📖“በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን።”
— መዝሙር 66፥12
ሰሞኑን ከሳምንቱ በአንደኛው ቀን የእጅ ስልኬ ላይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስልን ተመለከትኩ። ዓይኖቼ በሚያዩትና ጆሮቼ በሚሰሙት ነገር በመሳባቸው ትኩረቴን ሰጠሁት። ከስልኬ ውስጥ እንዲህ የሚልን ንግግር ሰማሁ፦ "እግዚአብሔር ስጦታ ሲሰጥህ በመከራ ወረቀት አሽጎት ነው።" ቀጠል አድርጎም ላነሳው ሀሳብ ደጋፊነት ያላቸውን ቃላቶች ተናገረ። "ምክንያቱም እርሱ የሚሰጠው ነገር እጅግ ዋጋ ያለው በመሆኑ ስጦታውን ለመቀበል ዝግጁ እንደሆንክ ማረጋገጥ ይፈልጋል።"
ይህንን ካደመጥኩ በኃላ ራሴን እንደዚህ በማለት ጠየኩት፦ "ስንት ጊዜ ይሆን የመከራ ማሸጊያ ወረቀቶችን መክፈት ባለ መፈለጌ ምክንያት ዕንቁ የሆኑ ስጦታዎቼን ያጣሁት?" ብዙዎቻችንን ተመሳሳይ ቁጭት እንዳለን እገምታለሁ።
ዳዊት የመከራን አስፈላጊነት ባጎላ መልኩ እንደዚህ በማለት ይናገራል፦ “በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን።” (መዝ 66፥12) “በእሳትና በውኃ” መካከል ማለፍ ቀላል ላይሆን ይችላል። በጊዜው የሚሰማን ስሜት ጥልቅ ነው። ነገር ግን እሳቱ ሊፈጀን ሳይሆን ወደ እኛ የሚመጣው እንደ ወርቅ አንጥረኛ ሊያጠራንና እንደ ሸክላ ሰሪ ጥሩና የተስተካከለ ቅርፅ ሊያሲዘን ነው። በውሃ ውስጥ ማለፋችን ግድ የሚለን ጠራርጎ ሊያጠፋን ሳይሆን እንደ ግንበኛ ባለንበት ፀንተን እንድንቆም ሊያጠነክረን፣ በሁኔታዎች ተፈረካክሰን እንዳንወድቅ ሊገነባን ነው።
ባለ ቅኔው ምን አልባት “በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥” ብሎ ቢያቆም ልባችን ሊያዝን ይችላል። ግና በዛ አልተቋጨም። “ወደ ዕረፍትም አወጣኸን” በማለት ይናገራል። ወገኖቼ፣ በእሳትና በውኃ መካከል ማለፋችንን አንጥላው። በመከራ ወረቀት የታሸጉ ስጦታዎቻችንን ለመክፈት ልባችን አይራድ። ሕይወታችን በዚህ አያበቃም። የኅላ ኅላ ሁሉ ነገር ወደ በረከት ይመጣልና።
🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ዕረፍቴና በረከቴ ስለሆንክ አከብርሃለሁ። በእሳትና በውኃ መካከል ማለፍ ግድ ሲሆንብኝ አንተን መታመንን አስተምረኝ። አሜን።
የህይወት ስንቅ ~ #BT
| KALTUBE
"Daily Spiritual Feeding"
👇💐👇💐👇💐👇💐👇💐
@KALTUBE
@KALTUBE
@KALTUBE