ሁለተኛ፡-
መካከለኛው የፊልም ዘመን በኢትዮጵያ እና የተከታታይ ድራማ አጀማመር በኢትዮጵያ ላይ የነበረ የአሠራር መንገድ፣ ተግዳሮት እና ዕድሎች ማጥናት ለሚሻ ሰው ትልቅ ፋይዳን የሚሰጥ መጽሐፍ ነው። ስለ መንትያ፥ የንዋይ ሰለቦች፥ ትዝታ፥ ፊርማ፥ ምርጫ፥ ይቅርታ፥ አጋጣሚ፥ መላ ... የተሰኙ ሥራዎቹን ከቅድመ-ቀረጻ እስከ ድኅረ-ቀረጻ የነበረውን በማተቱ በኩል የኢትዮጵያ የፊልም፣ የድራማ ታሪኮችን ለሚሰንድ የጥናት ባለሙያ አንዱ ዋቢ የሚሆን ቅምጥ ጽሑፍ ማዘጋጀቱ ትልቅ አበርክቶት ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት ለወደፊቱ ታሪኩን ሲሰንድ ኹነኛ ማጣቀሻ የሚኾን መጽሐፍም ነው።
ሦስተኛ፡-
የጋሽ ተስፋዬ የማስታወቂያ ሥራ አጀማመሩ፣ አካሄዱ እና ዕድገቱን በማካተቱ ወደዚህ ሥራ ለሚገቡ ሰዎች ቀላል የማይባል ጥቁምታ ሰጪ ነው። ባለታሪኩ ከምንም ተነስቶ እዚህ መድረሱ በራሱ፣ በቀቢጸ-ተስፋ ለሚናውዘው የሀገራችን ወጣት “ዝሆንም በልጅነቱ ትንሽ ነበር!” ብሎ እንዲነሳሳ የማድረግ አቅሙ ላቅ ያለ ነው።
አራተኛ፡-
በሀገራችን ያለው የግለሰብ ታሪክ አጻጻፍ የረጋ ሐይቅም አይደል? ልክ እንደ ሰዋሰው ባለቤት፥ ተሳቢና ግስ። ተወለደ፥ አደገና ሞተ የግለሰብ ታሪክ የአጻጻፍ ቀኖና መስሎ ነበር። ጋሽ ተስፋዬ ዐዲስ በኾነ የአጻጻፍ መንገድ መከሰቱ ለሀገራችን ሥነጽሑፍ አንድ ትልቅ ዕምርታ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናትና ውይይትን ይሻል።
አምስተኛ፡-
ይህ መጽሐፍ በጋሽ ተስፋዬ ዘመን ለነበሩ ጉምቱ የዘመን ጓዶች የራሳቸውን ታሪክ እንዲጽፉ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው ብዬ አምናለሁ። ጉምቱ ሰዎቻችንን ባጣን ቁጥር ለቀብር ቀን የሚነበብ የሟች የሕይወት ታሪክ ጽሑፍ እስከማጣት መድረስ እንደ ዓመት በዓል በየዓመቱ የምንደጋግመው የሲሲሰፈስ እርግማን ኾኖብናል። ታላላቆቻችንን ባጣን ቁጥር እዝራ እጅጉ ወደ ሚያዘጋጀው “መዝገበ አእምሮ” እና ወደ ማዕዛ ብሩ “የጨዋታ እንግዳ” መርሐግብር" የምናማትረው በዚህ ምክንያትም አይደል? ይህ መጽሐፍ ጉምቱ ሰዎቻችን በተለይም የጋሽ ተስፋዬ የዘመን ጓዶች እንዲጽፉ የሚያነሳሳ ነው። ሁሉም የራሱን መልክ በጽሑፍ ከገበረ ደግሞ የዘመን ምስል እና የሀገር ቁመና ይከስትልናል። ጋሽ ተስፋዬ የራሱን ፊት እስከነቡጉሩ በማሳየት “ኑ አብረን የዘመን እና የሀገርን መልክ ለዚህኛውና ለሚመጣው ትውልድ እናሳይ” የሚል ትልቅ ቀጨምታን (inspiration) ገብሯል፤ ለዘመን ጓዶቹ።
ስድስተኛ፡-
ከዚህ በኋላ ለሚጻፉ የግለሰሰብ ታሪኮች በእነዚህ ምክንያት ደንበኛ ማጣቀሻ የመኾን ዕድል ያለው ይመስለኛል። እጅጉን ግላዊ የሚባለው ነገር ለሰዎች ትምህርት ይኾን ዘንድ ሊሰዋ እንደሚገባ፥ ከታሪኮች መሃል የተሻለውን መርጦ መከተብ የመጽሐፉን አቅም እንደ ሚወስን፥ የራስ ታሪክ የሚደምቀው በሌሎች ታሪክ መሃል መኾኑን፣ የሌሎችን ታሪክ ስናስገባ ዐውዱን በጠበቀ መልኩ እና በልክ መኾን እንዳለበት መጽሐፉ በጉልህ ይናገራል።
ሥነ ጽሑፋዊ ውበት፥ ቋንቋ፥ ሥርዓተ ነጥብ፥ ሰዋሰው እጅግ ውብ በመኾኑ ከዚያ ውስጥ ሕጸጽ ለማውጣት መሞከር “ከቁንጫ ሌጦ” ማውጣትን የሚጠይቅ አድርጎብኛል።
የመጽሐፉ ርዕስ - ከማዕበል ማዶ
ደራሲ - ተስፋዬ ማሞ
ዘውግ - ኢ-ልቦለድ (ቅይጥ ወይም የተስፋዬ መንገድ)
የገጽ ብዛት - 364
የኅትመት ዘመን - 2017
የዳሰሳው አቅራቢ - ቢኒያም አቡራ (የባለቅኔዋ ሶሪት እና ወደ ፍቅር ጉዞ መጻሕፍት ጸሐፊ)
[email protected]