በየቀኑ 1,440 ብር ባንክህ ውስጥ ቢጨመርልህና በዚያው ቀን ካልተጠቀምክበት ወደሚቀጥለው ቀን የማይዘዋወር ቢሆን ምን ታደርጋለህ? “ሕይወት” የተሰኘ “ባንክ” አለህ፡፡ በዚህ ባንክ ውስጥ በየቀኑ 1,440 ደቂቃዎች ይጨመርልሃል፡፡ እነዚህን ደቂቃዎች በዚያው ቀን ካልተጠቀምክባቸው ለነገ አይዘዋወሩልህም፡፡
በዚህ የሕይወት ባንክ ውስጥ የተንቀሳቃሽ ሂሳብ እንጂ የማጠራቀሚያ ሂሳብ መክፈት አይቻልም፡፡ በዚህ “የሕይወት ባንክ” ብለን በሰየምነው ባንክና በገንዘብ ማጠራቀሚያ ባንክ መካከል ዋና የሆነ ልዩነት አለ፡፡
በገንዘብ ማስቀመጫ ባንክ ውስጥ ገንዘብ ማጠራቀም፣ እንዲያውም እንዲወልድልህ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፣ በሕይወት ባንክ ውስጥ ግን የተንቀሳቃሽ ሂሳብ ብቻ ነው ያለው፡፡
ከዚያም በተጨማሪ በሕይወት ባንክ ውስጥ የተሰጠህን ጊዜ ዛሬውኑ ካልተጠቀምክበት ነገ በፍጹም አታገኘውም፡፡ ዛሬ ያልተጠቀምክበት ጊዜ ከአጠቃላይ የሕይወት ዘመንህ ላይ ይቀነስና ሕይወት ከሚያልቀው ዘመንህ ላይ ሌላ ጊዜን ይዛ ትጠብቅሃለች፡፡በጊዜ የማይገደብ ፍጥረት የለም::
ጊዜ ደግና ጨዋ ነው፣ ለሁሉም እኩል እድልን ይሰጣል፡፡ ጊዜ ጨካኝም ነው፣ ላልተጠቀሙበት ሰዎች ምህረትንና ሁለተኛ እድልን አይሰጥም፡፡ ይህንን የጊዜ ባህሪይ ሲያስብ የራሱን ሕይወት ማየት የማይጀምር ሰው ካለ ያስገርማል፡፡ ለዚህ ነው ጊዜያችንን በሚገባ የመጠቀምን ጥበብ ማዳበር ያለብን፡፡
ጊዜያቸውን በአግባቡና በጥበብ የሚጠቀሙ ሰዎች ከሌሎቹ በጊዜ ላይ ግድ የለሽ አመለካከት ካላቸው ሰዎች የሚለዩባቸው ብዙ ጉልህ የሕይወት ጥራቶች አሉ፡፡ ጊዜአቸውን በአግባቡ የማይጠቀሙ ሰዎች የጊዜ ባሪያዎች እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት ጊዜ ያመጣውን በመቀበል ወዲህና ወዲያ ሲንገላቱ፤ ይህንና ያንን ለመፈጸም ሲሯሯጡ ይታያሉ፡፡ በእለቱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ፕሮግራሙን የሚያወጣላቸው ጊዜ ያመጣው ገጠመኝ እንጂ የራሳቸው እቅድ አይደለም፡፡
በአንጻሩ ጊዜያቸውን በሚገባ መጠቀም የበሰሉ ሰዎች ጊዜን እንደ አገልጋይ ይጠቀሙበታል፡፡ ጊዜ አይደለም ለእነሱ ፕሮግራሙን የሚያወጣላቸው፣ በተቃራኒው ጊዜያቸውን በማቀናጀት ያዙታል፡፡
ጊዜን ውጤታማ በሆነ መልኩ መጠቀም ከሚሰጠን ጠቀሜታዎች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
1. የውጥረትና የጭንቀት መቀነስ፡- ጊዜህን በሚገባ የመጠቀምን ጥበብ ስታዳብር ከስራ ብዛትና መጨናነቅ የሚመጣን ውጥረት የመቀነስ እድልህን ትጨምረዋለህ፡፡
2. የአእምሮ ሰላምና የመከናወን ስሜት፡- በጥንቃቄ እቅድ አውጥተህ የምትተገብራቸው ክንዋኔዎችህ በመጨረሻው ላይ ትርፍ ጊዜን ስለሚሰጡህ አረፍ ለማለትና ከተግባርህ ገለል ብለህ ደስ የሚልህን ነገር የማድረግን አድል ይሰጥሃል፡፡
3. የጉልበት መጨመር፡- በቅጡ የተደራጀና በጊዜው የሚጠናቀቅ ተግባር የትኩረትን መጠን፣ ከዚያም ለስራም ሆነ ከስራ በኃላ ለሚኖረን የእረፍት ጊዜ ይህ ነው የማይባል ጉልበትን ይሰጠናል፡፡
4. የገንዘብ መደላደልና ነጻነት፡- ጊዜህ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውል በገንዘብ አያያዝህ ላይ እና በገቢህ ላይ ታላቅ ተጽእኖ አለው፡፡
5. ጥራት ያለውና ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር፡- በሚገባ ያልተደራጀ
የጊዜ አጠቃቀም ሲኖርህ ተግባሮችህን በጊዜው ስለማትጨርሳቸው ከቤተሰብ ጋር ሊኖርህ የሚገባውን ሰዓት የመንካት ባህሪይ ይኖረዋል፡፡
6. የተሻለ ጤንነት፡- ጊዜህን በሚገባ ስትጠቀም ስራህን በሚገባ ካጠናቀቅህ በኋላ በቂ ጊዜ ስለሚኖርህ ጤንነትህን እንዴት በሚገባ እንደምትጠብቅ የማሰብ ጊዜ ታገኛለህ፡፡
Dr. Eyob Mamo
መልካም ቀን🙏