የኢስላም ጠላቶች የእስልምና ጮራ ከፈነጠቀበት ጊዜ አንስተው ብርሀኑን ለመግታት ከቻሉም ለማጥፋት ብዙ ሞክረዋል ። በተለይ የመጀመሪያው ትውልድ የኢስላምን አድማስ እያሰፋ በነበረበት ጊዜ በዐለም ላይ የነበሩ ሀያላን የሚባሉ ሀገራት ከኢስላሙ ብርሀን ፊት ለመቆም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል ። ግን ልፋታቸው ያ ትውልድ ከአላህ ጋር በነበረው ጥብቅ ትስስር ምክንያት መክኖ እንዲቀር አድርጎታል ።
ተስፋ የማይቆርጠው የሸይጣን ሰራዊት አንዱ ሜዳ ላይ ሲሸነፍ ሌላ ሜዳ ፊቱን እያዞረ ከአራሕማን ሰራዊት ጋር ሲፋጠጥ ምኞቱ ከስሞ ቅስሙ ተሰብሮ መመለስ እንጂ ወደ ፊት መቀጠል አልቻለም ። የዚህ አይነቱ ሽንፈት ሚስጢር ሳይገባቸው በማያውቁት ነገር የኪሳራ ካባ ሲደራርቡ ሚስጢሩን ማወቅ አለብን አሉ ።
በዚህም ቆም ብለው ያሳለፉትን በህሊናቸው መስኮት እያማተሩ ሲያዩ ብዙ ሰራዊት በቁጥርም በትጥቅም የማይገናኝ ከጥቂቶች ፊት መቆም እንዲያቅተው ያደረገው በአራሕማን ሰራዊት ልብ ውስጥ የነበረው የኢማን ሀይል መሆኑን አወቁ ።
እየተሸነፉ ያሉት በመሳሪያና በሰራዊት ብዛት እንዳልሆነ ይልቁንም ትንሹ ሰራዊት ከአላህ ጋር ባለው የጠበቀ ትስስር በአላህ እርዳታ መሆኑን ገባቸው ። እያሸነፋቸው ያለው የተውሒድ አቅም እንጂ የሰራዊት አቅም አለመሆኑን አመኑ ።
የዚህን ጊዜ እስትራቴጂ መቀየር አስፈላጊ ሆነ ። ጦርነቱ ከኢማን ጋር ከተውሒድ ጋር ሆነ ለዚህም ሰራዊት መመልመል ጀመሩ ። የአሁኑ መሳሪያ በጀርባ አዝለውት በትከሻ ተሸክመውት የሚሄዱት አይደለም ። ቀላል ሆኖ በጣም አጥፊ መሳሪያ ነው ። በሙስሊሞች ልቦና ውስጥ ያለውን ተውሒድ የሚያጨልም ኢማናቸውን የሚያቀልጥ የሹብሃ መሳሪያ የስሜት መከተል መሳሪያ መታኮስ መሳየፍ የማያስፈልገው በጥቂት ቃላቶች የሚገለፅ ቶሎ ልብ ላይ የሚሰርፅ መሳሪያ መጠቀም ጀመሩ ።
የጦርነቱ ሜዳ ከበረሀ ወደ ሽርክና ቢዳዓ ፋብሪካ ተዛወረ ። ከሙስሊሙ ውስጥ ለዚህ ፋብሪካ ሰራዊት መለመሉ ከበላይ የሚመራው የዐብዱላሂ ኢብኑ ሰበእ አልየሁድይ ሀላፊነቱ የተወሰነ የኩፍር ማህበር ሆነ ። የሺዓ ፋብሪካ ተከፈተ በወልይ ስም ሙታኖች ይጠቅማሉ ፣ ይሰማሉ ፣ ይረዳሉ ፣ አላህ ስልጣን ሰጥቷቸዋል በሚል አላህን ትቶ እነርሱን መጥራት ተንሰራፋ ። ጎን ለጎን የተለያዩ የቢዳዓ ፋብሪካዎች እየተከፈቱ የሙታን መንፈስ ማምለኩ አድማሱ እያሰፋ ቅርንጫፉ እየበዛ ለዓለም ተዳረሰ ። የሱፍያው እህት ኩባንያ ይህን ሽርክ የማስፋፋቱ ስራ በሰፊው ተያያዘው ።
በዚህም በቀላሉ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ አላህ ያዘነለት ሲቀር ከውስጡ በአላህ ማመን የሚባለውን ማውጣት ቻሉ ። በዚህም አብዛኛውን ሙስሊም ኮፍያ ጥምጣምና ጀለብያ የለበሰ ቆሞ የሚሄድ ውስጡ ባዶ የሆነ እስከሌተን አደረጉት ።
የኢስላም ጠላቶች ሀገራችን ላይ ሙስሊሙን ከኢማኑ ለማራቆት ከከፈትዋቸው የሽርክ ፋብሪካዎች አንዱ አብሬት ያለው ሀድራ ነው ። ቅርንጫፉ ጠቅላይ ቢሮ የሚባለው አ/አ ነው ።
ሰዎች በየአመቱ ወደ አብሬት የሚገርፉት በአላህ ላይ ለማጋራት ውስጣቸውን አላህ ይጠቅማል ከሚለው ኢማን ባዶ አድርገው ያብሬት ሸይኾች ይጠቅማሉ በሚል ቀይረው ለሳቸው ችግራቸውን ለመንገር ነው ። ‼
አው አብሬት የሚሄድ ሙሪድ ኮፍያ ያደረገ ፣ ጀለብያ የለበሰ ፣ ጥምጣም የጠመጠመ ወይም ስሙ ሙሐመድ ፣ አሕመድ ፣ ከማል ፣ ሰፋ ፣ ጀማል የሆነ የሙታን መንፈስ አምላኪ ነው ። ሀድራውን የሚመሩት ጫት ናላቸውን ያዞራቸው ጠንቋዮች ናቸው ። ህዝቡን ቁርኣንና ሐዲስ ሳይሆን ያብሬትዬ የሚሉት ሸይጣን ወሕይ የሚያደርግላቸው ገድል ነው ።
አብዛኛው አብሬትዬ ይመጣሉ በሚል ከሀገሩ የወጣ ነው ። ዱዓእ ሲያደርጉ በሀድራቸው አላህ ያስገባቸው የሚል ነው ።‼ ይህ ተራውን ህዝብ የሚያስተኙበት እንጂ ገስግስ እንደገደላቸው ያውቃሉ ። የራሳቸው ልጆች አንዱ ሌላውን አባታችንን አስገድለዋል በሚል ክስ ላይ ናቸው ። ይህ ከመሆኑ ጋር ወደ አብሬት የሚጎርፈው ህዝብ ችግሩን ለአብሬትዬ ይናገራል ። ዘር ስጡኝ ፣ ከጭንቅ አውጡኝ ፣ ድረሱልኝ ፣ ለማን ተውኝ ይላል ። መከራውን ፣ ችግሩን ፣ ሐዘኑን ፣ ማጣቱን ፣ መጎዳቱን ፣ ፍርሀቱን ለሳቸው ይናገራል ። እርዱኝ ፣ አክብሩኝ ፣ እጄን ያዙኝ ይላል ።
ኧናገራ ያለውን የአባታቸው ቀብር ( ኧቁባይ ) ሄዶ አፈር ይበላል ። በእንብርክኩ ወደ ቀብሩ ይደርሳል ። ስልኩን አጥፍቶ ጫማውን ከሐረሙ ( ከጊቢ ) ውጪ አስቀምጦ በእንብርክክ ሄዶ ቀብሩ ጋር ስጁድ አድርጎ በጠዋፍ ዞሮ ለአላህ እንጂ የማይገባ አምልኮ ያደርጋል ። ጉዱ በዚህ አይቆምም በየአመቱ የሚሄዱ አንድ ላምስት ተደራጅተው ወደዚህ ቀብር አምልኮ ለመጣራት ተስማምተው ይመጣሉ ።
አሕባሽና ሱፍዮች የዚህ አይነቱን የሽርክና የኩፍር ተግባር በገንዘብ በመርዳት አድማሱ እንዲሰፋና ሙስሊሞች ቀብር አምላኪ እንዲሆኑ ቀንና ለሊት ይሰራሉ ። ይህ ከእስልምና የሚያወጣ ሽርክ ነው ተብሎ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የቁርኣን አንቀፆች ሲነገራቸው ለከሀዲያን የወረዱ የቁርኣን አንቀፆች ለሙስሊሞች ያደርጋሉ ይላሉ ። ‼
እነዚያ አላህ ሙሽሪክ ያላቸው ከሀዲ ያላቸው ሰዎች ጥቁር ፣ቀይ ፣ ዐረብ ፣ ዐጀም ፣ አጭር ፣ ረዥም ፣ ስለነበሩ ነው ወይስ የሚሰሩት የነበረው ተግባር የኩፍርና የሽርክ ተግባር ስለነበረ ነው ? በእነዚ አባባል ስለ ሶላት ፆምና ዘካ የሚናገሩ አንቀፆች ለእነዛ በዛ ዘመን ለነበሩት ብቻ ነበር አሁን አይሰራባቸውም ማለት ነው ። ‼
ሁሉም በየትኛውም ጉዳይ የመጡ የቁርኣንና የሐዲስ መረጃዎች በየትኛውም ዘመን የትም ቦታ ይሰራሉ ። ሙሽሪኮቹ ሲሰሩት የነበረውን ሺርክ የሚሰራ ሙሽሪክ ይባላል ። ከሀዲያን የሚሰሩትን የኩፍር ተግባር የሚሰራ ካፊር ይባላል ። በግለሰብ ላይ ብይኑን ለመስጠት የሚያስችሉ መስፈርቶች ተሟልተው ከልካዮች ሲወገዱ መረጃው ሲደርስ ያግለሰብ ካፍር ነው ይባላል ። የቁርኣን ህጎች በወረዱበት ምክንያት የተገደቡ አይደሉም ። ቃሉ በያዘው ብይን እስከቂያማ ይሰራሉ ።
በመሆኑም እናትና አባቶቻችንን ከአሕባሽና ሱፍዮች እጅ ለማውጣትና ወደ ተውሒድና ትክክለኛ እስልምና ለማምጣት የምንችለውን ማድረግ ይጠበቅብናል ።
አላህ ይወፍቀን ።
https://t.me/bahruteka