ከሰባት ቀናት የሱባዔ ቆይታ በኋላም፤ ‹‹እንደተለመደው በሥዕለ ማርያም ሥር ተደፍተው ሲያለቅሱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ዑራኤልን አስከትላና ጽዋዓ እሳት አስይዛ መጥታ የሕይወት ጽዋዕ አጠጣቻችው፡፡ አባ ጊዮርጊስም የሕይወት ጽዋዕን ከጠጡ በኋላ የሰማይና የምድር ምስጢር ሁሉ ተገለጸላቸው››፡፡ ከዚህም በኋላ ከአርባ በላይ መጻሕፍትን ለመጻፍ ችሏል፡፡
የሕይወት ጽዋዕ›› የተባለውን መጠጥ በተመለከተ ገድሉ ላይ ‹‹የመረጥሁህና የልጄ ወዳጅ ጊዮርጊስ ብላ በስሙ ጠራችው፡፡ ከዕውቀት ወንዝ የመጣና ከጥበብ ምንጭ የተገኘ ከመለኮት ባሕር የተቀዳ ይህን ንጹሕ ጽዋ /እንካ/ ንሣ ጠጣ፡፡ ለስም አጠራርዋ ሰጊድ ይሁንና የዓለም ሁሉ ንግሥት እመቤታችን ያን ጊዜ በቀኝ እጅዋ ሰጠችው፡፡ ሳይጠጣውም ወደ ውስጡ ተመለከተ ይህን ጽዋ የጠጣ አይኰነንም ከሕይወት ባሕር ተቀድቶአልና የሚል መጽሐፍ አገኘ፡፡… ይህም በዮሴፍ ቤት በርሐ ጽዮን ሐዋርያት የጠጡት መንፈሳዊና ሰማያዊ መጠጥ ነው፡፡ በበዓለ ሃምሳ ከጠጡት ያልተለየ ነው፡፡ ይኸውም የሚናገር እሳት፣ የሚያድን እሳት መለኮታዊ እሳት ነው›› የሚል ተጽፎ ይገኛል (የደብረ ባሕርይ ጋስጫ አባ ጊዮርጊስና አቡነ በጸሎተ ሚካኤል አንድነት ገዳም፣ ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ እና ገድለ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል - ግእዝና አማርኛ፤ (ታኅሣሥ 2004) ገጽ 34 - አጽንዖት የግል)፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ‹‹ሐዋርያት የጠጡት መንፈሳዊና ሰማያዊ መጠጥ ነው›› ተብሎ የተጠቀሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሁለት ላይ ‹‹በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው›› የተባለው ቅዱሱ መንፈስ ነው፡፡ ‹‹ማርያም›› ለአባ ጊዮርጊስ ያጠጣችው መንፈስ ቅዱስን እንደ ሆነ በገጽ 44 ላይ ‹‹እመቤታችን ማርያምም የገለጠችለት የመጻሕፍትን ዕውቀት ብቻ አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ኀይልንም አለበሰችው እንጂ›› ተብሎ የተጻፈውን መመልከት ይቻላል፡፡ በገድሉ ትረካ መሠረት መንፈስ ቅዱስን የምትሰጠው ማርያም ናት ማለት ነው፡፡ በገድለ አባ ጊዮርጊስ እንደተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስ ‹‹… ከዕውቀት ወንዝ የመጣና ከጥበብ ምንጭ የተገኘ…››፣ ‹‹… ከሕይወት ባሕር …›› የተቀዳ ሳይሆን ራሱ ዕውቀት ሰጪ፣ ራሱ የጥበብ ባለቤት የሆነና ራሱ የሕይወት ምንጭ የሆነ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡ በፍጡር እየተቀዳና በዕቃ እየተጨለፈ የሚወሰድ ሳይሆን እሱ በዓለሙ ሁሉ የመላ ለሁሉ እንደ ወደደ የሚሠራ ገናና አምላክ ነው፡፡