የአፍሪካ መሪዎች በአህጉሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የዕዳ ቀውሶችን አስቀድሞ ለመከላከል ያለመ የ20 ቢሊዮን ዶላር አህጉራዊ የፋይናንስ ማረጋጊያ ፈንድ ማቋቋምን አጽድቀዋል ሲል የአፍሪካ ልማት ባንክ አስታውቋል።
ይህ እርምጃ አፍሪካ የራሷ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲኖራት ከማስቻሉም በላይ አገራቱ ለከፍተኛ የዕዳ ጫናዎች እንዳይጋለጡ እንደሚረዳ ተጠቁሟል።
ይህ ፈንድ፣ የአፍሪካ የፋይናንስ ማረጋጊያ ዘዴ በመባል የሚታወቀው፣ በአለም አቀፋዊ የካፒታል ገበያዎች ላይ ለመበደር የሚያስችለውን የራሱን የብድር ደረጃ ያገኛል። ይህ ማለት ፈንዱ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ገንዘብ ማግኘት ይችላል ያስችለዋል ተብሏል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ይህን ፈንድ የማስተዳደር ኃላፊነት እንደሚወስድ የተገለፀ ሲሆን የአፍሪካ ሀገራት ለሚገጥሟቸው የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት እና ዘላቂ ልማትን ለማበረታታት ይህን ፈንድ እንደሚጠቀምበት ተገልጿል።
አፍሪካ ለረጅም ጊዜ የራሷ የፋይናንስ ድጋፍ ስለሌላት ለውጭ ዕዳ እና ለኢኮኖሚ ድክመቶች በጣም ተጋላጭ ነበረች። ይህ አዲስ ፈንድ አፍሪካ እነዚህን ተግዳሮቶች እንድትቋቋም እና የራሷን ኢኮኖሚ እንድታሳድግ ይረዳታል ተብሎ ይጠበቃል።