የአደባባይ ችሎት እና የተጠየቅ ሙግት
የጥንቱ ችሎት በተነሳ ቁጥር . . . የሚነገርለት አንድ ነገር አለ። ይኸውም ተውኔታዊ ባህርይ የነበረው የከሳሽና የተከሳሽ አለባበስ፥ አቋቋም፥ ዘንግ አያያዝ፥ የሰውነት እንቅስቃሴ፥ የነገር አቀራረብና ባጠቃላይም ሞቅና ደመቅ ያለው ጥምር የአሞጋገቱ ስልት ነው። ተሟግቶ ለመርታት፥ ረትቶም እርካታ፥ ዝናና ክብርን ለመቀዳጀት በቅድሚያ የተሟጋቹን ንቃት፥ ብልህነትና ብርታት ይጠይቃል። ከዚህም የተነሳ ከሰውነት እንቅስቃሴው ሌላ፥ በተለይ የመሟገቻው ቋንቋ በተዋቡ ቃላት፥ በምሳሌያዊ አነጋገር፥ በተረት፥ በአፈታሪክ፥ በእንቆቅልሽና በመሳሰሉት ዘዴዎች የበለፀገና ለዛማ መሆን ይገባው ነበር። የነዚህ ሁሉ ውሁድ የችሎት ነፃ ትርኢት ነው እንግዲህ፥ ወጪ ወራጁን፥ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ይማርክና ያማልል የነበረው።
ሁሉንም ተሟጋቾች አይመለከት ይሆናል። ይህም ቢሆን የክት ልብስን ለብዞ፥ ድግድጋትን አሳምሮ (አደግድጎ)፥ ጎራዴም ሆነ ሽጉጥ በወገብ ላይ ገንደር አድርጎ፥ ረዢም ዘንግ ይዞ ግርማ ሞገስ በተቀላቀለበት ሁኔታ እችሎት ላይ መቅረቡ፥ ቀርቦም ወቅቱ ሲደርስ እየተንቆራጠጡና ነገርን እያራቀቁ መሟገቱ፥ ከአንድ ጥሩ ተሟጋች የሚጠበቅ ልማድ ወይም ወግ ነበር።
አንድ ተጓዥ እንዲህ ሲል የዛፍ ስር ሙግት ተሟጋቾችን ገልጿል «በተመልካቾች መካከል ተቀምጦ የነበረው ዳኛም የከሳሽን ጉዳይ በጥሞና አዳምጦ ካበቃ በኋላ፥ ተከሳሽ መልስ እንዲሰጥ ይጋብዘዋል። ተከሳሽም ተስፈንጥሮ ወደላይ በመዝለልና ሁለት እጆቹን ወደ ሰማይ በመዘርጋት፥ ክሱ የማይመለከተውና ንፁህ መሆኑን ለመግለፅ ይጥራል። ከዚያም በአንድ ጉልበቱ በርከክ ቀጥሎም ብድግ በማለትና በእግር ጣቶቹ ብቻ በመቆም ወደ ባላጋራው ሌባ ጣቱን ቀሰር ያደርጋል። ወዲያውም ሁለት እጆቹን በደረቱ ላይ ለጥፎ በአሳዛኝ መልክ ወደ ዳኛው ጠጋ ይላል። ይህ ሰው እነዚህን ሁሉ ድርጊቶች ሲፈፅም ከንፈሮቹ የማያቋርጡ ቃላትን እያነበነቡ ነበር።
ለነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ግን ይኽ ከንቱ ነበር፡ «አንዳንድ የውጭ ሀገር ስደተኞችም በልተን እንደር ሲሉ ያገራችን ሹማምንት ዛሬ የያዙትን የስህተት መንገድ እንዳይለቁ ያጠናክሩታል። አይዟችሁ እያሉም ከየመፃህፍቱ የለቀሙትን፥ —-አንዳንድ የተሰብሩ ቃላት ያስጠኗቸዋል። ያገራችንም ሹማምንት ሩቅ እንዳያዩ. . . አይናቸውን ሸፍነው ይከለክሏቸዋል። እውቀት አለንም ብለው ራሳቸው ይዞራል። ውሏቸውም ስራን ትተው በክርክርና በሙግት ብቻ ነው» ይላል።
«እመንደር ከዋለ ንብ አደባባይ የዋለ ዝንብ» እየተባለ ይተረታል - አደባባይ የፍርድ ችሎትን ይወክላል። ችሎት ለማየት በሚውል እና በማይውል ሰው ላይ ያለውን ማኅበራዊ ግምት ከተረዳን የገ/ሕይወት ባይከዳኝ ትችት የምር ሊያሳስበን ይችላል። ስራ ተፈቶ ክርክር ሲታይ ይዋል ነበር ማለት ነው? ፡)
ደግሞ ችሎት የአሞጋገትና የአነጋገር ስልትን የመቅሰሚያ፥ ህግና ዳኝነትን የመማሪያ፥ ከሹማምንትና ከመሳሰሉት ከፍተኛ ሰዎች ጋር የመተዋወቂያና ለዳኝነትም ሆነ ለሌላ ስልጣን የመመረጫ ቦታም ጭምር በመሆኑ አዳማቂዎቹ ወይም ደንበኞቹ ሙግት ያላቸውም፥ የሌላቸውም ነበሩ።
ባንድ ወቅት ከሳሽና ተከሳሽ እዳኛ ፊት ግራና ቀኝ ተቋቁመው ሲሟገቱ፤ አንደኛው የሌላውን ደካማ ጎን (እንከን) አውቆ ኖሯል። እንከኑም አደባባይን አላማዘውተሩና ከድህነቱም የተነሳ ሚስቱን ነጠላ እንጂ ኩታ አልብሷት እንደማያውቅ መሆኑ ነበር። ይህንን የተረዳው ጮሌ ተሟጋችም በዘመኑ የነበረውን የችሎት ላይ ያነጋግር ነፃነትና የአሞጋገት ስልትን በመጠቀም እንዲህ ብሎ ይሰድበዋል።
በላ ልበልሃ!
ያጤ ስርአቱን የመሰረቱ፡
አልናገርም ሀሰቱን፡
ሁሌ እውነት እውነቱን!
ላምህ ብትወልድ ዛጎላ፡
ሚስትህ ብትለብስ ነጠላ፡
አንተ ብትውል እጥላ!
ተሰዳቢው ተሟጋችም ምንም እንኳን አደባባይን የማያዘወትርና የኑሮ ደረጃውም ዝቅ ያለ ቢሆንም ቅሉ፥ ነገር አዋቂና አራቃቂ ነበርና፤ እሱም በበኩሉ በ’በላ ልበልሃ’ የአሞጋገት ስልት እንዲህ ብሎ መለሰለት ይባላል።
በላ ልበልሃ!
ያጤ ስርአቱን የመሰረቱን፡
አልናገርም ሀሰቱን፡
ሁሌ እውነት እውነቱን!
ላሜ ብትወልድ ዛጎላ
አውራውን አስመስል ብላ።
ሚስቴ ብትለብስ ነጠላ
ቀን እስቲያልፍ ብላ።
እኔ ብውል እጥላ፥
ያንተን ብጤ ነገረኛ ብጠላ!
😂 ዛሬ ይሄ ባህል ቢኖር እኔም ስራ ፈትቼ አደባባይ ፍርድ ሳይ ነበር የምውለው እምዬን።
***
‘የሞራል ውድቀት ዝንባሌ በትምህርት እድገት በኢትዮጵያ ላይ’ በሚለው መጽሐፋቸው ሀይሌ ወ/ሚካኤል እንዲህ ይላሉ፡ «በመካሰስና ነገር ካለበት ስፍራ በመዋል የኢትዮጵያ ህዝብ የታወቀ ሆኗል። ትልቅ ገበሬ ከመሆን አነስተኛ ጠበቃ መሆን ክብር ነው። ከአደባባይና ከትችት ቦታ መዋል የጨዋ ልጅ ምልክት ነው። የሰው ልጅነትህን በአንደበትህ ርቱዕነት ማረጋገጥ አለብህና»
ተሟጋችነት ከመከበሩ የተነሳ አንድ ተሟጋች ብቃት የሌለውን እንዲህ ብሎ ሰድቦታል፡ እዛው ችሎት አደባባይ
በላ ልበልሃ!
ያጤ ስርአቱን የመሰረቱ፡
አልናገርም ሀሰቱን፡
ሁሌ እውነት እውነቱን!
በሳማ ሲበላ ጣቱን የሚልሰው፥
አደባባይ ቆሞ አንድ እማይመልሰው፥
ሚስቱ ስትቆጣው እጓሮ እሚያለቅሰው፥
አንተም ከኔ ጋራ እኩል ሰው እኩል ሰው። 😄
ከሺበሺ ለማ ፡ ተጠየቅ
ገጽ 15 - 46