M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office @mormediumtaxpayersbranchoffice Channel on Telegram

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

@mormediumtaxpayersbranchoffice


This is official Telegram Channel of M.o.R Medium Tax payers No 1 Branch office
Join the channel.

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office (English)

Are you a medium tax payer looking for important updates and information regarding your tax obligations? Look no further! Welcome to the official Telegram Channel of M.o.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office. This channel is designed to provide you with all the necessary updates, guidance, and resources to ensure that you fulfill your tax obligations effectively and efficiently. Who is M.o.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office? They are a dedicated team of professionals who specialize in assisting medium tax payers with their tax needs. Whether you are an individual or a business owner, this channel is the perfect destination for you to stay informed and up-to-date on all tax-related matters. What is M.o.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office? This channel serves as a hub for all things related to medium tax payers. From important announcements to tax tips and tricks, you will find a wealth of information that will help you navigate the complex world of taxes with ease. By joining this channel, you will have access to exclusive content and personalized support that will make your tax journey hassle-free. Join the M.o.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office Telegram Channel today and take the first step towards achieving tax compliance and financial success. Don't miss out on this valuable resource - join now and empower yourself with the knowledge and tools you need to thrive in the world of taxes!

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

06 Jan, 08:38


እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ ግብር ከፋዮች እንዲሁም አጋር አካላት እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ እያለ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሁም የስድስት ወር የገቢ እቅዱን የሚያሳካበት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞቱን ይገልፃል፡፡

መልካም የገና በዓል!

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

06 Jan, 06:52


መረጃው ለሁሉም ግብር ከፋዮች እንዲደርስ ያጋሩት

ታሕሳስ 28/2017 ዓ.ም (የገቢዎች ሚኒስቴር)

የገቢዎች ሚኒስቴር ግብር ከፋዮችን በግብር ሕግ ተገዥነታቸው ልክ እየለየ እውቅና እና ሽልማት መስጠት ከጀመረ ዓመታት መቆጠሩ ይታወቃል፡፡ ግብር ከፋዮቹንም በአንጻራዊነት የሚለይበት የመመዘኛ መስፈርቶችን በገቢ እና በጉምሩክ ዘርፍ ለይቶ በማዘጋጀት እየሰራ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ በተለየዩ ጊዜያት አጭበርባሪዎች ይህንን እንደአጋጣሚ በመጠቀም በሐሰተኛ ማንነት ከገቢዎች ሚኒስቴር ለድርጅቶች ባለቤት ወይም ሥራ አስኪያጆች በተንቀሳቃሽ ስልክ እንደተደወለ በማስመሰል ለሽልማት ብቁ እንድትሆኑ እናደርጋለን በማለት በስልክ በማስፈራራትና በማደናገር ገንዘብ ለመቀበል የሚጥሩ አካላት ስልቶችን በመቀያየር ግብር ከፋዩን በማጭበርበር ላይ ናቸው፡፡

በመሆኑም በዚህ መልክ የሚፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል ግብር ከፉዩ እና ማህበረሰቡ ከአጭበርባሪዎች እራሳችሁን እንድትጠብቁ ሚኒስቴሩ ያሳስባል።

የገቢዎች ሚኒስቴር

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

04 Jan, 13:16


ለታክስና ጉምሩክ ክበብ የጥያቄና መልስ ዉድድር ለሚሳተፉ ተማሪዎች እና ለአብቂ መምህራኖች ሥልጠና ተሠጠ፡፡

ታህሳስ 26/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ዙር የጥያቄና መልስ ዉድድር ላይ ለሚሳተፉ ከስምንት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ተማሪዎችና አብቂ መምህራኖች በታክስና ጉምሩክ ፅንሰ ክበባት ሞጁል ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሠጥቷል::

ሥልጠናዉን በይፋ ያስጀመሩት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አቶ ተግባሩ ታምሩ ህገወጥ ንግድንና የታክስ ማጭበርበርን በማስወገድ በፍቃደኝነት ታክስ የሚከፍል ማህበረሰብ ለመፍጠር እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨዉን ገቢ ለመሰብሰብ የነገ ሀገር ተረካቢ ትዉልድ ላይ የታክስና ጉምሩክ ፅንሰ ሀሳቦችን ማስረፅ እንደሚገባ አፅንኦት በመስጠት የዛሬው መድረክ ደግሞ በተለይ ለተማሪዎች ለውድድር ትልቅ ስንቅ እንደሚሆናቸው ጭምር ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናዉ በሀገር ዉስጥ ገቢ እና በጉምሩክ ህጎችና አሰራሮች ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርት ዋና መሪ ባለሙያ በሆኑት ወ/ሮ ፈትያ ሙራድ እና በጉምሩክ ኮሚሽን የደንበኞች ትምህርት ቡድን አስተባባሪ በሁኑት አቶ አንዳርጌ ፈንታው አማካኝነት ተሰጥቷል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

03 Jan, 08:45


የተርን ኦቨር ታክስ እና ተጨማሪ እሴት ታክስ ተመሳሳይነት እና ልዩነት

በሀገራችን የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ዉስጥ ቀጥተኛ ታክሶች እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች የሚባሉ የታክስ አወቃቀሮች ያሉ ሲሆን የተጨማሪ እሴት ታክስ እና ተርን ኦቨር ታክስ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ተመሳሳይነት
  ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች መሆናቸው፤
  በፍጆታ ወይም በወጪ ላይ ተመስርተው የሚጣሉ መሆናቸው፤
  ከግብር ከፋዩ ካገኘው ገቢ የሚከፈል ሳይሆን በመንግስት ዉክልና በተሰጠው መሠረት ታክስ ከፋዮች ከተጠቃሚዉ ህብረተሰብ የሚሰበሰቡ መሆናቸው

ልዩነት
  ተጨማሪ ዕሴት ታክስ እንደ ሽያጭ ታክስ በታክስ ላይ አለማስከፈሉ
  ተጨማሪ ዕሴት ታክስ ሙሉ በሙሉ በደረሠኝ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ሽያጭ ታክስ ግን የሒሳብ መዝገብ ከሚይዙት በስተቀር በሌሎች ላይ ደረሰኝ የመያዝ አስገዳጅነት የሌለው በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በደረሰኝ ላይ የተመሰረተ አለመሆኑ፤
  የተጨማሪ እሴት ታክስ በግብዓት ላይ የተከፈለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለታክሱ የተመዘገበ ተመላሽ የሚደረግ ሲሆን በተርን ኦቨር ታክስ ግን አጠቃላይ የሽያጭ ዋጋው ላይ እየተከተለ ቀድሞ የተከፈለን ታክስ ሳያቀናንስ ተሰልቶ የሚሰበሰብ መሆኑ፤

በመጣኔያቸው
  የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልባቸው አቅርቦት ላይ የአገልግሎትን እና የዕቃ አቅርቦትን ሳይለይ አስራ አምስት በመቶ (15%) መጣኔ (rate) ታክስ የሚሰበሰብ ሲሆን
  የተርን ኦቨር ታክስ የሚከፈልባቸው አቅርቦት ላይ አገልግሎትንና ዕቃን በተለያየ መጣኔ የሚያሳይ የታክስ አይነት ሲሆን በዕቃ ሽያጭ ሁለት በመቶ(2%) በአገልግሎት አስር በመቶ(10%) መሆኑ

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

01 Jan, 11:18


በርቀት የታክስ ትምህርትን ለሚከታተሉ የድርጅት ኃላፊዎችና ሥራ አስኪያጆች የማጠናከሪያ/ቲቶሪያል/ ትምህርት ተሰጠ፡፡

ታህሳስ 23/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የታክስ ትምህርትን በአራተኛ ዙር በርቀት ለሚከታተሉ የድርጅት ኃላፊዎችና ሥራ አስኪያጆች በክፍል ሦስት ከሞጁል ዘጠኝ እስከ አስራ ሶስት ያለዉን የማጠናከሪያ/ቲቶሪያል/ ትምህርት በዛሬው ዕለት ተሠጥቷል፡፡

ሥልጠናው ክፍል ሦስት ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች የታክስ ከፋይ ምዝገባ፣ ስረዛ እና ክሊራንስ አሰጣጥ፣ ስለታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር አሰጣጥ አጠቃቀም እና ስረዛ፣ የታክስ ክሊራንስ የምስክር ወረቀት ስለሚያገለግልበት ጊዜ፣ ስለደረሠኝ አጠቃቀም፣ የክፍያ ጊዜ ስለሚራዘምበት ሁኔታ እና የራስ ታክስ ስለሚሻሻልበት ቅድመ ሁኔታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የስራ ሂደት አስተባባሪ በሆኑት አቶ ተግባሩ ታምሩ አማካኝነት ተሠጥቷል::

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

01 Jan, 08:39


የታክስ አይነቶችና የማሳወቂያ ጊዜያት

ታሕሳስ 23/2017 ዓ.ም

#ከመቀጠር_የሚገኝ_ገቢን_በሚመለከት
👉ከራስ ገቢ ላይ የሚቀንስ በየ3 ወሩ፣
👉ድርጅቶች በየወሩ፡፡

#ከቤት_ኪራይ_እና_ንግድ_ሥራ_ገቢ_ግብርን_በሚመለከት፤
👉ደረጃ “ሀ” ከሐምሌ 1 እስከ ጥቅምት 30፤
👉ደረጃ “ለ” ከሐምሌ 1 እስከ ጳጉሜን 5/6፤
👉ደረጃ “ሐ” ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሐምሌ 30፡፡

#በሰንጠረዥ “መ” ሌሎች ገቢዎች ምድብ ስር የሚመደቡት የገቢ አይነቶች
👉ሮያሊቲ፣
👉የትርፍ ድርሻ፣
👉ወለድ፣
👉ከእድል ሙከራ የሚገኝ ገቢ፣
👉የቴክኒክ እና ሰራ አመራር ክፍያ፣ 
👉ግብሩ ተቀናሽ ካልተደረገ በስተቀር ገቢውን ያስገኘው ግብይት ከተደረገበት ቀን
      ጀምሮ ባሉት ሁለት ወራት፡፡

#የቅድመ_ግብርን_በተመለከተ
👉በሀገር ውስጥ ከሚፈጽሙ ክፍያዎች ላይ በወሩ ውስጥ ቀንሶ ቀሪ ያደረገውን
  አጠቃላይ ግብር ከወሩ የመጨረሻ ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት፣
👉ከውጭ ሀገር በሚገቡ እቃዎች ላይ እቃዉ በገባበት ጊዜ ተጨማሪ እሴት ታክስን በሚመለከት ግብይቱ  
    ከተካሄደበት ቀን መጨረሻ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ፡፡

#የተርን_ኦቨር_ታክስን_በሚመለከት
👉ደረጃ “ሀ” በየወሩ፣
👉ደረጃ “ለ” በየሶስት ወሩ፣
👉ደረጃ “ሐ” በበጀት ዓመቱ መጨረሻ፡፡

#ኤክሳይዝ_ታክስን_በሚመለከት
👉ከአምራቹ ፋብሪካ በሚወጡበት ጊዜ የሚከፈለው በየወሩ፤
👉ፋብሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ዕቃዎች ጥቅም ላይ በዋሉበት ጊዜ፤የሚከፈለው
  በየወሩ

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

29 Dec, 15:38


የታክስ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው!
(አቶ ጌቱ ንጉሴ
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ)

ታህሳስ 20/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቢሾፍቱ ከተማ ከኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤትና ከስምንት ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለተውጣጡ 59 የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች እና ሠራተኞች በተለያዩ ታክስ ነክ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ከታህሳስ 19 ጀምሮ ለሁለት ቀናት ያህል ያህል ስልጠና ተሠጥቷል፡፡

ሥልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌቱ ንጉሴ የታክስ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ገልፀው ስልጠናው በስራችን ወቅት የሚገጥሙንን የአሰራር ክፍተቶች የምንምላበት እንዲሁም ተቋማችን ለትርፍ ሳይሆን ለአገልግሎት የተቋቋመ በመሆኑ በምንሰጠው አገልግሎት የሚጠበቅብንን ግብር ለታክስ ባለስልጣን መስሪያቤቱ በወቅቱ አስታውቀን እንድንከፍል የሚረዳንን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ በአግባቡ መከታተል ይጠበቅብናል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው ከመቀጠር የሚገኙ ገቢዎች፣ ቅድመ ግብር ታክስ፣ በገዢው ስለሚከፈል ታክስ፣ በአዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 1341/2016፣ በታክስ አስተዳደራዊ፤ የወንጀል ቅጣቶችና ተያያዥ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት አስተባባሪ በሆኑት አቶ ተግባሩ ታምሩ እና በታክስ ከፋዮች ትምህርት ዋና መሪ ባለሙያ በሆኑት በአቶ ታምራት ጅግሳ አማካኝነት ተሠጥቷል፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ማስታወቅ የሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደራራ በርሲሳ በስልጠናው ላይ ተገኝተው ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በኤሌክትሮኒክስ በሚያስታውቁበት እና ከተመላሽ ሥርዓት ጋር ተያይዞ በሚገጥሟቸው ችግሮች ከሰልጣኞች በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ደራራ አክለውም እናንተ የመንግስት መስሪያ ቤት እንደመሆናችሁና ከገቢ ሰብሳቢ ተቋሙ ጋር ለአንድ ዓላማ የቆማችሁ ስለሆነ የታክስ ህግ ተገዢነት ደረጃችሁን ማሻሻል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ስልጠና በተሰጠባቸው ርዕሰ ጉዳዮችና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ተነስተው የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት አስተባባሪ በሆኑት አቶ ተግባሩ ታምሩ እና የታክስ ማስታወቅ የሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ደራራ በርሲሳ ምላሽና የማጠቃለያ ሀሳብ ተሰጥቷል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

07 Dec, 08:16


ኢታክስ የሚያጠቃልላቸው የአገልግሎት ዓይነቶች
👉 ኢ-ፋይሊንግ ፦
ግብርን ወደ ታክስ ባለስልጣኑ መቅረብ ሳያስፈልግ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የማስታወቅ አሠራር ሥርዓት ነው፡፡
👉 ኢ-ፔይመንት ፦
ከየትኛውም ቦታ ሆኖ የኢንተርኔት አገልግሎት በመጠቀም ቀደም ሲል በኢ-ፋይሊንግ በላከው መረጃ ክፍያውን እንዲያስተናግዱ ውል በተፈራረሙ ባንኮች በኩል ክፍያውን የሚከፍልበት ስርዓት ነው፡፡
👉 ኢ-ክሊራንስ፦
ግብር ከፋዪ ድርጅት የሚኒስቴር መ/ቤት ድረ-ገጽ በመጠቀም የታክስ ክሊራንስ ለመጠየቅ የሚያስችለው ከመሆኑም በላይ በወቅቱ ግብሩን የከፈለ እና ምንም ዓይነት የታክስ ክፍያ የሌለው ግብር ከፋይ በቀላል መንገድ የዓመታዊ ንግድ ፈቃድ ማደሻም ሆነ ሌሎች ክሊራንሶች በኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት የአሠራር ሥርአት ነው፡፡
👉 የታክስ ነክ መረጃ አገልግሎት፦
ኢ-ታክስን ተጠቅሞ አንድ ግብር ከፋይ መጠየቅ የሚፈልጋቸውን ታክስ ነክ መረጃዎችና ማብራሪያዎች በቀላሉ ማግኘት የሚያስችለው ሲሆን ግብር ከፋዪች የሥርዓቱ ተጠቃሚ እየሆኑ በሄዱ ቁጥር ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር ያላቸው የሥራ ግንኝነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ እና የሚያቀራርብ በመሆኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የአሠራር ሥርዓት ነው፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

06 Dec, 11:48


ተቀናሽ የማይደረጉ ወጪዎችና ኪሳራዎች

በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 27 መሰረት የሚከተሉት ወጪዎች በተቀናሽነት አይያዙም፡-

👉  የካፒታል ባህሪ ያላቸው ወጪዎች፤
👉  የኩባኒያ አክሲዮን ወይም የሽርክና ማህበር መሠረት የሆነዉን ካፒታል ለማሳደግ የሚወጣ ወጪ፤
👉  ከተቀጣሪዉ የወር ደመወዝ 15% (አስራ አምስት መቶኛ) በላይ በፈቃደኝነት የሚደረግ የጡረታ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ መዋጮ፤
👉  የአክሲዮን ድርሻ እና የትርፍ ድርሻ ክፍፍል፤
👉  በመድን፣ በካሳ ወይም በዋስትና ዉል መሠረት የተመለሰ ወይም ሊመለስ የሚችል ወጪ ወይም ኪሳራ፤
  👉ማንኛዉንም ሕግ ወይም ዉል በመጣስ የሚጣል የገንዘብ ቅጣት ወይም የሚከፈል ካሳ፤
👉  ግብር ከፋዩ በሂሳብ መዝገቡ የሚይዘው በወቅቱ ወጪ ያልተደረገ ነገር ግን ለወደፊት በግብር ዓመቱ ለሚከሰቱ ወጪዎች ወይም ኪሳራዎች መጠባበቂያ ይሆን ዘንድ የሚያዝ ገንዘብ ወይም የመጠባበቂያ ሂሳብ፤
👉 በገቢ ግብር አዋጅ ወይም በዉጪ ሀገር የታክስ ህግ መሰረት የተከፈለ የገቢ ግብር ወይም ተመላሽ የሚደረግ የተጨማሪ እሴት ታክስ፤
👉 10 በመቶ በላይ ለግብር ከፋዩ ሠራተኛ የሚከፈል የኃላፊነት አበል ወይም የዉክልና አበል
👉  ግብር ከፋዩ ለራሱ የሚያወጣዉ የግል ወጪ፤
👉  ግብር ከፋዩ አንድን የንግድ ሥራ ሃብት ግንኙነት ላለዉ ሰው ሲያስተላልፍ የሚደርስ ኪሳራ፤
👉  ለበጎ አድራጎት ከሚሰጥ ከ10 በመቶ በላይ የሚሰጥ ስጦታ ወይም እርዳታ
👉  በአዋጁ፣ደንቡ እና መመሪያ ተቀናሽ እንዳይደረጉ የተጠቀሱ ሌሎች መመሪያዎችን ያካትታል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

05 Dec, 13:16


የመመዘኛ ፈተና ተሰጠ፡፡

ህዳር 26/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2017 በጀት ዓመት ክፍል ሦስት የሞጅላር ስልጠና ወስደው ላጠናቀቁ የሁለተኛ ዙር ሠልጣኞች እና ክፍል አንድ የሞጅላር ስልጠና ወስደው ላጠናቀቁ የሦስተኛ ዙር የሞጁላር ስልጠና ተከታታዮች የመመዘኛ ፈተና ተሰጠ፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

02 Dec, 13:18



የታክስ የቅሬታ ማመልከቻ ይዘት


በታክስ ዉሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ታክስ ከፋይ ቅሬታዉን ሲያቀርብ የሚከተሉትን ያሟላ መሆን አለበት፡-

   -ታክስ ከፋዩ የሚያቀርበው የቅሬታ ማስታወቂያ የቅሬታዉን ፍሬ ነገር እና ምክንያቶች መያዝ አለበት፤
   -ቅሬታ አቅራቢዉ የቅሬታዉን ፍሬ ነገር ምክንያቶች ከመግለፅ በተጨማሪ የሚከተሉትን መረጃዎች ያሟላ የቅሬታ ማስታወቂያ ማቅረብ ይኖርበታል፡-
👉  የቅሬታ አቅራቢዉን ስም፣ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር እና አድራሻ፣
👉  ቅሬታ የቀረበበትን የታክስ ዉሳኔ ይዘት፣
👉  ዉሳኔው የተሰጠበትን ቀን፣
👉  ዉሳኔው የሰጠዉን ቅ/ጽ/ቤት እና
👉  ሌሎች ለውሳኔ የሚረዱ ፍሬ ነገሮችና ማስረጃዎችን መግለፅ አለበት::

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

02 Dec, 06:34


የታክስ ክሊራንስ ምስክር ወረቀት ከመሰጠቱ በፊት ኦዲት የሚያስፈልጋቸው አገልግሎቶች

የሚሸጠው ወይም የሚተላለፈው የንግድ ሥራ ሀብት ከሃምሳ በመቶ ያነሰ ከሆነ የታክስ ክሊራንስ ምስክር ወረቀት ከመሰጠቱ በፊት አገልግሎት ኦዲት ሥራ መከናወን አለበት፡፡

በከፍተኛ እና በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት የሚስተናገድ ታክሰ ከፋይ በግብር ዘመኑ መካከለኛ እና ዝቅተኛ የስጋት ደረጃ ላይ የሚገኝ ከሆነ በሚከተሉት አገልግሎቶች ላይ የታክስ ክሊራንስ ምስክር ወረቀት ከመሰጠቱ በፊት አገልግሎት ኦዲት መደረግ አለበት፤
1. ከሃምሳ በመቶ በላይ የንግድ ሥራ ሀብት ለመሸጥ ወይም ለማስተላለፍ፣
2. ድርጅትን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለመዝጋት፣
3. የንግድ ዘርፍ ለመቀየር ወይም ለመቀነስ ከሆነ፡፡
ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ፡- https://shorturl.at/vmaop

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

29 Nov, 14:58


የግብር ከፋዮችን የህግ ተገዢነት በኦዲት በማረጋገጥ የመንግስትን ፍላጎት፣ የሀገራችንን እድገትና ለውጥ ወደ ተሻለ ቦታ ማድረስ ይገባናል
(አቶ ገዛኽኝ ታምሩ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅ/ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ)

ህዳር 20/2017 ዓ.ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የታክስ ኦዲት፣ የስጋት ህግ ተገዢነትና ስትራቴጂ አመራርና ሠራተኞች በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡

በውይይቱ ላይ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር 1 ቅ/ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኽኝ ታምሩ እንዳሉት የ2017 የገቢ እቅድን ለማሳካት በመካከለኛ የስጋት ደረጃ ላይ የሚገኙ ግብር ከፋዮችን ኦዲት በማድረግ፣ መልካም ሥነ ምግባር በተላበሰ መልኩ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የፀዳ በሁለንተናው የተሻለ አገልግሎት በመስጠት፣ ጥራቱን የጠበቀ ወጥ የሆነ ውሳኔ በማውጣት ውጤት ሊያመጣ የሚችል ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል::

አቶ ገዛኸኝ አያይዘውም የግብር ከፋዮችን የህግ ተገዢነት በኦዲት በማረጋገጥ የመንግስትን ፍላጎት፣ የሀገራችንን እድገትና ለውጥ ወደ ተሻለ ቦታ ማድረስ ይገባናል ሲሉ የማጠቃለያ ሀሳባቸውን ሠጥተዋል::

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

29 Nov, 13:36


ግብር የሚከፈልበት የቤት ኪራይ ገቢን በተመለከተ ተቀናሽ የሚደረጉ ወጪዎች

በአንድ የግብር ዓመት የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ የሌለበት ግብር ከፋይ ግብር የሚከፈልበት ገቢ በሚሰላበት ጊዜ የሚከተሉት ወጪዎች በተቀናሽ ይያዛሉ፡-

👉ታክስን ሳይጨምር ለመሬቱ ወይም ከተከራየው ቤት ጋር በተገናኘ ግብር ከፋዩ ለመንግስት ወይም ለከተማ አስተዳደር በግብር ዓመቱ ውስጥ የከፈላቸው ክፍያዎች፣
👉 ለቤቶች፣ለቤት ዕቃና መሳሪያ ማደሻ፣ መጠገኛና ለእርጅና መተኪያ የሚሆን ከቤት ዕቃና ከመሣሪያ ኪራይ ከሚገኘው ጠቅላላ ገንዘብ ላይ 50% በመቶ ተቀናሽ ይፈቀድለታል፡፡
👉 ከላይ የተመለከተው 50% ተቀናሽ በማናቸውም ሁኔታ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ላለባቸው ግብር ከፋዮች ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

የሂሳብ መዝገብ የሚይዝ ግብር ከፋይ በግብር ዓመቱ ግብር የሚከፈልበት ገቢ በሚሰላበት ጊዜ ገቢውን ለማግኘት የወጣና በግብር ከፋዩ የተከፈለ አስፈላጊ (necessary) የሆነ ወጪ ተቀናሽ የሚደረግ ሲሆን ይህም ወጪ የሚከተሉትን ይጨምራል፡-

👉ቤቱ ያረፈበት የመሬት ኪራይ (lease)፣
👉የጥገና ወጪ፣
👉 የቤቱ፣ የቤት ዕቃዎችና የመሣሪያዎች የእርጅና ቅናሽ፣
👉ወለድና የመድን አረቦን፣
👉ታክስን ሳይጨምር ለመሬቱ ወይም ከተከራየው ቤት ጋር በተገናኘ ግብር ከፋዩ ለመንግስት ወይም ለከተማ አስተዳደር የከፈላቸው ክፍያዎች፣

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

29 Nov, 08:23


በተሻሻለዉ የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀምና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 188/2017 መሠረት የተካተቱና የተደረጉ ለዉጦች፦

👉 እያንዳንዱ የደረሰኝ ቅጠል ሲታተም ልዩ መለያ ኮድ (unique QR code) ተካቶ ካልታተመ ተቀባይነት አይኖረዉም፡፡
👉 ከአንድ በላይ የንግድ ሥራ ዘርፍ እና የንግድ አድራሻ ያለዉ ታክስ ከፋይ፣
ሀ) ድርጅት ከሆነ፡-

(1) የማንዋል ደረሰኝ ለማሳተም ጥያቄ ሲያቀርብ ለእያንዳንዱ ቅርንጫፍ የሚያስፈልገዉን የጥራዝ ብዛት መግለጽ አለበት፤
(2) ከዋናዉ አድራሻ በተጨማሪ ደረሰኙ ሊታተምለት የተፈለገዉ የንግድ ዘርፍና የቅርንጫፍ አድራሻዉ ተገልጾ መታተም አለበት፡፡

ለ) ግለሰብ ከሆነ፡-

(1) የማንዋል ደረሰኝ ለማሳተም ጥያቄ ሲያቀርብ እያንዳንዱ የንግድ ሥራ ዘርፍ ለሚካሄድበት ቦታ የሚያስፈልገዉን የጥራዝ ብዛት መግለጽ አለበት፡፡
(2) ከዋናዉ አድራሻ በተጨማሪ ደረሰኙ ሊታተምለት የተፈለገዉ የንግድ ዘርፍ እና የንግድ ሥራ ዘርፉ የሚካሄድበት ቦታ ወይም አድራሻ ተገልጾ መታተም አለበት፡፡

👉 ማተሚያ ቤቱ በማንዋል ደረሠኝ QR code አስተዳደር ፖርታል (Manual Rceipt Web Portal) የተጋራዉን መረጃ (ለሶስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ በማድረግ ደህንነቱን እና ሚስጢራዊነቱን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡
👉 ማተሚያ ቤቱ ምንም አይነት ስህተት ወይም ልዩነት ሳይኖር ደረሰኞችን ልዩ መለያ ኮድ(unique QR code) በማካተት ለማተም በማንዋል ደረሠኝ QR code አስተዳደር ፖርታል (Manual Rceipt Web Portal) የተጋራዉን ዳታ በትክክል ተቀብሎ የመተግበር ግዴታ አለበት፡፡
👉 ማንኛውም ማተሚያ ቤት እንዲታተም የተፈቀደውን እና የታተመዉን ደረሠኝ በተመለከተ በተዘጋጀው ስስተም በወቅቱ ሪፖርት በወቅቱ የመላክ ኃለፊነት አለበት፡፡
👉 ማንኛዉም ማተሚያ ቤት በታክስ ከፋዩ ደረሠኝ እንዲያትም ሲጠየቅ፣ በታክስ ባለስልጣኑ ለታክስ ከፋዩ የተሰጠ የደረሠኝ ህትመት ፈቃድ ደብዳቤ ሳይቀበል ደረሠኝ ማተም የለበትም፡፡
በዚህ መመሪያ መሰረት የደረሠኝ ህትመት አገልግሎት የሚሰጥ ማተሚያ ቤት ከሚኒስቴሩ ጋር የቅንጅት አሠራር ስምምነት የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

28 Nov, 13:10


#በሀገር ዉስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያዎች ላይ ግብር ቀንሶ ስለማስቀረት

በአዋጁ አንቀፅ 92 መሰረት በግዢ ወቅት ከሚፈጽሙት ክፍያ ላይ ግብር ቀንሰው እንዲያስቀሩ የተጣለባቸው ሰዎች ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው፡፡

1.  በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች፡- የአክሲዮን ማህበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ የሽርክና ማህበር፣ የህብረት ስራ ማህበር፣…ወ.ዘ.ተ
2.  የመንግስት መ/ቤቶች፡- በፌደራል እና በክልል የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ መሰረት ለመንግስት መ/ቤቶች በተሰጠው ትርጉም ውስጥ የሚካተቱ ወይም በተቋቋመበት ሕግ የመንግስት መ/ቤት የተባሉ የፌደራል፣ የክልል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከተማ አስተዳደር እና የድሬደዋ አስተዳደር የመንግስት መ/ቤቶች፣
3.  ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች፡- ለትርፍ ላልሆነ ለተለያዩ ዓላማዎች የተቋቋሙ ማህበራትና የሃይማኖት ድርጅቶች፣
4.  መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፡- በሲቪክ ማህበራት አዋጅ መሠረት የተቋቋሙ "የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች" ወይም "የኢትዮጵያ ማኅበሮች" ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በዉጪ አገር የተቋቋሙ ተመሳሳይ ድርጅቶች፣
5.  የገቢዎች ሚኒስቴር በአዋጁ አንቀጽ 92(1) በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሚያወጣው መመሪያግብር ቀንሰው እንዲያስቀሩ ግዴታ የተጣለባቸው ግለሰብ ግብር ከፋዮች፣
6.  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በምርት ገበያው አማካኝነት ከሚከናወን ግብይት ጋር በተያያዘ ገዥዉን በመወከል የሚፈፅመው ግብይት፣

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

28 Nov, 08:29


የትራንስፖርት አበል እና የመጓጓዣ ወጪ ከግብር ነፃ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች

ሕዳር 19/2017 ዓ.ም (የገቢዎች ሚኒስቴር)

ከገቢ ግብር ነፃ የተደረጉ ገቢዎች አፈፃጸም መመሪያ ቁጥር 1/2011 መሰረት የትራንስፖርት አበል እና የመጓጓዣ ወጪ ከግብር ነጻ የሚሆነው፡-

1. በስራ ባህሪው ምክንያት ስራውን ከቦታ ወደቦታ በመዘዋወር የሚያከናውን ተቀጣሪ ለአንድ ወር ጉዞ የሚከፈለው የትራንስፖርት አበል ከገቢ ግብር ነፃ የሚደረገው ከጠቅላላ የወር ደመወዙ ከአንድ አራተኛ(1/4) ባልበለጠ መጠን ብቻ ነው፡፡ ይሁንና የተቀጣሪው ጠቅላላ የወር ደመወዝ አንድ አራተኛ ከብር 2,200 የሚበልጥ ሲሆን ከግብር ነፃ የሚደረገው የትራንስፖርት አበል በማንኛውም ሁኔታ ከብር 2,200 ሊበልጥ አይችልም፡፡

2. አንድ ተቀጣሪ በስራ ባህሪው ምክንያት በመዘዋወር ለሚሰራው ስራ ለነዳጅ ወጪ የሚከፈለው ጥሬ ገንዘብ ለትራንስፖርት አበል እንደተከፈለ ተቆጥሮ ከገቢ ግብር ነፃ የሚደረገው ከጠቅላላ የወር ደመወዙ ከአንድ አራተኛ(1/4) ባልበለጠ መጠን ብቻ ነው፡፡ ይሁንና የተቀጣሪው ጠቅላላ የወር ደመወዝ አንድ አራተኛ ከብር 2200 የሚበልጥ ሲሆን ከግብር ነፃ የሚደረገው የነዳጅ ወጪ በማንኛውም ሁኔታ ከብር 2,200 ሊበልጥ አይችልም፡፡

3. አንድ ተቀጣሪ ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ስራው ቦታ እንዲሁም ከስራው ቦታ ወደ መኖሪያ ቤቱ የሚጓጓዝበት የመስርያ ቤቱ የትራንስፖርት ሰርቪስ ቢቀርብም ባይቀርብም ለዚህ ዓይነቱ የትራንስፖርት አበል ከገቢ ግብር ነፃ የሚደረገው ከብር 600 ባልበለጠ መጠን ብቻ ነው፡፡

ሙሉውን ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ፡- https://shorturl.at/F9ahO

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

27 Nov, 13:25


በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ የአንድ ጊዜ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ህዳር 18/2017 ዓ.ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት ከመንግስት ታክስ ማስታወቅ የሥራ ሂደት ጋር በመተባበር ለመንግስት የልማት ድርጅት፣ ለመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች እና ሀላፊነቱ ከተወሰኑ ድርጅቶች ለተዉጣጡ 149 አመራርና ሠራተኞች በመሰረታዊ የታክስ ህጎችና አሠራሮች እንዲሁም አዋጆች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ታስቦ በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ የአንድ ጊዜ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ሥልጠናው ስለቅድመ ግብር ምንነት፣ ሠንጠረዥ "መ" ታክሶች እና በገዢው ተይዞ ስለሚከፈል ታክስ ዙሪያ በቅ/ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት አስተባባሪ በሆኑት አቶ ተግባሩ ታምሩ አማካኝነት ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የመንግስት ተቋማት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሀንስ ግዛው ታክስን በወቅቱ መክፈል ካላስፈላጊ ቅጣት እንደሚያድንና ግብር ከፋዮች ደግሞ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እንዳለባቸው በመጠቆም እንዲሁም ከሠልጣኞች ለተነሱ ሀሳቦች አስታያትና የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

22 Nov, 19:05


ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በጥቅምት ወር ብቻ 10.53 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ህዳር 13፣ 2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2017 በጀት ዓመት በጥቅምት ወር ብቻ 10.53 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በጥቅምት ወር ከሰበሰበው ብር 10.53 ቢሊዮን ውስጥ ብር 7.94 ቢሊዮን ከቀጥታ ታክሶች፣ ብር 2.55 ቢሊዮን ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች እና ብር 0.037 ቢሊዮን ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች በመሰብሰብ የእቅዱን 110 በመቶ ማሳካት መቻሉን የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የእቅድና አፈፃፀም ክትትል ቡድን አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት ጌታቸው የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ባካሄዱት የ2017 በጀት ዓመት የጥቅምት ወር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወቅት ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ገልፀዋል፡፡

አፈፃፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ክንውን ጋር ሲነፃፀር የብር 3.49 ቢሊዮን ወይም 50 በመቶ ብልጫ እንዳለውና በወሩ ከተሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 47 በመቶ ከመንግስት ተቋማት የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቀረቡት ሪፓርቶች ላይ የሁሉም የስራ ክፍል የሥራ ሂደትና ቡድን አስተባባሪዎች እንዲሁም የየዘርፉ ምክትል ሥራ አስኪያጆች በጥቅምት ወር በየስራ ክፍሉ በነበሩ ጠንካራ ጎኖችና በቀጣይ ወር ቢሰሩ የገቢ አፈፃፀሙን ሊያሳድጉ በሚችሉ አንኳር ነጥቦች ዙሪያ ሠፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ታምሩ እንዳሉት እንደ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በጥቅምት ወር ለመሰብሰብ የተያዘው በ2017 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ ከተያዘው የገቢ እቅድ 17.4 በመቶ የሚሸፍን እንደሆነና ይህንንም የገቢ እቅድ ለማሰካት በየደረጃው የሚገኙ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞች ተቀናጅተው በመደበኛና በትርፍ የሥራ ሰዓታቸው በነበራቸው የሥራ እንቅስቃሴ ከእቅድ በላይ ገቢ መሰብሰብ በመቻሉ ምስጋና አቅርበው፤ ለዚህም ስኬት ምክንያት የሚሆኑት የጥቅምት ወር የንግድ ትርፍ ማሳወቂያ ወቅት መሆኑ፣ የተለያዩ ኮሚቴዎች ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸው፣ በአዲስ አበባና በዙሪዋ ባሉ ቦታዎች በተለያዩ አማራጮች በተጠናከረ ሁኔታ ግብር ከፋዮችን የመቀስቀስ እና የማስታወስ ስራ መሰራቱ፣ ውዝፍ ዕዳ አሰባሰባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ በመሆኑ፣ የመንግስታዊ ተቋማትን ከዚህ በፊት ያልተከፈሉትን ውዝፍ መክፈል መቻላቸው በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ አክለውም የህዳር ወር የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ከምንጊዜውም በላይ በሙሉ አቅም መስራት፣ ያላስታወቁ ታክስ ከፋዮች ላይ በልዩ ሁኔታ ክትትል ማድረግ፣ ከመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች የሚሰበሰበውን ገቢ በትኩረት መከታተል፣ በፈቃደኝነት የሚያስታውቁ ታክስ ከፋዮችን በልዩ ሁኔታ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ሁሉም አመራርና ፈጻሚ ሙስናን በመዋጋት፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ምንም ዓይነት የሚሻገሩ ስራዎች ሳይኖሩን እና ገቢ ሊያስገኙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እቅዳችንን ማሳካት ይገባናል ሲሉ አፅንኦት ሠጥተው ተናግረዋል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

22 Nov, 13:19


#የታክስ_ደረሰኝ_አጠቃቀም_እና_አስተዳደር_መመሪያ_/ማሻሻያ/_ቁጥር_188/2017

ለእያንዳንዱ የንግድ ሥራ ዘርፍ እና የንግድ አድራሻ የተለያየ ደረሰኝ እንዲታተም ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ እና በእያንዳንዱ ደረሰኝ ላይ ልዩ QR ኮድ (unique QR code) ማካት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ገቢዎች ሚኒስቴር በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 19(4) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ይህን የማሻሻያ መመሪያ አውጥቷል፡፡

የመመሪያውን ሙሉ ክፍል ለመመልከት ሊንኩን ይጫኑ፡- https://shorturl.at/JNqW7

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

20 Nov, 12:28


"ግብር በወቅቱ መክፈል የዜግነት ትልቁ ግዴታ ነው" /አቶ ሄኖክ በላይ የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.1 ቅ/ጽ/ቤት የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ/

ህዳር 11/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ገቢያቸውን ካላስታወቁ ግብር ከፋዮች ጋር ዉይይት ተካሄደ፡፡

የቅ/ጽ/ቤቱ የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ በላይ በዉይይቱ ላይ ግብርን በወቅቱ መክፈል የዜግነት ትልቁ ግዴታ እንደሆነ ገልፀው ግብራቸውን በወቅቱ አስታዉቀው ላልከፈሉ ግብር ከፋዮች ግብርን በወቅቱ አስታዉቆ ባለመክፈል ሊመጡ በሚችሉ አላስፈላጊ ቅጣቶች፣ የግምት ዉሳኔዎች፣ ግብርን ዘግይቶ ማስታወቅ ግብር ከፋዮች ላይ ሊያሳድር የሚችለው ከፍተኛ ጫና ዙሪያ ሠፋ ያለ ዉይይት አካሂደዋል፡፡

በዉይይቱ ላይ የተሳተፉት ግብር ከፋዮችም እስካሁን አስታዉቀዉ ያልከፈሉበትንም ምክንያት ጠቅሰው በቀጣይ በአንድ ሳምንት ዉስጥ ሁሉም ግብር ከፋዮች መክፈል እንደሚችሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በመጨረሻም አቶ ሄኖክ ግብርን በወቅቱ አስታዉቆ መክፈል ካላስፈላጊ ቅጣትና ወለድ እንደሚያድን ገልፀው በቀጣይ ሁሉም ግብር ከፋዮች በወቅቱ በመክፈል የታክስ ህግ ተገዢነት ደረጃቸውን ማሻሻል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

20 Nov, 10:27


ለፋይናንስ ኃላፊዎችና የሂሳብ ሠራተኛ ግብር ከፋዮች የአንድ ጊዜ ሥልጠና ተሠጠ፡፡

ህዳር 11/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለፋይናንስ ኃላፊዎችና የሂሳብ ሠራተኛ ግብር ከፋዮች በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ የአንድ ጊዜ ስልጠና ተሠጠ፡፡

ሥልጠናው ስለደረሰኝ አጠቃቀም፣ አወጋጋገድና አስተዳደር፣ በሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ የተመለከቱ የአድራሻ ለውጥ፣ የባለቤት ለዉጥ አወጋገድ እንዲሁም በደረሰኝ እና ሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ዙሪያ በአዋጅና በመመሪያ የተደነገጉ ጉዳዮች ቢጣሱ የሚያስከትሉትን አስተዳደራዊ እና የወንጀል ቅጣቶች ዙሪያ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርት ዋና መሪ ባለሙያ በሆኑት በወ/ሮ ፈትያ ሙራድ  አማካኝነት ተሠጥቷል::

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

19 Nov, 12:47


3ኛው ዙር የምጅላር ስልጠና መሰጠት ተጀመረ፡፡

ህዳር 10/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁ.1 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ግብር ከፋዮችን በመሰረታዊ የታክስ ህጎችና አሠራሮች እንዲሁም አዋጆች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ታስቦ በተከታታይነት የሚሰጠው የምጅላር ስልጠና በ2017 በጀት ዓመት ለሦስተኛ ዙር ሠልጣኞች በክፍል አንድ ቀጥተኛ በሆኑ ታክሶች ከመቀጠር የሚገኝ ገቢና የወጪ መጋራት ዙሪያ በዛሬው ዕለት መስጠት ተጀመረ፡፡

ስልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ተግባሩ ታምሩ ስልጠናው ለግብር ከፋዮች በጣም አስፈላጊና በታክስ ህግ እውቀት ክፍተት ምክንያት አንድም ግብር ከፋይ እንዳይቀጣ ለማድረግ እንዲሁም በፈቃደኝነት ግብር የመክፈል ባህልን ለማሳደግ በማሰብ የሚሰጥ ስልጠና በመሆኑ ሠልጣኞች ስልጠናውን ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡

የእለቱን ስልጠና የሰጡት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታምራት ጅግሳ ናቸው::

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

09 Nov, 14:26


የምስጋና መርሃግብር

ጥቅምት 30/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 የግብር ዓመት ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ግብር አስታውቆ መክፈያ የመጨረሻው እለት በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም ግብራቸውን በወቅቱ ላስታወቁ ግብር ከፋዮች የሻይ ቡና መርሃ ግብር አካሂዷል:፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ታምሩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በጥቅምት ወር ለመሰብሰብ የያዘውን የገቢ እቅድ በስኬት ለማጠናቀቅ በመደበኛ እና ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጪ አገልግሎት ሲሰጡ ለቆዩ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

08 Nov, 06:02


ታክስን ዘግይቶ መክፈል የሚያስከትለው ቅጣት

ማንኛውም ታክስ ከፋይ በታክስ መክፈያ ጊዜው ውስጥ ታክስ ሳይከፍል ከቀረ ለዘገየበት ጊዜ፦

ሀ) ለአንድ ወር ወይም የወሩ ከፊል ለሆነው ጊዜ ባልተከፈለው ታክስ ላይ 5% (አምስት በመቶ)፤ እና

ለ) ከዚያ በኋላ ለዘገየበት ለእያንዳንዱ ወር ወይም የወሩ ከፊል ለሆነው ጊዜ ባልተከፈለው ታክስ ላይ ተጨማሪ 2% (ሁለት በመቶ)፤ ቅጣት ይከፈላል፡፡

👉የሚጣለው የቅጣት መጠን ከዋናው የታክስ ዕዳ መብለጥ የለበትም፡፡
👉መከፈል በማይገባው ታክስ ላይ ሳይከፈል በዘገየበት የተጣለ ቅጣት በመጀመሪያ (ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀንሶ የሚቀረውን ታክስ ሳይጨምር) ታክስ ከፋዩ በፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት የሚፈለግበትን ማንኛውንም ታክስ ክፍያ ማዋል፣ ቀሪው ታክስ ከፋዩ በሌላ በማንኛውም የታክስ ሕግ ለሚፈለግበት ታክስ ክፍያ ማዋል እንደተጠበቀ ሆኖ ተራፊ ገንዘብ ካለ ለታክስ ከፋዩ ይመለሳል፡፡
👉 ታክስን ዘግይቶ መክፈል የሚያስከትለው ቅጣት ከተከፋይ ሂሣብ ላይ ተቀንሶ ከሚከፈል ታክስ ጋር በተገናኘ የሚጣል ቅጣት በሚመለከተው ያልተከፈለ ታክስ ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

06 Nov, 14:54


https://youtube.com/watch?v=9k0-AscXkcI&si=0ZGvJ3ItUFBxiYFW

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

04 Nov, 09:27


#ግብሩን ቀንሶ እንዲያስቀር ግዴታ የተጣለበት ሰው ተግባርና ኃላፊነት

- በአገር ውስጥ ከሚፈፀሙ ክፍያዎች ላይ በወሩ ዉስጥ ቀንሶ ቀሪ ያደረገዉን አጠቃላይ ግብር ከወሩ የመጨረሻ ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ዉስጥ ለባለስልጣኑ ገቢ ማድረግ አለበት፡፡
-ከሚፈፀሙ ክፍያዎች ላይ ቀንሶ ያስቀረውን ግብር ገቢ በሚያደርግበት ጊዜ ክፍያ የተፈፀመለትን እና ግብር የተቀነሰበትን፡-
👉የእያንዳንዱን ሰው ወይም ድርጅት ስም፤
👉የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር/TIN/፤
👉በወሩ ውስጥ ለተጠቀሰው ሰው የተከፈለዉን ገንዘብ አጠቃላይ ድምር፣
👉ተቀናሽ ተደርጎ የቀረውን ግብር፣
👉 በእያንዳንዱ ሰው ስም ለባለስልጣኑ ገቢ የተደረገዉን ሂሳብ የሚያሳይ ዝርዝር ባለስልጣኑ በሚያዘጋጀው ቅጽ መሰረት ማቅረብ አለበት፡፡
👉 ከላይ የተገለፁትን ሰነዶች ኮፒ ባለስልጣኑ በሚሰጠው ቅፅና ሁኔታ እንዲሁም በሚወሰነው የጊዜ ልዩነት እንዲያቀርቡ ሲጠይቅ ማቅረብ፡፡
👉ግብር ቀንሶ የማስቀረት ግዴታ ያለበት ሰው በክፍያ ወቅት ግብር ቀንሶ ሲያስቀር የግብር ከፋዩን ስም አድራሻና የግብር ከፋዩን መለያ ቁጥር በመጠቀም መመዝገብ እና ሒሳቡን በዚሁ መሰረት መያዝ አለበት፡፡
👉ግብር ለተቀነሰበት ሰው ተከታታይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ መስጠት፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

02 Nov, 13:05


የታክስ ንቅናቄ መርሃግብር

ጥቅምት 23/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ገቢ አስታውቆ የመክፈያ ወቅት ሊጠናቀቅ 7 ቀናት ብቻ ስለቀረው ግብራቸውን ያላሳወቁ ግብር ከፋዮች ባሉት ቀሪ ቀናቶች ውስጥ ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት ባለሙያዎች አዘጋጅነት በተሽከርካሪዎች ላይ የምስል እና የድምፅ መልዕክቶችን በመያዝ በአዲስአበባ በሚገኙ ዋና ዋና ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ በመንቀሳቀስ ግብር ከፋዮችን የማንቃት እና የማስታወስ ስራ እየተሠራ ይገኛል::

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

01 Nov, 12:56


የገቢዎች ሚኒስትር ድንገተኛ የስራ ጉብኝት አካሄዱ፡፡

ጥቅምት 22/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በዛሬው እለት ድንገተኛ የስራ ጉብኝት አካሄዱ፡፡

ሚኒስቴሯ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ተገኝተው በጥቅምት ወር የገቢ አሰባሰብ በስኬት እንዲጠናቀቅ እና በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ዉይይት አካሂደዋል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

01 Nov, 09:14


የመመዘኛ ፈተና ተሠጠ፡፡

ጥቅምት 22/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ሰልጥነው ለጨረሱ በአራተኛ ዙር የታክስ ትምህርትን በርቀት ለሚከታተሉ የምጁላር ሠልጣኞች የመመዘኛ ፈተና ተሠጠ፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

01 Nov, 07:39


የ2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ ሒሳብ ሲቀርብ መሟላት ያለባቸው ዋና ዋና ሰነዶች

1. ዓመታዊ ሽያጭ ማጠቃለያ (Z- riport Summary) 
2.ከሽያጭ መመዝገቢያ ዉጪ በእጅ በእጅ ደረሰኝ (Manual Sales) የተደረገ ሽያጭ ካለ ማጠቃለያ ሪፖርት (Exel summray) 
3.ድርጅቱ ከሚጠቀምበት ባንክ የባንክ ስቴትመንት
4.የትርፍና ኪሳራ መግለጫ (profit Loss statement)፣ የሃብትና እዳ መግለጫ (Balance Sheet)፣ የገንዘብ ፍሰት ማሳያ(Cash Flow),የባለቤቶች ሁኔታ(Owners equity Position) እንዲሁም  የመረጃ ቋት (Ledger)ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
5. Withholding Tax ካለ ማጠቃለያ ሪፖርት (Exel Summary) እና ኦርጅናል ደረሰኝ 
6.ለጥገና እና ማሻሻያ የወጡ ወጪዎች ለየትኛዉ ቋሚ እቃ መጠገኛ ስለመዋሉ የሚያስረዳ ማስረጃና (Exel Summary)
7.የእርጅና ቅናሽ የተያዘለት የንግድ ስራ ሀብት በሠንጠረዥ የተሰላ ቅጽ ተያይዞ መቅረብ አለበት
8.የተሰብሳቢ እና ተከፋይ ሂሳቦች (Advance and Accrued) ዝርዝር መግለጫ
9.የገቢ ክፍፍል ቅጽ ተሞልቶ (Revenue Sharing Format) ወይም የሠራተኛ ወጪ ፎርም ተሞልቶ መቅረብ አለበት
10. የታደሰ የንግድ ፍቃድ
11.ዓመታዊ ማስታወቂያ ቅጽ ከደንበኞች አገልግሎት በመዉሰድ መሙላት
12.በግብር እፎይታ ላይ (ከታከስ ነፃ መብት ያለዉ) ግብር ከፋይ ይሄንን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ
13.ለእርዳታ የተሰጠ ስጦታ ካለ የጥሪ ደብዳቤ እና ገንዘቡ ገቢ የተደረገበት የባንክ ስሊፕ
14.ኦንላይን ያሳወቁበትን/Declaration (E.file print out) 
15.የኦዲት ቦርድ የተመዘገቡበት የምስክር ወረቀት ቅጅ ተያይዞ መቅረብ አለበት
16. ሒሳቡ በተፈቀደላቸዉ ሂሳብ አዋቂዎች የተሰራ ከሆነ የሂሳብ ሠራተኛዉ የታደሰ የንግድ ፍቃድ፣ የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀት፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ቅጅ 
17.ሒሳቡ በድርጅቱ ሒሳብ ሠራተኛ የተሰራ ከሆነ የሒሳብ ሠራተኛዉ የትምህርት መረጃ፣ ሠራተኛዉ የተካተተበት የሦስት ወር payroll ተያይዞ መቅረብ አለበት፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

31 Oct, 12:49


የታክስ ንቅናቄ መርሃ ግብር

ጥቅምት 21/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ገቢ አስታውቆ የመክፈያ ወቅት ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ስለቀረው ግብራቸውን ያላሳወቁ ግብር ከፋዮች ባሉት ቀሪ ቀናቶች ውስጥ ግብራቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ ለማስታወስ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና መረጃ አቅርቦት የሥራ ሂደት ባለሙያዎች አዘጋጅነት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመተበባር  በተሽከርካሪ ላይ የድምፅ እና የቪዲዮ መልዕክቶችን በመያዝ በአዲስአበባ በሚገኙ ዋና ዋና ጎዳናዎችና አደባባዮች በመንቀሳቀስ ግብር ከፋዮችን የማንቃት ስራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

31 Oct, 10:35


ታክስን ዘግይቶ መክፈል የሚያስከትለው ቅጣት

ማንኛውም ታክስ ከፋይ በታክስ መክፈያ ጊዜው ውስጥ ታክስ ሳይከፍል ከቀረ ለዘገየበት ጊዜ፦

ሀ) ለአንድ ወር ወይም የወሩ ከፊል ለሆነው ጊዜ ባልተከፈለው ታክስ ላይ 5% (አምስት በመቶ)፤ እና

ለ) ከዚያ በኋላ ለዘገየበት ለእያንዳንዱ ወር ወይም የወሩ ከፊል ለሆነው ጊዜ ባልተከፈለው ታክስ ላይ ተጨማሪ 2% (ሁለት በመቶ)፤ ቅጣት ይከፈላል፡፡

👉የሚጣለው የቅጣት መጠን ከዋናው የታክስ ዕዳ መብለጥ የለበትም፡፡
👉መከፈል በማይገባው ታክስ ላይ ሳይከፈል በዘገየበት የተጣለ ቅጣት በመጀመሪያ (ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀንሶ የሚቀረውን ታክስ ሳይጨምር) ታክስ ከፋዩ በፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት የሚፈለግበትን ማንኛውንም ታክስ ክፍያ ማዋል፣ ቀሪው ታክስ ከፋዩ በሌላ በማንኛውም የታክስ ሕግ ለሚፈለግበት ታክስ ክፍያ ማዋል እንደተጠበቀ ሆኖ ተራፊ ገንዘብ ካለ ለታክስ ከፋዩ ይመለሳል፡፡
👉 ታክስን ዘግይቶ መክፈል የሚያስከትለው ቅጣት ከተከፋይ ሂሣብ ላይ ተቀንሶ ከሚከፈል ታክስ ጋር በተገናኘ የሚጣል ቅጣት በሚመለከተው ያልተከፈለ ታክስ ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

31 Oct, 08:32


በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ሽልማት ከተሰጣቸው ግብር ከፋዮች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

ጥቅምት 20/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በህግ ተገዢነት ደረጃቸው የተሻሉ ሆነው በሀገር አቀፍ ደረጃ በስድስተኛው ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅናና ሽልማት መርሃግብር ከተሳተፉ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ግብር ከፋዮች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

በውይይቱ ላይ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ሥርዓት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ እቴነሽ ደሱ፣ የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ በላይ፣ የታክስ ማስታወቅ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደራራ በርሲሳ፣ የስጋትና ህግ ተገዢነት ስትራቴጂ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኤርሚያስ ግርማ ተገኝተው ግብር ከፋዮቹ የ2016 በጀት ዓመት ዓመታዊ የንግድ ትርፍ ገቢ አሳውቆ መክፈያ ወቅት ሊጠናቀቀቅ ጥቂት ቀናት ስለቀሩት ከወዲሁ አስታውቀው እንዲከፍሉ እና በህግ ተገዢነት ደረጃቸው የተሻሉ ሆነው እንዲቀጥሉ ተወያይተው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

22 Oct, 10:48


የመመዘኛ ፈተና ተሠጠ፡፡

ጥቅምት 12/2017 ዓ/ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2017 በጀት ዓመት ክፍል አንድን ላጠናቀቁ ሁለተኛ ዙር የምጁላር ሥልጠና ተከታታዮች የመመዘኛ ፈተና ተሠጠ፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

21 Oct, 08:01


የታክስ ክሊራንስ ምስክር ወረቀት አገልግሎት ለማግኘት መሟላት የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

  እንዲሰጠው በጽሑፍ ጥያቄ ማቅረብ፤
  ውዝፍ የታክስ ዕዳ /ወቅታዊ የታክስ ክፍያ የፈፀመ ወይም ለመክፈል የክፍያ ስምምነት የገባና በውሉ መሠረት እየተከፈለ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ፤
  በደረሰው የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ላይ ቅሬታ ያለው ታክስ ከፋይ በታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ክፍል ወይም ይግባኝ ሰሚ ኮሚሽን ወይም በየደረጃው ለሚገኝ ፍርድ ቤት ቅሬታውን አቅርቦ በመታየት ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ የጽሑፍ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
  ታክስ ከፋዩ የታክስ ነጻ መብት ያለው ወይም በግብር እፎይታ ጊዜ ላይ ያለ ስለመሆኑ የጽሑፍ ማስረጃ፤
  በግብር ዓመቱ በታክስ ከፋይነት ያልተመዘገበ ከሆነ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር አለመውሰዱ እና የታክስ ፋይል በስሙ አለመከፈቱ አስኪረጋገጥ፤
  በንግድ ሥራ ፍቃዱ ምንም ዓይነት ሥራ አለመሥራቱን የገለጸ ታክስ ከፋይ አለመሥራቱ እስኪረጋገጥ፤
  በኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማከራየት ዘርፍ የተሠማራ ታክስ ከፋይ፣ በታክስ ጊዜው ታክስ ያልከፈለው ማሽነሪው በመበላሸቱ ምክንያት መሆኑንና ይህንኑ በታክስ ሕጉ መሠረት ማስታወቁን እና ለዚሁም በ3ኛ ወገን የተረጋገጠ ማስረጃ እስኪያቀርብ፤
  ታክስ ከፋዩ ቦሎ ለማደስ የኮንስትራክሽን ማሽን በመበላሸቱ ምክንያት ያለመስራቱን በ30 ቀናት ውስጥ ማስታወቁ እስኪረጋገጥ፤
  የኮንስትራንሽን ማሽነሪ ለመሸጥ ከሆነ ማሽነሪው ከቆየበት ቦታ (ጋራዥ) ወይም ከቆመበት ቀበሌ አስተዳደር ማረጋገጫ ማስረጃ እስኪያቀርብና እስኪረጋገጥ፤
  በታክስ ጊዜው ታክስ ያልከፈለው የተሽከርካሪው ሊብሬ እና ታርጋ ለመንገድ ትራንስፖርት በመመለሱ/መድን ድርጅት ቅሪት አካልን በመረከቡ ምክንያት ስለመሆኑ ማስረጃ እስኪያቀርብ፤
  የወጪ መጋራት አገልግሎት/ክፍያ ተጠቃሎ እስኪፈጽም ድረስ፤
  ከታክስ ከፋዩ የሚፈልገው ታክስ የሚሰበሰብ ስለመሆኑ ስጋት ሲኖረውና ታክሱ በአስቸኳይ መሰብሰብ ያለበት ሆኖ ሲገኝ ታክሱ ሳይሰበሰብ የታክስ ክሊራንስ የምስክር ወረቀት አይሰጥም፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

19 Oct, 13:40


👉 በሥራ ሰዓት ብቻ ሳይሆን (በሳምንት 7 ቀን በእያንዳንዱ ቀን ለ24 ሰዓት ወይም 365 ቀን) ግብርን ማስታወቅ ያስችላል፡፡
👉 ፈጣን፣ ዘመናዊና ከፍተኛ ጥራት ያለው አገልግሎት ያስገኛል፡፡
👉 አላስፈላጊ የጊዜ፣ የሰው ሃይል እና የገንዘብ ወጪዎች ይቀንሳል፡፡
👉 በየጊዜው የሚሰወሩና የሚጠፉ ሰነዶችን በቀላል መንገድ መቆጣጠር ያስችላል፡፡
👉 ግብር ከፋዮች ክፍያን ለመፈፀም ወደ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መሄድና ወረፋ መያዝ ሳይጠበቅባቸው በየትኛውም ቦታ ሆነው ግብራቸውን አስታዉቀው መክፈል ያስችላቸዋል፡፡
👉 አደጋን/የገንዘብ መጥፋትን ይቀንሳል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

18 Oct, 07:46


ማንኛውም አሰሪ፡-

1. የቀጠራቸውን ተጠቃሚዎች ዝርዝር ለባለሥልጣኑ ወይም ለሚመወክለው የማስታወቅ፣
2. በገንዘብ ለመክፈል ግዴታ ከገቡ ተጠቃሚዎች የሚፈለግባቸውን እዳ የሚያሳይ ማስረጃ ከተጠቃሚዎቹ በመቀበልና ስለ ትክክለኛነቱ ከሚኒስቴሩ በማረጋገጥ በየወሩ ከጥቅል ደመወዛቸው ቢያንስ 10% እየቀነሰ ከእያንዳንዱ ወር መጨረሻ አንስቶ ባሉት ሰላሳ ቀናት ውስጥ ለሚኒስቴሩ ወይም ለሚወክለው የመክፈል፣
3. ተጠቃሚዎች ከተቋሙ የተሰጣቸውንና የሚፈለግባቸውን እዳ የሚያሳየውን ማስረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ካልሆኑ የጥቅል ደመወዛቸው አንድ ሶስተኛ እየቀነሰ ለሚኒስቴሩ ወይም ለሚወክለው ገቢ የማድረግ፣
4. ገንዘብ በመክፈልም ሆነ አገልግሎት በመስጠት እዳቸውን ከፍለው ያጠናቀቁ ተጠቃሚዎችን ዝርዝር ክፍያው በተጠናቀቀበት ወር ለሚኒስቴሩ ወይም ለሚወክለው የማሳወቅ፣
5. አገልግሎት በመስጠት እንደሚከፍሉ ተገልጾ የተመደቡለትን ተጠቃሚዎች ተገቢውን ክትትል በማድረግ ማሰራትና አገልግሎት ካቋረጡ ሙሉ ለሙሉ ማቋረጣቸውን በማረጋገጥ ወዲያውኑ ለሚኒስቴሩ፣ ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ለመደባቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

17 Oct, 13:04


የታክስ ክፍያ ጊዜ ማራዘሚያ ስምምነት የማይፈቃድባቸው ሁኔታዎች:-

- በታክስ ማስታወቂያ(በራስ ታክስ ስሌት ማስታወቂያ) ማቅረቢያ ጊዜ መከፈል ያለበት የታክስ ዕዳ ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ ወይም ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀንሶ ገቢ መደረግ ያለበት ሲሆን፣
  - ታክስ ከፋዩ አስቀድሞ የክፍያ ጊዜ ስምምነት የተሰጠው ሆኖ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ሳይኖር ዕዳዉን ያልከፈለ ሆኖ ሲገኝ፣
   - የታክስ ክፍያ ጊዜ ማራዘሚያ የተጠየቀበት የታክስ ዕዳ መጠን እንደ ታክስ ከፋዩ አመዳደብ ከተቀመጠው አነስተኛ የገንዘብ መጠን በታች ከሆነ፣
   ታክስ ከፋዩ፡-
  ለዕዳው ማስከፈያ ሃብቱ እንዲያዝ የዕግድ ትዕዛዝ የተላለፈበት ከሆነ፣
  በዕዳው የተያዘበትን ንብረት ለመሸጥ የጨረታ ማስታወቂያ የወጣበት ከሆነ፣ የክፍያ ጊዜ ማራዘሚያ የሚሰጠው ለዕዳው ተመጣጣኝ የሆነ የባንክ ወይም የንብረት ዋስትና ሲያቀርብ ብቻ ይሆናል፡፡

M.O.R. Medium Tax Payers No 1 Branch Office

17 Oct, 12:16


ምዕራፍ ሁለት ሥልጠና ተጠናቀቀ፡፡

ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም

በገቢዎች ሚኒስቴር በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2017 በጀት ዓመት በክፍል ሁለት ለሁለተኛ ዙር የምጁላር ሥልጠና ተከታታዮች የሚሰጠው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

ሥልጠናው ቀጥተኛ ባልሆኑ ታክሶች ማለትም Turn Over Tax(የሽያጭ ታክስ)፣ የቴምብር ቀረጥ እና ሱር ታክስ ዙሪያ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት አቶ ታምራት ጅግሳ ተሰጥቷል::

5,036

subscribers

2,283

photos

4

videos