አማኝ ታዳሽ ኅይል አለው። ይህም ኅይል አምላኩን ተስፋ ከማድረጉና ከርሱ ጋር ከመሆኑ—ከመጣበቁ—የተነሣ የሚመጣ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ በደከመበት፣ ተስፋ በጣለበትና ባመነታበት ጊዜ መልእክት መጣለት፤ "እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም" (ኢሳ 40፥31)። ሕይወት ብዙ ትግልና ውጣ ውረድ ስላለው ኅይል ጨራሽ ነው፤ ሰዎችም ይደክማሉ፤ ይታክታሉም። አቅም የሆነውን አምላክ የሚጠጋጉ ግን ደክመው አይቀሩም፤ ይታደሳሉ፤ ጕዟቸውም እንደ ንስር ወደ ላይ ይሆናል።