ዳዊት ትንሣኤውን አስቀድሞ አይቶ እንዲህ ሲል ስለ እርሱ ትንቢት ተናገረ፦
“ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።” (ሐዋ.2፥27)
እዚህ ላይ ዳዊት ስለ ራሱ አይደለም የሚናገረው። ዳዊትማ እንደ አባቶቹ ሁሉ ሞቶ፥ ተቀብሮ መበስበስን አይቷል።
“ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው (ኢየሱስ) ግን መበስበስን አላየም።” (ሐዋ.13፥36-37)
ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የዳዊት ዘር ነው፥ ዳዊት በትንቢት መንፈስ በዘሩ የሚሆነውን ነገር ተረድቶ፥ በዘሩ የሚሆነውን በራሱ እንደሚሆን አድርጎ፥ ስለ እርሱ የተናገረው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፦
“ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን።” (ሐዋ.2፥29-32)
ቀድሞ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቶስ ተገልጦለት ካመነ በኋላ ወደ አይሁድ ምኵራብ እየገባ፥ “... ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤ ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ ‘ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው’ ይል ነበር።” (ሐዋ.17፥1-3)
“እውነትን አምናችሁ እንድትድኑ መርጧችኋል” ሲል (2ተሰ.2፥13)፥ ይህን እውነት በማመን ማለቱ ነው። አንዳንዶች ሞቱ ኃጢአታችንን ለማስተስርየት የግድ እንደሚያስፈልግ ስላልተረዱ ክርስቶስ የእውነት መሞቱን አያምኑም። ሌሎች ደግሞ ሙታን እንደሚነሡ ስለማያምኑ ክርስቶስም ከሞት መነሣቱን አያምኑም። ወንጌሉ ግን እንዲህ ይላል፦
“... በልብህ ‘ማን ወደ ሰማይ ይወጣል’ አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም በልብህ ‘ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል’ አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና።” (ሮሜ.10፥6-10)
ይቀጥላል ...