ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ እንዲኽ አለ። “ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ #ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም።” (ዘጸ. 4፥10)
ትኁቱ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊትም እንዲኽ ብሏል። “እኔ ግን #ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ።” (መዝ. 22፥6)
ብዙ መከራን የተቀበለው ጻድቁ ኢዮብም “እነሆ፥ እኔ #ወራዳ ሰው ነኝ፤ የምመልስልህ ምንድር ነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ” አለ። (ኢዮ. 40፥4)
ልዑለ ቃል ነቢዩ ኢሳይያስም እንዲኽ ይላል። “ከንፈሮቼ #የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ!” (ኢሳ. 6፥5)
እስራኤልን ከአምልኮተ ጣዖት ወደአምልኮተ እግዚአብሔር ለመመለስ ለ23 ዓመታት የተጋው፥ መከራንም የተቀበለው ነቢዩ ኤርሚያስም “ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ #ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም” አለ። (ኤር. 1፥6)
ንጉሥ ዳዊት ‛ልጄ ኾይ ሰው ኹን’ ብሎ የመከረው ጠቢቡ ሰሎሞንም እንዲኽ አለ። “እኔ በእውነት ከሰው ሁሉ ይልቅ #ደንቆሮ ነኝ፥ የሰውም ማስተዋል የለብኝም።” (ምሳ. 30፥2)
ከአስራ ኹለቱ ደቂቀ ነቢያት እነዱ የኾነው አሞጽም ይናገራል። “እኔ ላም #ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፥ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፥ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ። አሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ አንተ በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፥ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል።” (አሞ. 7፥14-16)
እናንተስ ስለራሳችኹ ምን ትላላችኹ?
እግዚአብሔር ቢፈቅድ ቀጣይ ክፍል ይኖረዋል፤ ተከታተሉን!