"ሰማይን በስንዝር ልለካልሽ" ስላት
"ባሕሩን በገንቦ ልስፈርልሽ" ስላት
"ሺ ምንተሺ ኮከብ ላዝንብልሽ" ስላት
ውሸቴን መሰላት!
አታውቅም ይህቺ ሴት ፥ ደረጃና ልኳን
ለእሷ መዳፈሬን ፥ መለኮትን እንኳን!
፨
አወይ የእኔ ብጤ ፥ ሞኝ አፍቃሪ መሆን
የወደደ ጉንዳን ፥ "ልጣል" ይላል ዝሆን!
ዝሆንን እንኳ አንዴ ፥ ይጥሉት ይሆናል
ተነስቶ ሲመጣ ፥ ግን እንዴት ይዳናል?
፨
እኔና ወይኔ ላይ ፥ ስካር የለው ስልጣን
ስበላም በገደብ ፥ አያውቀኝም ቁንጣን
በልኬ እንዳልበላሁ ፥ በልኬ እንዳልጠጣሁ
መጥኖ ማፍቀሪያ ፥ ልብ ምነው አጣሁ?
፨
ምድርን ተሸክሟል ፥ አትላስ ያ ገርጋራ
በዕውቀቱም° አዝሏል ፥ ምድርን ካትላስ ጋራ
ይኸው እኔም አለሁ...
ከሁለቱም በላይ ፥ ደክሜና ዝዬ
እሷን ከፍቅሯ ጋር ፥ ተሸክሜ አዝዬ!
፨
የቆጠርኩት ሀሁ ፥ የገለጥኩት መጣፍ
የቤተስኪያን አፀድ ፥ የጸሎቴ ምንጣፍ
እሷ ፊት ሲቆሙ ፥ አይገዳደሯት
ጭራሽ አበረቷት ፥ ጭራሽ አደደሯት!
የመረሳት ልጅ ሆንኩ ፥ የመገፋት ወንድም
ምነው አይቆርጥ ልቤ ፥ እግሬ አይራመድም?
ጸሎቴ አይሰማም ፥ አይሰምርም ስለቴ?
ቆርጦ ጣለኝ መቁረጥ ፥ የት ሄደ ብስለቴ?
"ሙት" እንኳን ብትለኝ ፥ አላስብ ሁለቴ!
እሷን የጊዜ ገድ ፥ ሲያሳምር ሲኩላት
ስንቴ እየተነሳሁ ፥ ስንትዜ ሞትኩላት?
፨
ያጣሁኝ ይመስል ፥ ሸክም ባይነት ባይነት
አሻፈረኝም ብዬ ፥ በእምቢ ባይነት
ጠርጣራ ልቤ ላይ ፥ እንዳልተሸከምኳት
ስዝል ራቀችኝ ፥ ሲደክመኝ ደከምኳት!
፨
"እለቅ" ሲልኝ እንጂ
"ባክን" ሲለኝ እንጂ
የመከነ ፈንጂ
ሁን ሲለኝ ነው እንጂ
ልክ እንደ ልጥ ዘገር
እንደው ያለነገር
የነፍሴ ነበልባል ፥ አልተንቀለቀለም
አለቅኩ እንደ ላምባ ፥ ነጠፍኩ እንደ ቀለም!
፨
ፍዝ ኩራዝ ተግ ይላል ፥ ላምባ ሲንቆረቆር
ስብራት ይገጥማል ፥ ይድናል ቆረቆር
በደል ይሠረያል ፥ ይካሳል በእጥፍ
ግን ምን ያድርጉታል ፥ ሰው ነፍሱ ሲነጥፍ?
ቢላ ቢዶለዱም ፥ መቁረጡንም ቢተው
ያስቀጠቅጡታል ፥ ለአንጥረኛ ሰጥተው
ሸማውን ላጣቢ
ገንዘብ ለቆጣቢ
ባደራ ይሰጣል
ያደፈ ይነጣል
ጎፈር ያድርጉታል ፥ ጨብራራን ከርክመው
ምን መላ አለው ለሰው ፥ ሰው መሆን ሲደክመው?
በእሷው ዝዬ ብታይ ፥ እሷው ሳቀችብኝ
እንደህል እንደ ውኃ ፥ ነፍሴ አለቀችብኝ!
፨
የእሷ ገመምተኛ ፥ የማልቆርጥ ወላዋይ
በከንቱ ጩኸቴ ፥ እላለሁ እንጂ "ዋይ"
እሷ እንደኹ አይገርማት ፥ ሞቴንም ናቀችው
ቯለሰች °° በጣሬ ፥ ዕምባዬን ሳቀችው!
፨
እንድድናት ታመምኩ
እንድትይዘኝ ዘመምኩ
በእሷው እንዳልመጣ ፥ ሕመም በሽታዬ
አንድ "ይማርህ" አጣች ፥ ለሺ እንጥሽታዬ?
፨
ቧልቴ ወጋወጌ ፥ የአንደበቴ ፌዝ
እሷን ማሳቅ ከብዶት ፥ አጥሮት ለዛና ወዝ
እንዲያው ስድከመከም ፥ እንዲያው ስወዘወዝ
ይኸው አንድ ዘዴ ፥ ይኸው አንድ መላ
ቀልድ አደረኩላት ፥ ሕይወቴን በሞላ!
ይሄን ተመልክታ
ፈክታ ተንከትክታ
ስቃ ስታበቃ
ጥላኝ ሄደች በቃ?
ሁሌ እንድትስቀኝ ፥ ከፊቷ ባልርቅም
የተደገመ ቀልድ ፥ ለካ አያስቅም!
ሳቅ የተለበጠ ፥ ሺ ዕምባ ቀፍቅፌ
ብቻዬን ቀረኹኝ ፥ ቀልድ ሕይወት ታቅፌ!
፨
ግን ይሁን!
መቀበል ነው እንጂ ፥ የሕይወት አሰስ
ዳኛውን ለራሱ ፥ ምን ይረባል መክሰስ?
ምን ያመጣል ልቤ ፥ ቢያዝን ቢበሳጭስ?
ወዳልፈለገው ነው ፥ ሰውና የእጣን ጭስ!
፨
ባት[ሰ]ሚኝም ስሚኝ...
ባት[ስ]ሚኝም ስሚኝ...
መልኩን አሳምሮ ፥ ቢኮፈስ ቢኮራ
ከ"እኝክ - እንትፍ" ዕጣ ፥ አያመልጥ ሸንኮራ
እኔም እንደዚያ ነኝ ፥ አገዳና ቅንጥሽ
ካፍሽ ብውል እንኳን ፥ ችዬ ማልዋጥሽ
መሆኔን አውቃለሁ ፥ ጣፋጭ ግን አላቂ
ስትጎርሺኝ አልቅሰሽ ፥ ስትተፊኝ ግን ሳቂ!
መተፋቱ ላይቀር ፥ መስቲካ ታኝኮ
ምንምሽ ነኝ እኔ ፥ ምንምሽ ነኝኮ!
፨ ፨ ፨
°° ቯለሰች - "ቯልስ ደነሰች" የሚለውን ቃል የሚተካ የቃላተ-ፈጠራ ሙከራ