**
የግዥና ንብረት ባለስልጣን በካልም ፕሮጀክት ድጋፍ በርካታ ተግባራትን ሲያከናዉን መቆየቱን ተከትሎ ከተሰጠዉ ተግባርና ሃላፊነት አንጻር በግዥ አቤቱታናጥፋተኝነት፣ በካልም ኦዲት እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ጋር በተያያዘ ክልሎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም እና በቁልፍ የግዥ አፈጻጸም መለኪያ ዙሪያ የክልሎች የ2015 እና የ2016 ዓ/ም አፈጻጸም በጋራ ለማየት ታቅዶ የተዘጋጀ መድረክ ነዉ ሲሉ አቶ ፀጋዬ አበበ (የካልም ፕሮጀክት አስተባባሪ) መድረኩን ባስተዋወቁበት ወቅት ገልጸዋል።
መድረኩን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ የከፈቱት ሲሆን በካልም ኦዲትና በግዥ አቤቱታናጥፋተኝነት ቦርድ ዙሪያ ክልሎች ያሉበትን ደረጃ የምናይበት መድረክ ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አያይዘዉም የካልም ፕሮጀክቱ የግዥ አስተዳደር ስርዓታችን የሰለጠነና ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያለው የተናበበ ጥምር እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም የፕሮጀክቱ ዓላማ የተሻለ ተፈጻሚነት እንዲኖረዉና ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ያለዉ የተናበበ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ተግባሮቻችን በዲጂታል ሲስተም በዘመነ እይታ መቃኘት አስፈላጊ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 1333/2016 አዲስ የጸደቀዉ አዋጅ፣ በመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ትግበራ እና በተሸከርካሪ እና የነዳጅ አጠቃቀም( ኢፍሊት ማኔጅመንት) ዙሪያም ጭምር ገለጻ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
አዋጁን የገንዘብ ሚኒስትር የህግ አማከሪ አቶ ሃብታሙ መነሻ ለተሳታፊዎች ያቀረቡ ሲሆን የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ወልደአብ ደምሴ ከኢጂፒ ሲስተም ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ ዝርዝር ጉዳዮችን ከሲሰተሙ ጅማሮ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ባስቃኘ መልኩ ገለጻቸዉን አቅርበዋል፡፡
ከቀረበዉ ገለጻ ጋር ተያይዞ ተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡ የባለስልጣኑ የበላይ አመራሮች ፣ የፕሮጀክት ማናጀሩ ፣ የገንዘብ ሚንስትሩ የህግ አማካሪ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለስልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች ለቀረቡ ሃሳብ አስተያየቶች ግልጽና ተቋማዊ ምላሽ ሰጥተዉበታል፡፡
በመጨረሻም የመድረኩ አብይ ዓላማ አዋጁን ከክልሎች አሠራርና አዋጅ ጋር ማጣጣምና የኤክትሮኒክ ግዥ ሲስተምን ልክ እንደ ፌደራል ተቋማት ሁሉ በክልሎች ማስፋፋት ሚቻልበት ግንዛቤን ለሠፍጠር ጭምር መሆኑ በማጠቃለያው ተካትቷል።
ቀጣይ በሚኖረን መርሃ-ግብር ቀደም ሲል የተገለጹ ከካልም ኦዲት፣ ከግዥ አቤቱታና ጥፋተኝነት እና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ ጉዳዮች የሚቀርቡ ይሆናል፡፡