========================
[“ሕያው ሁኖ የሚኖር፣ ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው?" መዝሙር 89:48]
ዶ/ር አንዷለም ዳኜ ከአባታቸው ከአቶ ዳኜ ጠብቀው እና ከወ/ሮ ደጌ ጥጉ ግንቦት 5 ቀን 1980 ዓ•ም• በምዕራብ ጎጃም ዞን ጓጉሳ ወንበርማ ወረዳ ቡራፈር ቀበሌ ተወለዱ። በወላጆቻቸው እንክብካቤ አድገው ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በቡራፈር የመጀመሪያ ደርጃ ት/ቤት፣ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሽንዲ ከተማ ሽንዲ ት/ቤት ተከታትለዋል።
ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን በቡሬ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተምረዋል። ከዚያም የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሁሉንም የትምህርት ዓይነት <<A>> በማምጣት በከፍተኛ ነጥብ አልፈዋል። ከዚያም የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የላቀ ውጤት በማምጣት አጠቃላይ ከት/ቤቱ አንደኛ በመሆን አጠናቀዋል።
ከዚያም በ2000 ዓ•ም• ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ በውስን የህክምና ተማሪዎች የተያዘውን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በ2005 ዓ•ም• የመጀመሪያ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳሊያና በዩኒቨርሲቲ ደርጃ የዋንጫ ተሸላሚ ሁነዋል።
በመቀጠልም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሌክቸረርነት ማዕረግ ተቀጥረው ከማስተማሩ እና ከምርምሩ ጎን ለጎን የሚውዱትን የህክምና ሙያ በመተግበር እያሉ ለላቅ ብቃት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቀዶ ህክምና ት/ት ክፍል ውስጥ በመማር በ2011 ዓ•ም• ተመርቀው ታዋቂ የቀዶ ህክምና ሀኪም ለመሆን በቅተዋል። በተጨማሪም በበጎ አድራጎት ህክምና በተለያዩ ሆስፒታሎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለማህበረሰባቸው ሰጥተዋል።
ወጣትና ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር አንዷለም ዳኜ ከነበራቸው የዕውቀት መሻት እና ከተገነዘቡት ከፍተኛ የወገን ችግር በመነሳት የጉበት፣ የሀሞት ከረጢት እና የቆሽት ሰብ ስፔሻላይዜሽን ት/ት በአ•አ• ዩኒቨርሲቲ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተከታትለው በ2016 ዓ•ም• አጠናቀው ዕንቁ ባለሙያ ለመሆን ችለው ነበር።
ዶ/ር አንዷለም ዳኜ በተለያዩ የት/ት እርከን ሲያልፉ በተለያዩ የውጭ ሀገራት ማለትም በጀርመን፣ በእንግሊዝ፣ በህንድ፣ በደ/አፍሪካ እና በቱርክ የተለያዩ ስልጠናዎችን የወሰዱና በዚህም ከፍተኛ ከበሬታን እንዳተረፉ የሙያ አጋሮቻቸው፣ መምህሮቻቸው፣ ተማሪዎቻቸው እና ታካሚዎቻቸው ይመሰክራሉ።
በስራቸውም ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቁ ቅን ፣ ትሁት፣ ሰው አክባሪ አዛኝና ሩህሩህ ሐኪም ነበሩ:: ለዚህም ብዙ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተቋማት ለቅጥር ሲያጯቸው <<የማስቀድመው፣ እየተቸገረ ያስተማረኝ ማህበረሰብ አለ>> በማለት ለሚቀርብላቸው አጓጊ ገንዘብ እና ክብር አልተንበረከኩም::
ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ህዝባቸውን ለማገልገል ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት ሁሉ በቅንነት ፈጽመዋል:: ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ሀይማኖተኛ፣ ለሰው ሁሉ መልካም አሳቢ፣ ታጋሽ፣ ደግ፣ አንደበተ ርቱዕ ነበሩ::
የቤተሰባቸውን ሁኔታ በተመለከተ ጋብቻቸውን በስርዓተ ተክሊል በታላቁ ደብረ ሮሀ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም በ2006 ዓ•ም• የፈጸሙ ሲሆን ከውድ ባለቤታቸው ከወ/ሮ ቤዛየ ግርማ የስምንት ዓመትና የአምስት ወር ዕድሜ ያላቸው ሁለት ሴቶችና የአምስት ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል። ለቤተሰባቸውም ፍቅር የሚሰጡ፣ እጅግ የሚናፈቁ ተወዳጅ አባት ነበሩ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወጣቱ ሐኪም፣መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ ሩቅ አስበው ስራ ውለው ወደ ቤታቸው ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው መኪናቸውን እያሽከረከሩ እያለ በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ጥር 24/2017 ዓ• ም• በተወለዱ በ 37 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል::
ሥርዓተ ቀብራቸውም ቤተሰቦቻቸው፣ የሥራ ባል ደረቦቻቸው፣ ተማሪዎቻቸው፣ታካሚዎቻቸው እና ወዳጆቻቸው በተገኙበት ጥር 25 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ7:00 በባህር ዳር ከተማ በድባንቄ መካነ-ህያዋን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ሁሉ መጽናናትን እየተመኘን ፤ ነፍሳቸውን በአባቶቻችን በአብርሃም፣ በይስሀቅ እና በያዕቆብ ቦታ በአጸደ ገነት ያሳርፍልን።
የሀዘን እንጉርጉሮ
==========
በክፉ በደጉ ከፊት የሚቀድም ፣
አንዷለም አንዷለም አንዱ እንቋችን የለም።
ለጆሮ ይከብዳል ውስጥን ለማሳመን ፣
ይኸንን ሞት መስማት እንደምን ያሳዝን።
ስንቱ እየለመነህ ስንቱ እያማተረ፣
ዕንቁ ጭንቅላትህ ቆሼ ላይ አደረ፣
የወዳጅ ዘመድህ ልቡ ተሰበረ።
ሜዳሊያ ያንተ ነው ሞራልና ወርቁ፣
አንተን የሚመሰል አይገኝም ዕንቁ።
አሜሪካ አማትራህ ለምኖህ አውሮፓ፣
ለወገንህ ፍቅር በገንዘብ ሳትለካ፣
ሌት ተቀን ስትለፋ ነበር የምትረካ።
ጉበቱና ጣፊያው ቆሽቱ ተቃጠለ፣
አንተ እምታክመው ለአንተ ሲል ቀለለ፣
ሀዘኑ ቅጥ አጣ <<ምን ልበል>> እያለ።
በዶ/ር ዓለማየሁ ባዬ