ጌታዬ ሆይ! በውስጤ ነው የምወድህ ? በላይኛው እንቅስቃሴዬ ብዬ አመነታለሁ ። ለራሴ ጸጋን እየጠቀስኩ ሰዎች ግን በሕግ መጠየቅ አለባቸው ብዬ አስባለሁ ፣ በኦሪት ነኝ ወይስ በሐዲስ ብዬ የራሴን አድራሻ ለማወቅ አመነታለሁ ። ጽድቅን ለአንድ ጊዜ ፣ ኃጢአትን በተደጋጋሚ ስመርጥ ከእውነት የምወደው የቱን ነው? ብዬ አመነታለሁ ። ከቤትህም አልቀርም ፣ ከዓለምም አልታጣምና “የቱን ልያዝ ?” ብዬ በአንዱ ሰውነቴ ለሁለት ጌታ ማደር ፣ እንደ አክርማ መሰንጠቅ ፣ አንተንና ሰይጣንን ማስታረቅ ያምረኛል ። የሌሎችን ስህተት በአጉሊ መነጽር እያየሁ የራሴን ግን ላለማመን “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” ብዬ እምላለሁ ፣ ይህን ባሰብሁ ጊዜ እውነተኛ ነኝ ወይ ? ብዬ አመነታለሁ ።
🌿@father_advice🌿
የተሰጠኝን ዘንግቼ ያልተሰጠኝን ስሻ ፣ የራሴን ትቼ የሌሎችን ጸጋ ስጋፋ ፣ በመንፈስህ መመራቴን አመነታለሁ ። በአገሬ ለመኖር “ሰዉና አየር ንብረቱ..” ስል በሰው አገር ለመኖር “ንጽሕናውና ነጻነቱ” እያልሁ አመነታለሁ ። ሁለት ነገር እያባረርሁ አንዱንም አጣለሁ ። የተፈቀደልኝን ቀን ፣ የመደሰት መብቴን አሳልፌ እሰጣለሁ ። ሁለት መልካም ነገሮችን አንዳንዴም ደግነትና ክፋትን ለመምረጥ አመነታለሁ ። እፈልጋለሁ ግን አልፈልግም ፣ ከራሴ ጋር ስብሰባ እቀመጣለሁ ግን አልወስንም ። ልቤ ይሞቃል ፣ ላደርግ ስነሣ መልሶ ይበርዳል ። አመነታለሁ ። ካንተ ጋር ልኖር ፣ ወደ ሰማይ ልመጣ እሻለሁ ፣ ያለበስኳቸውን ጨርቆች አስብና እንደገና በዚህ መኖርን እፈልጋለሁ ። አንደኛው ልቤ ባሕታዊ ፣ ሁለተኛው ልቤ ዓለማዊ ይሆንብኛል ። በአንድ ጊዜ ጽርሐ አርያም ወዲያው እንጦሮጦስ እገኛለሁ ። “ማረኝ” እያልኩህ “አትማራቸው” እላለሁ ። አመነታለሁ ፣ የማን ወገን እንደምሆን እጨነቃለሁ ። የዚያኛው ድግስ ጮማ ብርንዶ ቢኖረውስ? ይህኛው እልበት ፣ ሽሮ ቢሆንስ ? እያልሁ በመንታ መንገድ ላይ ቆሜ ሰዓቱን አሳልፋለሁ ።
ደግነትን እመርጥና ውጤቱ ቢዘገይስ? ክፋት ይሻላል ፣ አሳማውን በልቶ መቀደስ ይቻላል እላለሁ ። ለእምነት የተሰጠውን ንስሐ ለብልጠት እጠቀምበታለሁ ። መድኃኒት አለና በሽታ ቢይዘኝ እላለሁ ። ደግሞም ጭቃ ከነካኝ አይቀር ብጨማለቅስ ? እላለሁ ፣ ከኃጢአተኝነት ወደ ሰይጣንነት ለመሄድ እቆርጣለሁ ። የሰማሁት ቃልህ “ተው” ሲለኝ ፣ ልቤ “ግፋ” ሲለኝ በእነዚህ ሁለት አሳቦች አመነታለሁ ። ንጉሥ የወደደው ጣዖት የታቦት ያህል ነው ብዬ ከኤልያስ አክአብን መርጬ ፣ ማወቄን ባለማወቅ ለውጬ ፣ የዝናብ አምላክ “በኣል ነው” ብዬ ልጠፋ እሰናዳለሁ ። ጥሩ አማኝ ወይም የለየለት ከሀዲ አልሆንሁም ። ጌታ ሆይ አመነታለሁ።
ልቤ ከአንደኛው ሸለቆ ጥግ ወደ ሁለተኛው ጽንፍ ሲላጋ ፣ ተቀምጬ መሮጥ ፣ ተኝቶ መብረር ሥራዬ ሆኖአል ። የተፈጥሮ ስጦታ እያልሁ ስናገር ያንተን ሰጪነት መካዴ ነው ፣ እግዚአብሔር ብዬ ከምናገር “ፈጣሪ ይባርክህ” ብል ሁሉም ይወደኛል ብዬ ስምህን እዘላለሁ ። ዘላለምንም ዘመንንም ለማትረፍ እታገላለሁ ፣ አዎ አመነታለሁ ። ልበ ሙሉ ከሀዲ ለመሆን “ምነው ቃሉን ባልሰማሁ” እያልሁ እመኛለሁ ። አውቆ እንዳላወቀ ሰው መኖርን እናፍቃለሁ ። የበጋ መብረቅ ክፉዎችን ሲቆርጥ ያን ጊዜ ደግሞ “ወደ ወጣሁበት ቤቴ ልመለስ” ብዬ እገሰግሳለሁ ። ትክክልም ስህተትም አይደለም ብሎ ባለመናገር ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ በመጠቀም ካለውም ከሚመጣውም ጋር ጓድ ለመሆን አሰላለሁ ። ፍርድን ትቼ ፍርሃትን እዛመዳለሁ ። ሳልኖር ለመሞት እሰጋለሁ ። አዎ አመነታለሁ ። የሥነ ምግብ ባለሙያዎች እንደሚመክሩኝ ለመኖር አስብና መልሼ ቀለል አድርጎ መኖርን እፈልጋለሁ ። ስፖርት ለቀኑ ጤንነት እንጂ ለዕድሜማ ሰጪው አንተ ብቻ መሆንህን እዘነጋለሁ ። ጥሩ የሚንቀሳቀሰው ልቡ ቀጥ ሲል “የቱ ነው ለዓለም የሚሻለው ?” እያልሁ አመነታለሁ ። ምዕራባዊነትን ከዘመናዊነት ጋር ሳምታታው ፤ ዘመናዊነት መሰልጠን ፣ ምዕራባዊነት ሌላ ባህል መሆኑን ስዘነጋው የቱን ልምረጥ ብዬ አመነታለሁ ።
የሚያመነታ ገንዘብ ቢኖረው አይገዛ ፣ እግር ቢኖረው አይራመድ ፣ ሃይማኖት ቢኖረው አያመልክ ፣ ፍቅር ቢኖረው አብሮ አይዘልቅ ፣ ቤት ቢኖረው አያርፍ ፤ ስቁል ልብ ፣ ከርታታ መንፈስ አለው ። ጌታዬ ሆይ የወንጌልህን ቃል ለመስማትም ለመኖርም ጨካኝ መሆን እሻለሁ ። በቍርጥ እንዳዳንኸኝ ፣ በቍርጥ ልከተልህ እመኛለሁ ። በአብርሃም ድንኳን እንደ ተገኘህ ፣ በድንኳን ሰውነቴ ፣ በሚነዋወፀው አካላቴ ተገኝና በአማን ይስሐቅ ይሁንልኝ ።
አሜን🙏
🌿@father_advice🌿