"ፈወስናሃ ለባቢሎን ወኢተፈወሰት"
ባቢሎን ፈወስናት እርስዋ
ግን አልተፈወሰችም።
ትንቢት ኤርምያስ 51፤9
ጥር 7ቀን ሕንጻ ባቢሎን
የፈረሰበት ሐልወተ እግዚአብሔር
የተገለጠበት በዓል ነው።
ሐብተ ውልድና ስመ ክርስትና ይዘን
ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ የምናሳዝን
በከበረ የደሙ ፈሳሽነት ወልደ እግዚአብሔር እንዳዳነን የዘነጋን በፈቃዳችን በእግረ አጋንንት የተረገጥን በጥላቻ የሰከርን
የሰናዖርን ሕንጻ መፈረስ እየተረክን እየሰበክን ነገር ግን ከባቢሎን ሰዎች ያልተማርን የዘረኝነትን ካብ ያልናድን አብረን ያለን የሚመስለን ግን ያልተግባባን ያልተናበብን ቋንቋችን እንደ ባቢሎናውያን የተደባለቀብን ፍቅር ከመሐላችን የጠፋችብን ልባችን ሐሳባችንም የተበታተነብን የዘረኝነት ጣኦት በየልቦናችን አቁመን ከሰውነት የወረድን ማስተዋል የተጋረደብን
ሕንጻ ሥላሴ መሆናችንን የዘነጋን በኪሎዋችን ልክ አፈር የተሸከምን በፈቃዳችን ያበድን በዘር ቁና ሰው የምንሰፍር በብሔር ከረጢት የተቋጠርን በዘረኝነት ቁስል የተመታን ብዙዎች ነንና መሐሪው ሥሉስ ቅዱስ እግዚአ ዓለማት ቅድስት ሥላሴ ይማረን ምሕረት ፈውስን ይላክልን ከዚ በላይ ከባድ በሽታ የለምና ከተራፊ ከራሚዎቹ ሕብረት ይደምረን ፍቅርን ይናኝብን አንድነታችንን ያጽናው የክርስቲያን ደም በከንቱ ፈሶ አያስቀርብን ከነፍስና ከስጋ መከራ ይሰውረን ብርሃን ይሁን ብለው ዓለማትን የፈጠሩ ቅድስት ሥላሴ በሕይወታችን በስራችን በሐገራችን የጨለመብን ብዙ ነገር አለና ቅዱስት ሥላሴ ብርሃን ይሁነን
አሜን አሜን አሜን