_ ♧ __
"A drunk mind speaks a sober heart."
— Jean-Jacques Rousseau
“የጉለሌው ሰካራም” የደራሲ ተመስገን ገብሬ አጭር ልብወለድ ሲሆን፣ ታትሞ የወጣው በህዳር 22 ቀን 1941 ዓ.ም.፣ (በነፃነት ማተሚያ ቤት)፣ አዲስ አበባ ነው፡፡
በእርግጥ ከዚያ በፊት በሀገራችን ሰዎች የተጻፉ ሌሎች ሥራዎች ቢኖሩም ብዙ የስነ ጽሑፍ ሐያሲያን ይህ የተመስገን ገብሬ “የጉለሌው ሰካራም” በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ አጭር ልብ ወለድ ድርሰት እንደሆነ ይናገሩለታል፡፡
መቼቱ አዲስ አበባ ከተማ፣ ጉለሌ ነው፡፡ መጠጥ ቤቷ ደሞ በሰባራ ባቡር፣ ከዮሐንስ ቤተክርስትያን አጠገብ የምትገኝ የበቀለች አምባዬ ግሮሰሪ ናት፡፡ ባለታሪኩ የጉለሌው ዝነኛ ሰካር ተበጀ ነው፡፡
ተበጀ - ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሰፈር ባለው ሰፊ ግዛቱ - በዶሮ ንግድ እጅጉን የታወቀ የዶሮ ነጋዴ ነው፡፡ እጅጉን የታወቀው በዶሮ ነጋዴነቱ ብቻ አይደለም፡፡ በስካር ዝናው ጭምር ነው፡፡
የተበጀ ስካር የየሰፈሩ የቡና ማጣጫ ሆኗል፡፡ እያንዳንዷ የማታውቀውም የምታውቀውም ሴት ቡና ሲኒ ይዛ ስትቀመጥ - ተበጀ ያደረገውንም ሌላ ሰው ያደረገውንም እየጨማመረች ተበጀ አደረገ ብላ አዳዲስ ግብር ትሰጠዋለች፡፡
እና ዝናው ጉለሌን አልፎ አዲስ አበባን አካሏል፡፡ እና ተበጀ ይሄን ሲያስብ በንዴት እንዲህ ይላል፡- "ጉለሌ ሥራው ወሬ ማቡካት ነው፣ የፈለገውን ያቡካ!"
በአጠቃላይ ግን - ሰካራም እየተባለ የሚያደርገው መልካም ተግባር ሁሉ ሳያውቀው እንዳደረገው እየተቆጠረ አመድ አፋሽ ሆኖ ቀረ እንጂ - ተበጀ መልካም ሰው ነው፡፡
አንዴ ወንዝ የገባችን ገረድ አድናለሁ ብሎ ራሱን ለጎርፍ አሳልፎ የሰጠ፣ ግን አሳማ ይዞ የወጣ - ለመልካም ግብ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ መልካም ሰው ነው፡፡
ራሱን ይጠይቃል፦ "የሰው ታላቅነቱ ምኑ ላይ ነው? መጠጥ ስላልጠጣ፣ ሚስት ስላገባ፣ ልጅ ስለወለደ፣ ሀብታም ወይም ደሃ ስለሆነ ነው? እኔ ከሙሉ ሰውነት ምን አጉድዬ፣ ምን አጥፍቼ ነው ይሄን ያህል ሁሉም ሰው እየተነሳ ‹‹ሰው ሁን!›› እያለ ሊመክረኝ የሚነሳው?" - እያለ ለራሱ፡፡
"እስቲ ሰው ልሁን" እያለ ለጋብቻ የጠየቃት ሴት ሁሉ ዝናውን ሰምታ በቁሙ ታሰናብተዋለች፡፡ የነፍስ አባቱ ሳይቀር - "ስካርህን ካላቆምክ አልባርክህም" ብለው - "ጉለሌ ያውጣህ!" ብለው ለቁም ገሃነም ጥለውት ሄደዋል!
ሁለተኛውን የነፍስ አባቱን ሁሌ እሁድ በመጣ ቁጥር አገኛቸዋለሁ ይላል - እርሱ ግን እሁድ ዕለት መገኛው - በከባድ ሀንጎቨር እየተጠቀጠቀ ከአልጋው ላይ!!
የተበጀ ህልምና የተበጀ እውን አልገናኝ ብለውት የተቸገረ - እና ብስጭቱን ለመርሳት፣ ወይ ለመስከር፣ ወይ ለመደሰት የሚጠጣ - እና የሚስቅ፣ የሚጮኽ - እና ደግሞ ተመልሶ የሚፀፀት - ባህርየ-ሰብዕ ነው - የጉለሌው ሰካራም!
ተበጀ መጠጥን ብዙ ጊዜ ለማቆም ከራሱ ጋር መሐላ ፈጽሟል፣ በበነጋው ግን ያው ነው፡፡ ውስኪ! ውስኪ ከነጠርሙሱ ነው የተበጀ ምሱ! በሰካርነቱ ያልደረሰበት ውርደት የለም! ሰክሮ ያልወደቀበት መንገድ የለም! በሰከረበት ዝናብ ወስዶት እሳት አደጋ ተጠርቶ አንስቶት ያውቃል፡፡
የጉለሌ ህዝብ ከወደቀበት ቦይ ተረባርቦ ያነሳዋል፡፡ እርሱ በማግስቱ ወደ ሥራው ይገባል፡፡ ለውለታው ተበጀ "የጉለሌ ልጅ ነኝ!" ይላል፡፡ "ደሃም ሆንን ሃብታም፣ ሰካራምም ሆንን ህርመኛ - ሁላችንም አባታችን ጉለሌ ነው!" እያለ ይፎክራል፡፡
ፀጉሩን መቀስ አስነክቶት አያውቅም፡፡ መጠጥና ትምባሆ፣ እና ሳቅና ጩኸት - አይለዩትም፡፡
"ደብረሊባኖስ ገዳም ብትገባ የሚጠብቅህ
ዝምታ ነው፣ ወፍ እንኳን ጩኸት የላትም፣
ባህታውያኑ ውሃ ይጣፍጣቸዋል - ሰካራም
ምን ልክፍት አምጥቶበት ነው የመረረ ጌሾና
ብቅል የሚጋተው እና የሚጮኸው?"
እያለ ያውጃል የጉለሌው ሰካራም - ተበጀ፡፡ ራሱን ይኮንናል፣ በራሱ ይሳለቃል፡፡ ውሃ እንዲጣፍጠውም ይመኛል፡፡ ግን ከአልኮል መጠጥ መላቀቅ አልሆንለት አለ፡፡
በመጨረሻ አንድ ባለ ዳስ ጎጆ ይሰራና - በቤቱ ኩራዝና ክብሪት ከአልኮል መጠጥ ጋር ይዞ ይገባል፡፡ ሲያስበው "መጠጥና እሳት ባንድ ቤት መግባት የለበትም" ይላል ለራሱ፡፡
ሰክሮ ቤቱን ቢያቃጥለውና አመዱ ቢወጣ - "እዚህ ጋር አንድ ጎጆ የነበረው ሰካራም ነበረ…" እያለ የጉለሌ ሰው እየተጠቋቆመ እስከ ዘለዓለሙ ሲስቅበት ሊኖር ነው፡፡ የጉለሌው ሰካራም - ለቤቱ ክብር ሲል - መጠጥ ለማቆም ወስኖ - ለአንድ ዓመት፣ ከ9 ወር፣ ከ9 ቀን፣ አቆመ፡፡
እና በዓመት ከ9 ወር፣ በ9ኛ ቀኑ ግን - ወደ መጠጥ ቤት ሲሄድ - የናፈቁት ወገኖቹ እንደ ሀገር መሪ ባለ እልልታና ሆታ ሲቀበሉት - መልሶ ሰክሮ ባቡር ሃዲድ ላይ ወደቀ። ባቡር እግሮቹን ደፈጠጣቸው።
ከእርሱ ጎን የተደፈጠጠ አህያንም አሞሮች ሲቀራመቱት - ሃኪም ጋር ሄዶ "እግሩ ይቆረጥ" ሲባል - ሃኪሞቹ "እስከ ጉልበቱ ከቆረጥነው የእንጨት እግር አስገብቶ ለመጠጣት ስለሚወጣ - እስከ ቂጡ አስጠግተን እንቁረጠው" ተባብለው ሲቆርጡት - እንደ ሰመመን ሆኖ ይሰማዋል።
እግሮቹን መዝኑና አስታቅፉት ተብሎ - 10 ኪሎ እግር ሲያስታቅፉት - ወዘተ - እነዚህ ሁሉ አስፈሪ ትዕይንቶች ይቀያየራሉ። እና በመጨረሻ - ህልም ይሁን እውን ተቸግሮ ይጠይቃል። የጉለሌው ሰካራም፦
“ስንት እግር ነው ያለኝ?”
“ስንት እግር ነው ያለኝ?”
የቤቱ ገረድ ይመልሱለታል፡-
“ልጆቼን ያሳደገችው ላም አራት እግር ነው ያላት…!”፡፡
ይሄ የደራሲ ተመስገን ገብሬ ኢትዮጵያዊ ቀደምት አጭር ልብወለድ በጨዋታ የተዋዛ አቀራረብ ያለው፣ የማይሰለች፣ የሰውን ውስጣዊ ስነልቦናና ማንነት ዘልቆ የሚያይ፣ ማኅበረሰባችንን ጠንቅቆ የተረዳ፣ እና በድንቅ ሚዛናዊ ሥፍራ ላይ ሆኖ የገጸባኅርያቱን እሳቤና ድርጊት የሚተርክ - እጅግ ሸግዬ ዘመናዊ የፈጠራ ጥበብ ውጤት ነው፡፡
እና ደግሞ እንደ አንድ ድንቅ የጥበብ ሥራ አዲስ ግዙፍ ነፍስን ከመንገድ ዳር መዝዞ፣ ሥጋ አላብሶ፣ ነፍስ ዘርቶ፣ እያጠጣና እያናገረ በህሊናችን አይረሴ የሆነ በቅርብ የምናውቀውን ሰው ይከስትልናል።
እንደ ሞናሊዛ፣ እንደ ዶን ኪኾቴ፣ እንደ ጉዱ ካሣ፣ እንደ አባ ዓለም-ለምኔ፣ እንደ ባለካፖርቱ አካኪ አካኪቪች። እንደ ታራስ ቡልባ። እንደ አደፍርስ። እንደ ሌሎችም ኃያል የብዕርና የቀለም ጋብቻ የወለዳቸው አይረሴ ፍጡራን። አንዴ "የጉለሌው ሰካራም"ን ያነበበም - ፈጽሞ አይረሳውም!
ምናልባትም - እንዲህ እንደ ተበጀ በግላጭ ዝነኛ አንሁንበት እንጂ - አሊያም እንዲህ ጨርሶ አይለይልን እንጂ - ሁላችንም ብንሆን - ሰው ነንና ጥቂት ጥቂት ተበጀነት አያጣንም። የጉለሌው ሠካራም በሁላችንም ውስጥ አለ።
በተለያዩ የሕይወት መስኮች ስንንከላወስ - ከምንሸሸው ነገር መውጣት አቅቶን - እየተፀፀትን ወደዚያው ወደምንኮንነው ነገር ደግመን ደጋግመን ለምንመላለስ ብዙ ሰዎች - ይሄ የጉለሌው ሰካራም ድርሰት በዘዋራ ሁነኛ መልዕክት የሚነግረን - እውነተኛ የውስጥ ደወል ነው!
በበኩሌ ተበጀ ውስጤ ነው! ይታየኛል በጉለሌ! በሰባራ ባቡር! በዮሐንስ! ባዲሳባ! በደጃች ይገዙ ሰፈር! በበቀለች አምባዬ ግሮሰሪ! ያውና እዚያ ማዶ - የጉለሌው ሰካራም! የሲሲፈሷ ህይወታችን መስታወት!
“የጉለሌው ሰካራም”። በደራሲ ተመስገን ገብሬ ከ67 ዓመታት በፊት (በኅዳር 1940 ዓ.ም.) የተፃፈ አጭር ልብወለድ።