አስተማማኝና ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ ችግር የሚታይባቸዉ መስመሮችን በመለየት የመልሶ ግንባታ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ የደብረ-ብርሃን ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ገለጹ፡፡
ሀገረ ማርያም 33 ኬ.ቪ፣ እነዋሪ 33 ኬ.ቪ፣ አጣዬ 15 ኬ.ቪ እና አረርቲ 33 ኬ.ቪ መስመሮች የኃይል መቆራረጥ የሚስተዋልባቸው ከፍተኛ መስመሮች መሆናቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ የእንዋሪ 33 ኬ.ቪ መስመር 42 ሳታላይቶችን እና የእንዋሪ ከተማ መጋቢ መስመር በሸክላ ሲኒ የተዘረጋ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ሪጅኑ ባከናወነው መስመር ፍተሻ ስራ ከደብረ ብርሃን እስከ እንዋ ሪ የተዘረጋው 67 ኪ.ሜ መስመር፤ ከደነባ-አንጭቆረር 12.5 ኪ.ሜ እና ከደነባ - ሲያ ደብር 16 ኪ.ሜ በአጠቃላይ 95.5 ኪ.ሜ መስመር ላይ ያሉት 6000 የሸክላ ሲኒዎች ሙሉ በሙሉ የማያገለግሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሪጅኑና ማዕከላቱ በጋራ ባከናወኑት ሥራ ከደብረ ብርሃን እስከ እንዋሪ አና ከደነባ እስከ አንጭቆረር የተዘረጉ 3,300 ሸክላ ሲኒዎችን ወደ ፕላስቲክ ሲኒ የመቀየር ስራ እንዲሁም የረገቡ መስመሮችን የመወጠር ስራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ዳይሬክተሩ በ2017 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ሪጅኑ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን የመለየት እና የቅድመ ጥገና ሥራዎችን በስፋት ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ 1365.4 ኪ.ሜ መካከለኛ መስመር ላይ ያሉ ችግሮችን የመለየት ሥራ በማከናወን 251.5 ኪ.ሜ የቅድመ ጥገና እና 1785 ቁጥር ያለው አስቸኳይ ጥገና ስራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡