መጽሐፍ እንዲኽ ይላል፦
❝ ረዳትና ወንድሞችና በመከራ ቀን ይጠቅማሉ ፤ ከኹለቱም ይልቅ ግን ለማዳን ምጽዋት ትሻላለች፡፡... ምጽዋትን መመጽወት አታቃልል! ከወርቅ ድልብ ይልቅ ፈጽሞ ምጽዋት ይጠቅምኻል። ምጽዋትን በድኾች ቤት አድልባት። እርሷም ትሻላለች። ከመከራኽም ኹሉ አንትን ማዳን ትችላለች።
... በጦርም ቢኾን በመሣሪያም ቢኾን እርሷ ቀደማ ጥንተ ጠላትኽን ድል ትነሣልኻለች። የዕለት ጠላትኽንም ታጠፋልኻለች።... በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም ፤ ጽድቅ (ምጽዋት) ግን ከሞት ታድናለች፡፡... ምጽዋት ኹሉ ይቅርታን ያመጣል።
... ምጽዋትን ለሚሰጥ ሰው በፍጻሜ ዘመኑ እግዚአብሔር ዋጋውን ያስብለታል። በመከራም በተሰነካከለ ጊዜ የሚድንበትን ረድኤት ያገኛል።
... ምጽዋት መመጽወት ድልብ ታደልብልኻለችና ጥቂትም ቢኾን ምጽዋትን ለመመጽወት በገንዘብኽ አትዘን። ምጽዋት በመከራ ቀን ከሞት ታድናለችና። ወደ ጨለማ ይገቡ ዘንድ አታሰናብትም።
... ስጦታ በስውር ቍጣን ታጠፋለች፥ የብብትም ውስጥ ጉቦ (ሥውር ምጽዋት) ጽኑ ቍጣን ታበርዳለች።… መከራም እንዳታገኛችኹ በጎ ሥራን ሥሯት። ምጽዋት ከሞት ታድናለችና ከኃጢአትም ኹሉ ታነጻለችና ወርቅ ከማድለብ ምጽዋት መስጠት ይሻላል።
...ምጽዋትንና ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎች ኹሉ ለራሳቸው ሕይወትን ያገኛሉ።... ምናሴ ምጽዋት መጸወተ ፥ እውነትንም አደረገ። ከመከሩበት ከሞት መቅሰፍትም ዳነ። ልጄ ምጽዋት የምታደርገውን እይ - ከሞት ታድናለች ታጸድቃለችም❞¹
ስለዚኽ ፥ ኢንሹራንስ ከመግባት ምጽዋት መመጽወት ይሻላል ማለት ነው። ልበ በል አንባቢ! “ይሻላል” አልኹ እንጂ “አያስፈልግም” አላልኹም! ይኽ ጽንፍ መያዝ ነውና! አንድም ይኽ እንደ እምነትኽ የብቃት ደረጃ ይወሰናልና!
ግድ የለም ወዳጄ! ዘበኛ ከምታደልብ ምጽዋትን አድልብ! ቤትኽን ይጠብቅልኽ ዘንድ ዳግመኛ ውሻ ቀጥረኽ ከምታደልብ ምጽዋትን ባጡ በነጡ ድኾች ላይ ማድለብ ይሻላል።
‘ምረጥ!’ ብሎ የሚያስጨንቅኽ የለም እንጂ ፥ እንዲኽ ብሎ የሚያስጨንቅ ቢኖር ፥ እውነት እልኻለኹ - ምጽዋት ሺሕ ጊዜ ትሻላለች። ነገር ግን እምነታችን ገና ፍጹም አይደለምና ፥ ግድ የለም ፥ ውሻም ዘበኛም ማድለቡ አይከፋም! ዳሩ ግን ፥ ምጽዋትን ማድለብ እንዳንዘነጋ!
____
¹ ሲራ.፵ ፥ ፳፬ ፣ ፳፱ ፥ ፲፩ - ፲፫ ፣ ፫ ፥ ፳፰ ፣ ፯ ፥ ፲ ፣ ፲፮ ፥፲፬ ፣ ምሳ. ፲፩ ፥ ፬ ፣ ፳፩ ፥ ፲፫ - ፲፬ ፣ ጦቢ.፬ ፥ ፱ - ፲ ፣ ፲፪ ፥ ፯ ፣ ፲፪ ፥ ፱ ፣ ፲፬ ፥ ፲ - ፲፩
✍️ ዲ/ን ዳዊት ሰሎሞን።
(ጽሑፉ ጠቅሞኛል ብለው ካመኑበት ለሌሎች በማጋራት አገልግሎቱን ይደግፉ)
@Tibebsenayit
@Dndawitsol