+ + + + +
4. የአብነት ትምሕርት ቤቶች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በብዙ መልኩ ይበልጥ ለማገልገል፣ የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ ለመገንዘብ (ታሪካችን በአብዛኛው ተሰንዶ ያለው በግዕዝ ስለሆነ)፣ የአብነት ትምሕርት ቤቶች በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሊከፈቱ ይገባል፡፡ የአብነት ተማሪዎች ትምህርት ቤት ፍለጋ ከሀገር ሀገር መዞርም ሆነ በየመንደሩ እየዞሩ ቁራሽ መለመን (አኩሪና የበረከት ምንጭ ቢሆንም) ጊዜ ያለፈበት አሠራር ሆኗል፡፡ በመሆኑም በሁሉም አሕጉረ ስብከቶች ለዚህ አገልግሎት አብያተ ክርስቲያናት መለየት ይገባቸዋል፡፡ የመጽሐፍ መምሕር፣ የአቋቋም መምሕር፣ የድጓ መምሕር፣ የቅኔ መምሕር እየተባሉ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የተመደቡ ባለሙያዎች ሥራ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ሕጻናትና ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ካለበቂ ዕውቀት (በድምጫ ብቻ) ዲያቆን፣ ካሕን፣ መሪጌታ የሆኑ ሁሉ የሚማሩበት፣ የዓቅም ማሻሻያ የሚያገኙበት ሊሆን ይገባዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከአብነት ትምሕርት ቤቶች ሊወጡ ይገባል፡፡ ካህናት በሁለት በኩል የተሳሉ ሰይፎች (ሰይፍ ዘክልኤ አፉሁ) መሆን ይገባቸዋል፡፡ በዘመናዊው ዕውቀትም ሆነ በዓለማዊው ዕውቀት የበቁ ከሆኑ ጥቅማቸው ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርና ለዓለም ይተርፋል፡፡
+ + + + +
5. ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት (ከሙዓለ ሕጻናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም)
በብዙ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሰፋፊ መሬት (ይዞታ) ያላቸው ናቸው፡፡ ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት ረዘም ላለ ጊዜ ዘመናዊ ትምሕርት ቤት ከፍተው የማስተማር ልምድ አላቸው፡፡ በመሆኑም ለዚህ አገልግሎት የሚውሉ አብያተ ክርስቲያናት ተለይተው የግንባታና መሰል ፈቃዶች በሀገረ ስብከቶች በኩል እንዲያልቁ ተደርጎ የሚያስተምሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥር በሚገኙ ትምሕርት ቤቶች የተማሩ ልጆች (ዜጎች) ሀገርን በፖለቲካው፣ በማኅበራዊው፣ በኢኮኖሚው፣ በቴክኖሎጂው የሚመሩና የሚያሻግሩ በምግባርና በሃይማኖት የታነጹ ይሆናሉ፡፡
+ + + +
6. የሕክምና ተቋማትን ማስፋፋት በተመለከተ
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እስከሚያውቀው ድረስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት የሚተዳደሩ የሕክምና ተቋማት፤ሲግናል አካባቢ የሚገኘው ምግባረ ሠናይ ጠቅላላ ሆስፒታልና ቅድስት ልደታ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት እንኳን ለኢትዮጵያ ለአንድ አገረ ስብከትም ያንሳሉ፡፡ በመሆኑም በሀገረ ስብከት ደረጃ የሚተዳደሩ ሆስፒታሎች፣ ከፍተኛ ክሊኒኮች፣ ክሊኒኮችና ኮሌጆች ሊኖሩ ይገባል፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክሕነት ሥር ደግሞ ቢያንስ አንድ ቲቺንግና ሪፈራል ሆስፒታል ሊኖር ይገባል፡፡
+ + + + +
7. የጎጆ ኢንደስትሪና መካከለኛ ፋብሪካዎችን በተመለከተ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልባቸው ብዙ ንዋያተ ቅድሳት ከውጪ ሀገር የሚገቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመጾር መስቀል፣ ጽዋ፣ ዘቢብ፣ መጋረጃ፣ ምንጣፍ፣ ልብሰ ተክህኖ እና የመሳሰሉት፡፡ እነዚህን ንዋያተ ቅድሳት በሀገር ውስጥ በዚያውም በአብያተ ክርስቲያናት ቢመረቱ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚኖረው ትርጉም እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ምርቶቹን መሠረት አድርጎ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና አሕጉረ ስብከቶች የልየታ ሥራ በመሥራት የሚመረቱበትን አሠራርና የገበያ ተሥሥር እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በሕትመት በኩል ዕድሜ ጠገቡ ትንሣኤ ዘጉባዔ ማተሚያ ድርጅት ዘመኑን የዋጀ ሊሆንና የአገልግሎት አድማሱን ሊያሰፋ ይገባል፡፡
+ + + + +
8. የፕሮጄክት አስተዳደርን በተመለከተ
በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚታዩ ፕሮጄክቶች የጠለቀ ጥናት ያልተደረገባቸው፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ደረጃም ቢሆን ስምምነት ያልተደረሰባቸው (የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሆኑ) የሚጀመሩበትና የሚጨረሱበት ጊዜ የማይታወቁ፣ ተደራራቢ (በአንድ ጊዜ ሁለት ሦስት ፕሮጄክቶች) የሆኑ፣ ኃላፊዎች ሲቀያየሩ የሚቆሙ፣ የገንዘብ አሰባሰብ፣ አወጣጥ፣ አስተዳደር ዘዴ ያልተበጀላቸው (ለምዝበራ የተጋለጡ)፣ ተገቢ የሆነ የክትትል የድጋፍ እና የቁጥጥር አሠራር ያልተበጀላቸው ናቸው፡፡ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች አንድ ቀላል ፕሮጄክትን ለመፈጸም ብዙ ዓመታትን ይወስዳል፡፡ በአብያተ ቤተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉና ዓመታትን ያስቆጠሩ ብረቶች፣ ጠጠር፣ አሸዋ እና የደረቁ ሲሚንቶዎችን መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡
በመሆኑም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በክፍለ ከተማ ደረጃ በሌሎች አሕጉረ ስብከቶች ደግሞ በሀገረ ስብከት ደረጃ በባለሙያ (ቅጥርና በበጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች) የተደራጀ የሥራ ክፍል ሊያደራጅ ይገባል፡፡ የሥራ ክፍሉ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሚቀርቡ ፕሮጀክቶችን የሚመረምር፣ የአካል ጉብኝት በማድረግ ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚሆን ፕሮጄክቶችን የሚቀርጽ፣ የሚከታተል፣ የሚደግፍና የሚቆጣጠር እንዲሁም የእርምት እርምጃ የሚወስድ ሊሆን ይገባዋል፡፡
+ + + + +
9. የሥነ ምግባር መከታተያ መምሪያ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊትና ሰማያዊት ብትሆንም በምድር ያለች፣ በምድራውያን ሰዎች የምትተዳደር ናት፡፡ ምድራውያን ሰዎች ደግሞ ሊያለሙም ሊያጠፉም ይችላሉ፡፡ በመሆኑም በአብየተ ክርስቲያናትና በሌሎች መዋቅሮች የሚታዩ የአስተዳደር ብልሹነቶችን የሚመለከት፣ የሚመረምር፣ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ ቢያንስ በክፍለ ከተማ ደረጃ መዋቅርና በአጥቢያ አቤ ክርስቲያን ደረጃ አንድ ባለሙያ ሊመደብ ይገባል፡፡
+++++++
የቤተ ክርስቲያን ደጆች በምሕረትና በሃይማኖት እንዲከፈቱ ያድርግልን፡፡
ሼር በማድረግ አድርሷቸው