ነሐሴ 12-ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ረድቶ በድል
ያነገሠበት ዕለት ነው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ገና በወጣትነቱ አባቱ ስለሞተ
የአባቱ ባለሟሎችና ህዝቡ ተስማምተው በ18 ዓመቱ ቆስጠንጢኖስን በአባቱ
ቦታ ሐምሌ 25 ቀን 300 ዓ.ም በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያ አነገሡት፡፡
እርሱም በጦር ሜዳዎች ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሠራ በሠራዊቱ ዘንድ
ይወደድ ነበር፡፡
ንግሥት ዕሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና
ስለክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው
አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይም በ312 ዓ.ም
ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት እንደተነሣ በራእይ በሰማይ ላይ ‹‹በዚህ
የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ›› የሚል መስቀልና ጽሑፍ ስላየ
ለሠራዊቱ ሁሉ የመስቀል ምልክት በመሣሪያቸውና በሰንደቅ ዓላማው ላይ
እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም በቲቤር ወንዝ ድልድይ ላይ
ጠላቱን ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ሆነ፡፡
ይኸውም የሆነው በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ነው፡፡ ‹‹ከዋነኞቹ
አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ›› (ዳን 10፡13)፣ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ
ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፡፡›› ዳን 12፡1፡፡
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ጠላቶቹን ሁሉ
ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግሥት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ከሆነ በኋላ በ300
ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነፃነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡
ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡ ንግሥት እሌኒም ይህን ጊዜ የጌታችንን
ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡
እርሷም ልጇ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ አምኖ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም
ሄዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና
አብያተ ክርስቲያናትን ለማነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሥ
ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ.ም ተጠመቀ፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስቀድሞ ገና ሳይጠመቅ በቅዱስ መስቀል
ምልክት ድል ማድረግ የጀመረ ነው፡፡ በእናቱ በቅድስት ዕሌኒ ስዕለት ካመነ
በኋላ በ325 ዓ.ም ጉባዔ ኒቂያን የጠራና ጸሎተ ሃይማኖት እንዲደነገግ አደረገ፡፡
በዓለም ላይ አብያተ ጣኦታትን አጥፍቶ አብያተ ክርስቲያናትን ያሠራና በከሃዲው
ዲዮቅልጥያኖስ የተዘጉትን ያስከፈተ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ነው፡፡
በነገሥታት ደረጃ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንደ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
ያገለገላትና ያከበራት የለም፡፡
"የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል" መዝ
33፡7
የቆስጠንጢኖስ ረዳት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ጥበቃው ረዳትነቱ በእኛም
በአማላጅነቱ በምንታመንበት በተዋሕዶ ልጆች ሁሉ ላይ ይሁን!
@newayekidisat
@newayekidisat