በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ ሐዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደ ሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ።
ወዲያውኑ ሁሉም ሐዋርያት የሞቱትም ከመቃብራቸው ተነሥተው ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት አምላካችን ከአንቺ የተወለደ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እርሱ ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከርሱ ጋር ያሳርግሻልና አሏት።
በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በዐልጋዋ ላይ ተቀመጠች ሐዋርያትንም እንዲህ አለቻቸው ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን አወቅሁ ከዚህ ከሥጋዬም ወጥቼ ወደዘላለም ሕይወት እሔዳለሁ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ ከዚህም ዓለም እንደምለይ ከወዴት አወቃችሁ ።
ጴጥሮስና ሐዋርያት ሁሉም ወዳንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን በደመና ላይም በተጫን ጊዜ ወዳንቺ እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነን ደረስን አሏት።
እመቤታችን ማርያምም ይህን ነገር ከሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈጽሜ አመሰግናለሁ። የእኔን የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል።
ጸሎቷንና ምስጋናዋን ስትጨርስ ሐዋርያትን እንዲህ አለቻቸው ዕጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ጥሩት እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ። በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት መላእክት አጅበው እያመሰገኑት መጣና አረጋጋት ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት በዚያንም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተደረጉ ዕውሮች አይተዋልና፣ሐንካሶች ቀንተው ሔደዋልና ደንቆሮዎች ሰምተዋልና ለምጻሞች ነጹ አጋንንትም ከሰዎች ወጥተው ሔዱ ዲዳዎች ተናገሩ በሽታና ደዌ ያለበት ሁሉ ዳነ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወዳለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌያቸው ይፈወሳሉና።
ከዚህም በኋላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጅዋን እንዲህ አለችው በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስደነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሣ ከእሳት ባሕርም እፈራለሁ ጌታችንም ከእርሳቸው ለማንም በአንቺ ላይ ሥልጣን የለውም አላት።
ከሥጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሐዋርያትና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኑዋት እጅዋን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው በዚያንም ጊዜ ጌታችን ንጽሕት ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጐናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው ወደ ጌቴሴማኒ ተሸክመው እንዲወስዷት ሐዋርያትን አዘዛቸው።
ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃንን እያየች ነበር የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስም እንግዲህ ሥጋሽን ተድላ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ ዳግመኛም ሥጋሽን ከነፍስሽ ጋር አዋህጄ አስነሥቼ መላእክት በውስጡ በፊትሽ ሁነው በሚያመሰግኑበት ተመሳሳይ በሌለው ተድላ ደስታ በአለበት ማደሪያ አኖርሻለሁ አላት።
እመቤታችንም እንዲህ አለች አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሠራህ አመሰግንሃለሁ ሁለተኛም ልመናዬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ በስሜ ወዳንተ የሚለምነውን ሁሉ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወዳንተ የሚለምነውን ከመከራው ሁሉ አድነው በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሀሊ ነህና መታሰቢያዬን በውስጧ የሚያደርጉባትን ቦታ ሁሉ ባርክ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መሥዋዕታቸውን ተቀበል።
ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት የለመንሺኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ ደስ ይበልሽ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ጸጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም አይጠፋም።
እመቤታችንም ከአረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴሴማኒ ሊወስዷት ሐዋርያት ገንዘው ተሸከሟት። አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊአቃጥሉ ወጡ ከእርሳቸው አንዱ ከምድር ላይ ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን ዐልጋዋን ያዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በዐልጋዋ ላይ ተንጠለጠሉ።
ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ እለምንሻለሁ በሐዋርያትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ ።
በቀበሩዋትም ጊዜ ከዚያ ሦስት ቀን ኖሩ ዕረፍቷም የሆነው እሑድ ቀን በጥር ወር በሃያ አንድ በዚች ቀን ነበረ ጌታችንም ብርሃናውያን መላእክትን ላከ እነርሱም ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሩዋት።
ሐዋርያ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲአሳርጓት እመቤታችንን አገኛት መላእክትም ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ና እጅ ንሣ አሉት እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ ። እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበሩዋትም ነገሩት ቶማስም ሥጋዋን እስከማይ አላምንም አላቸው።
ሥጋዋንም ያሳዩት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቶማስ ነገራቸው። ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን ዕርገቷን ስለ አላዩ እጅግ አዘኑ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው። ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ስጣቸው እነርሱም እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት በተስፋ ኖሩ።
የእመቤታችንም የዕድሜዋ ዘመን ስልሳ አራት ዓመት ነው በአባትና እናቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሰባት ወር፣ በቤተ መቅደስም ዐሥራ ሁለት ዓመት፣ በዮሴፍም ቤት ሠላሳ አራት ዓመት ከሦስት ወር፣ ከጌታ ዕርገት በኋላ በወንጌላዊ ዮሐንስ ቤት ዐሥራ አራት ዓመት ነው።
የእመቤታችን የድንግል ማርያም በረከቷን ጣዕሟን ታሳድርብን ፤ እኛንም ቤተክርስቲያንንም ሀገራችንንም ከክፉ ትጠብቅልን🙏🏿
✨✨✨እንኳን አደረሳችሁ ✨✨✨
https://t.me/raiye_mariyam