~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ሕዳር 12/2017 [ወራቤ ኮሙኒኬሽን] በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ስራቸውን በአግባቡ በማይወጡ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ እንደተናገሩት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት በቴክኒክ እና በስነ ምግባር የታነጹ ሰልጣኞችን ማብቃት አለባቸው ብለዋል።
ለትራፊክ አደጋ መከሰት በአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት በቂ ስልጠና አለመስጠት በምክንያትነት ይጠቀሳል ብለዋል።
የአሽከርካሪዎችን ስነ ምግባር እንዲሻሻል ማድረግ ፣የቴክኒክ ብቃት ማሳደግ፣ የእግረኛ መንገድ አጠቃቀም ግንዛቤ ማጎልበት በአደጋው የሚደርሰዉን ሰብአዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ማስቀረት ያስችላል ሲሉም ጠቁመዋል።
በክልሉ ክትትል ከተደረገባቸው የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ 22 ማሰልጠኛዎች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን 6 ተቋማት ደግሞ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተሰጣቸው የማሻሻያ ሀሳብ መሰረት ካላስተካከሉ የሚሰረዙ መሆኑ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የቡታጅራ ፣ የቡኢ ፣ የወልቂጤ ፣ የወራቤ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ፣ከሀዲያ ዞን ኬ ኤን እና አውቶዳይናሚክ ተቋም ፣ ከምባታ ዞን ግሪንላንድ ተቋማት ለአንድ ወር አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱ ሲሆን ነገር ግን ፈጥነው ጉድለታቸውን ካረሙ መቀጠል የሚችሉ መሆኑ ተወስኗል።