በ9 ሰዎች ላይ የጤና ጉዳት ደርሷል ብሏል ።
በመርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ የደረሰውን የእሳት አደጋ መንስኤ እየመረመርኩ ነው - የአዲስ አበባ ፖሊስ
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሸማ ተራ ነባር የገበያ ማዕከል እና በአካባቢው በደረሰ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል፡፡
የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
አደጋውን ለመከላከል እና በአደጋው ምክንያት ሌላ ወንጀል እንዳይፈፀም እንዲሁም የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ እና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሠላምና ፀጥታ መዋቅር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች ተቋማት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አደጋው እንዳይባባስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡
አደጋውን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ 33 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን እና ከአደጋው ጋር በተያያዘ በ7 ሰዎች ላይ ቀላል በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱንም አመላክቷል፡፡
አደጋውን ለመከለከል የፀጥታና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ላደረገው ድጋፍ እና ተባባሪነትም ፖሊስ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ በደረሰው የእሳት አደጋ የተሰማውን ሃዘን ገልፆ ወደ ፊት በምርመራ የደረሰበትን ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ገልጿል፡፡