እንደለመድኩት ገና በማለዳው የእለት ጉርሴን ከማገኝበት ስፍራ ላይ ተሰይሜ አለው። አዲስ ነገር የማይገኝበት ኑሮዬ እንዲሁ ነው ማለዳ ወደስራ ሲመሽ ወደ ማደሪያዬ። ደህና ስራ ያለኝ እንዳይመስላችሁ "ለማኝ ነኝ"። ጥቂት ለኑሮ የምትሆነኝን ለማግኘት የሰውን ፊት የማይ... ለነገሩ ምን አይን አለኝና ነው "የማይ" የምለው? ይኸው እውርነቴ ነውኮ ለማኝ ያደረገኝ። ከስሜ በፊት እውርነቴ መጠሪያዬ ሆኖ "እውሩ በርጠሚዎስ" የምባል ነኝ።
ታዲያ መለመን በፍጹም አልሰለችም፤ በተስረቀረቀው ድምፄ ለምኜ ለሆዴ ያገኘኋትን ከፋም ለማ ሳልል ይዤ ወደ ቤቴ እገባና በማግስቱ ማለዳ ዳግም ቦታዬ እገኛለሁ። ዛሬም እንዲሁ በተለመደው የእለት ውሎዬ ላይ ሳለው ከመስማት ያልቦዘነው ጆሮዬ የብዙ ህዝብ ግርግር አደመጠ። ጥቂት ኮቴዎች ሳይሆን የሰራዊት በመሰለ እርምጃ ሰው ይጎርፋል። ድምፅና ኮቴው የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አልሆን ቢለኝ ይህ አይነቱ ክስተት በአካባቢዬ እንግዳ ነውና የእኔም ግራ መጋባት ጨመረ። እንደምንም እየዳበስኩ፣ እየተጋፋውና እየተጋጨው በቅርብ ያለ ወደመሰለኝ ሰው ተጠግቼ ነገሩን ባጣራ የጆሮዬን ጤንነት የሚያጠራጥር መልስ አገኘው። "ማን አልከኝ !" ሳይታወቀኝ ጮሄ ጠየኩ "የናዝሬቱ ኢየሱስ እያለፈ ነው" ሌላኛው ሰው ከእኔ በሚበልጥ ድምፅ መለሰልኝ። ገንዘብ ከሰው ለመቀበል ሳይደክም የጮኸው ጉሮሮዬ ዛሬ ፈውሱን ይቀበል ዘንድ ለምህረት ተጣራ..."የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ!"።
አዎ ያሉኝ "የናዝሬቱ ኢየሱስ" ነው ነገር ግን እያለፈ ያለው ሰው በናዝሬት ካሉ ጎልማሶች አንዱ የሆነ ብቻ ሳይሆን "የዳዊት ልጅ ንጉሡ ኢየሱስ" ስለመሆኑ ነፍሴ ገብቶታልና ከነፍሴ ጩኸት ጋር ጉሮሮዬ ተባበረ... "የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ ማረኝ!"። ምንም እንኳ ሮጬ ልይዘው ባልችል መጮህ አያቅተኝም..."የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ!"። እያለፈ ያለውን ንጉስ ያላወቁት ደግሞ ዝም በል እያሉ ይነዘንዙኛል ግን እንዴት ዝም እላለሁ? እርሱኮ ይመጣል ተብሎ በመፅሐፍት የተነገረለት መሲሑ ነው ፤ ደዌን ሊሸከም የተገባው የህማም ሰው የተባለለት ለእርሱ እኮ ነው፣ ለዓይኖቼ ብቻ ሳይሆን ለልቤም ብርሃን ነዉና ለምን ዝም ልበል?... "የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ ማረኝ!"
ድንገት ግርግሩ ቆመና በፀጥታው መሀል... የጠራኝን አምጡት ሲል ሰማሁት። አላልኩም እርሱ እኮ እንደዚህ ነው። በሌላ ከተማም የሰማሁት ይህንኑ ርህራሄውን፣ አዛኝነቱን፣ ሰው ወዳድነቱንና ደግነቱን ነው። ያልተጋነነ ዜና እውነተኛ ማንነት።
"ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?" ጠየቀኝ ይሄ ትሁት ጌታ
"ጌታ ሆይ አይ ዘንድ" መለስኩ
"እይ እምነትህ አድኖሃል" ከማለቱ አይኖቼ በሩ።
መጠሪያ ስም የሆኝ እውርነቴን፣ መገኛዬ የነበረ መለመኛ ቦታዬን፣ መለያዬ የነበረ ጉድለቴን ሁሉ ዳግም በእኔ ዘንድ ላይገኝ አስወገደው። አሁን መጠሪያዬ እርሱ፣ መገኛዬ እርሱ ባለበት፣ መለያዬ ተዓምራቱ ለአብ ክብር እንዲሆን ለዓይኔን ብቻ ሳይሆን ለነፍሴም ብርሃን ሆኖልኛል።
እናም ፈውስ ለምኔ እርሱን ካላየሁኝ፤ በፈወሰው አይኔ የአለምን ከንቱ ውበት ተመልክቼ ልሸፍት አልሻምና "መድሀኒቴ ሆይ ከዛሬ ጀምሬ እከተልሃለሁ" ስል ወሰንኩ።
ሉቃ 18:35-43
ማር 10:46-52
https://t.me/sistersmi