ ለመናድ መሞከራቸው በእርግጥም ከሰይጣን መላካቸውን ያሳያል::

በወቅቱም በመወገዙ "ተበደልኩ" ብሎ የጮኸው አርዮስ ከ2ቱ አውሳብዮሶች ባልንጀሮቹ (ዘቂሣርያና ዘኒቆምድያ) ጋር ሆኖ ወደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ሔዶ ከሰሰ:: ቅዱሱ ንጉሥም የጉዳዩን ክብደት ተመልክቶ የዓለም ሊቃውነት ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ::

ከሚያዝያ 21 እስከ መስከረም 21 ተጠቃለው ገቡ:: በ325 ዓ/ም (በእኛው በ318 ዓ/ም) ለ40 ቀናት የሚቆይ ሱባኤን ያዙ:: ሱባኤውን ሲጨርሱም በ4ቱ ፓትርያርኮች (እለእስክንድሮስ: ሶል ጴጥሮስ: ዮናክንዲኖስና ኤዎስጣቴዎስ) መሪነት: በእለእስክንድሮስ ሊቀ መንበርነት: በአትናቴዎስ ጸሐፊነት ጉባኤው ተጀመረ::

በጉባኤው ሙሉ ስልጣን በሰማይ ከፈጣሪ: በምድር ከንጉሡ የተሰጣቸው አበው አርዮስን ተከራክረው ከነ ጀሌዎቹ ምላሽ አሳጡት:: ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: ሥግው ቃል: ራሱም እግዚአብሔር መሆኑን አስረዱት:: በጉባኤው መጨረሻም:-
1.አልመለስም በማለቱ አርዮስን አወገዙ::
2.ጸሎተ ሃይማኖትን "ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም" እስከሚለው ድረስ ተናገሩ::
3.ፍትሐ ነገሥትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ብለው አዘጋጁ::
4.ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚገባ አደራጁ::
5.በስማቸው የሚጠራ አንድ ቅዳሴን ደረሱ::

ይህ ሁሉ ሲሆን መድኃኒታችን ክርስቶስ 319ኛ ሆኖና ገሊላዊ ጳጳስን መስሎ ሁሉን አከናውኖላቸዋል:: አባቶችም ሥራቸውን
ከጨረሱ በኋላ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ባርከው ወደየ ሃገረ ስብከታቸው ተመልሰዋል::

††† በየዘመኑም ዐርፈው ለክብረ መንግስተ ሰማያት በቅተዋል:: እኛም እነሆ "አባቶቻችን:
መምሕሮቻችን:
መሠረቶቻችን:
ብርሃኖቻችን:
ምሰሶዎቻችን" እያልን እናከብራቸዋለን::

††† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት በጸሎታቸው እኛንም: ቤተ ክርስቲያናችንንም ከክፉ ጠላት ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† ኅዳር 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን 318ቱ ሊቃውንት
2.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
3.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
4.አባ ይስሐቅ ሊቀ ጳጳሳት
5.ሊቁ አካለ ወልድ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
3.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
4.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ
5.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ

††† "እውነት እላቹሃለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል:: በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል:: ደግሞ እላቹሃለሁ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል:: ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና::" †††
(ማቴ. ፲፰፥፲፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan

መዝገበ ቅዱሳን

11 Nov, 15:34


+በ381 ዓ/ም መቅዶንዮስ: አቡሊናርዮስና ሰባልዮስ በካዱ ጊዜም ለጉባኤው ወደ ቁስጥንጥንያ ከሔዱ ሊቃውንት አንዱ ይሔው ቅዱስ ኪርያቆስ ነው:: ወደ ጉባኤው የሔዱትም ከታላቁ ሊቅና የኢየሩሳሌም ሊቀ ዻዻሳት ቅዱስ ቄርሎስ መንፈሳዊ ጋር ነው::+ሁለቱ እጅግ ወዳጆች ነበሩና:: በጉባኤውም መናፍቃንን ረትተው: ሃይማኖትን አጽንተው: ሥርዓትን ሠርተው ተመልሰዋል:: ቅዱስ ኪርያቆስም በተረፈ ዘመኑ በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል::=>አምላከ አበው የወዳጆቹን የቅድስና ምሥጢር ለእኛም ይግለጽልን:: በረከታቸውንም አትረፍርፎ ይስጠን::

=>ኅዳር 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ (ዘደብረ በንኮል)
2.ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ጻድቅ (የሠራዊት አለቃ)
3.ቅዱስ ኪርያቆስ ሊቅ
4.ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ንጉሥ (ልደቱ)
5.ቅዱሳን አትናቴዎስና እህቱ ኢራኢ (ሰማዕታት)
6.አቡነ ፍሬ ካህን

=>ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)

=>+"+ በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል:: +"+ (ምሳሌ 10:6)

   << <ወስብሐት ለእግዚአብሔር>>>
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5

መዝገበ ቅዱሳን

11 Nov, 15:33


=>+"+ እንኩዋን ለቅዱሳን ጻድቃን "አቡነ መድኃኒነ እግዚእ" : "ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል" እና "ቅዱስ ኪርያቆስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+*" አቡነ መድኃኒነ እግዚእ "*+

=>መዘንጋታቸው እጅግ ከሚያስቆጭ ኢትዮጽያውያን አባቶች ትልቁን ሥፍራ እኒህ አባት ይወስዳሉ:: የማር ወለላን በሚያስንቅ ጣዕመ ሕይወታቸው ሃገራችንን ያጣፈጡ: ብርሃን ሆነው ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው::

+አባ መድኃኒነ እግዚእ የተወለዱት በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ትግራይ (አዲግራት) ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸውም ቀሲስ ሰንበትና ሒሩተ ማርያም ይባላሉ:: በደግነትም እጅግ የታወቁ እንደ ነበሩ ገድላቸው ይናገራል:: "መድኃኒነ እግዚእ" ማለት "ጌታ መድኃኒታችን ነው" ማለት ነው::

+ብዙ ጊዜም "ዘደብረ በንኮል - ሙራደ ቃል" እየተባሉ ይጠራሉ:: "ደብረ በንኮል" ማለት ትግራይ ውስጥ የሚገኝና ጻድቁ በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ያነጹት ገዳም ነው:: "ሙራደ ቃል" ደግሞ "የቃል (የምሥጢር) መውረጃ" እንደ ማለት ሲሆን በቦታው ሱባኤ የያዘ ሰው ልክ እንደ ቅዱስ ያሬድ ምሥጢር እንደሚገጥለት የሚጠቁም ስም ነው::

+ጻድቁ መድኃኒነ እግዚእ በልጅነታቸው ከሊቁ ካህን አባታቸውና ከሌሎችም መምሕራን ተምረው: ምናኔን መርጠው ገዳም ገብተዋል:: በጾም: በጸሎትና በስግደት ተግተው ጸጋ እግዚአብሔር ሲሰጣቸው ወደ ደብረ በንኮል ሒደው ገዳም መሠረቱ::

+በኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መካከለኛው ዘመን (በተለይ ከ13ኛው እስከ 15ኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለው) የብርሃን ዘመን ይባላል:: ምክንያቱም ዘመኑ
*ክርስትና ያበበበት::
*መጻሕፍት የተደረሱበት::
*ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት::
*ገዳማዊ ሕይወት የሠመረበት ወቅት በመሆኑ ነው::

+ለዚህ ትልቁ አስተዋጽኦ ደግሞ:-
¤አቡነ ተክለ ሃይማኖት::
¤አቡነ ኤዎስጣቴዎስ::
¤አባ ሰላማ ካልዕ::
¤አቡነ ያዕቆብ::
¤ቅዱሱ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ::
¤አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ::
¤አቡነ መድኃኒነ እግዚእን የመሰሉ አበው መነሳታቸው ነው::

+በተጨማሪም:-
¤12ቱ ንቡራነ ዕድ::
¤7ቱ ከዋክብት::
¤47ቱ ከዋክብት::
¤5ቱ ከዋክብት የሚባሉ አበው አስተዋጽኦም ልዩ ነበር:: ከእነዚህ መካከልም የ7ቱ እና የ47ቱ ከዋክብት አስተማሪ: የአበው 3ቱ ሳሙኤሎች (ዘዋልድባ: ዘጣሬጣና ዘቆየጻ): የሌሎችም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን አባት የሆኑት አባ መድኃኒነ እግዚእ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ::

+ጻድቁ ቅዱሳኑን ሰብስበው: አስተምረው: አመንኩሰው: መርቀው ሰደው: ሃገራችንን እንዲያበሩ በማድረጋቸው እንደ አባ ኢየሱስ ሞዐ እርሳቸውም "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" ይባላሉ:: ታላቁ ጻድቅና ሰባኬ ወንጌል አባ ዓቢየ እግዚእም (ጐንደር ውስጥ እባብና ጅብ እንዳይጐዳ የገዘቱ አባት ናቸው) የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ነበሩ ይባላል::

+ጻድቁ መድኃኒነ እግዚእ በተትረፈረፈ የቅድስና ሕይወታቸው ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: አራዊትን ገዝተዋል: በአንበሳ ጀርባ ላይ እቃ ጭነዋል:: ከረዥም የተጋድሎ ሕይወት በሁዋላም ኅዳር 3 ቀን ዐርፈዋል:: እድሜአቸውም 180 ነው::

¤" መድኃኒነ እግዚእ አቡነ መስተጋድል::
ምንኩስናሁ ምዑዝ ከመ ኮል::
በመንፈሰ ጸጋ ክሉል::" (መጽሐፈ ሰዓታት)

¤" ተአምረ ኃይልከ አባ መድኃኒነ እግዚእ አቡነ::
እም አፈ ዜናዊ ሰማዕነ:: ወበዓይነ ሥጋ ርኢነ::
መንክርኬ አእላፈ ቤትከ ንሕነ::
ባሕቱ በዝ ተአምሪከ ርድአነ::
ለሰይፈ አርዕድ ንጉሥ ዘወሀብኮ ኪዳነ::
ከመ ረድኤቱ ታፍጥን ጊዜ ጸብዕ ኮነ::" (አርኬ)

+"+ ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል +"+

=>የዚህ ቅዱስ ኢትዮዽያዊ ዜና ሕይወት ለሁላችንም ትልቅ ትምርትነት ያለው ነው:: በተለይ በምክንያት ከቅድስና ሕይወት እንዳንርቅ ያግዘናል ብየም ተስፋ አደርጋለሁ:: የቅዱሱ ወላጆች ገላውዴዎስና ኤልሳቤጥ ሲባሉ በምድረ ሽዋ በበጐ ምጽዋታቸው የተመሰከረላቸው ነበሩ::

+ፈጣሪ ሰጥቷቸው ኅዳር 8 ቀን (በበዓለ አርባዕቱ እንስሳ) ወልደውታልና "ዓምደ ሚካኤል - የሚካኤል ምሰሶ" ሲሉ ሰይመውታል:: ገና በልጅነቱ ብዙዎችን ያስገርም የነበረው ቅዱሱ አንዴ በ3 ዓመቱ ከቅዳሴ መልስ ጠፋቸው::

+ወላጆቹ እያለቀሱ በሁሉ ቦታ ፈለጉት:: ግን ሊገኝ አልቻለም:: በ3ኛው ቀን የሞቱን መታሠቢያ ሊያደርጉ ካህናትና ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ግን ባዩት ነገር ተገረሙ:: ሕጻኑ ዓምደ ሚካኤል ከቤተ መቅደሱ መሃል: ከታቦቱ በታች ካለው መንበር (ከርሠ ሐመር ይሉታል) ቁጭ ብሎ ይጫወታል::

+ያየ ሁሉ "ዕጹብ ዕጹብ" ሲልም አደነቀ:: ምክንያቱም በተፈጥሮ ሥርዓት ሕጻን ልጅ ያለ ምግብ 3 ቀን መቆየት ስለማይችልና ሕጻኑ በዚያ የቅድስና ሥፍራ ላይ ምንም ሳይጸዳዳ በመገኘቱ ነው::

+ብጹዕ ዓምደ ሚካኤል ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እየተማረ: በጾምና በጸሎት አደገ:: በ15ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ላይ ንጉሥ የነበረው ጻድቁ አፄ ዘርዓ ያዕቆብም ቅዱሱን የሠራዊት አለቃ (ራስ ቢትወደድ): ወይም በዘመኑ አገላለጽ የጦር ሚኒስትር አድርጐ ሾመው::

+መቼም እዚህ ቦታ ላይ ተቀምጦ መልካምን መሥራት ልዩ ነገርን ይጠይቃል:: በተለይ ደግሞ በዙሪያው የሚከቡትን ተንኮለኞች ድል መንሳቱ ቀላል አልነበረም:: ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ግን በዘመነ ሲመቱ እነዚህን ሠራ:-

1.በጠዋት ተነስቶ ነዳያንን ይሰበስብና ቁርስ: ምሳ ያበላቸዋል:: ይሕም ዕለት ዕለት የማይቁዋረጥ በመሆኑ ሃብቱ አልቆ ደሃ ሆነ::

2.ከቀትር በሁዋላ ዘወትር ቆሞ ያስቀድስና ጸበል ተጠምቆ ይጠጣል:: ማታ ብቻ እህልን ይቀምሳል::

3.ሽፍታ ተነሳ ሲባል ወደ ዱር ወርዶ: ጸልዮ: ሽፍታውን አሳምኖት ይመጣል እንጂ አይጐዳውም::

4.ጦርነት በሚመጣ ጊዜ ክተት ሠራዊት ብሎ ይወርዳል:: ግን ለምኖ: ጸልዮ: ታርቆ ይመጣል እንጂ ጥይት እንዲተኮስ አይፈቅድም ነበር::

+በዚህ መንገድ በ3ቱ ነገሥታት (በዘርዐ ያዕቆብ: በዕደ ማርያምና እስክንድር) ዘመን ሁሉ አካባቢውን ሰላም አደረገው:: ዓለም ግን ዓመጸኛ ናትና በአፄ እስክንድር ዘመን (በ1470ዎቹ) በሃሰት ተከሶ ስደት ተፈረደበትና ወደ በርሃ ተጋዘ::

+በዚያም ቅዱስ ሚካኤል ሰማያዊ መናን እየመገበው: ሥጋ ወደሙን እያቀበለው ኖረ:: ትንሽ ቆይቶ ግን የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በንጉሡ አደባባይ ተገደለ:: ለ30 ቀናትም በመቃብሩ ላይ የብርሃን ምሰሶ ወረደ በዚህም ንጉሡ በእጅጉ ተጸጸተ::

+"+ ቅዱስ ኪርያቆስ +"+

=>ሊቅነትን ከገዳማዊ ሕይወት የደረበው ቅዱስ ኪርያቆስ የቆረንቶስ ሰው ሲሆን አበው "ጥዑመ ቃል - አንደበቱ የሚጣፍጥ" ይሉታል:: ገና በልጅነቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያነብ ከአንደበቱ ማማር: ከነገሩ መሥመር የተነሳ ከዻዻሱ እስከ ሕዝቡ ድረስ ተደመው ያደምጡት ነበር::

+በወጣትነቱ ጣዕመ ዓለምን ንቆ ከቆረንቶስ ኢየሩሳሌም ገብቷል:: ቀጥሎም ወደ ፍልስጥኤም ተጉዞ የታላቁ አባ ሮማኖስ ደቀ መዝሙር ሁኖ መንኩሷል:: በገዳሙ ለበርካታ ዘመናት ሲኖርም እጅግ ብዙ ተአምራትን ሠርቷል::

መዝገበ ቅዱሳን

09 Nov, 18:15


<<< በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። >>>

"" ኅዳር 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ""

+" ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ "+

+ሃገራችን ኢትዮዽያ በሁሉም ዘርፍ ቅድስና ያላቸው ቅዱሳን ባለቤት ናት:: በዘመኑ ያለን ወጣቶችም ሆነ ጐልማሶች ከቤተ ክርስቲያንና ከቅድስና ሕይወት ለምን እንደራቅን ስንጠየቅ ከምንደረድራቸው ምክንያቶች አንዱ ሥራችን ነው::

+ነገር ግን ሥራው በራሱ ኃጢአት እስካልሆነ ድረስ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ቢሆን ቅድስናን ማስጠበቅ እንደሚቻል አበው አሳይተውናል:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም ከእነዚህ ቅዱሳን አንዱ ነው::

*እርሱ ንጉሥ ነው: ግን ገዳማዊ ሕይወትን በቤተ መንግስቱ ውስጥ ያሳየ ጻድቅ ነው::
*ሁሉ በእጁ ነው: እርሱ ግን ንጹሕና ድንግል ነው::
*እርሱ የጦር መሪ ነው: ግን በእጁ ደም አልፈሰሰም::

*እርሱን 'ወደድንህ: ሞትንልህ' የሚሉ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ነበሩት:: ለእርሱ ግን ፍቅር ማለት ክርስቶስ ነበር::
*የሃገር መሪ: የኢትዮዽያ ንጉሠ ነገሥት እንደ መሆኑ እጅግ ባተሌ (busy) ነው:: ግን ደግሞ ለክርስትናው ጊዜ ያጣ ሰው አልነበረም::

+እኛ ቤተ ክርስቲያንን "በሐኪ" ለማለት (ለመሳለም) እንኳ 'ጊዜ የለኝም' ስንል እርሱ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ይፈለፍል: ያንጽ: በክህነቱ ያገለግል: ማዕጠንት ያጥን: ለረጅም ሰዓትም ይጸልይ ነበር::

+እኛ 'ሥራ ውያለሁና ደክሞኛል' ብለን ከስግደት ስንርቅ እርሱ ግን ንጉሥ ሆኖ ሳለ: ጦር በፊት: በኋላ: በቀኝና በግራ ተክሎ ይሰግድ ስለ ነበር ደሙ እንደ ውሃ በምድር ላይ ፈሷል:: ይህንን ሁሉ ያደረገው ቅዱሱ የኢትዮዽያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ነአኩቶ ለአብ ነው::

"ለመሆኑ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ማን ነው?"

#‎ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግስት ከነገሡ 11 ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም 2ኛ ነው:: እርሱን በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናት:: ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው::

+እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጀሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር:: ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች:: ሕጻኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ "ነአኩቶ" እያለ ሲዞር ሰማችው::

+እዚያው ላይም 'ነአኩቶ ለአብ' (አብን እናመስግነው) ስትል ስም አወጣችለት:: ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግስቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በርሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕጻን ወደ አጐቱ ላሊበላ ቤተ መንግስት ውስጥ ገባ::

+የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕጻኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ:: በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና:: ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም እድሜው 30 ደረሰ::

+በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ:: ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት:: ቤተ መንግስቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ::

+በውስጡም በ4 አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው:: ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር: ቅዳሴ ሲቀድስ: በጾም ይውላል:: ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቁዋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል::

+ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል:: ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል:: እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል:: በተለይ ዐርብ ዐርብ ሲሆን ደሙ: እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር:: እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና::

+ከተጋድሎው ጐን ለጐን ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር:: በተለይ በ1211 አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት:: እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግስቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት: ይቀድስባትም ነበር::

+ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ሥውራን ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ:: እርሱም "ወገኖቼ! ከወዴት መወጣችሁ?" ቢላቸው "መዐዛ እጣንህን አሽተን መጣን" ሲሉ መለሱለት:: በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ "አሽተን (አሸተን) ማርያም" ስትባል ትኖራለች::

+ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠ በ30 ዓመቱ ነው:: ለ40 ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ 70 ዓመት ሞላው:: በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ሰላምታንም ሰጠው::

+"ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለ40 ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም:: ከፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና:: የሚያከብርህን አከብረዋለሁ:: ደጅህን የሳመውን: ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን: መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው::

+ቀጥሎም "ይሕች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር" አለው:: እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጸበል ይንጠበጠባል:: ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን:: ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና::

+ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደውታል:: የተሰወረበትን ዕለት ስንክሳር ሕዳር 1 ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በ3 ነው ይላሉ:: በዙፋኑም ላይ የአጐቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል::

+አምላከ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በቃል ኪዳኑ ይማረን:: ከበረከቱም አትረፍርፎ ይስጠኝ::

+ኅዳር 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
2.ቅዱሳን መክሲሞስና ባልንጀሮቹ (ሰማዕታት)

ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር


++"+ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን: ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን:: ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን:: +"+ (ሮሜ. 6:5)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

መዝገበ ቅዱሳን

08 Nov, 18:34


=>ወርኃዊ በዓላት1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
3.አባ ሣሉሲ ጻድቅ

++" ... እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተ

ባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ:: ዼጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሏት አንዲት አገልጋይ ትሰማ ዘንድ ቀረበች:: የዼጥሮስ ድምጽ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሳ ደጁን አልከፈተችም:: ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ዼጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች:: +"+ (ሐዋ. 12:12-15)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan

መዝገበ ቅዱሳን

08 Nov, 18:33


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ ጥቅምት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

+" ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ "+

✞✞✞ በዚሕች ዕለት ከ72ቱ አርድእት አንዱ የሆነ: ወንጌላዊ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ዘአንበሳና ርዕሰ ሊቃነ ዻዻሳት የተባለ ቅዱስ ማርቆስ ተወልዷል ::

+ቅዱስ ማርቆስ እናቱ ማርያም: አባቱ አርስጥቦሎስ ይባላሉ:: በልጅነቱ ኦሪትንና የዘመኑን ጥበብ ሥጋዊ በሚገባ ተምሮ ክርስቶስን ከቤተሰቦቹ ጋር ተከትሏል:: የመጀመሪያ ስሙ ዮሐንስ ሲሆን ከ120ው ቤተሰብ በእድሜ በጣም ትንሹ /20 ዓመት/ እርሱ ነበር::

+ለ3 ዓመታት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብዙ ደክሟል:: በተለይ የግብፅና የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው:: ክህነትን ያገኘን ከርሱ ነውና::

+ቅዱስ ማርቆስ 16 ምዕራፍ ያለውን ወንጌሉን ሲጽፍ ኪሩብ ገጸ አንበሳ በቀኙ: ሊቀ ሐዋርያት በግራው ሆነው ይራዱት ነበር:: ቅዱሱ ክቅዱስ ዻውሎስ: ከበርናባስና ዼጥሮስ ጋር ተጉዟል:: ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ሰሜን አፍሪካ አካባቢ አረማውያን ገድለውታል:: ይህቺ ዕለት የልደቱ መታሠቢያ ናት::

+ዳግመኛ በዚህ ቀን የቅዱስ ማርቆስን ወላጆችን እናስባቸው ዘንድ ይገባል:: ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ) የጌታ ቅን አገልጋይ የነበረ: ቅድስት ማርያም (እናቱ) ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ: ጌታችንን ያገለገለች ቤቷን ለሐዋርያትና ለጌታ በስጦታ ያበረከተች ቅድስት ናት::

+ቤቷም (ጽርሐ ጽዮን) የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ይህች ቤት መንፈስ ቅዱስ ወርዶባታል:: የእመቤታችን ግንዘትም ተከናውኖባታል::

+እግዚአብሔር ከሐዋርያዊው ቅዱስ ቤተሰብ በረከትን ያድለን::

+" ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ "+

+ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

*የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

*ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

*ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

*የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በኋላ በዚህች ቀን (ሰኔ 30) ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

*ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

*እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

*ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

*ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

*ከዚህ በኋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

*ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

*ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

*"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

*በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

*ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

*ከዚሕ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

✞✞✞ ይህች ዕለት ለቅዱሱ 'አስተርዕዮተ ርዕሱ' ወይም ቅድስት ራሱ ከተወረችበት የተገለጠችበት ነው::+ጥቅምት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ)
3.ቅድስት ማርያም (እናቱ)
4.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
5.አባ አብርሃም ገዳማዊ
6 ቅዱስ ይስሐቅ ንጉሥ

መዝገበ ቅዱሳን

07 Nov, 17:57


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

=>+"+ እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን "ሳሙኤል ዘወገግ": "ጸቃውዐ ድንግል" እና "ድሜጥሮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+"+ አባ ሳሙኤል ዘወገግ +"+

=>ሃገራችን ኢትዮዽያ ማኅደረ ቅዱሳን (ምዕራፈ ቅዱሳን) እንደ መሆኗ ፍሬ ክብር: ፍሬ ትሩፋት ያፈሩ ብዙ አባቶችና እናቶችን አፍርታለች:: ብርሃን ሁነው ካበሩላት ቅዱሳን መካከል አንዱ ደግሞ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ ናቸው::

+በእኛው ሃገር ብቻ ብዙ "ሳሙኤል" የሚባሉ ቅዱሳን በመኖራቸው ስንጠራቸው "ዘእንትን" እያልን ነው:: ለምሳሌም:

*ሳሙኤል ዘዋሊ
*ሳሙኤል ዘወገግ (የዛሬው)
*ሳሙኤል ዘጣሬጣ
*ሳሙኤል ዘቆየጻ
*ሳሙኤል ዘሃሌ ሉያና
*ሳሙኤል ዘግሺን መጥቀስ እንችላለን:: ሁሉም የመካከለኛው ዘመን ሐዋርያዊ አባቶች ናቸው::

+ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ የተወለዱት በ13ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ሃገረ ሙላዳቸው የብዙ ቅዱሳን ቤት የሆነችው ሽዋ ናት:: መንደራቸውም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ብዙም አይርቅም::

+የጻድቁ ወላጆች እንድርያስና አርሶንያ የሚባሉ ሲሆን ደጐች ነበሩ:: ጻድቁ በተወለደ ጊዜ የቤታቸው ምሰሶ ለምልሞ ተገኝቷል:: አቡነ ሳሙኤል ከልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው በጉብዝናቸው ወራት ይህችን ዓለም ንቀዋል::

+የታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው በደብረ ሊባኖስ መንነዋል:: ከ12ቱ ኅሩያን (ምርጦች) አርድእት አንዱ ነበሩና በክህነታቸው ደብረ ሊባኖስን ተግተው ያጥኑ ነበር:: በዚያውም በንጹሕ ልቡና በጾምና ጸሎት ይተጉ ነበር::

+አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በሁዋላ በደጉ ዻዻስ በአቡነ ያዕቆብ ዘመን 12ቱ ንቡራነ እድ ተመረጡ:: እነዚህ አባቶች በወንጌል አገልግሎት: በተለይ ደቡብና ምሥራቁን የሃገራችን ክፍል ያበሩ ናቸው:: ቅዱሳኑ ሲመረጡም ከአቡነ ፊልዾስ ቀጥለው በ2ኛ ደረጃ የተመረጡ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ ናቸው::

+ሃገረ ስብከታቸውም ሐረርና ሱማሌ ነበር:: ጻድቁ በሃገረ ስብከታቸው ወርደው በሐረርና ሱማሌ አካባቢ ለዘመናት የወንጌልን ዘር ዘርተው እልፍ ፍሬን አፍርተዋል:: አካባቢውንም መካነ ቅዱሳን አድርገውታል::

+ቀጥለው ገዳማዊ ሕይወትን ያጸኑ ዘንድ በምሥራቁ የሃገራችን ክፍል በአፋር ሱባኤ ገቡ:: ቦታውም ደብር ሐዘሎ ነበር:: በቦታው ለ155 ቀናት ከቆሙ ሳያርፉ: ከዘረጉ ሳያጥፉ: እህል ውሃ ሳይቀምሱ ጸለዩ::

+በሱባኤያቸው ፍጻሜ ግን ቅዱስ መልአክ መጥቶ "ሳሙኤል ወደዚያ ተራራ ሒድ:: የስምህ መጠሪያ እርሱ ነውና:: ይህ ግን የሌላ ሰው (የአባ አንበስ ዘሐዘሎ) ርስት ነው" አላቸው:: ጻድቁም ወዳላቸው ተራራ ሒደው ቢጸልዩ ከሰማይ ብርሃን ወረደላቸው::

+በመንፈቀ ሌሊት የበራው ብርሃን እስከ ጐረቤት መንደር ሁሉ በመድረሱ የአካባቢው ሰው "ወገግ አለኮ-ነጋ" ብለውዋል:: በዚህ ምክንያት ዛሬም "ደብረ ወገግ" ይባላል:: ይህ ቦታ ዛሬም ድረስ ንጹሕ ልብ ላላቸው አበው በብርሃን ተከቦ ይታያል::

+ጻድቁ የወለዷቸው ብዙ ሥውራንም በሥፍራው ይገኛሉ:: ቦታው የአንበሶች መኖሪያ በመሆኑ ጠላት መናንያኑን ማጥቃት አይችልም:: ሳሙኤል ዘወገግም የሚጸልዩት በአናብስት ተከበው ነበር::

+በቦታው አንዳንዴም አንበሶች ሲሰግዱ ይታያል ይባላል:: ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ግን እንዲህ በቅድስና ተመላልሰው በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ሱማሌ ክልል ውስጥ በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: የጻድቁ ልደት ሐምሌ 10: ፍልሠታቸው ደግሞ ግንቦት 27 ነው::

+"+ አባ ጸቃውዐ ድንግል +"+

=>እኒህ ጻድቅም ኢትዮዽያዊ ናቸው:: የስማቸው ትርጉም "የድንግል ማርያም ወለላ ማር" ማለት ሲሆን ዜና ሕይወታቸው እንደ ስማቸው ጣፋጭ ነው::

+የእኒህ ጻድቅ አባታቸው የተመሰከረላቸው ሊቅና የገዳም መምሕር ናቸው:: ምክንያቱም ጸቃውዐ ድንግልን ከወለዱ በሁዋላ መንነዋልና:: አባት የደብረ ዘኸኝ መምሕር ሳሉ ልጃቸው ጸቃውዓ ድንግልን ወደ ገዳሙ ወስደው አሳደጉዋቸው::

+በዚያውም ጾምና ጸሎትን: ትዕግስትና ትሕርምትን አስተማሯቸው:: ቅዱሳት መጻሕፍትንም በወጉ አስጠኗቸው:: አባ ጸቃውዐ ድንከግልም በጐውን የምናኔ ጐዳና ከተማሩ በሁዋላ መዓርገ ምንኩስናን ተቀበሉ::

+40 ዓመት ሲሞላቸው ግን አባታቸው ዐረፉ:: መነኮሳት አበውም ተሰብስበው "ከአንተ የተሻለ የለም" ሲሉ ጸቃውዐ ድንግልን የደብረ ዘኸኝ መምሕር አድርገው ሾሟቸው:: ጻድቁም ቀን ቀን ሲያስተምሩ ይውሉና ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ ያድሩ ነበር::

+በሌሊትም ከባሕሩ ወጥተው የአካላቸው ርጥበት ደርቆ ላበታቸው እስኪንጠፈጠፍ ድረስ ይሰግዱ ነበር:: በዚህ መንገድም ራሳቸውን ገዝተው: መነኮሳትንም ገርተው ያዙ:: እግዚአብሔርም ክብራቸውን ይገልጽ ዘንድ ብዙ ተአምራትን በእጃቸው አሳይቷል::

+አንድ ቀን አባ ጸቃውዐ ድንግል መንገድ ሲሔዱ ሁለመናው በቁስል የተመታ አንድ መጻጉዕ ነዳይ ወድቆ አዩ:: ወደ እርሱ ሲደርሱ ምጽዋትን ለመናቸው:: ጻድቁ ግን "የምሰጥህ ነገር የለኝም:: ግን የፈጣሪየን ስጦታ እሰጥሃለሁ" ብለው: በውሃ ላይ ጸልየው ረጩት::

+ያ መጻጉዕም አካሉ ታድሶ: እንደ እንቦሳ ዘሎ ተነሳ:: ደስ እያለው: ፈጣሪውንም እያከበረ ወደ ቤቱ ሔዷል:: አባ ጸቃውዐ ድንግልም በዚህች ቀን ዐርፈው በገዳማቸው ተቀብረዋል::

+"+ ቅዱስ ድሜጥሮስ ሰማዕት +"+

=>ይህ ቅዱስ በዘመነ ሰማዕታት: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከነበሩ ክርስቲያኖች አንዱ ነው:: ቅዱስ ድሜጥሮስ ስቅጣር ከሚባል ደግ ባልንጀራው ጋር በበጐው ጐዳና ሲኖሩ የመከራው ዘመን ደረሰ:: መወሰን ነበረባቸውና ፈጣሪያቸውን ከሚክዱ ሞትን መረጡ::

+አስቀድሞም ሲያስተምር በመገኘቱ ቅዱስ ድሜጥሮስ በንጉሡ እጅ ወደቀ:: ንጉሡ መክስምያኖስም እሥራትን አዘዘበት:: በዚያ ወራት ደግሞ የንጉሡ ወታደር የሆነና በጣዖት የሚመካ አንድ ጉልበተኛ ነበር::

+ማንም በትግል አሸንፎት ስለማያውቅ ጣዖታዊው ንጉሥ ይመካበት ነበር:: አንድ ቀን ግን አንድ ክርስቲያን ወደ እሥር ቤት ገብቶ ቅዱስ ድሜጥሮስን "ባርከኝና ያንን ጣዖታዊ ጉልበተኛ እጥለዋለሁ" አለው::

+የቅዱሱን ጸሎትና በረከት ተቀብሎም በንጉሡ አደባባይ ታግሎ ጣለው:: ንጉሡና የጣዖቱ ካህናትም በእጅጉ አፈሩ:: በሁዋላ ግን ይህንን ያደረገው ቅዱስ ድሜጥሮስ መሆኑ በመታወቁ ከባልንጀራው ቅዱስ ስቅጣር ጋር በዚህች ቀን ገድለዋቸዋል::

=>አምላከ አበው ቅዱሳን ጸጋ ክብራቸውን ያብዛልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

=>ጥቅምት 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አቡነ ሳሙኤል ጻድቅ (ዘደብረ ወገግ)
2.አባ ጸቃውዐ ድንግል (ዘደብረ ዘኸኝ)
3.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ስቅጣር ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
2.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
3.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
4.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
5.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
6.ቅድስት አርሴማ ድንግል

=>+"+ በእሸቅድምድም ሥፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ: ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ:: የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል:: እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው:: እኛ ግን የማይጠፋውን:: +"+ (1ቆሮ. 9:24)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

@mezigebekidusan
@mezigebekidusan
@mezigebekidusan

መዝገበ ቅዱሳን

02 Nov, 17:14


††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ጥቅምት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት †††

+" ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ "+

††† በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::

+ታላቁ ቅዱስ አብላርዮስ ደግሞ ካለ ማመን ወደ ማመን: ከማመን ወደ መመንኮስ: ከመመንኮስ ወደ መጋደል: ከመጋደል ወደ ትሕርምት: ከዚያም ወደ ፍጹምነት የደረሰ: በምድረ ሶርያም ገዳማዊ ሕይወትን ያስፋፋ አባት ነው::

+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::

+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::

+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::

+ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::

+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::

+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::

+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል:: ከእነዚህም አንዱና ዋነኛው ዛሬ የምናከብረው ታላቁ ጻድቅ አባ አብላርዮስ ነው::

+ቅዱስ አብላርዮስ ሶርያዊ ሲሆን የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው:: በቀደመ ሕይወቱ ክርስትናን ፈጽሞ የማያውቅ ሰው ነበር:: ለዚህ ምክንያቱ የወላጆቹ ኢ-አማንያን መሆን ነው::

+ገና በልጅነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልስፍና: የዮናናውያንን ጥበብ ተምሮ ፈላስፋ ሁኗል:: በ16 ዓመቱም በምድረ ሶርያ አሉ ከሚባሉ የጥበብ ሰዎች አንዱ ሆነ:: ቅዱሱ ማንበብና መጠየቅን አብዝቶ ይወድ ነበር::

+የሚያነበው ነገር በሶርያ ቢያጣ በ17 ዓመቱ ተጨማሪ ጥበብን (እውቀትን) ፍለጋ ወደ ግብጽ (እስክንድርያ) ወረደ:: በዚያ ግን ከሰማቸው ትምሕርቶች አንዱ ልቡን ገዛው:: በወቅቱ በግብጽ ላይ ፓትርያርክ የነበረው ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ስለ ምድራዊው ያይደለ ስለ ሰማያዊው ጥበብ ሲያስተምር ሰምቶ ተገረመ::

+ቅዱስ አብላርዮስ በዚህ ሰዓት የሰበሰባቸውን የፍልስፍና መጻሕፍት ጥሎ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነብ ጀመረ:: ቅዱስ እለ እስክንድሮስም የሚከብድበትን እያፍታታ ተረጐመለት:: በአጭር ጊዜም ክርስቲያን ሆኖ ተጠመቀ::

+በዚያው ዓመትም ከከተማ ወጥቶ ወደ በርሃ ገባ:: ከአባ እንጦንስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሆኖ መነኮሰ:: በዚያም በጾምና በጸሎት: በመታዘዝና በትሕትና ለዓመታት ኖረ:: ቀጥሎም ወሬ ነጋሪ መጥቶ ወላጆቹ ማረፋቸውን ነገረው::

+በዚህ ጊዜ ቅዱስ አብላርዮስ ከአባ እንጦንስ ዘንድ ተባርኮ: ማኅበሩንም ተሰናብቶ ሶርያ ገባ:: የወላጆቹን ሃብትና ንብረት በሙሉ መጽውቶ ወደ ሶርያ በርሃ ወጣ:: በወቅቱ በአካባቢው ምንኩስና እየተነቃቃ ነበርና የቅዱሱ መምጣት ይበልጥ አጠናከረው::

+ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ኤዺፋንዮስን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርትንም አፈራ:: በአካባቢውም ታላቅ መካሪ: ናዛዥ: አጽናኝ: መሪ ሆነ:: ከብዙ ተአምራቱ ባለፈ ሃብተ ትንቢት የተሰጠው አባት ነውና እጅግ ክቡር ነበር::

*የገድሉን ነገርማ ማን ተናግሮ ይፈጽመዋል!

+እርሱ ከዕለተ ሰንበት በቀር እህልን አይቀምስም:: ለዚያውም እሑድ በነግህ (ጧት) ትንሽ ሳር ነጭቶ ከመብላት በቀር ሌላ የሚበላው አልነበረውም:: እንዲህ ባለ የበርሃ ሕይወት ለ63 ዓመታት ኖረ:: በዓለም የኖረበትን 17 ዓመት ብንደምረው 80 ይሆናል:: ቅዱሱ በተወለደ በ80 ዓመቱ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በዚህች ቀን ዐርፏል::

+አምላከ ቅዱስ አብላርዮስ ጥበቡን: ፈሊጡን: ሕይወቱን ይግለጽልን:: ከበረከቱም አይለየን::

+ጥቅምት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አብላርዮስ ገዳማዊ
2.ቅድስት ጸበለ ማርያም
3.ቅድስት አውስያ
4.አባ ዻውሎስ ሊቀ ዻዻሳት

በ 24 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

    1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
    2.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
   3.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
   4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
   5.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ)
   6."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
    7.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
    8.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን


++"+ ወንድሞች ሆይ! መጠራታችሁን ተመልከቱ:: እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች: ኃይለኞች የሆኑ ብዙዎች: ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም:: ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝነት መረጠ . . . ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ:: ነገር ግን:- የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ:: +"+ (1ቆሮ. 1:26)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

መዝገበ ቅዱሳን

01 Nov, 08:54


+በዚህ ጊዜም ይህንን ድንቅ ያዩ 477 ያህል አሕዛብ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተሰይፈዋል:: የስብከት ዘመኑም ከ36 ዓመታት በላይ ነው::✞✞✞ አምላከ ቅዱስ ሉቃስ ምሥጢሩን: ፍቅሩን: ጥበቡን ይግለጽልን:: ከሐዋርያው በረከትም ያሳትፈን::+ጥቅምት 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ሲላስ አረጋዊ (የቅዱስ ሉቃስ ረድእ)
3.ቅዱስ ታኦፊላ
4."477" ሰማዕታት (የቅዱስ ሉቃስ ማሕበር)

ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዑራኤል መላእክ
2.ቅዱስ ደቅሲዮስ(የእመቤታችን ወዳጅ)
3.አባ እንጦኒ (የመነኮሳት አባት)
4.አባ ጳውሊ
5.ቅዱስ ዮልዮስ ሰማዕት


++"+ የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ! ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን: በእኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ: እኔ ደግሞ ስለ ተማርከው ቃል እርግጡን እንድታውቅ: በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ:: +"+ (ሉቃ. 1:1)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

መዝገበ ቅዱሳን

01 Nov, 08:53


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ✞✞✞

✞✞✞ ጥቅምት 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

+" ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ "+

✞✞✞ ቅዱስ ሉቃስ:-
*ሐዋርያ ነው
*ወንጌላዊ ነው
*ሰማዕት ነው
*ዓቃቤ ሥራይ (ዶክተር) ነው
*የጥበብ ሰው (ሰዓሊ) ነው

*ዘጋቢ (የሐዋርያትን ዜና ሕይወት የጻፈ) ነው:: ይሕስ እንደምን ነው ቢሉ:-

+በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን መነሻ አካባቢ: በተወደደች የጌታ ዓመት ከእሥራኤላውያን ወገኖቹ ቅዱስ ሉቃስ ተወልዷል:: ያደገውም መቄዶንያ አካባቢ ነው:: ጌታችን ተጠምቆ ማስተማር ሲጀምር ከተከተሉት የ5 ገበያ ሕዝብ መካከል 120ውን ለቤተሰብነት መምረጡ ይታወቃል::

+ታዲያ እንዲጠቅም አውቆ ቅዱስ ሉቃስን ከ72ቱ አርድእት ደምሮታል:: ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከተከተለ በኋላ ለ3 ዓመት ከ3 ወር: ከዋለበት እየዋለ: ካደረበትም እያደረ የቃሉን ትምሕርት: የእጆቹን ተአምራት በጥሞና ይከታተል ነበር::

+ጌታችን ለዓለም ድኅነት ተሰቅሎ: ሙቶ: ከተነሳ በኋላ ስለዚህ ቅዱስ የሚናገር አንድ የወንጌል ክፍል እናገኛለን:: በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ላይ ከምናያቸው የኤማሁስ መንገደኞች አንዱ ይህ ቅዱስ እንደ ሆነ አባቶች አስተምረውናል::

+በእርግጥ 'ቀለዮዻ' የሚለው ስም በዘመኑ የብዙዎች መጠሪያ ቢሆንም እርሱም ጌታን ከመከተሉ በፊት በዚህ ስም ይጠራ እንደ ነበር ይታመናል:: በወቅቱ ታዲያ 2ቱ ደቀ መዛሙርት (ሉቃስና ኒቆዲሞስ) ወደ ኤማሁስ ሲሔዱ ጌታ መንገድ ላይ ተገልጦ እያጫወታቸው አብሮ ተጉዟል::

+እነርሱም ማንነቱን አላወቁምና ስለ ራሱ ለራሱ እየሰበኩለት ተጉዘዋል:: ከሐዘናቸው ብዛት ማስተዋል ተስኗቸው: ቀቢጸ ተስፋም ወሯቸው ነበርና መድኃኒታችን ክርስቶስ የነቢያትን ትንቢት ተረጐመላቸው::

+በዚህ ጊዜም ከነገሩ ማማር: ከምሥጢሩ መሥመር ጋር እየገረማቸው ልቦናቸው ይቃጠል (ይቀልጥባቸው) ነበር:: "አኮኑ ይነድደነ ልበነ" እንዲል:: ወደ ኤማሁስ ሲደርሱ ግን ደጐች ናቸውና "በቤት ካላደርክ: ራት ካልበላህ" ብለው ግድ አሉት::

+በማዕድ ሰዓት ግን ቡራኬውን ሰጥቷቸው: ቸር አምላክነቱን ገልጦላቸው ተሰወራቸው:: እነርሱም በሐሴት ከኤማሁት ተመልሰው እየሮጡ ኢየሩሳሌም ደርሰው ትንሳኤውን ሰበኩ::

+የመንገዱ ርዝመትም አልታወቃቸውም ነበር:: ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሉቃስ እንደ ሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ: መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::

+" ቅዱሱ ዶክተር "+

✞✞✞ በትውፊት ትምሕርት እንደ ተማርነው ቅዱስ ሉቃስ ጌታን ከመከተሉ በፊት ሥራው ሐኪምነት (ዶክተር) ነበር:: በዚህም አበው "አቃቤ ሥራይ / ባለ መድኃኒት" ይሉታል:: በተሰጠው ሙያም ብዙዎችን አገልግሏል::

+የጌታ ደቀ መዝሙር ከሆነ በኋላ ደግሞ "አቃቤ ሥራይ ዘነፍስ-የነፍስ ሐኪም" ተብሏል:: እንዲያውም አባቶቻችን ሐዋርያትን ያክማቸው ነበር ይባላል:: ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት አብዛኞቹ በሽተኞች ነበርና ነው:: ከደግነታቸው የተነሳም እልፍ አእላፍ ድውያንን በተአምራት ሲፈውሱ እነርሱ ግን በስቃይ ይኖሩ ነበር::

+ሕመማቸው ሲጠናባቸው ግን ቅዱሱ ዶክተር ሉቃስ ይራዳቸው ነበር:: ይሕንንም ቅዱስ ዻውሎስ በቆላስይስ መልእክቱ ላይ "የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ: ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላቹሃል" ሲል ገልጾታል:: (ቆላ. 4:14)

+" ዘጋቢው ሐዋርያ "+

+ቅዱስ ሉቃስ እንደ ዛሬው ነገሮች ምቹ ባልነበሩበት ዘመን እጅግ አድካሚ የሆነ ጉዞ አድርጐ የሐዋርያትን ዜና ሕይወት ዘግቦልናል:: ልክ ወንጌሉን ለታኦፊላ (ቴዎፍሎስ) ደቀ መዝሙሩ እንደ ጻፈለት ግብረ ሐዋርያትንም ለእርሱ በትረካ መልክ አቅርቦለታል::

+ሲጽፍለትም "ሰማሁ" እያለ ሳይሆን: አብሮ እያለ ያየውንና የተሳተፈበትን ነው:: አተራረኩም በአንደኛና በ3ኛ መደብ አድርጐ እያቀያየረ ነው:: ማለትም አንዳንዴ "እኛ" እያለ ሌላ ጊዜ ደግሞ "እነርሱ" እያለ ነበር የሚተርክለት::

+መጽሐፉም 28 ምዕራፎች ሲኖሩት በጌታ ዕርገት ጀምሮ በኢየሩሳሌምና በአሕዛብ የነበረውን ስብከተ ወንጌል ገልጦ: የቅዱስ ዻውሎስን ጉዞዎች በሰፊው ዳስሶ ይጠናቀቃል::

+" ወንጌላዊው ሐዋርያ "+

+ቅዱስ ሉቃስ ወንጌልን እንዲጽፉ ከተመረጡ (ከተፈቀደላቸው) ሐዋርያት አንዱ ነው:: በቤተ ክርስቲያንም "ዘላሕም" እየተባለ ይጠራል:: ለዚህም ምክንያቱ:-

1.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበረት: በላምና በአህያ መካከል መወለዱን በመጻፉ
2.ጌታችንን "መግዝአ ላሕም-የሚታረድ ሜልገች (ላም)" ብሎ በመግለጹ እና
3.ከ4ቱ እንስሳ (ኪሩቤል) አንዱ (ገጸ ላሕም) ይራዳው: ይጠብቀውም ስለ ነበር ነው::

+ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው ጌታ ባረገ በ22ኛው ዓመት ሲሆን ይኼውም በ56 ዓ/ም አካባቢ ማለት ነው:: ሲጽፍም ብቻውን አልነበረም:: ልክ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን የጻፈው ከሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር እንደ ሆነው ሁሉ: ቅዱስ ሉቃስም የጻፈው ከብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ጋር ነው:: ምክንያቱም ለረዥም ዓመታት አብረው ለስብከተ ወንጌል ተጉዘዋልና::

+ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍ በነ ዘካርያስ ቤተሰብ ጀምሮ: ብሥራተ ገብርኤልን: ክብረ ድንግል ማርያምን: የጌታን ልደት: እድገት: መጠመቅ: ማስተማር: መሰቀል: መሞት: መነሳትና ማረግ በቅደም ተከተል ይተርክልናል::

+" ጥበበኛው (ሰዓሊው) ሐዋርያ "+

+ቅዱስ ሉቃስን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች ሌላኛው ደግሞ ጐበዝ ሰዓሊ የነበረ መሆኑ ነው:: በሐዲስ ኪዳንም የመጀመሪያውን የእመቤታችንን ስዕል (ምስለ ፍቁር ወልዳን) የሳለው እሱ ነው::

+አንድ ቀን የአምላክ እናት ባለችበት ከጌታ አስፈቅዶ የሳላት ስዕለ አድኅኖ ሥጋን የለበሰች: ከፊቷ ወዝ የሚወጣ: የምታለቅስ: ስትወጋ የምትደማና ድውያንን የምትፈውስ ሆና ተገኝታለች:: ይህች ስዕል ዛሬ ሃገራችን ኢትዮዽያ ውስጥ አለች ይባላል::

+" ሰማዕቱ ሐዋርያ "+

+ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ባለ ሕይወት ሲመላለስ በትጋት (ያለ ዕረፍት) ወንጌልን እየሰበከ ነበር:: በ66 እና በ67 ዓ/ም ብርሃናተ ዓለም ዼጥሮስ ወዻውሎስ በኔሮን ቄሣር እጅ ሲገደሉ የሮም ግዛት ክርስቲያኖች ኃላፊነት በእርሱ ላይ ነበረ::

+ከወንጌሉና ግብረ ሐዋርያቱ ባለፈ በመልእክታት: አንድም እየዞረ ክርስቲያኖችን አጸና: አሕዛብንም አሳመነ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ዝናውን የሰማው ኔሮን ሊገድለው ፈለገ:: በዚህ ጊዜ ቅዱስ ሉቃስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሲላስ የሚባለውን ሽማግሌ መርጦ መጽሐፎቹን ሁሉ አስረከበው::

+በድፍረትም ወደ ኔሮን ቄሣር ቀርቦ ተናገረው:: ንጉሡም "ክርስቶስን አምልኩ የምትል ቀኝ እጅህ መቆረጥ አለባት" ብሎ እጁን ከትክሻው በሰይፍ ለይቶ መሬት ላይ ጣለው:: ሁሉ ሰው ሲደነግጥ ቅዱሱ ተጐንብሶ የወደቀች እጁን አነሳትና እንደ ነበረችው አደረጋት::

+በዚያ የነበሩ አሕዛብም "ግሩም" አሉ:: መልሶ ግን "አሁን እጄ ሥራዋን ስለ ጨረሰች አልፈልጋትም" ብሎ እንደ ገና ለይቶ ጣላት::
"ከመ ያርኢ ኃይለ ቅድመ ኔሮን ወተዓይኑ:
አስተላጸቃ ወሌለያ ለምትርት የማኑ:
እስመ ላዕሌሁ ተሰውጠ ለክርስቶስ ስልጣኑ::" እንዲል::

መዝገበ ቅዱሳን

30 Oct, 18:12


ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ስብከታቸውና ወደ ሕዝባቸው መመለስን በአሰቡ ጊዜ ስለ ቅድስናቸውና ስለ ትምህርታቸው ጣዕም ስለ ወደዳቸው የተከበረው ንጉሥ መመለስን ከለከላቸው በእርሱ ዘንድ እነርሱ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ሁነዋልና ፊታቸውም እንደ ፀሐይ ያበራል።

ከጥቂት ወራትም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ በላዩ ደዌ ላከበት በዚያውም ደዌ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_አላኒቆስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ አቡነ አላኒቆስ የትውልድ ቦታቸው ሸዋ አንኮበር ሲሆን አባታቸው ንጉሡ ዐፄ ይኩኖ አምላክ ነው፡፡ ንጉሡ አባታቸው ‹‹አግባና መንግሥቴን ይዘህ ተቀመጥ›› ቢላቸው እርሳቸው ግን ንግሥናን በመናቅ እምቢ ብለው ሄደው ከእመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቀው ቢለምኗት እምቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹ክፍልህ ምናኔ ነው፣ የአባትህ መንግሥት ያልፋል የልጄ መንግሥት ግን ዘላለማዊ ነው›› አለቻቸው፡፡ ጻድቁም ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ሄደው በዚያው መንኩሰው ገዳሙን እያገለገሉ ተቀመጡ፡፡ ከጸሎታቸው በኋላ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበርና አንድ ቀን እንዲሁ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ሲጥሉ መላእክት አውጥተዋቸዋል፡፡ አቡነ አላኒቆስ ወደ አክሱም እንዲሄዱ ታዘው ከሄዱ በኋላ በዚያም የጽላተ ሙሴ የታቦተ ጽዮን አጣኝ ሆነው 40 ዓመት ተቀምጠዋል፡፡ እመቤታችንም ተገልጣላቸው በዓታቸውን እንዲያጸኑ ከነገረቻቸው በኋላ ከአክሱም ወጣ ብሎ የሚገኘውን ማይበራዝዮ ገዳምን መሠረቱ፡፡ በዚያም እጅግ አስገራሚ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እያስተማሩ አገልግለዋል፡፡

አንድ ቀን መኰንኑ ወደ ሩቅ ቦታ ሲሄድ ቤተሰባቸውን ለንስሓ አባታቸው አደራ ሰጥተው ሄዱ፡፡ የንስሓ አባታቸውም የአቡነ አላኒቆስ ጓደኛ ነበሩ፡፡ መኰንኑም ከሄዱበት ሲመለሱ ሚስታቸው ከአሽከሯ አርግዛ ጠበቀቻቸው፡፡ ‹‹ከማን አረገዝሽ?›› ብለው ጽኑ ግርፋት ቢገርፏት ዋሽታ ‹‹ያረገዝኩት ከንስሓ አባቴ ነው›› አለች፡፡ መኰንኑም መነኩሴውን እገላለሁ ብሎ ሲነሣ መነኩሴውም ወደ አቡነ አላኒቆስ ሄደው አለቀሱ፡፡ አቡነ አላኒቆስም የመኰንኑን ሚስት ቢጠይቋት ባሏን ፈርታ ‹‹አዎ ከመነኩሴው አባት ነው ያረገዝኩት›› አለች፡፡ እሳቸውም ‹‹የተረገዘው ከዚህ መነኩሴ ከሆነ በሰላም ይወለድ፣ ካልሆነ ግን አይወለድ›› ብለው በቃላቸው አስረውና ገዝተው ሸኟቸው፡፡

በግዝታቸው መሠረት ሴቲቱ ድፍን 22 ዓመት ሙሉ ሳትወልድ በጭንቅና በጣር ኖረች፡፡ በአልጋ ላይ ሆና ተጨንቃ ስትኖር በመጨረሻ ለቤተሰቦቿ ተናግራ ወደ አቡነ አላኒቆስ ዘንድ በቃሬዛ ወሰዷትና ይቅርታ ጠይቃ እውነቱን ተናገረች፡፡ እሳቸውም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታሽ›› ቢሏት 22 ዓመት ሙሉ ተረግዞ የነበረው ልጅ ትልቅ ሰው ሆኖ ጥርስ አውጥቶ፣ ፂም አብቅሎ በሰላም ተወለደ፡፡ እርሱም ከተወለደ በኋላ አባቱ ማን እንደሆነ ተናገረ፡፡ ጻድቁ አባታችንም ልጁን አሳድገውት አስተምረው አመንኩሰውታል፡፡ ስሙንም ተወልደ መድኅን አሉት፡፡ በስሙ የተሠሰራ ቤተ ክርስቲያን በትግራይ ጽንብላ ወረዳ ይገኛል፡፡

ጻድቁ አቡነ አላኒቆስ ሌላም የሚታወቁበት አንድ ግብር አላቸው፡፡ የማይበራዝዮ ገዳማቸው አገልጋይ የሆነው መነኩሴ በሬ ጠምዶ ሲያርሱ አንበሳ ከጫካው ወጥቶ አንዱን በሬ በላው፡፡ መነኩሴውም መጥተው ለአቡነ አላኒቆስ ነገሯቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹ጸሎቴን እስክጨርስ ድረስ ወደ ጫካው ሂድና አንበሳውን ‹አላኒቆስ ባለህበት ጠብቀኝ እንዳትንቀሳቀስ ብሎሃል› ብለህ ተናገር›› ብለው ለመነኩሴው ነገሯቸው፡፡

መነኩሴውም እንደታዘዙት ወደ ጫካው ሄደው ጮኸው በሉ የተባሉትን ተናገሩ፡፡ አቡነ አላኒቆስም ጸሎታቸውን ሲጨርሱ ወደ ጫካው ሄደው አንበሳውን የበላውን በሬ አስተፍተውት በሬውን ነፍስ ዘርተውበት ከሞት አስነሥተው ዕለቱን እንዲታረስ አድርገውታል፡፡ አንበሳውንም ገዝተው ወደ ገዳማቸው ወስደው ሰባት ዓመት ውኃ እያስቀዱት እንዲያገለግላቸው አድርገውታል፡፡

አቡነ አላኒቆስ አንበሳውን አስረው ያሳድሩበት የነበረው ዛፍና ውኃ ያጠጡበት የነበረው ትልቅ የድንጋይ ገበታ ዛሬም ድረስ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ከ22 ዓመት እርግዝና በኋላ ሴቲቱ ጥርስና ፂም ያለው ልጅ እንድትወልድ ያደረጉበት ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይም ከነቅርጹ በገዳሙ በግልጽ ይታያል፡፡ ጻድቁ ጥቅምት 21 ቀን ዐርፈው በዚያው በማይባራዝዮ ገዳማቸው ተቀብረዋል፡፡ ጸበላቸው እጅግ ልዩ ነው፣ ያላመነውን ሰው አስፈንጥሮና ገፍትሮ ይጥለዋል እንጂ አያስቀርበውም፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶች ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት እና #ከገድላት_አንደበት)

መዝገበ ቅዱሳን

30 Oct, 18:12


#ጥቅምት_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ አንድ በዚህችም ቀን #እመቤታችን_ተአምራትን_አድርጋ_ሐዋርያው_ማትያስን ከእሥራት ቤት ያወጣችበት፣ #የነቢይ_ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ፣ የማርታና የማርያም ወንድም #የቅዱስ_አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት፣ የቅዱስ አባት #አባ_ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም እረፍት ነው፣ ታላቁ ጻድቅ #አቡነ_አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እመቤታችን_ለሐዋርያው_ማትያስ_ያደረገችለት_ተአምር

በዚህችም ቀን እመቤታችን ማርያም ተአምራትን አድርጋ ደቀ መዝሙር ማትያስን ከእሥራት ቤት አዳነችው።

የከበሩ ቅዱሳን ወንጌልን በዓለም ዞረው ይሰብኩ ዘንድ ዕጣ ሲጣጣሉ ለቅዱስ ማትያስ ዕጣ የደረሰው ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ነበር፡፡ ይህችም ሀገር እስኩቴስ የተባለች ሩሲያ እንደሆነች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ማትያስም እነዚህ ሰውን የሚበሉ ሰዎች አገራቸው እንደደረሰ ዐይኑን አውልቀው አሠሩት፡፡ ምግባቸውም የመጻተኛ ሰው ሥጋ ነው፡፡ በልማዳቸው መሠረት መጻተኛን ሰው ገና እንደያዙት ዐይኖቹን ዐውልቀው በእሥር ቤት ያኖሩታል፡፡ እስከ 30 ቀንም ድረስ ሳር እያበሉ ያስቀምጡትና በ30ኛው ቀን አውጥተው አርደው ይበሉታል፡፡

ሐዋርያው ማትያስንም በልማዳቸው መሠረት ዐይኖቹን አውልቀው አሠሩት፡፡ ሐዋርያውም በእሥር ቤት ሆኖ በዚያ ላይ ዐይኖቹን ታውሮ ሳለ በጭንቅ ወደ ጌታችንና ወደ እመቤታችን ይለምን ነበር፡፡ ነገር ግን እመብርሃንና ልጇ መድኃኔዓለም 30ኛው ቀን ሳይፈጸም ሐዋርያው እንድርያስን ወደ እርሱ ላኩለት፡፡ ማትያስም ዐይኑን ፈወሱለትና ማየት ቻለ፡፡

እንድርያስም በተዘጋው በር በተአምራት ገብቶ አሥርቤቱ ውስጥ ያሉ እሥረኞችን በስውር አውጥቶ ከከተማው ውጭ ካስቀመጣቸው በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት ተመልሰው ሰውን ለሚበሉት ሰዎች ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ይዘው በአንገታቸው ገመድ አግብተው ለ3 ቀን በሀገራቸው ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ጎተቱዋቸው፡፡ ሁለቱም ሐዋርያት በጸሎታቸው ከእሥር ቤቱ ምሰሶ ሥር ውኃ አፈለቁና ውኃው ሀገራቸውን ሁሉ እስኪያጥለቀልቅና ሰዎቹንም እስከ አንገታቸው ድረስ እስከሚደርስ ሞላ፡፡ ሁሉም በተጨነቁ ጊዜ ሁለቱ ሐዋርያት በፊታቸው ተገለጡና ‹‹በጌታችን እመኑ ትድናላችሁ›› በማለት ወንጌልን ሰብከውላቸው አሳመኗቸው፡፡ ምሥጢራትንም ሁሉ ገለጡላቸው፡፡ ደግሞም የአራዊት ጠባይን ከሰዎቹ ያርቅላቸው ዘንድ ወደ ጌታችንና ወደ ተወደደች እናቱ ከጸለዩ በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ያ የአውሬነት ጠባያቸውም ጠፍቶላቸው የዋህ፣ ቅንና ሩኅሩኆቸ ሆኑ፡፡ ሐዋርያትም ሃይማኖትን እያስተማሯቸው 30 ቀን አብረዋቸው ከተቀመጡ በኋላ አገልጋይ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ካህናትንና ዲያቆናትን ሾመውላቸው ወደ ሌላ ሀገር ሄዱ፡፡

ለሐዋርያት ሞገሳቸው ጣዕመ ስብከታቸው የኾነች ክብርት እመቤታችን ለእኛም ትለመነን!

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኢዩኤል_ነቢይ

ዳግመኛም በዚህችም ቀን የነቢይ ኢዩኤል የዕረፍቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህም የእስራኤልን ልጆች የሚያስተምርና የሚገሥጻቸው ነበር ስለ ክርስቶስም በኢየሩሳሌም መኖርና ማስተማር ትንቢት ተናገረ። ደግሞም ስለ መከራው በሐዋርያትና በሰባ ሁለቱ አርድእት በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ላይ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ እንዲህ ሲል ተናገረ።

ከዚህ በኋላ በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ ከመንፈሴ አሳድርበታለሁ ሴቶች ልጆቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ ትንቢትን ይናገራሉ አለቆቻችሁ ሕልምን ያልማሉ ጎልማሶቻችሁም ራእይን ያያሉ። ሁለተኛም እንዲህ አለ ያን ጊዜ ከተራራው ማር ከኮረብታውም ወተት ይፈሳል በቤተ እግዚአብሔር አጠገብ ካሉ ከይሁዳ አገሮች ሁሉ ምንጩ ከላይ ወደታች ይፈሳል።

ሙታን በሚነሡ ጊዜ ስለሚሆነው የፍርድ ሰዓት እንዲህ አለ ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ የከዋክብትም ብርሃናቸው ይጠፋል። የትንቢቱንም ወራት አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አልዓዛር የማርታና የማርያም ወንድም

በዚችም ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው የቅዱስ አልዓዛር ሥጋው ከቆጵሮስ አገር የፈለሰበት ሆነ።

ከክርስቲያን ነገሥታትም አንዱ ሥጋው በቆጵሮስ እንዳለ በሰማ ጊዜ ከቆጵሮስ ደሴት ወደ ቊስጥንጥንያ አፈለሰው። ሊአፈልሱትም በወደዱ ጊዜ በከበረ የደንጊያ ሣጥን ውስጥ ሁኖ በምድር ውስጥ ተቀብሮ አገኙት በላዩም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ ይህ በመቃብር ውስጥ አራት ቀን ከኖረ በኋላ ከሙታን ለይቶ ላስነሣው ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ የሆነ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋ ነው።

ይህንንም በአዩ ጊዜ ደስ ተሰኙበት ተሸክመውም ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ወሰዱት ካህናቱም ሁሉ ወጥተው በታላቅ ክብር በመዘመርና በማመስገን ተቀበሉት በአማረ ቦታም አኖሩት በዚችም ቀን በዓልን አደረጉለት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ዘኢየሩሳሌም

በዚህችም ቀን ለከበረች አገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት የሆነ ቅዱስ አባት አባ ዮሐንስ እግዚአብሔርን በሚወድ የንጉሥ ሰይፈ አርዕድ ደግሞ ቈስጠንጢኖስ ለሚባል ልጁ በሆነ በንጉሣችን በዳዊት ዘመን አረፈ።

ይህም ቅዱስ ከምስር አገር ታላላቆች እግዚአብሔርን የሚፈሩ የክርስቲያኖች አባቶች ልጅ ነው። የዲቁና መዓረግንም ለመሾም እስከ ተገባው ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት። ከዚህም በኋላ በዲቁናው ሹመት አገልግሎቱን በአሳመረ ጊዜ የቅስና መዓረግ የሚገባው ሁኖ ቅስና ተሾመ።

በጾም በጸሎት እግዚአብሔርንም በመፍራት የተጠመደ ሁኖ ድኆችንና ችግረኞችን የሚወዳቸው የሚረዳቸው ሆነ ያን ጊዜ የሐዋርያት የሆነች የጵጵስና ሹመት የምትገባው ሁና በከበረች አገር በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ ሕዝቡንም በፈሪሀ እግዚአብሔርና በትሕትና የሚያስተምራቸው ሆነ።

እነርሱም ስለ ቅድስናው እጅግ የሚወዱት ሆኑ መልኩና የአንደበቱ አገላለጥ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ያማረ ነበር። በሹመቱም ጥቂት ዘመናት ከኖረ በኋላ ከመንበረ ሢመቱ እስከ አራቀው ድረስ በላዩ ሰይጣን ምክንያትን አመጣ።

ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ማርቆስ ዘመን በግዛቱ ውስጥ ያሉ እስላሞች ስለ ዐመፁበት የኢትዮጵያ ንጉሥ ፈጅቷቸው ነበርና ስለዚህ በግዛቱ ውስጥ በሚኖሩ እስላሞች ላይ ክፉ እንዳያደርግ ለኢትዮጵያ ንጉሥ መልእክት እንዲልክ ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን የምስር ንጉሥ አዘዘው።

አባ ማርቆስም ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለሚላኩ ሰዎች ከመኳንንቱ ከኤጲስ ቆጶሳቱና ከሀገር ታላላቆች ሽማግሌዎች ጋር ተማክሮ እሊህን ብሩሀን ከዋክብት የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስን የምስር ኤጲስቆጶስ አባ ሳዊሮስን በእውቀታቸው በአስተዋይነታቸውና በቅድስናቸው መረጡአቸው ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥም ይሔዱ ዘንድ ግድ አሏቸው።

እነርሱም ታዛዦች ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ የኢትዮጵያ ንጉሥም መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው እሊህንም ቅዱሳን አባቶች ይቀበሏቸው ዘንድ አሽከሮቹን በቅሎዎችን አስይዞ ላከ በመጡም ጊዜ በታላቅ ደስታ ሰላምታ አቀረበላቸው ከእርሳቸውም ቡራኬን ተቀበለ ታላቅ ክብርንም አከበራቸው ። እነርሱም የሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ተቀብሎ አንብቦ ለሊቀ ጳጳሳቱ ቃል ታዛዥ መሆኑን ገለጠላቸው።

መዝገበ ቅዱሳን

28 Oct, 16:07


1.ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ (ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ዘጸይለም
3.አባ ስምኦን ገዳማዊ
4.ቅዱሳን በርተሎሜዎስና ሚስቱ (ሰማዕታት)
5.አበው ኤዺስ ቆዾሳት (ሳምሳጢን ያወገዙ)
6.ጻድቃን እለ መጥራ

በ 19 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

++"+ አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል::በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል:: የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው::የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም:: በበጐ በረከት ደርሰህለታልና::ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱላይ አኖርህ:: ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም::ለረጅም ዘመን ለዘለዓለሙ:: በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው:: +"+ (መዝ. 20:1-5)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

መዝገበ ቅዱሳን

28 Oct, 16:07


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ ጥቅምት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞

+" ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ንጉሥ "+

✞✞✞ የሰው ልጅ 'ንጉሥ' ተብሎ 'ቅዱስ' መባል ግን ምን ይደንቅ?! ይህ ታላቅ ኢትዮዽያዊ መሪ ንጉሥ ሲሆን: እንደ ደናግል ድንግል: እንደ ባሕታውያን ገዳማዊ: እንደ ቀስውስት ካህን: እንደ ሐዋርያት ሰባኪ ሆኖ መገኘቱ ይደንቃል::

+የሚያሳዝነው ይህንን እንቁ ንጉሣችን ብዙ ኢትዮዽያውያን መዘንጋታችን ብቻ ነው:: የላስታ አካባቢ እጅግ የታደለችና የተቀደሰች ናት:: እንደ ሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ሁሉ እሷም መካነ ቅዱሳን ናትና::

+ቅዱስ ይምርሐ የዘር ሐረጉ ከዛግዌ ነገሥታት ሥር ሲሆን አባቱ ግርማ ስዩም ይባላል:: ይኸውም በመጀመሪያው ሺህ ዓመት (Millenium) መጠናቀቂያ ላይ ነግሶ የነበረ ነው:: ዣን ስዩም
(የላሊበላ አባት): ጠጠውድም (ንጉሡ) እና ግርማ ስዩም ወንድማማቾች ናቸው::

+ቅዱሱ ሲወለድ አባቱ በሕይወት አልነበረም:: እናቱና የወቅቱ አባቶች "ይምርሐነ ክርስቶስ-ክርስቶስ ይምራን" አሉት:: ገና ከሕጻንነቱ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና ረቡዕና ዓርብ ቀን እስከ 9 ሰዓት ድረስ የእናቱን ጡት አይቀምስም ነበር:: እናቱ ግን ባለመረዳት ትጨነቅ ነበር::

+የወቅቱ ንጉሥ ጠጠውድም "ከእኔ ቀጥሎ የሚነግሠውን ባወኩት" እያለ ሲመኝ በሕልሙ "ሕጻኑ ይምርሐ ነው" የሚል በማየቱ ሕጻኑን አስመጣው:: ከደም ግባቱ የተነሳም ቅንዓት አድሮበት አማካሪዎቹን "ምን ላድርገው?" አላቸው::

+እነርሱም "ብትገድለው እግዚአብሔር በደሙ ይጠይቅሃል:: ግን እንዳይወርስብህ ከፈለክ እረኛ አድርገው" አሉት:: (የዋሃን! ቅዱስ ዳዊት ከእረኝነት መጠራቱን ዘንግተውታል) ከ7 ቀናት በኋላ ግን መጥተው "ንጉሥ ሆይ! ፈጣሪ ካለ የሚቀር ነገር የለምና በቃ ዝም ብለህ ግደለው" አሉት::

+በዚያች ሰዓት ቅዱስ ሩፋኤል ከሰማይ ወርዶ እናቱን "ይምርሐን ስጭኝ" አላት:: እናት ናትና ጨነቃት:: መልአኩ ግን እንደሚጠብቀው ቃል ገብቶላት ከላስታ ነጥቆ ኢየሩሳሌም አደረሰው::

+ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስም ለዓመታት ተምሮ ዲቁናን ተቀበለ:: በኢየሩሳሌም አካባቢም በጾምና በጸሎት ተወስኖ ፈጣሪውን እያገለገለና ወንጌልን እየሰበከ የወጣትነት እድሜውን ገፋ::

+አንድ ቀን ግን መድኃኒታችን ተገልጦ "ወዳጄ ይምርሐ! ሚስት አግብተሀ: ቅስና ተቀብለህ አገልግለኝ" አለው:: ቅዱሱ ይህንን ሲሰማ አዝኖ "ጌታየ! የእኔስ ፈቃዴ በድንግልና አገለግልህ ዘንድ ነው" አለው:: ጌታችንም "ግዴለህም! ሁሉም አይቀርብህም" ብሎ አንዲት ሕዝባ የምትባል ደግ እሥራኤላዊት ጠቆመው::

+ቅዱስ ይምርሐም ቅድስት ሕዝባን በተክሊል አግብቶ: ቅስናን ተቀበለ:: ግሩም የሚያሰኘው ግን 2ቱ ቅዱሳን ከ40 ዓመታት በላይ በትዳርም: በድንግልናም መኖራቸው ነው:: "ለሚያምን ሁሉ ይቻላል" ይል የለ ቅዱስ መጽሐፍ!

+ቅዱሳኑ ወዲያው ለአገልግሎት ወደ ግብጽ ወረዱ:: በዚያ ለጥቂት ዓመታት እንደቆዩ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ወደ ኢትይዽያ መመለስ ፈለገ:: አንድ ቀን ሕዝቡ ተሰብስበው ጸሎተ ኪዳንን ሲመራ "እግዚአብሔር አብ ወሐቤ ብርሃን-ብርሃንን የምትሰጥ እግዚአብሔር አብ" ከሚል ሲደርስ ወደ ሰማይጮኸ::

+ከሰማይም "አቤት ልጄ ሆይ!" የሚል መልስ መጣለት:: ይምርሐም "ምነው ጌታየ በሰው ሃገር ረሳኸኝ?" ቢለው "አልረሳውህም:: ይልቁኑ ሊገድልህ የሚፈልግህ ንጉሥ ሙቷልና ሒደህ ንገሥ" ሲል አዘዘው::

+ቅዱሱም ሚስቱን ሕዝባን ይዞ ላስታ ሲደርስ ሕዝቡ በዕልልታ ተቀብሎ ወዲያው አነገሠው:: በዚያም ለ15 ዓመታት ቅዱስ ሩፋኤል እየተራዳው: ሕብስትና ጽዋዕ ከሰማይ እየወረደለት ቀድሷል:: ሃገሪቱንም መርቷል::

+አንድ ቀን ግን ክፉ መካሪዎች "ተጨማሪ ሚስት አግባ" ቢሉት ተቆጣቸው:: በኋላ ደግሞ 'ለምን ተቆጣሁ' ብሎ አዘነ:: ስለዚህም ሃሳቡ ሰማያዊው ስጦታ ቀረበት::

+እያለቀሰ ጌታን ቢማጸን ጌታችን "ስላሰብከው ክፉ ሃሳብ (ለምን ተቆጣሁ ማለቱ ወደ ምክራቸው ማዘንበሉን ያሳይነበርና) ይቅር ብየሃለሁ:: ነገር ግን እኔ ወደ ማሳይህ ቦታ ካልሔድክ 2ኛ አይወርድልህም" አለው::

+ቅዱሱ ለጊዜው ትንሽ ቢከራከርም "እሺ" ብሎ በቅዱስ ሩፋኤል መሪነት ዛሬ ወደ ምናውቀው አካባቢው ሔደ:: በዚያም አራዊትን በጸሎቱ አድክሞ: መሠሪዎችን አስተምሮ: ሕዝቡንም አሳምኖ አጠመቃቸው::

+ጌታም "ከኢየሩሳሌም በደመና እየጫንክ በዚህ ባሕር ላይ ቤቴን ሥራልኝ" አለው:: ቅዱስ ይምርሐም መስከረም 13 ቀን (በበዓለ ባስልዮስ) ጀምሮ ሰኔ 20 (በበዓለ ሕንጸታ) ፈጸመና ታቦተ ገብርኤልን ሰኔ 21 ቀን ቀደሰው::

+ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ግን በዚያ ቦታ እየቀደሰ ለ25 ዓመታት ሃገሪቱን አስተዳደረ:: አንድ ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ለንጉሡ ከሰማይ ሕብስትና ጽዋዕ ሲያወርድለት 1 ባሕታዊ አይቶ "ለምን?" ብሎ ተቆጣ:: መልአኩ ግን የንጉሡን ክብር ነግሮ "እየዞርክ ስበክ" ብሎታል::

+በዚያ ባሕታዊ ስብከትም ከመላው ዓለም ብዙ ሺህ ሰወች መጥተው ቅዱስ ይምርሐን "ቀድሰህ አቁርበን?" ብለውለምነውታል:: ቅዱሱም ሲያቆርባቸው በመምሸቱ ጸሐይን አቁሟታል::

+ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ እንዲህ ባለ ጣዕመ ሕይወት ኑሮ: ለ40 ዓመታት ሃገራችንን አስተዳድሮ ጥቅምት 19 ቀን ዐርፎ በዚያው ሥፍራ ተቀብሯል:: ጌታችንም "መታሰቢያህን ያደረገውን: ደጅህን የረገጠውን እምርልሃለሁ" ብሎታል::

+" ቅዱስ ዮሐንስ ዘጸይለም "+

✞✞✞ በምድረ ግብጽ በዘመነ ጻድቃን የተነሳው ታላቁ አባ ዮሐንስ "ሐዋርያዊ ጻድቅ" ይባላል:: ወላጆቹ ደጋግ: የተወለደው በጾምና ጸሎት: ያደገውም በሥርዓት ነው:: በወጣትነቱ ከቤተሰቦቹ ጠፍቶ: በርሃ ገብቶ የአባ ስምዖን ደቀ መዝሙር ሆኗል::

+በዚያም በፍጹም ትሕርምት ሲኖር ባልንጀሮቹ ይጠፉበታል:: እነሱን ሊፈልግ ሲሔድ ግን አረማውያን ይዘው አሠሩት: አሰቃዩት:: መንገድ ላይ ውሃ ጠምቷቸው ሲጨነቁ "ውሃ ባጠጣችሁሳ?" አላቸው:: "እንለቅህ ነበር" አሉት::

+ጸልዮ: ውሃ አፍልቆ ቢያጠጣቸው "አንተማ ታስፈልጋለህና አንለቅህም" አሉት:: ወስደውም ጸይለም በምትባል ሃገር ለባርነት ሸጡት:: በዚያ ሲያሰቃዩት ተአምራትን አድርጐ በክርስቶስ አሳምኗቸዋል::

+ወደ ጐረቤት ሃገር ሔዶም ዛፍ ሲያመልኩ አገኛቸው:: "ወደ ክርስቶስ ተመለሱ" አላቸው:: "እንቢ" ሲሉት ምሳር (መጥረቢያ) ይዞ: ወደ ዱሩ ውስጥ ገብቶ ጸለየና ምሳሩን አነሳ::

+"በስመ ሥላሴ እገዝመክሙ" ብሎ ቢቃጣቸው አጋንንት የሠፈሩባቸው 10,000 ዛፎች ባንዴ ወደቁ:: በዚህ ምክንያትም 400,000 ሰዎች አምነው ተጠምቀዋል:: ወደ ሌላ ሃገር ሒዶም ስቃይን ታግሦ: ተአምራትን ሠርቶ ብዙዎችን አሳምኗል:: በቅድስና ኑሮም በዚህች ቀን ዐርፏል::

✞✞✞ አምላከ ይምርሐ ደጉን መሪ: አምላከ ዮሐንስ ቸሩን አስተማሪ ያምጣልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

+ጥቅምት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=

መዝገበ ቅዱሳን

25 Oct, 15:59


በግራኝ አሕመድ ወረራ ወቅት የግራኝ ሠራዊት አብያተ ክርስቲያናቱን እናጠፋለን ብለው ሲመጡ በተኣምራት ሰምጠው እንደጠፉ አባቶች ያስረዳሉ። አዛዦቹንም በዋሻ ውስጥ የሚገኙት ወፍ የሚያህሉ ተርቦች ነድፈው ጨርሰዋቸዋል። እነዚያ ተርቦች አሁንም ድረስ በገዳሙ ውስጥ ያልተፈቀደ ነገር ሲደረግ በመናደፍና በመከልከል ዋሻውን የሚጠብቁ ሲሆኑ አንዱ ተርብ ከነደፈ ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ። ከዚኸም በላይ ዋሻው በነብርም ይጠበቃል።

ገዳሙ ባለብዙ ቃልኪዳን ሲሆን ብዙ ስውራን አበው ዛሬም የሚኖሩበት ትንቢታቸው የማይነጥብ ብዙ ግሁሳን የከተሙበት ነው። ስውራኑ አበው ዛሬም እግዚአብሔር ለፈቀደለት ሰው ይገለጣሉ። ደገኞቹ የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት የገዳሙን ክብር በመረዳት ቦታው ድረስ በመሔድ በረከት ይቀበሉ ነበር። ዳግማዊ ምኒሊክ ለጀር ሥላሴ ገዳምና ለገዳማውያኑ አለኝታ ስለነበሩ በገዳሙ የታሪክ መዝገብ ስማቸው ዘወትር ይነሳል። ግርማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቦታውን ይንከባከቡት የነበረ ሲሆን ለገዳሙ መርጃ የሚሆን አዲስ አበባ ላይ የሚከራይ ቤት አሠርተው በኪራዩ ገቢ ገዳሙ እንዲጠቀም አድርገው ነበር። በአካልም ገዳሙ ድረስ በመሔድ በረከትን ይቀበሉ ነበር።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምትና #ከገድላት_አንደበት)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5

መዝገበ ቅዱሳን

25 Oct, 15:58


#ጥቅምት_16

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_ያቃቱ አረፈ፣ የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም እረድዕ የነበሩት #አቡነ_ኢያሱ_ዘጀር_ሥላሴ በዓለ ዕረፍታቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ያቃቱ

ጥቅምት ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ዘጠነኛ የሆነ ቅዱስ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ያቃቱ አረፈ።

ከርሱ በፊት የነበረ አባ ብንያሚን በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም ብዙ ችግር ደርሶበታል ስሙ ቴዎዶስዮስ የሚባል አንድ መለካዊ ሰው ነበረ እርሱም ወደ ደማስቆ ንጉሥ ወደ ዘይድ ሒዶ ብዙ እጅ መንሻ ሰጥቶ ለእስክንድርያ አገረ ገዥ ሁኖ ተሾመ።

ይህንንም አባት አባ ያቃቱን ሊአስጨንቀው ጀመረ በየዓመቱ ግብር ሰባት ሺህ የወርቅ ዲናር ከእርሱ እስከተቀበለ ድረስ እግዚአብሔርም እስከ አጠፋው ድረስ ይህን አባት እንዲህ አሠቃየው።

በዘመኑም የብዙዎች ቅዱሳን አባቶች አባት የሆነ የአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጸመ።

በአንዲት ሌሊትም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዚህ አባት ተገለጸለት ፍዩም በሚባል አገር በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ዮሐንስ የሚባል ጻድቅ ሰው መነኰስ እንዳለ ነገረው። ሕዝብን በማስተማርና በመምከርም ይረዳው ዘንድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲአስመጣውም አዘዘው ሁለተኛም ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን ገለጠለት።

በዚያንም ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሥራውንም ሁሉ አስረከበው ይህንንም አባት ከብዙ ድካም የሚያሳርፈው ሆነ በሹመቱ ወንበር ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ኑሮ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኢያሱ_ዘጀር_ሥላሴ

አቡነ ኢያሱ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ሸዋ የተነሡ ሲሆን ምንኵስናቸውን ከደብረ ሊባኖሱ ከዕጨጌ አቡነ መርሐ ክርስቶስ እንደተቀበሉ ታሪካቸው ያስረዳል። ትውልዳቸው አምሐራ ሳይንት ሲሆን መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳምን የመሠረቱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው።

እርሳቸው የመሠረቱት ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም በግራኝ ወረራ ሳይወድም ስለቀረ ጥንታዊነቱን እንደጠበቀ ስለሚገኝና ታላቅ የበረከት ቦታ የቅዱሳን መናኸሪያ ስለሆነ ብዙዎች ነገሥታት ገዳሙን እየሔዱ ተሳልመው በረከት አግኝተውበታል። የአቡነ ኢያሱን ገድላቸውን ከአቡነ ሀብተ ማርያም ገድል ጋር ጣልያናዊው ራይኔሪ በሀገሩ ሮም እንዳተመው ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ጽፈዋል። (0s valdo Raineri, Atti di Habta Māryam (†1497) e.di Iyasu (†1508), Santi Monaci Etiopici, Roma 1990 (Or ChrA 235), 165-265.)

የጻድቁ በዓለ ዕረፍታቸው ጥቅምት 16 በገዳሙ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን ስለ ጻድቁ ገድል በዝርዝር ተጽፎ አላገኘንም፣ ይልቁንም አቡነ ኢያሱ ስለገደሙት ታላቁ ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም ነው በብዛት የሚነገረው።

አቡነ ኢያሱ ጀር ስላሴ ከመምጣታቸውም በፊት አስቀድመው በአቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም፣ በደብረ ሊባኖስ እና በሌሎችም ገዳማት እየተዘዋወሩ በተጋድሎ ሲቀመጡ ‹‹ቦታኸ ይኸ አይደለም›› ተብለው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ነው ወደ ጀር ሥላሴ የመጡት። ወደ ቦታው ከመምጣታቸው በፊት አካባቢው ባእድ አምልኮ የተስፋፋበት ነበር፣ ነገር ግን ጻድቁ ሕዝቡን ክርስትናን አስተምረው ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰውታል። የምንኵስናን መሠረት ጥለውበታል። የአቡነ ኢያሱ የዕረፍታቸው ቦታ ደብረ ሊባኖስ ቢሆንም መታሰቢያቸው በመራቤቴ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ይታሰባል። በገዳሙ በክብረ በዓሉ ወቅት ታቦት አይወጣም፣ ከበሮ አይመታም። ምክያቱም ፍጹም የጸሎት የጽሞና ቦታ ስለሆነ ነው።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስደናቂ ሲሆን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በደንቢ ግራርጌ ቀበሌ ጀር በሚባል ስፍራ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው። ገዳሙ ከአዲስ አበባ 137 ኪ.ሜ ከደብረ ብርሃን 91 ኪ.ሜ ከለሚ ከተማ 4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ከጥንት ጀምሮ ስዉር ገዳም ሆኖ የቆየ ነው። ገዳሙ በ1495 ዓ.ም በዐፄ ናኦድ ዘመነ መንግሥት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ጻዲቁ አቡነ ኢያሱ ወደዚህ ቦታ መጥተው መሥርተውታል። በጅረት ታጂቦ ስለሚገኝ ነው ጀር ሥላሴ የተባለው። የክብር ባለቤት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ አስመልክቶ ከመሠረታቸው ገዳማት አንዱ ነው። አቡነ ኢያሱም በገዳሙ በሚገኘው አንድ ትልቅ ዋርካ ሥር ቆመው ይጸልዩ እንደነበር አባቶች ያስረዳሉ። አሁንም ድረስ ዋርካው በሥፍራው ላይ ሕያው ማስረጃ ሆኖ ይገኛል።

ገዳሙ ከአቡነ ኢያሱ ዕረፍት ከዘመናት በኋላ በግራኝ አህመድ ወረራ ጥቃት ደርሶበት መነኰሳቱም ተበታትነው ለ247 ዓመት ጠፍ ሆኖ ከቆየ በኋላ በ1747 ዓ.ም አቡነ ዮሴፍ የተባሉት ጻድቅ በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከአምባሰል ተነሥተው መጥተው ገደሉን ቦርቡረው ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስትና ቅዱሳንን ያሟላ ቤተ መቅደስ በማነጽ ዳግም ገዳሙን በማቅናት የቀደመውን የአባቶችን ታሪክ ማስቀጠል ችለዋል። በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ቅርሶቹና ነዋየ ቅዱሳቱ አደጋ እንዳይደርስባቸው አባቶች ሰብስበው በስውር ከቀበሩ ከረጅም ጊዜ በኋላ የቀበሩበት ቦታ ጠፍቶባቸው ነበር ነገር ግን የወንዙ ውኃ አቅጣጫውን ቀይሮ ሽቅብ ፈስሶ ቅርሶቹ ያሉበትን ቦታ አመላክቷል።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም የበርካታ መናንያን አበው በኣት ከመሆኑም ባሻገር የወንዶች ብቻ ገዳም ሲሆን መናንያኑ ከአራዊት ጋር ተስማምተው የሚኖሩበት ነው። ዙሪያው በገደል የተከበበ ሲሆን ወደ ገዳሙ ለመውረድ የዕንጨት መሰላልን ተጠቅሞ መጓዝ ግድ ይላል። ወደ ገዳሙ መግቢያ የሚያስወርደው መሰላል ደቡብ ወሎ ከሚገኘው ከታላቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም መግቢያ ጋር ይመሳሰላል። የመሰላሉ ርዝመት ከ15 ሜትር በላይ ይሆናል።

ገዳሙ ከእግዚአብሔር ጋር በሱባዔ ለመገናኘት ፍጹም ጸጥታ የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ ረድኤተ እግዚአብሔር ያለበት ቅዱስ ቦታ ነው። ዋሻው የሚከፈተው ዐቢይ ጾም ላይ እና በእመቤታችን የፍልሰታ ጾም ወቅት ነው። በዋሻው ውስጥ ሱባዔ የሚያዘው በደረቅ ሽምብራ ቆሎ እና በአንድ ኩባያ በሶ ብቻ ነው። አባቶች በኣት ዘግተው ጾመ ፍልሰታን፣ ጾመ ነቢያትን፣ ጾመ ሐዋሪያትን በይበልጥ በምነና ሕይወት የሚያሳልፉበት የበረከት ገዳም ነው።

በጀር ሥላሴ የሚገኘው ታሪካዊ ታላቅ ተራራ በልበሊት ኢየሱስን ግራኝ አሕመድ ሲያቃጥል ሁለት በወርቅ የታነጹ አብያተ ክርስቲያናት በፍቃደ እግዚአብሔር እንደሰወረ አባቶች ይናገራሉ። ይኸም ጥንታዊና ታሪካዊ ተራራ አሁንም በቦታው የሚገኝ ሲሆን በዋሻው ውስጥ የክብር ባለቤት ጌታችን በስደቱ ወራት ከእናቱ ድንግል ማርያም፣ ከዮሴፍና ከሰለሜ ጋር ለጥቂት ጊዜ የተቀመጠበት ሲሆን አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በምነና የተጋደሉበት ታላቅ ዋሻ ነው። ዋሻው እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ ሲሆን በውስጡ ከ40 በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንደተሰወሩበት አባቶች ይናገራሉ።

መዝገበ ቅዱሳን

25 Oct, 15:57


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለአባቶቻችን ቅዱሳን "12ቱ ሐዋርያት" እና ለቅዱስ "ቢላሞን ሰማዕት" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ ቅዱሳን 12ቱ ሐዋርያት +"+

=>በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከእመቤታችን በቀር ከቅዱሳን ሐዋርያት የሚበልጥ አልተነሳም:: "ሐዋርያ" ማለት "ፍንው: ልዑክ: የተላከ: የጽድቅ መንገደኛ" እንደ ማለት ነው:: በምሥጢሩ ግን "ባለሟል" ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል::

+ይህስ እንደምን ነው ቢሉ:-

¤የፍጥረታት ሁሉ ጌታ: የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ከድንግል ማርያም ተወልዶ: አድጐ: ተጠምቆ: ጾሞ: ከገዳመ ቆረንቶስ ሲመለስ ቀዳሚ ሥራው ያደረገው ደቀ መዛሙርቱን መጥራት ነበር::

+ከተከተሉት የ5 ገበያ ሕዝብ መካከል "ወሐረየ እምሰብአ ዚአሁ አሠርተ ወክልኤተ ሐዋርያተ" እንዲል በመጀመሪያ 12ቱን ሐዋርያት መረጠ::

+እሊህም:-
1.ዼጥሮስ የተባለ ስምኦን
2.እንድርያስ (ወንድሙ)
3.ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ
4.ዮሐንስ (ወንድሙ)
5.ፊልዾስ
6.በርተሎሜዎስ
7.ቶማስ
8.ማቴዎስ
9.ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ
10.ታዴዎስ (ልብድዮስ)
11.ናትናኤል (ቀናተኛው ስምዖን) እና
12.ማትያስ (በይሁዳ የተተካ) ናቸው:: (ማቴ. 10:1)

+እነዚህን 12 አርድእቱን ከጠራ በሁዋላ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከዋለበት ሲማሩ ይውሉ ነበር:: ሌሊት ደግሞ ምሥጢር ሲያስተረጉሙ ያድሩ ነበር::

+ጌታ እንደሚገባ ካስተማራቸው በሁዋላ ከፍ ያለ ኃላፊነትን ሾማቸው:: ለዓለም እረኞች: የእርሱም ባለሟሎች ሆኑ:: እጅግ ብዙ መከራ እንደሚገጥማቸው ነገራቸው:: (ማቴ. 10:16, ዮሐ. 16:33) በዚያው ልክ ክብራቸውንም አከለላቸው:: (ማቴ. 19:28)
+ሥልጣናቸው ደግሞ እስከዚህ ድረስ ሆነ:: "በምድር ያሠራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል: በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሆናል::" (ማቴ. 18:18) "ይቅር ያላችሁዋቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል: ያላላቹሃቸው ግን አይቀርላቸውም::" (ዮሐ. 20:23)

+የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ (ማቴ. 16:19): እረኝነትን (ዮሐ. 21:15) ተቀበሉ:: ጌታ በንጹሕ አንደበቱ ሐዋርያቱን እጅግ ሲያከብራቸው "ጨው: የዓለም ብርሃናት" (ማቴ. 5:13) አላቸው:: ወንድሞቹም ተባሉ:: (ዮሐ. 7:5) ከዚህም በሚበልጥ በሌላ ክብር አከበራቸው::

+ከዚህ ሁሉ ነገር በሁዋላ በጌታ ሕማማት ጌዜ ገና ነበሩና አንዳንዶቹ ፈርተው ተበተኑ:: ተመልሰው ግን በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩ ሰንብተው የጌታን ትንሳኤ ተመለከቱ:: እጆቹን: እግሮቹንም ዳስሰው ሐሴትን አደረጉ::

+ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓት: ሌላም በፍጡር አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢራትን ተምረው: ጌታ ሊቀ ዽዽስናን ሹሟቸው ዐረገ::

+ለ10 ቀናት በእመ ብርሃን ሥር ተጠልለው ሲጸልዩና በአንድ ልብ ሲተጉ ሰንብተው መንፈስ ቅዱስ ወረደላቸው:: በአንዴም ከፍርሃት ወደ ድፍረት ተመልሰው ፍጹማን: ብርሃናውያን ሆኑ:: 71 ልሳናትን ነስተው በአንዲት ስብከት ብቻ 3ሺ ነፍሳትን ማረኩ:: (ሐዋ. 2:41)

+ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት ያህል በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ እየተመላለሱ አስተምረው ብዙ እሥራኤላውያንን ወደ ክርስትና ማርከዋል:: ከዚህ በሁዋላ ግን እንደ ትውፊቱ በዚህች ቀን ዓለምን በእጣ ለ12 ተካፈሏት::

+ይህ ሲሆን መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ነበርና ለእያንዳንዳቸው እንደሚገባቸው አሕጉረ ስብከቶች ደረሷቸው:: እነርሱም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አስከትለው ለታላቁ መንፈሳዊ ዘመቻ ወረዱ::
+በሔዱበት ቦታም ከተኩላ: ከአንበሳና ከነምር ጋር ታገሉ:: በጸጋቸውም አራዊትን (ክፉ ሰዎችን) ወደ በግነት መልሰው ለክርስቶስ አስረከቡ:: በየሃገሩ እየሰበኩ ድውያንን ፈወሱ:: ለምጻሞችን አነጹ:: እውራንን አበሩ:: አንካሶችን አረቱ:: ጐባጦችን አቀኑ:: ሙታንንም አስነሱ:: እልፍ አእላፍ አሕዛብንም ወደ መንጋው ቀላቀሉ::

+ስለዚህ ፈንታም ብዙዎቹ በእሳት ተቃጠሉ:: ቆዳቸው ተገፈፈ:: በምጣድ ተጠበሱ:: ደማቸው በምድር ላይ ፈሰሰ:: ከአንድ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በቀር ሁሉም ይህችን ዓለም በሰማዕትነት ተሰናበቱ:: ጨው ሆነው አጣፍጠዋልና: ብርሃንም ሆነው አብርተዋልና እናከብራቸዋለን:: "አባቶቻችን: መምሕሮቻችን: ጌቶቻችንና ሊቆቻችን" እንላቸዋለን::

+"+ ቅዱስ ቢላሞን ሰማዕት +"+

=>በዘመነ ሰማዕታት የነበረው ቅዱስ ቢላሞን በወቅቱ ይታወቅ የነበረው በክርስቲያንነቱ ሳይሆን በፈላስፋነቱ ነበር:: እጅግ የተማረ ጥበበኛ: ግን ደግሞ ወገኑ ከኢ-አማንያን በመሆኑ ክርስቶስን አያውቀውም ነበር::

+እግዚአብሔር ግን እንዲጠፋ አልፈቀደምና አንድ ካህንን ላከለት:: ከመቀራረብ የተነሳ ብዙ ስለተነጋገሩ ቢላሞን ወደ ክርስትና እየተሳበ ሔደ:: በመጨረሻም ተምሮ በካህኑ እጅ ተጠምቁዋል:: ቀጥሎም ይጾም: ይጸልይ: ይጋደል ነበር::

+በትንሽ ጊዜም ከጸጋ ደርሶ ድውያንን ይፈውስ ገባ:: ብዙ አሕዛብን እያስተማረ: ከደዌአቸውም እየፈወሰ ወደ ክርስትና መለሳቸው:: አንድ ቀን ግን "ዐይነ ሥውር አብርተሃል" በሚል ተከሶ ሞት ተፈረደበት::

+ከመገደሉ በፍትም ጌታችን ከሰማይ ወርዶ "ወዳጄ!" ሲለው ወታደሮች ሰሙ:: በዚህ ምክንያት አምነው በዚህች ቀን 158 ወታደሮች አብረውት ተሰይፈዋል::
=>አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት ቸርነቱን: ምሕረቱን ያብዛልን:: በምልጃቸው ሃገራችንን ከክፉ ጠብቆ ከበረከታቸው ይክፈለን::

=>ጥቅምት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1."12ቱ" ቅዱሳን ሐዋርያት
2.ቅዱስ ቢላሞን ሰማዕት
3."158" ሰማዕታት (የቅዱስ ቢላሞን ማሕበር)
4.ቅዱስ ሲላስ ሐዋርያ
5.ቅድስት ጾመታ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብፃዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና

=>+"+ በዚያን ጊዜ ዼጥሮስ መልሶ:- 'እነሆ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ:: እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?' አለው:: ጌታ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው:- 'እውነት እላቹሃለሁ! እናንተስ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት: የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ:: +"+ (ማቴ. 19:27)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

25,531

subscribers

1,984

photos

9

videos