°•ምክር ቢጤ ለሰለምቴ እህቶች °•
1) ስላሰለመሽ ብቻ አታግቢው ፦ ስላሰለመሽ ዲንን ያውቃል፣ ስነምግባሩ የተስተካከለ ነው ማለት አይደለም።
ለትዳር ደግሞ በወንድ ልጅ ላይ ሁለቱ የሚፈለጉ መስፈርቶች ናቸው። ስለሆነም ስላሰለመኝ አምነዋለሁ በሚል እሳቤ ከማግባት ተጠንቀቂ።
2) እንደሰለምሽ ቶሎ አታግቢ ፦ ከሰለምሽ በኋላ ትልቁና የመጀመሪያ ስራሽ ዲንን ማወቅ ማንበብና መማር ይሁን። ያኔ ምናልባትም የኢስላም አካል የሚመስሉሽ ግን ያልሆኑ ጉዳዮች ካሉ ይገለጡልሻልና።በኢስላም ስለሴት ልጅ የተደነገጉ ብይኖች ላይ የሚያጠነጥኑ የዲን እውቀት ዘርፎች ላይ ተሳተፊ።
3) የሒጃብ ጓደኛ ትኑርሽ፦ ሸሪዐዊ ሒጃብን ጠንቅቃ የምትለብስ ባለትዳር ጓደኛ ትኑርሽ።የትዳር ጥያቄዎች ሲመጡ የምታማክሪያት ትሁን።
4) ቤተሰቦችሽ ይወቁ ፦ ከሰለምሽ በኋላ በዲኑና በአኽላቁ መልካም ሰው ከገጠመሽና ከተስማማሽ ቤተሰብ ባንቺ እምነት ላይ ባይሆኑም ማሳወቅና ማሳመን ያስፈልጋል።
ትዳር የዘር ሰንሰለት የሚፈጠርበት ተቋም እንደመሆኑ እናትነቱና አባትነቱ መኖሩ ግዴታ ስለሆነ የቤተሰብ ጉዳይነቱ ግልፅ ነው። በኋላም ተያይዘው የሚመጡ ጉዳዮች እነርሱ ጋር የሚደርሱ እንደመሆናቸው ቤተሰቦችሽን አሳውቂ።
5) ዳዒያ ከመሆን ተጠንቀቂ ፦ አሁን ላይ እንደፋሽን የተያዘ ዳዕዋ ላይ ከመሳተፍ ራስሽን ጠብቂ። ዛሬ ተሰልሞ ነገ ሚዲያ ላይ ዳዒ የሚኾንበት ስርአት በኢስላም የለም።ዲን በእውቀት ላይ መጣራት ስለሆነ ፊትሽን ወደ እውቀት አዙሪ።
6) ለትዳር የጠየቀሽን ሰው አጥኚ፦ ቤተሰቡን፣ አኗኗሩን ታሪኩን የማጥናትና የመጠየቅ መብት አለሽ።በዲኑ ጠንካራና መልካም ሰለምቴ ካገኘሽ ለጋራ የስነ ልቦና መናበብ በላጭ ስለሆነ አግቢ።ካልሆነም ጥሩ አኽላቅና ዲን ያለው በኢስላም ላይ ያደገን አግቢ።
7) ቃዲ ምረጪ(ጡ) ፦ ወሊይ የሌላት ሰለምቴ ወሊዩዋ ቃዲ መሆኑ ግልፅ ነው።ስለሆነም ቃዲው ኒካህ ከማሰር በዘለለ የወሊይነት ሚናውን የሚወጣ የሱና ሰው መሆኑን ማየት የግድ ነው። ሰዎች የሚያውቁት፣ ተሰሚ ሸይኽ ዘንድ ሄዳችሁ ኒካህ አድርጉ። አለመግባባት ቢኖር ጥፋተኛውን ተው የሚል የሚገስፅ ይሆናል።በባል መበደል ቢኖር (ብዙ ጊዜ የሚከሰት እንደመሆኑ) በአላህ የሚወቅስ ቃዲ (ወሊይ) መሆን ይኖርበታልና።
(ብዙ ጊዜ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ሰለምቴ እህቶቻችን ጋር ልብ እንደማይባሉ ስላየሁ ነው። ተጨማሪ ካለ ጨምሩበት ።)
የቴሌግራም ቻናል ፦ t.me/ismaiilnuru