ጴጥሮስም ‘በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው’ አለው
በዚያን ሰዓት ሦስቱ ሐዋርያት ማለትም ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ (ሉቃ ፱፥፴፪)። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ምስጢረ መለኮት፣ ማለትም የጌታ በብርሃነ መለኮት ማሸብረቅና ልብሶችም እንደበረዶ ነጭ መሆን እንደዚሁም የእነዚህ የቅዱሳን የነቢያት መምጣት እና ከጌታችን ጋር መነጋገራቸውን ከሰማ በኋላ “እግዚኦ እግዚእ ሠናይ ለነ ኃልዎ ዝየ/ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው/“አለ፡፡ ቅዱሳን ነቢያቱ የወትሮ ሥራቸውን እየሠሩ ማለትም ሙሴ ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላት እያስገደለ፤ ኤልያስም ሰማይ እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናመ እያቆመ፤ አንተም አምላካዊ የማዳን ሥራን እየሠራህ ገቢረ ተአምራትህን እያሳየህ፤ በዚህ በተቀደሰ ቦታ “በደብረ ታቦር” መኖር ለእኛ እጅግ መልካም ነው”፡፡ “ወእመሰ ትፈቅድ ንግበር በዝ ሠለስተ ማኅደረ አሐደ ለከ ወአሐደ ለሙሴ ወአሐደ ለኤልያስ” አምላካዊ ፈቃድህስ ከሆነ በዚህ ተራራ ላይ አንድ ለአንተ፤ አንድ ለሙሴ፤ አንድ ለኤልያስ ሦስት ዳስ እንሥራ ብሎ ጠየቀ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› ሲል መናገሩም ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በደብረ ታቦር ለመኖር መሻቱን ያመላክታል፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሦስት ጎጆ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ›› በማለት የእርሱንና የሁለቱን ሐዋርያት ጎጆ ሳይጠቅስ አርቆ መናገሩ በአንድ በኩል ትሕትናውን ማለትም ‹‹ለእኛ›› ሳይል ነቢያቱን አስቀድሞ ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን አለመጥቀሱን፤ እንደዚሁም ከጌታችን ጋር ለመኖር ያለውን ተስፋ ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቅዱስ ጴጥሮስን ድክመት ማለትም የክርስቶስን አምላክነት በሚገባ አለመረዳቱን ያሳያል፤ ጌታችንን በተራራ ላይ በሰው ሠራሽ ቤት ይኖር ዘንድ ጠይቆታልና፡፡ጌታችንም ሐዋርያቱን ወደ ተራራው የወሰዳቸው ብርሃነ መለኮቱን ሊገልጥላቸው እንጂ በዚያ ለመኖር አልነበረምና ቅዱስ ሉቃስ ጴጥሮስ በደብረ ታቦር የተናገረውን ‹‹የሚለውንም አያውቅም ነበር›› በማለት ገልጦታል፡፡
ከደመናም ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት’ የሚል ቃል መጣ
ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ሲናገር ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ ከደመናውም “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ/ልመለክበት የወደድኩት ለምስጢረ ተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት/” የሚል ቃል መጣ፡፡ በዚህም የሥላሴ ምስጢር ለዓለም ለሦስተኛ ጊዜ ተገለጸ፡፡ እግዚአብሔር አብ ደመናን ተመስሎ “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” እያለ፣ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ሲሆን ፍጹም ሰውም ሆኖ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነጭ ደመና ተመስሎ ተገልጸዋል፡፡ ስለዚህም ደብረ ታቦር ጌታችን ብርሀነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግስቱን የገለጠበት እንዲሁም የስላሴ አንድነትን ሦስትነት የተገለጠበት ብላ ቤተክርስቲያናችን ታስተምራለች፡፡
የደብረ ታቦር በዓል ከዘጠኙ የጌታችን አበይት በዓላተ አንዱ ስለሆነ በቤተክርስቲያናችን ከዋዜማው ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ ማኅሌት ይቆማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ በዓሉ የደረሰው «ሰበሕኩከ በደብር በቅድመ ሙሴ ወኤልያስ ነቢያት ምእመናኒከ» በታማኞችህ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ ፊት የባሕርይ ልጅነትህን መሰከርሁልህ›› የሚለው መዝሙር በመዘመር ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ተሰጥቶት ይውላል፡፡ የአብነት ተማሪዎች እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት ሃይማኖትን የሚማሩ ናቸውና ለሐዋርያት ነገረ መለኮቱን የገለጠ አምላክ እንዲገልጥላቸው በዓለ ደብረ ታቦርን በተለየ ድምቀት ያከብሩታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ ነጎድጓዳማ ድምጽ መሰማቱን የብርሃን ጎርፍም መውረዱን በማሰብ በሀገራችን በኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች የነጎድጓዱ ምሳሌ አድርገው ጅራፍ በማጮኽ፣ የብርሃን ጎርፍ ምሳሌ አድርገው ችቦ በማብራት ያከብሩታል፡፡
አባቶቻችን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ በዓላትን በትምህርት ከማስተላለፍ ባሻገር ምሳሌነታቸውን በባሕላችን ውስጥ እንድንይዘው በማድረግ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲገለጽ ያደርጋሉ፡፡ ይህን የማይረዱ ሰዎች ግን ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን በባሕላዊ ጨዋታ በመተካት በበዓለ ደብረታቦር፣ በቤተ ክርስቲያን መሠረታዊውን ነገረ ተዋሕዶ ከማስረዳት ይልቅ ስለባሕል በመጨነቅ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ለቤተ ክርስቲያን በዓለ ደብረታቦር በዋናነት የነገረ ተዋሕዶ ማሳያ እንጅ የባሕል ትርኢት ማሳያ ቀን አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ ባሕል የሚያስፈልገው ለሃይማኖተኛ ሕዝብ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ከምንም በላይ መሠረተ እምነቱን ጠንቅቆ ሊያውቅ፣ ከመናፍቃንም ቅሰጣ ሊጠብቅ ይገባል፡፡ እኛም በዓሉን ስናከብር በምስጋና በመዘመር እንጂ ሌሎች ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸውን ባሕላዊ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር መሆን የለበትም፡፡
በአጠቃላይ በወንጌሉ ያመንንና በስሙ የተጠመቅን ክርስቲያኖች የደብረ ታቦርን በዓል ስናከብር ቅዱስ ጴጥሮስ “ለእኛ በዚህ መኖር መልካም ነው” እንዳለው በደብረ ታቦር በምትመሰለው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን የቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት አክብረን፣ በምግባር በትሩፋት አጊጠን፣ ሕገ ተፋቅሮን አስቀድመን መኖር በሥጋዊ ዓይን መከራ ወይም ድካም መስሎ ቢታየንም ፍጻሜው ግን ዘለአለማዊ ሕይወት ስለሆነ በቤቱ ጸንተን እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ መኖር መንፈሳዊ ግዴታችን መሆኑ ማወቅ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን!አሜን!