ኢትዮ ነጋሪ፣ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም
1. በትግራይ ክልል ሽረ እንዳስላሴ ከተማ በደረሰ የቦንብ ጥቃት 16 ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው። በትግራይ ክልል ሽረ እንዳስላሴ ከተማ በደረሰ የቦንብ ጥቃት 16 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተናግረዋል። ጥቃቱ የደረሰው ትላንት ምሽት 3፡00 አከባቢ በከተማዋ በሚገኝ አንድ የመዝናኛ ክበብ ውስጥ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፤ 16 የሚገመቱ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በከተማው በሚገኝ ሆስፒታል በህክምና ላይ ይገኛሉ፡፡ በአደጋው ህይወቱ ያለፈ ሠው የለም። ጥቃቱን አድርሰዋል ተብለው ከተጠረጠሩት መካከል አንድ ግለሰበብ መያዙን እና ሌሎችንም ለመያዝ ፖሊስ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡
2. በጉዳያ ቢላ ወረዳ ውስጥ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሟቾች ቁጥር 43 ደርሷል። ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ መኪና በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉደያ ቢላ ወረዳ ውስጥ ጫሊ ጂማ በሚባል ቀበሌ ሲደርስ በመገልበጡ ነው አደጋው የደረሰው። መኪናው ወደ 87 የሚደርሱ ሰዎች ጭኖ ነበር፡፡ ተሸከርካሪው ከፍጥነት በላይም ሲያሽከርክር እንደነበር የተነገረ ሲሆን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ገደማ በዚሁ አደጋ ከሞቱት በተጨማሪም በ42 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን እና በ3 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት ደርሷል።
3. ኢትዮጵያ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ፖሊሲ በቀየሩ ቁጥር ችግር ውስጥ እንዳትገባ የራሷን ፖሊሲ ልታሻሽል ይገባል ሲል የኢትዮጵያ የሲቪል እና የሞያ ማህበራት ኮንግረስ መከረ፡፡ ሀገሪቱ ብዙ ሀብት እያላት በምግብ ዋስትና የምትቸገረውና የውጭ እርዳታ ጠባቂ የሆነችውም በፖሊሲ ችግር እንደሆነም ማህበሩ ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች፣ በድርቅና ስር በሰደደ ድህነት እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች እያሉ ከሰሞኑ የአሜሪካ እርዳታ መቆም ችግሩን ሊያወሳስበው ይችል የሚል ስጋት እንዳላቸው የሚናገሩም ብዙዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን የምግብ ዋስትና ችግሯን ለመፍታት በሁሉም ዘርፍ ያሉ ምሁራንን ያሳተፈ ፖሊሲ አውጥታ ተገግባራዊ ማድረግ እንዳለባትም ማህበሩ ያስረዳል፡፡ በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ልትበረታ ይገባልም ብሏል፡፡
4. የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በአንድ ሰከንድ አንድ ኪሎሜትር መጓዝ የሚያስችላቸው ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ተመረቀ። ኢትዮቴሌኮም ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር ያዘጋጀው ከመገናኛ ቦሌ መንገድ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያን ክፍት አድርጓል። ተጠቃሚዎች 24/7 አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን አገልግሎቱን ካገኙ በኋላ ክፍያውን በቴሌ ብር አማካኝነት የሚከፍሉ ይሆናል፣ የአንድ ኪሎ ዋት ክፍያ አስር ብር ነው ተብሏል። ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ጣቢያዎች በግንባታ ላይ ሲሆኑ በቅርቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ ተነግሯል።
5. የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፍልስጤማውያኑ የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት /ሐማስ/ የያዛቸውን የእስራኤል ታጋቾች በሙሉ እንዲለቅ አስጠነቀቁ፡፡ እስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን የጊዜ ገደብ እንደሰጡት ቢቢሲ ፅፏል፡፡ ትራምፕ ሐማስ ታጋቾቹን በሙሉ በተባለው ጊዜ ካልለቀቀ ጋዛን ገሐነብ አደርጋታለሁ ሲሉ መዛታቸው ተሰምቷል፡፡ ቀደም ሲል በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጡ ደረጃ በደረጃ በየምዕራፉ እንዲከናወን ይጠይቃል፡፡ ሐማስ ለመጨው ቅዳሜ ታቅዶ የነበረውን የታጋቾች መለቀቂያ በደፈናው ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሜዋለሁ ብሏል፡፡ አዝማሚያው የጋዛውን የተኩስ አቁም ፉርሽ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡
ለበለጠ እና ትኩስ መረጃዎች ከስር ያሉትን ሊንኮች በመጫን ቤተሰብ ይሁኑ።
�Telegram https://t.me/EthioNegarii
�Twitter https://twitter.com/EthioNegari
� YouTube https://youtube.com/channel/UCxywavkb3e3K7BY3BEh2piQ
Facebook https://www.facebook.com/EthioNegarii/
Website https://ethionegari.com/
LinkedIn https://www.linkedin.com/company/ethio-negari