=========
አሏህ (ሱብሐነሁ ወተዓላ) ከዓመቱ ቀናቶች መሀከል ባሮቹን በተለየ ሁኔታ በስጦታ የሚያጣቅምበት'ና ምህረቱን ያለ-ገደብ የሚለግስበት ልዩ ቀናትና ሌሊቶች አሉት ። የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት እና ቀኑ ደሞ ከነዚህ ልዩ የአሏህ ቀናት ውስጥ እንደሚመደቡ ዑለሞቻችን የተለያዩ የሐዲሥ ዘገባዎችን በማጣቀስ ያስረዳሉ ። የእንደነዚህ አይነት ውድ ቀናቶች መኖር ባሮች በዒባዳ ላይ ያላቸውን ተነሳሽነት ከፍ ማድረግ ከመቻላቸውም ባሻገር ፤ ከአላህ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማደስ'ና በዓመቱ ውስጥ ከዒባዳ በመዘናጋትም ሆነ ወንጀል ውስጥ በመውደቅ ሊፈጠር የሚችልን ጉድለትና ኪሳራ ለማካካስ ይረዳሉ ።
****
የሻዕባን ወር'ና የአጋማሹ ሌሊት ደረጃዎችና ታሪካዊ ክስተቶች
=====
የሻዕባን ወር ስራዎች ወደ አላህ የሚቀርቡበት ወር ነው ፣ የሻዕባን ወር ነቢዩ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ከሌሎች ወራቶች በበለጠ ፆም የሚያበዙበት ወር ነው ፣ የሻዕባን ወር በአጋማሹ ሌሊት አላህ ለፍጡራኑ ሁሉ ምህረትን የሚለግስበት ነው ፣ የሻዕባን ወር የሰላት አቅጣጫ ቂብላ ከመስጂደል አቅሳ ወደ መስጂደል ሐራም እንዲቀየር የታዘዘበት ወር ነው ፣ የሻዕባን ወር ጨረቃ ለሁለት የተገመሰችበት ታላቁ የሰዪዳችን (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተዐምር የታየበት ወር ነው ፣ የሻዕባን ወር " إِنَّ اللَّهَ وَمَلائِكَتَهُ يُصَلّونَ عَلَى النَّبِيِّ يا أَيُّهَا الَّذينَ آمَنوا صَلّوا عَلَيهِ وَسَلِّموا تَسليمًا
የሚለው የቁርአን አንቀፅ የወረደበት ወር ነው ፣ እንዲሁም ሻዕባን "የሶለዋት ወር ፣ የቁርአን አንባቢዎች ወር" እየተባለ የሚጠራ ወር ሲሆን የአጋማሹ 15,ኛ ሌሊት እና ቀኑ ደሞ የተለያዩ ትሩፋቶችን የያዙ እንደሆኑ በዑለሞቻችን አንደበት ይነገርላቸዋል ።
****
=====
የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት እና የቀኑን ደረጃ የሚገልፁ በርካታ ሐዲሶች የሚገኙ ሲሆን ለአብነት ያህል ቀጣዩን ሀዲስ እንጥቀስ፦
ሰዪዱና ዐሊይ ኢብኑ አቢጧሊብ ( ረዲየሏሁ ዐንሁ ወከረመላሁ ወጅሀሁ ) ባስተላለፉት ሐዲሥ ነቢዩ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል ፦
👉 « የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት የሆነ ጊዜ ሌሊቷን ቁሙ ፣ ቀኑን ፁሙ ...
(ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል)
***
👉 አቡ ሙሳ አል-አሽዐሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፉት ሐዲሥ ነቢዩ (ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ቀጣዩን ተናግረዋል ፦
« አላህ በሻዕባን አጋማሽ ሌሊት ወደ ባሮቹ ይመለከታል በአላህ ከሚያጋራና ከወንድሙ ጋር በቂም ከተኳረፈ ሠው በስተቀር ለፍጡራኑ ሁሉ ምህረትን ይለግሳል ። »
(ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል)
****
የሻዕባን ሌሊት በዑለሞች አንደበት
======
> ኢማሙ አሽ-ሻፊዒይ እንዲህ ይላሉ ፦ « በአምስት ሌሊቶች ውስጥ ዱዐ ይበልጥ ተቀባይነት ያገኛል ፤ በጁሙዐ ሌሊት ፣ በዒድ አሌ-አድሐ ሌሊት ፣ በዒድ አል-ፈጥር ሌሊት ፣ በረጀብ ወር የመጀመሪያው ሌሊት እና በሻዕባን አጋማሽ ሌሊት »
( አል ኡም 1/265 )
> ኢማም ኢብኑ ሐጀር አል ሀይተሚይ እንዲህ ይላሉ ፦
« ይህች ሌሊት በልዩነት የአላህን ማርታና የዱዐ ተቀባይነትን የምታስገኝ የተላቀች ሌሊት ናት ። »
( አል ፈታዋ ፊቅሂያህ ኩብራ 377/3 )
> ኢብኑ ኑጀይም አል-ሐነፊያህ የሸዕባን አጋማሽ ሌሊትን በዒባዳ ህያው አድርጎ ማደር በሸሪዐ "መንዱብ" የሆነ ተግባር እንደሆነ "በሕሩ አር-ራኢቅ " በሚሰኝ ኪታብ ላይ አስፍረዋል ።
> ኢማም በሁቲይ አል-ሐንበሊይ እንዲህ ይላሉ ፦
« የሻዕባን አጋማሽ ሌሊት አያሌ ትሩፋቶች ያሏት ሌሊት ናት ፣ ከሰለፎች መሀከል ሌሊቷን በመስገድ የሚያሳልፉ ነበሩ ። »
( ሸርሑ ሙንተሀ አል-ኢራዳት 80/2 )