የመኖሪያ ቤት ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ 1320/2016 መውጣቱን ተከትሎ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዋጁ ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር 7/2016 በማውጣት ሰኔ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ ምዝገባ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ በሁሉም ክፍለከተማ እና ወረዳዎች የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት ከሰኔ1- ሰኔ 26/2016 ዓ.ም ድረስ 248,469 የኪራይ ውል የተመዘገበ ሲሆን አሁንም ምዝገባው እንደቀጠለ የሚገኝ መሆኑንም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ያሳውቃል።
በመሆኑም በርካታ ተመዝጋቢ በመኖሩ ምክንያት ቀኑ እንዲራዘም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄው በስፋት በመነሳቱ እና ቀሪ ያልተመዘገበው የተከራይ አከራይ ውል እስከ ሰኔ 30/2016 መዝግቦ ለማጠናቀቅ አዳጋች እንደሆነ ተቋሙ የተገነዘበ ስለሆነ በጊዜ ገደቡ ሳይመዘገብ የሚቀር ውል እንዳይኖር ለማስቻል የምዝገባ ጊዜውን ማራዘም በማስፈለጉ የምዝገባ ጊዜው እስከ ሐምሌ 24/2016ዓም መራዘሙን ቢሮው ይገልፃል።
የግል መኖሪያ ቤት አከራይም ሆነ ተከራይ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ሳይዘናጉ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ ጊዜያቸውን ተጠቅመው እንዲመዘገቡ ቢሮው በድጋሚ ያሳስባል።
የውል ምዝገባው ከመደበኛ የስራ ሰአት ውጪ በምሽት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የሚካሄድ ስለሆነ ተመዝጋቢዎች ሳይጨናነቁ በተመቻቸው ሰአት መሄድ እና መመዝገብ ይችላሉም ተብሏል።