መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች @melikt_weg_gitim Channel on Telegram

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

@melikt_weg_gitim


✞ ይህ ቻናል መንፈሳዊ የሆኑ ግጥሞች ፣ ወጎች እንዲሁም መልዕክቶች የሚቀርቡበት ነው ✞
አስተያየት ካለ እንዲሁም ግጥም ወግ እንዲተላለፉ የምትፈልጓቸው መንፈሳዊ መልክቶች ለማድረስ https://t.me/+a3-5g5CslOkwNjBk ተጠቀሙ

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች (Amharic)

በዓለም አቀፍ ምላሽዋ ግጥሞች እና ወጎች ከባድ እና ከከፍተኛ በቀል እንዲሁም መልእክቶችን ማግኘት እንደሚችል እርምጃ እና ቅንብሮች ያበርሰዋል ተመልከቱ። ይህ ቻናል መንፈሳዊ የሆኑ ግጥሞች ፣ ወጎች እንዲሁም መልዕክቶች የሚቀርቡበት ነው። ከበጀቴዎቹ ውስጥ ያለ መሀከል እና ስንዴት የሚሆነውን ያገኙታል። ጠቃሚውን ስለመረቃ እና በመጠቆማ ያለን ከሆነ በዚህ ቦታ የእናትን ዓለም እና ትራት፣ ሰላምና ተዛውንበት ለመገንባት እና ከመካከል በፊት የማገናኘት ጥቃት ለመደም የሚቻለውን መረጃ ያግኙታል። የቻናሎች እንደተለያዩን ቡድን በመምራት ላይ እና ቢሮዎች ምን እንደሚሆኑ በመለዋወጥ የእንጀራን መረጃ እንደሚፈልግ ይጠናቀቃል።

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

04 Nov, 03:31


#ትጋሀ #ሌሊት

ትጋሀ ሌሊት (የሌሊት ትጋትን) ቢይዙ የምትሰጥ ጸጋ ደስ የምታሰኝ ናት፡፡

በትጋሀ ሌሊት አድሮ
ቀን ደግሞ መጽሐፍ መመልከት
መልካም ነው
፡:

ሌሊቱን #በጎነገር በማሰብ አሳልፈው፡፡

ወዳጆቼ
ትሩፋት ከመሥራት እና
ከኀጢአት ከመጠበቅ
እንዳናርፍ መሆን ይገባናልና


[ማር ይስሐቅ ክፍል ፯፤  አንቀጽ 15]

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

02 Oct, 04:04


በየአመቱ ሁሌ እየመጣ ይጎፈላል።ካልደበደብኩሽ
ይላታል፡፡ማርያምን እኮ ነው...እዚህ ምድር ላይ ማንን ትጠላለህ ቢባል ቀድሞ የሚጠራው የማርያምን ስም ነው.....ሲሰድባት ለአፉ ለከት የለውም።ደሞ እጁ ላይ የያዘውን ድንጋይ ብታዩት ሀገር ይጨርሳል።በየአመቱ "አንቺን ብሎ ማርያም" እያለ እየዛተ ነው ያረጀው.....
አንቺን ብሎ ማርያም!!!አንቺን ብሎ አዛኝ!!አንቺን ብሎ እናት!!ደግ ብቶኚ እኔን ትበድያለሽ??ሀቄን ትወስጃለሽ?? ብቻዬን ትጥዪኛለሽ??አንቺ ብሎ ማርያም!! በዚ ዲንጋይ ነበር ማለት...
ንግሷ ተጀምሮ እስኪያልቅ በሯ ላይ ሲጎፈላ አምሽቶ በረድ ሲልለት ወደ ከተማ ይመለሳል።በአመተ ክብሯ እግዚኦ እየተባለ ቢለመን፤በሽማግሌ ቢመከር፤በጎረምሶች
ቢታሰርም እሱ ግድ አይሰጠውም።በአመቱ ያው እራሱ ጉልላት ሆኖ ነው ሚመጣው..አይለወጥም።
ዛሬ ጉልላት የት ሄደ?? ምነው ጭር አለሳ??( አለ ጓደኛዬ ገና ቤተክርስትያን እንደደረስን
አረ ሰአቱን ጠብቆ ይመጣል....ደሞ የሱ ነገር...አሁን ታቦቷ ሲወጣ ብቅ ይል የለ?(ብዬ ወሬዬን ከአፌ ሳልጨርስ አረንጓዴዋ ታክሲ ስትበር መጥታ አጠገባችን ቆመችና
ብዙ ወጣቶች ከመኪና ወርደው አንዳች ነገር ከመኪናው
ለማውጣት ሲጣደፉ የሁለታችንም ቀልብ መኪናዋ ላይ አረፈ...
በስመአብ ወወልድ ጉልላት!! አለ ጓደኛዬ ቀደም ብሎ...
ምንድነው ምን ተፈጠረ?? ብዬ እኔም ከአንገቴ ስንጠራራ ጉልላትን በደም የተለወሰ ፊት አይቼ ደንዝዤ ቀረሁ...
ወጣቶቹ ለሬሳ የቀረበ የተዝለፈለ አካሉን ተሸክመው ለንግስ በተሰለፈው ምእመን መሀል ሰንጥቀው ወደ ማርያም ግቢ ሲዘልቁ ከጓደኛዬ ጋ ሳናወራ ተጣድፈን ተከተልናቸው....
ምንድነው??ምን ጉድ ተፈጠረ??ጉልላት ምን ሆነ?? (አሉ አባ መቋሚያና ፅናፅላቸውን እንደያዙ ባዶእግራቸውን እየተጣደፉ መጥተው።ከማህሌቱ ተጠርተው እንደመጡ ያስታውቃል..
በዋዜማው ጠጅ ቤት ነበር አሉ...ጠዋት ማዞሪያ ድልድይ ውስጥ ወድቆ ነው የተገኘው። ሆስፒቲል አድርሰነው ቤት አስገቡት ደክሟል አሉ...ጉልላት ደሞ ቤት የለው....(አለ አንዱ ጎረምሳ
ውይ የአደራ ልጄን.... እኔን እኔን..በሉ ቤት አግቡት
አባ ካባቸውን እየሰበሰቡ ቤታቸውን ከፍተው ሲገቡ ገልላትን ይዘን ተከተልናቸው ቀድሞም መድሐኒት አዋቂ ናቸው።ቁስል እጃቸው ላይ አይበረክትም፤ህመም ከፊታቸው አይቆምም፤ ፀሎታቸው ጠብ አትልም፤እቤታቸው ገብተን እንደቆምን
በሉ ሂዱ ውጡ እናንተ... አይዟችሁ አሉ ሲጣደፉ።እሺ ብለን ወጣን ....
ቆይ የጉልላት ፀባይ ምንድነ?? ለምንድነው በዚህ ልክ ማርያምን ሚጠላት??አለኝ ጓደኛዬ እጁን አገጩ ላይ አድርጎ እንደተከዘ
ማርያም እናቴን ቀማቺኝ ነው ሚለው....እርግጥ ጉልላት ከልጅነቱም የተበደለ ነው።እናቱን በሰፈሩ የማያውቃት የለም።እሱን አርግዛ እስከምጧ ቀን ድረስ አሻሮ እየቆላች ቀንስራ እየሰራች እቺ ቤተክርስትያን ስትሰራ በጉልበቷ እና በደሀ ገንዘቧ ትረዳ ነበር።በኋላ ጉልላት ተወለደ።ያኔ የማርያም ቤተክርስትያንም እየተሰራ ጉልላቱ ላይ ደርሶ ስለነበር ልጇን ጉልላቴ አለችው።የሚገርመው ግን እሱ አይደለም... ወልዳው በአራስነቷ ቁስሏ ሳይጠግ አቅሟ ሳይበረታ ጉልላቷ ሲሰራ አሸዋ እያቀበለች ድንገት ወድቃ እዚያው ሞተች።ጉልላትም ያለ አሳዳጊ በመንደሩ ሰው እርዳታ ሲያድግ ይህንን የእናቱን ታሪክ እየሰማ ነበር...በቃ ከዛ ወዲህ ይኸው እድሜ ልኩን ከማርያም ጋ ጥሉ
እንደከረረ ዛሬ ደረሰ...
ልጆች አላችሁ....?በሉ ኑ አንሱና አልጋ ላይ አድርጉልኝ አሉ አባ ከበራቸው ብቅ ብለው
ሁሉም ተበትኖ ስለነበር እኔና ጓደኛዬ ስንሮጥ ተከትለናቸው ገባን።የጉልላት ደሙ ተጠርጎ ቁስሉ ታክሞ ተሸፍኖ ሞት ከሚመስል እንቅልፉ ነቅቶ
ማሪኝ እመብርሀን ....ማሪኝ እናቴ....አትቀየሚኝ.... ትቼዋለሁ....ማርያም...ማርያም....ይቅር በዪኝ እያለ
ያቃስታል
በል ትንሽ እረፍ ጉልላቴ አሁን ደና ነክ....አየህ እናትህ ስምህን ስትሰይመው በዋዛ አደለም። የቤተክርስትያን ጉልላቷ በሰጎን እንቁላል ይመሰላል።ግዙፏ ሰጎን እንቁላል ከጣለች በኋላ እንቁሏሏን አቅፋ እስኪፈለፈል ድረስ አይኗን ከእንቁላሉ እንደማታነሳው አንተም ብትዝትባት ብትሰድባት አይኗን ካንተ አትነቅልም ዞሮ መግቢያክ ናት።እናትህ ይህችን ጉልላት ስትሰራ ወድቃ ብትሞትም ለህንፃዋ ግን ከገንዘቧ እስከ ደሟ ከፍላለች ማርያም እናትህን ቀምታህ ሳይሆን ወደ እቅፏ ወስዳት ነው።አንተ ምትጠላት ማርያም ለኛ ጉልላታችን ናት ሰገነታችን ናት መድሀኒታችን ናት።ይኸው አንተም ዘመንህን ስትዝትባት ኖረህ ሀኪም
ያቃተው በሽታህን ፈውሳ በእለተ ቀኗ በምህረት ጎበኘችህ
እንዳተ ዛቻና ስድብ ቢሆንማ.....አሁን ተው ጉልላቴ
ተመለስ ...ተው ግድየለም (አባ ቁስሉን በመስቀል
እየደባበሱ በስስት እያዩት ሲያወሩ ጉልለላት ሳል በቀላቀለ ድምፅ
አንቺን ብሎ ማርያም!!....ብሎ ፀጥ ሲል ደንግጠን
እያየነው
"ማን አፈረ' ብሎ ቀጠለ
እውነትም "አንቺን ብሎ ማርያም ማን
አፈረ ማንም!! አሉ አባ በፈገግታ ሁላችንንም
እያዩ።


✍️ ቻቻ

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

23 Sep, 11:39


እግዚአብሔር አብ

አባታችን ወርሐዊ መታሰቢያ ቀኑ ነው ብናስበውስ

በአካል ስሙ አብ ጥንት መሰረት አስገኝ ማለት ነው።
በባሕሪያዊ አወላለድ ለወልድ አባቱ ለመንፈስ ቅዱስ አስራጺ ነው።ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ መሰረት ነው።በዚህም ጥንተ ሃይማኖት እሱ ነው።ለሰው በእግዚአብሔር ማመን የታወቀችው ከአብ በኋላ ነው።


ሰማይ እና ምድር የሚታየውና የማይታየው ሁሉ በሱ ታስቦ በሱ ተፈጥሯል።

ከሁሉ በላይ ሰውን በራሱ አርአያና አምሳል ፈጥሯል።በጸጋ ልጅነትም አክብሯል።ይህን ላደረገ ለሱ ክብር ምስጋና ይሁን።


በግብር ስሙ ወላዲ አስራጺ ነው።


በኩነት ስሙ ልብ ይባል።ለራሱ ማሰቢያ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ማሰቢያቸው ነው።
የሚደንቀው የእግዚአብሔር ሐሳቡ አካላዊ ነው።ሁሉ በሱ ታስቧሎ የበጎ ሐሳብ ሁሉ ምንጭ እሱ ነው።

ለአዳምም ማኅጸኑ እሱ ነው። በአብ ልብነት ታስቧልና።የአፈጣጠራችን አላማም በአብ ታስበን 1000 ዓመት በቃል ተሰርተን በመቀጠል ወደፍጻሜው ወደመንፈስ ቅዱስ ደርሰን ወደአባት ሙሉ ሰው ሆነን መመለስ ነበር ።አዳም አባታች ለሺ አመት 70 ሲቀረው ሞተብን።😭

ክብር ይግባውና ወልድ ያቺን የአዳም ጉድለት ሞላልን በቃልነቱ ራሱ ሰራንና ወደመንፈስ ቅዱስ ማዕረግ አደረሰን።(በ50ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ መውረዱ የወልድወደአብ በ10ኛ ቀን መሄዱ በኋላ መሆኑን ልብ ይሏል)

እሱ ለልጁ የባሕርይ አባት እንደሆነ ለኛም በጸጋ አባታችን ነው።ልጁ አባ አባት እንድንል አስችሎናል።አባቱን አሳውቆናል የአባቱን ፈቃድ ነግሮናል ከአባቱ ጋር አስታርቆናል።ስንጸልይ አቡነ ዘበሰማያት ማለት ተፈቅዶልናል።ውሉድ ዘበሰማያት ሆነናል።ልጆች ከሆንን እንግዲህ ወራሾች ነን።


ታዲያ እግዚአብሔር አባቴ ነው ማለት ምን ማለት ነው ያልን እንደሆነ ፦

ሕያው ነው ሕያው ሆኜ እኖራለሁ፤
ጠቢብ ነው ጥበበኛ ያደርገኛል፤
ከሃሊ ነው ሁሉን ያስችለኛል!
ብርሃን ነው, የብርሃን ልጅ ብርሃን ያደርገኛል፤
ዘለዓለማዊ ነው፡ ለዘለዓለም ሕይወት አለኝ፣
ረቂቅ ነው ያራቅቀኛል፡
መንግሥቱ የዘለዓለም ናት፡ ለዘለዓለም ያነግሠኛል፣
መዋዒ ነው ሁሉ በእርሱ አሸንፈዋለሁ፣
ስውር ነው ይሠውረኛል!
ዐዋቂ ነው. ያሳውቀኛል፣
ስፉሕ ነው፡ የትም ብሔድ ቀኙ ትመራኛለች፤
ባለጸጋ ነው ለሁለንተናችን ይበቃል!
ንጹሕ ነው ያነጻኛል ፥ንጽሕም ይወዳል!
ልዩ ነው በምድርም በሰማይም ከኃጢአት ከአጋንንት ልዩ ያደርገኛል፤
ክቡር ነው ያከብረኛል፡
ንጉሥ ነው ያነግሠኛል (በሥልጣን ሰማያዊት) እረኛ ነው ይጠብቀኛል፣
ነባቢ ነው ያናግረኛል!
ከሣቲ ነው ይገልጥልኛል፤
ኃያል ነው ያጸናኛል!
እርሱ ራሱን አልብሶ፣ ራሱን አብልቶ የሚያሳድግ ቸር አባት ነው ማለት ነው፡፡



እግዚአብሔርን “አቡነ ዘበሰማያት” ስንለው እኛ ደግሞ ውሉድ ዘበሰማያት (የሰማያት ልጆች) መሆናችን ትዝ ካለን ኑሮ ማለት በዚህ ደስ መሰኘት ነው፡፡ አርሱም የሰማይ አባታችን ነው፣ እኛም የስማይ ልጆቹ ነን ማለታችን ነው፡፡

ይህን ሁሉ መናገርም ዘመነ ፍስሐ መምጣቱን መናገር ነው፡፡

ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ፤”
ኤፌሶን 3፥14-15


ስለአባታችን እግዚአብሔር አብ በመልክአ እግዚአብሔር አብ ድርሰት እንቋጭ።

ሰላም ለአካለ ቆምከ ኢውሱን እም አቅም። ወለመልክእከ ዓዲ ዘግርማ ራዕይ መድምም ፡ እግዚአብሔር አብ አበ ብርሃናት ግሩም ፣
ቃልከ ወሕይወትከ ግሩመ መልክእ ወቆም። ለመንግሥትከ ዘአልቦ ተፍጻም ።


ኦ አምላከ ኵሉ እንዘ አምላከ ጽድቅ ባሕቲትከ። ወኵሉ ገበርከ በፈቃድከ ፡
እግዚአብሔር አብ አምጣነ ተጽናስ አልብከ
፡ ምርሐኒ ፍኖተ ጽድቅ ወአለብወኒ ሕገከ።
ወኵሉ ቅሩብ ወሥሩዕ በኀቤከ።


ስብሐት ለከ እግዚአብሔር በኍልቈ ዕለታት ወለያልይ። ስብሐት ለከ እግዚአብሔር በኍልቈ ክረምት ወሐጋይ። ስብሐት ለከ እግዚአብሔር በኍልቈ መዋዕል ብሉይ። ስብሐት ለከ እግዚአብሔር በኍልቈ ኵሉ ዘኢይትረአይ፡ ስብሐተ ቅድምናከ ዘልፈ ይነግር ሰማይ።

ኦ እግዚአብሔር አብ ዕቀበነ ወአድኅነነ እመከራ ሥጋ ወነፍስ ሊተ ለኵልነ ውሉደ ጥምቀት ለዓለመ ዓለም አሜን።


ምንጫችን ጸያሔ ፍኖት፣3ኛው ኪዳን ፣መልክአ እግዚአብሔር አብ ፣መጽሐፍ ቅዱስ ነው

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

11 Sep, 17:14


ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ምላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል
፩ኛ ጴጥሮስ ፫÷፲

#ይቅርታ_አድርጉልኝ!

ትናንት ለበደለን ፡ አምና ላስቀየመን
ቅሬታን አጥፍተን ፡ በደል መቁጠር ትተን
የንስሀን ጊዜ ፡ ጨምሮ ሊሰጠን
ይቅርታ እንድናደርግ፡ ጷጉሜ ተለገሰን ።

ፈንድቆ ለመኖር ፡ እንደ ጨቅላ ህፃን
በሰላም ይፈታ ፡ የቂም ቋጠራችን
ይቅር እንባባል ፡ አንዳችን ለአንዳችን
ለዚህ ነው የተሰጠን ፡ ጷጉሜ ድልድያችን።

እስካሁን ላረኩት ፡ በደል በናንተ ላይ
ይቅርታ አድርጉልኝ ! !

ይቅርታ የሚያደርግ ፡ ነውና አስተዋይ።
ለጥሩም ለመጥፎም ፡ ፍርድ አለ ከሰማይ
ግን እስካለን ድረስ ፡  በጥፉት ምድር ላይ
ለገዛ ጥቅሜ ስል  ፡ ለሰራሁት ጉዳይ
እያወኩኝ ሳላውቅ ፡ እያየሁኝ ሳላይ
ለበደሌ ሁሉ ፡ በሞት ሳንለያይ

ይቅርታ አድርጉልኝ ! !
በአዲሱ አመት ልባችንን ለይቅርታ እናዘጋጂ !

"ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ"
"በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ"
                          (መዝ_64:11)


@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim


#Join_and_Share🙏

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

11 Sep, 14:04


🌻🕊 ሥርዓተ በዓል ወጾም ዘኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን 🕊🌻

❀✞ ዓመተ ምህረት፥ ፳፻፲፯(2017 ዓ.ም)
❀✞ ወንጌላዊ፥ ማቴዎስ
❀✞ የዘመን መለወጫ ቀን፥ ረቡዕ
❀✞ አበቅቴ፥ ፩(1)
❀✞ መጥቅዕ፥ ፳፱(29)
❀✞ ጾመ ነነዌ፥ የካቲት ፫(3)
❀✞ ዐቢይ ጾም፥ የካቲት ፲፯(17)
❀✞ ደብረ ዘይት፥ መጋቢት ፲፬(14)
❀✞ ሆሳዕና፥ ሚያዝያ ፭(5)
❀✞ ስቅለት፥ ሚያዝያ ፲(10)
❀✞ ትንሣኤ፥ ሚያዝያ ፲፪(12)
❀✞ ርክበ ካህናት፥ ግንቦት ፮(6)
❀✞ ዕርገት፥ ግንቦት ፳፩(21)
❀✞ ጰራቅሊጦስ፥ ሠኔ ፩(1)
❀✞ ጾመ ሐዋርያት፥ ሠኔ ፪(2)
❀✞ ምሕላ ድኅነት፥ ሠኔ፬(4)

🌻🌼✞ እንኳን አደረሳችሁ ✞🌼🌻
🌻🌼✞ እንኳን አደረሰን ✞🌼🌻

🌻🌻 በእግዚአብሔር ፈቃድ 🌻🌻
🌾መጪው ፳፻፲፯ ዓ.ም፦
🌻የተከፋ፣ የአዘነና የአለቀሰ፤ የሚደሰትበት።
🌻የተራበና የተጠማ፤ የሚጠግብበት።
🌻የተሰደደ፤ በሰላም ተመልሶ የሚኖርበት።
🌻ፍቅር፣ ዕምነትና ትዕግሥት፤ የምንጎናጸፍበት።
🌻ዕውቀቱን፣ ጥበብና ማስተዋሉን፤ የምናገኝበት።
🌻ከችግርና ከመከራ፤ ተላቀን በሐይማኖት በምግባር የምንጸናበት ዘመን ይሁንልን። ✞አሜን✞
🙏✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ✞🙏

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

23 Aug, 03:07


#ተመስገን


ተመስገን አምላኬ
ተመስገን ተመስገን
ባከነም ተኖረ  ለቆጠርኩት ዕድሜ
ላሳለፍኩት ዘመን ...

እያየህ ላለፍከኝ ህግህን ስቀጥፍ
ጸጸት ሳያውከኝ ለሚወስደኝ እንቅልፍ

ላልሰለቸኝ ልብህ እያደር ስቀየር
ስቤ ላወጣሁት የተቃጠለ አየር

ለገረፈኝ ጅራፍ ላበረታኝ ክንድህ
ስፍገመገም ነጥቆ ለሚያወጣኝ እጅህ ...

ተመስገን ተመስገን
ተመስገን ለሁሉም
ያንተው ናቸውና ደስታውም ስቃዪም !!

@kiyorna


@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim


#Join_and_share🙏

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

21 Aug, 19:01


ብርሃኑን ያዩ የወደቁለት
ይህች ሴት ቻለች ማቀፍ መለኮት
ንፅሕት
ቅድስት
ቡርክት
እመቤት
ድንግል
እናት
በማን በምን እንመስላት?
ብለው አበው ነ' የከትቧት
ቢያጡ ቃላት መመሰያ
እርሷን መጥሪያ
.............
ብቻ...
ቢያቀምሱኝ ሐዋርያት
ተመኘሁኝ እኔም ላያት
ከሰበኗ እንዳገኝ ፈውስ
በደመና እንዳገኛት እንደ ቶማስ
ከእጄ አንዲያርፍ መቀነቷ
ከሱባኤው ገባሁ ቤቷ
ንዒ አልኳት ለሊት ቆሜ
ከውዳሴው ከሰዐታት ደጋግሜ
..............
ሙኃዘ ትፍስሕት የፍቅር ውሀ መቅጃ
ተጎናፅፈሽ ያለሽ ወርቀ ዘቦ ግምጃ
ልተርፍ እወዳለሁ ዛሬም ባንቺ ምልጃ
ልነደፍ በፍቅርሽ ክበቢኝ በብርሃን
ስምሽን እየጠራሁ ልደርድር ዲሎሳን
...........
ከዳዊት ጋር ባይገዳደር ምስጋናዬ
ባይሆንልኝ እንደ ያሬድ ዝማሬዬ
ተማጸንኋት ማሪኝ ብዬ
ቢበራልኝ ልቡናዬ
........
እንድትቸረኝ መሸፈኛ ለእርቃኔ
እንዲታደስ ያጎደፍኩት ያን ዘመኔ
በኃጢአት ክፉ ሽታ ብከረፋ
ደጇ ቆሜ ሳልቆርጥ ተስፋ
ሳላቋርጥ ስሟን ጠራሁ
ለምላሿ መቀበያ 'ጄን ዘረጋሁ
......
ይልቃል ፍቅርሽ ከወይን ዘለላ
ሸሽጊኝ ድንግል በረድኤትሽ ጥላ
እያልኩ ከረምኩ ሆኜ ከቅጥሯ
አይዘጋምና የምሕረት በሯ
.........
ሁለት ሱባኤ ደጇ እንደጠናሁ
እንባ ጸሎቴ ሰምሮልኝ አየሁ
ደግሞ....
ልክ እንደ ልጇ ማረጓን ሰማሁ
........
አረገች አሉኝ ድንግል በደመና
እኔ ግን አልኩኝ....
ሰማይ ሰማይን ቻለ ሊሸከም
የፀሐይ መውጫ ድንግል
ማርያምም ሰማይ ናትና።

ኤልዔዘር

#እንኳን_ለእናታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም_የዕርገት_በዓል_አደረሳችሁ!!!


@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim


#Join_and_share🙏

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

19 Aug, 19:10


#ደብረ_ታቦር
.
.
ብርሃነ መለኮት ከተገለፀበት፤
መልኩ ተለዉጦ ፀዳል በሆነበት፤

አብም ስለ ልጁ እርሱን ስሙት ብሎ ከመሰከረበት፤
የጌታ አምላክነት የሥላሴ ምስጢር ከተሰበከበት፤

ልብን ከሚመስጥ ከዚህ ድንቅ ስፍራ፤
መንፈስ ከሚያድስ ከታቦር ተራራ፤

በዚህ መኖር ለእኛ .......
እጅጉን መልካም ነዉ ከጌታችን ጋራ።

እንኳን አደረሳችሁ

በዔደን ታደሰ

@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

18 Aug, 18:18


+++ "የምወደው ልጄ ይህ ነው" +++

ጌታችን ከሐዋርያቱ መካከል "አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ጴጥሮስ፣ ዮሐንስንም" ወደ ቅዱሱ የታቦር ተራራ ብቻቸውን ይዟቸው ወጣ።(ገላ 2፥9) ከተራራውም ጫፍ ሲደርሱ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የመምህራቸው ፊት እንደ ፀሐይ ሲያበራ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሲሆን ተመለከቱ። እነሆም ከቀደሙት ጻድቃን ታላላቆቹ ሙሴና ኤልያስ በታቦር ተገኝተው ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

እነዚህ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የትንቢታቸው ፍጻሜ ከሆነው ክርስቶስ ጋር ምን ተነጋገሩ? መቼም በጊዜው ከጌታ ጋር ውለው ያድሩ እንደ ነበሩት ተማሪዎቹ ሐዋርያት "አትሙትብን" አይሉትም። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሱባኤ የያዙለትና ደጅ የጠኑት የድኅነት ተስፋ እናዳይፈጸም "ይቅር አትሙት" እንዴት ይላሉ? ስለዚህ ከብሔረ ሕያዋን የመጣው ኤልያስና ከብሔረ ሙታን የመጣው ሙሴ በአንድ ላይ "በኢየሩሳሌም ሊፈጸም ስላለው ስለ መውጣቱ (ስለ መከራው፣ ሞቱ)" ያነጋግሩት ነበር።(ሉቃ 9፥31)

በታቦር ተራራ ላይ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መልእክተኞች ተገናኙ። በባሕር ላይ በእግሩ የተራመደው ጴጥሮስ፣ የኤርትራን ባሕር እጁን ዘርግቶ የከፈለው ሙሴን አየው።(ማቴ 14፥29፣ ዘጸአ 14፥21) የሰማርያ ሰዎች በተቃወሙ ጊዜ "እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው" ያሉ ያዕቆብና ዮሐንስ፣ ከሰማይ እሳት አዝንሞ ሃምሳ አንዱን ወታደሮች ያስበላ ኤልያስን ተመለከቱት።(ሉቃ 9፥54፣ 2ኛ ነገ 1፥10)

ሁለቱ ምስክሮች እንደ ተሰወሩም ወዲያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ ሦስት ዳሶች እንሥራ ብሎ ጌታውን ጠየቀ። ሐዋርያው በዚህ ተራራ ላይ መቅረት የፈለገው ያለ ምክንያት አይደለም። መድኃኒታችን አስቀድሞ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ዘንድ ብዙ መከራ ይቀበልና ይሞት ዘንድ እንዳለው ሲነግራቸው ቅዱስ ጴጥሮስ "አይሁንብህ፤ አይድረስብህ" ሲል ሊከላከለው ሞክሮ ነበር። ለዚህም በጊዜ "ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል" ተብሎ ተገስጾበታል።(ማር 9፥31-33) ይሁን እንጂ አሁንም ቅዱስ ጴጥሮስ ያለውን ሁሉ እድል ተጠቅሞ ጌታን ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄድና በካህናት አለቆች እጅ ተላልፎ ከመሰጠት ማስቀረት ስለሚፈልግ "ጌታ ሆይ፦ በዚህ(በታቦር ተራራ) መሆን ለእኛ መልካም ነው" ብሎ ተናገረ።

እርሱም ይህን ገና ሲናገር ሳለ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው። ከደመናው "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት" የሚል ድምፅ መጣ። ሐዋርያቱ ይህን ድምጽ የሰሙት ሙሴ እና ኤልያስ ከክርስቶስ ተለይተው ከሄዱ፣ እነርሱም ወድቀው ከነበሩበት ከተነሡ በኋላ ነው። ይህም ከደመናው ውስጥ ሲወጣ ስለ ሰሙት ቃል "ለማን የተነገረ ይሆን?" ብለው እንዳይጠይቁና ምስክርነቱ ለክርስቶስ ብቻ የተሰጠ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ እንዲረዱ ነው። በዚሁም ላይ ደመናው ወርዶ የጋረደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ ሳይሆን ሐዋርያቱንም ጭምር ነበር። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሚነግረን ደመናው ጌታን ብቻ ጋርዶት ቢሆን ኖሮ፣ ሐዋርያቱ "እርሱን ስሙት" የሚለውን ቃል ራሱ ክርስቶስ ለራሱ የተናገረው ሊመስላቸው በቻለ ነበር።

ቅዱስ ጴጥሮስ "አትሙት" ያለው መምህሩን በፍጹም ልቡ ስለሚወደው መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን ጴጥሮስ ጌታን የቱንም ያህል ቢወደው፣ ፍቅሩ ግን ከወለደው ከባሕርይ አባቱ ከአብ አይደለም ሊበልጥ ሊነጻጸርም አይችልም። ታዲያ አብ በእርሱ ደስ የሚለው፣ የሚወደው፣ አንድያ ልጁ እንዲሞት ፈቃዱ ከሆነ፣ የአብን ያህል ሊወደው የማችለው አረጋዊው ጴጥሮስ ለምን "አትሙት" እያለ ይቃወማል?!

አብ ምትክ የሌለው ልጁ ወልድ ሰው ሆኖ በክፉዎች እጅ ሲንገላታ እና እስከ መስቀል ሞት ሲደርስ እያየ ዝም ያለው ስለማይወደው አይደለም። ዓለም ያለ ልጁ መከራና ሞት ስለማትድን ነው እንጂ። ከዚህ ምን እንማራለን? ዛሬም ወደ መከራ የምንገባ የጸጋ ልጆቹ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች "እግዚአብሔር እንዲህ ስሆን ዝም ያለኝ ስለማይወደኝ ነው" አንበል። ባገኘን ጥቂት የሥጋ መከራና ሕመም የሚበልጠውን የነፍስ ጤና የምንሸምት ከሆነ እግዚአብሔር ዝም ይላል። ዝም የሚለው መከራችንን ስለማያይ ሳይሆን ከመከራው ጀርባ ያለው ዓላማ ታላቅና የተቀደሰ እንደ ሆነ ስለሚያውቅ ነው።

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ነሐሴ 13፣ 2014 ዓ.ም.
ደብረ ታቦር፣ እስራኤል

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

14 Aug, 13:07


ግልብ ነው ነገሬ
ድልብ ነው ነውሬ

ፍቅርሽ ድርብ በፍታ
ሸፈነልኝ ሁሉን
እስርስሩን ፈታ
በለመንኹሽ አፍታ

አበረደው ጥሉን
አወረደው ጠሉን
ልቤ ተራራ ላይ

አጮልቄ እንዳይ
አሸብርቄ እንድታይ
ደፋብኝ ጸበሉን
ዝቅ አርጎት ጠለሉን።

***

የብርሃን እናት ደጅ ኩራዝ ይዤ መጣሁ
ከምስራቋ በራ'ፍ
ያ'ለም ጸሐይ ናፍቆኝ ትንሽ ኮከብ ወጣሁ፤

በጸሎቷ አቅም
በምሕረቱ ብዛት
በረከት ስለቅም
ላምባዬን ሲያበዛት፥

አማረበት በጣም፣ ደመቀ ሰማዩ
ልጥግብ ከመዓዛሽ፣ ልሙቅ ከጸሐዩ።

ዮሐንስ ሞላ


@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim


#Join_and_Share🙏

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

06 Aug, 15:16


#ሱባዔ

ሱባዔ ምንድን ነው ?
ሱባኤ በሰዋሰው ትርጉሙ "ሰባት"ማለት ሲሆን በመንፈስ አተረጋጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከ ዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪየ ጋር እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው ፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ ፦ ፈጣሪ አለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፋጥረትን ከመፋጠር ማረፋ ፥ለጸሎት የሚተጉ ምዕመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥር ፋጹምነት ያመለክታል ፡፡ (ዘፍ 2፥2 , መዝ 118፥164) አንድ ሰው 7 ቀናት ቢጾም "አንድ ሱባኤ ጾመ" ይባላል ፡፡

ሱባኤ መቼ ተጀመረ?
የተጀመረው ከውድቀት በሓላ በመጀመርያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት እንዳስተማሩት የቤተ ክርስቲያናችን መዛግብት ያስረዳሉ በምላሹም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስጋን ለብሼ ከ 5 ቀን ተኩል በኋላ አድንሃለሁ የሚለውን ቃል ኪዳን የሰማው ሱባኤ በመግባቱ ነው፡፡

ሱባዔ ለምን ይጠቅማል?
የሰው ልጅ ሓጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈፀመው በደል ህሊናው ይወቅሰዋል ይጸጸታል፡፡ በመጀመርያ ደፋሮ በሰራው ሀጥያት በኋላ ይደነግጣል ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፋጥረት ኀሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው ፡፡ በዚህ ግዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኝት ያስባል ይተክዛል፡፡ ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ አለም ሲያስጨንቀው  ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት  መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይህውም በጥቂት ድካም ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡

1- እግዚአብሔርን ለመማጸን፦
ማንኛውም ሰው ሱባኤ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው ( የምንማፀነው) ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኝው መልስ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ሱባኤ ከመግባታችን በፊት፦ ሱባዔ የምንገባው ለምንድን ነው ?  በማለት እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ፡፡

2- የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ
ቅዱሳን አባቶችና እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባኤ የቅዱሳን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ በጾመ ነብያት የነብያትን፣ በጾመ ሀዋርያት የሀዋርያትን፣ በጾመ ፋልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፋ ሱባኤ መግባት የነበረ ነው፡፡

የሱባዔ አይነቶች፦
1- የግል ሱባኤ ( ዝግ ሱባዔ)፦
አንድ ሰው ብቻውን አመች ቦታ ማንም ሳያየው በግሉ የጸሎት በአቱን ዘግቶ በሰቂለ ኀሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው በኀቡዕ የሚፈፅመው ሱባኤ ነው ፡፡

2- የማህበር ሱባዔ፦
ካህናት ምዕመናን ወንዶች ሴቶች ሽማግሌወች ፤ወጣቶች ፤በአንድ ሆነው በቤተ ክርስትያንና አመች በሆኑ ቦታወች ሁሉ ተሰብስበው የሚገብት ሱባዔ ነው፡፡

3- የአዋጅ ሱባዔ፦
በሀገር  ላይ ድንገተኛ አደጋ ፤ አባር ቸነፈር ጦርነት ሲነሳ እንዲሁም በማህበረ ምዕመናን ላይ አስጊ የሆነ መቅሰፋት ሲከሰት እግዚአብሔር መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግስት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ አይነት ነው፡፡

ለሱባዔ የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት፦
ሱባኤ ከመግባታችንም ሆነ ከገባን ግዜ እንዲሁም ከጨረስን በኋላ ምእመናን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባናል፡፡

➢ ሱባኤ ከመግባት አስቀድሞ
በመጀመርያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል ፡፡
፪ ሱባኤ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሃ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
፫ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል ፡፡ሱባኤ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡
፬ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተክርስቲያናችን በአብዛሀኛው ግዜ ሱባዔ የሚገባው በአጽዋማት ወቅት በመሆኑ ይህንን መለየት ነው፡፡ ምክንያቱም በጾም ወቅት ብዙ አባቶች ጸሎት የሚይዙበት ስለሆነ ፀሎታችን ከእነርሱ ጋር አብሮ ያርግልናልና ነው፡፡ እዚህ ላይ በማንኛውም ግዜ ሱባኤ አይያዝም ለማለት አይደለም በማንኛውም ግዜ ፈተና ያጋጠመው ሰው ሱባዔ ሊይዝ ይችላል፡፡

➢ በሱባዔ ግዜ 
ሀ. በጸሎት ሰአት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምስራቅ መልሶ መቆም ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰቂለ ህሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡
ለ . በቅደም ተከተል መፀለይ ይገባል በመጀመርያ አአተብ ከሚለው ተጀምሮ አቡነ ዘበሰማያትን ጠቅሶ ጸሎተ ሀይማኖትን መጨረስ ፡፡ሰግዱ እና ስለ መስቀል በሚያነሳው ላይ እየሰገዱና እያማተቡ መጸለይ ፡፡ በማስቀጠል አቡነ ዘበሰማያት ፤መዝሙረ ዳዊት ውዳሴ ማርያም ሌሎችንም ማስከተል ከዚያ 41 ግዜ ኪራላይሶ ይባላል ፡፡
ሐ.  በሱባዔ ግዜ ከተሐራሚው የሚጠበቀው ነገር ሐጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ለእያንዳንዱ በደል ማልቀስ ማዘን ይገባዋል ፡፡
መ.  በመጨረሻም ሱባዔ የገባው ሰው ሱበዔውን ሳይጨርስ ወይም አቋርጦ ከማንኛውም ሰው ጋር ፈፅሞ መገናኝት የለበትም ፡፡

3- ከሱባዔ በኋላ
ላቀረብነው ተማፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር  መጠበቅ ይኖርብናል። ሱባዔ የገባ ሰው ሁሉ ራዕይ ላያይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኝው የህሊና ሰላም ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባኤ ገብተን ያሰብነውን  ካላገኝን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት በመማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡፡

መጭው ጾመ ፋልሰታ (የመቤታችን ጾም ) በመባል የሚታወቀው እና ቤተ ክርስቲያናችን አበይት አጽዋማት ብላ ከደነገገቻቸው ወስጥ አንዱ ነው ፡፡ በዚህ ወራት ብዙዎቹ አባቶቻችንና እናቶቻችን በረከተ ስጋ ወነፍስ ያገኙበት የበረከት ጾም ነው እኛም ቢቻለን በሱባኤ ባይቻለን አቅማችን የፈቀደውን እየጾምን በጸሎት አምላካችንን መጠየቅ እንዲሁም እመቤታችን በምልጃዋ  ታስበን ዘንድ መማፅን ያስፈልገናል ፡፡


(ቃለ ተዋሥኦ ቁጥር 2 )

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
D.N  Yarrgal abegaz

እንኳን ለፆመ ፍልሰታ አደረሳችሁ

#መልካም_ፆመ_ፍልሰታ
     

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

25 Jul, 19:50


#ቅዱስ_ገብርኤል

የንጉስ ጭካኔ ፥ ክንዱ ቢበረታ፤
ለጣዖት ሳንሰግድ፥ እኛ ሳንረታ፡፡
የምናምነው አምላክ፥ ሊያድነን ወደደ፤
ገብርኤል መጣና፥  እሳቱ በረደ፡፡

ፍላፃና ሠይፉን፥ አጠፈው መላኩ፤
ሰላም ይዞ መጣ፥ ባለም ለታወኩ፡፡
አትጠራጠሩ፥ ምልጃው ያስምረናል፤
የሚነደው እሳት፥ ሳይነካን ወተናል፡፡

የሰልስቱ ደቂቅ፥ የእየሉጣ ብርታት፤
የድንግል አብሳሪ፥ የቂርቆስ ረዳት፡፡
በሚመጣው አለም፥ እንዳይበላኝ እሳት፤
አማልደኝ ከጌታ፥ ነፍሴን እንዲምራት፡፡

የነገርኩህ ሁሉ፥ በቀኑ ደረሰ ፤
በዘብር ገብርኤል፥ እንባዬ ታበሰ፡፡
ና ልጄ ስትለኝ፥ አልልህም እንቢ፤
ስለቴን ተቀበል፥ አባቴ ቁልቢ፡፡

የልቤን ነግሬህ፥ የቁልቢው ገብርኤል፤
ሳትረሳ ፈፀምከው፥ ስለቴን  ተቀበል፡፡
ለንግስ እንመጣለን፥ አንተ አትረሳምና፤
ደሞ የዛሬ አመት፥ አድርሰን በደህና፡፡


እንኳን ለሃያሉ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን!!!

@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim


#Join_and_Share🙏

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

17 Jul, 04:54


#ጳውሎስ

በኪልቅያ ጠርሴስ፣ የተዘራህ ፍሬ
ከሮም የተገኘህ፣ የወንጌል ገበሬ
ከኦሪቱ ምሁር፣ ከገማልያል እግር
ጠንቅቀህ የተማርህ፣ የኦሪትን ግብር

ታዛዥ ለሙሴ ሕግ፣ ቀናኢ ለሥርዓት መሆንህንአይቶ፣ አምላክ በቸርነት
ሳውል ሳውል የሚል፣ የተሳዳጅ ጥሪ
ጽልመትን የሚገፍ፣ የዓለም ፈጣሪ

የእረኛውን በጎችን፣ ስታስር ስታባርር
በደማስቆ ጣለህ ፣ክርስቶስ በፍቅር
አሮጌውን ዓይን፣ በሚያድስ ብርሃን
ሊሰጥህ ወደደ፣ ሰማያዊውን ዓይን

ሠራዊት ነህና፣ ከጥልቁ ተዋጊ
በኃይል እንድትሆን፣ ብርቱ ፋና ወጊ
የሃይማኖት ዝናር፣ አስታጠቀህ ወንጌል
አይሁድና አሕዛብን፣ እንድታገለግል

ከጌታ ጋር ሳትዞር የእጁን ተአምር ሳታይ
በደማስቆ ምርኮ ለመባል የበቃህ ሐዋርያው ኅሩይ
የአስማተኞች ብልጠት፣ የጠርጡለስም ክስ ሳያስደነግጥህ፣ የሮም ጨካኝ ንጉሥ

በእነ ቤርያሱስ፣ በእነ አርጤምስ ቤት
የሮማን አማልክት፣ የግሪክን ጣኦት
ርኩሰት ከንቱነት፣ ገልጠህ እያሳየህ
በክርስቶስ ትምህርት፣ ድቅድቁን አበራህ

የፈሪሳውያንን፣ አሳሳች ትምህርቶች
የቢጽ ሐሳውያንን፣ የጎበጡ ልቦች
ተርትረህ አቀናህ፣ የደረቀ እንዲያብብ
ብሉይን ከሐዲስ፣ አጋምደህ በጥበብ

በቆጵሮስ ጵንፍሊያ፣ ጰርጌን አንፆኪያ
ኢቆንዮን ተርሴስ፣ ቆሮንቶስ ገላቲያ
በዐረብ በልስጥራን፣ እልዋሪቆን ሦሪያ

ወኅኒ የሚያናውጽ፣ የመዝሙርህ ቅኝት
ድውይ የሚፈውስ፣ ጥላህ ያረፈበት
መከራና እንግልት: እስር ግርፉቱ
ላንተ ቦታ የለው፣ ሁሉ የከንቱ ከንቱ

አምስቱ መልእክታት፣ በእስር ተጻፉ
የአይሁድን ስድብ፣ ትቢያ አራገፉ
በብርሃን ወድቀህ፣ ብርሃን የተባልህ
ደጉ ሐዋርያ፣ ጳውሎስ ቅዱስ ነህ

እኛም ግልገሎችህ፣ ስንኖር በዚህ ዓለም
ጸላኢ በርትቶ፣ እንቅልፍ ቢነሳንም
ፍሬ የታጣበት፣ ባዶ ቤታችንን በሃይማኖት-ምግባር፣ እረስ ልባችንን
በኃይል በትጋትህ: በፀጋህ አለኝታ
ባዝነን እንዳንቀር: አማልደን ከጌታ::

@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim


#Join_and_Share🙏

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

04 Jul, 08:07


#መድሃኔዓለም_ነው!

ከሰማያት ወርዶ
ከድንግል ተወልዶ
ክብሩን ሁሉ ትቶ
ያከበረኝ ሞቶ
የነፍሴ ቤዛዋ
ዘውድ ማአረጉዋ
የንጉሶች ንጉስ
የድኩማን ሞገስ
አምላኬ የምለው
መድሃኔዓለም ነው።

              ቃልኪዳን ተፈራ

@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

19 Jun, 12:28


#የአፎምያ_አጽናኝ
   
ከቀደመው መንገድ ከላይ በተሰጠን
ዕድሳት በማያውቅ በማይሻርው ዘመን
በድንቅ ምስክሮች ብርሃን በሆኑን
እንድንጓዝ ሁሌም የአፎምያ አጽናኝ
ጠላት ቀስቱን ሰብቆ ሊያጠፋን ሲመጣ
እንደ ቋጥኝ ከቦን የዚህ አለም ጣጣ
በከንቱ ስንሮጥ ኋላ እንዳንቀጣ
አማልደን መላኩ የነፍሳችን ዕጣ
የሁሉንም ጸሎት ከአምላክ የምታደርስ
ፍቅር እና ርህራሄ በሰው የምታለብስ
ልክ እንደ ትላንቱ ዛሬም ፈጥነህ ድረስ
በአንደበትህ ፍሬ ውስጣችን ይታደስ
የዳንኤል አጽናኝ የአፎምያ ረዳት
በህይወት የቀየርክ የባህራንን ጽሕፈት
በለአምን የታደክ ከእርግማን መቅጸፍት
እኛንም ጠብቀን ከምናየው መአት
የምጽአት ዋዜማ ለመሆኑ ምስክር
በመጽሐፍ ያለው ቃሉ ሲተገበር
መተማመን ጠፍቶ ሲቀዘቅዝ ፍቅር
በወንጌሉ አንድምታ ልባችን ይታጠር
ይቅርታ ምህርቱ ይምጣልን የእግዚአብሔር
እረኛ እንደሌለው ሲጨነቅ ትውልዱ
ተመሳስሎ ቆሞ ሲያስት በመንገዱ
ግራ በመጋት ስንቶቹ ተጎዱ
በየዋህነታቸው አብረው ተሰደዱ
ዘንዶ አፉን ከፍቶ ነፍሳት እንዳይወጥ
የተዋህዶን መዝገብ እውነቱን ለመግለጥ
የቆመውን ሁሉ በአውደ ምህረቱ
ያበረታን አምላክ እሰከ ምጽአቱ።

          
እንኳን ለሊቀመላአኩ ለቅዱስ ሚካኤል ክብር በዓል በሰላም አደርሳቹ አደረሰን የመላአኩ ረድኤት እና ምልጃው አይለየን አሜን!

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

19 Jun, 04:58


#ከዲያብሎስ_መንጋጋ_ቅድስት_አፎሚያን_ያስጣለበት ።
   

#ቅድስት_አፎሚያ ሀገሯ ኪልቅያ ነው ባለቤቷ አስተራኒቆስ ይባላል የኪልቅያ መስፍን ነበረ  ታሞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ አፎምያ ከሀብቷ ከንብረቷ ለነዳያን እየሰጠች እየመጸወተች በጾም በጸሎት ተወስ ትኖር ነበር

ሰይጣን ለምቀኝነት አያርፍምና ደግ መነኩሴ መስሎ አጋንንትን ሴት መነኮሳይያት አስመስሎ መጥቶ ደጅ ሆኖ አስጠራት ከቤት ገብታችሁ በቅዱስ ሚካአል ሥዕል ፊት ጸልዩልኝ አለቻቸው ።

መነኩሴውም እኛማ በነግህ ጸልየናል እንደው አንቺ ግን ይህ ሁሉ ጾም ጸሎት ምን ያደርግልሻል ? በዚያም ላይ ስትደክሚ የሚደግፍሽ ስታረጂ የሚጦርሽ ልጅ የለሽም እነአብርሃም እነዳዊት ከብዙ ሴቶች ብዙ ልጆች ወልደው የለምን ስለዚህ ቤት ሠሪ ጎመን ዘሪ ጧሪ ቀባሪ ልጅ ያስፈልግሻል ባል አግብተሽ ብትኖሪ ይሻልሻል አላት ።

❝ #ቆብህ_መልካም_ነበር_ንግግርህ_ግን_ክፉ_ነው ❞ አትጹሚ አትጸልይ ያልከኝ ጌታችን ❝ #ከመሥዋዕት_ይልቅ_ምጽዋትን_እመርጣለሁ ❞ ብሎ የለምን ፤ ሁለተኛ ባል አግቢ ማለትንስ ከምን አገኘኸው ርግቦች እንኳን ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ከሌላ ወንድ አይቀርቡም ታዲያ ጥንቱን በንጽሕና ሊኖር የተፈጠረ ሰው ሁለተኛ አላገባም ብሎ ቢኖር ዕዳ ፍዳ ሊሆንበት ነውን ? ብላ ባሏ ታሞ ሳለ ያሠራላትን ሥዕለ #ቅዱስ_ሚካኤል አውጥታ ብታሳየው ሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን መጥቼ ከተመካሽበት ከዚህ ግብሱስ ሥዕል ጋር አጠፋሻለሁ ብሎ ዝቶባት እንደ ትቢያ በኖ ጠፍቷል ::

#ሰኔ_12 ቀን በነግህ ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጥቶ ጾም ጸሎትሽ ፣ ስግደት ምጽዋትሽ ዐርጎልሻል ያ ስሁት አጠፋሻለሁ እንዳለሽ አውቄ ላድንሽ መጥቻለሁና አላት አንተ ማነህ ? አለችው ሊቀ መላእክት ሚካኤል ነኝ አላት
የንጉሥ መልእከተኛ ያለማኅተም ይሄዳልን ? በትረ መስቀልህ ወዴት አለ ? አለችው ።

መስቀል አሲዞ መሣል ልማድ ነው እንጂ እኛስ አንይዝም አላት ቆየኝ ሥዕሉን ላምጣልህ ብላ ዘወር ስትል አርአያውን ለውጦ ደብረ ጽልመት መስሎ አንገቷን አነቃት #ቅዱስ_ሚካኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥኖ ደርሶ ቀጥቶ አስምሎ ገዝቶ እመቀ እመቅ ጥሎታል ።

እሷንም ብፅዕት ሆይ ጾም ጸሎትሽ ስጊድ ምጽዋትሽ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶልሻል ፤ ዕረፍትሽ ዛሬ ነው ብሏት ዐርጓል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዳ ሥጋውን ደሙን ተቀብላ ጳጳሱንና ካህናቱን ወደ ቤት ጠርታ አብልታ አጠጥታ ወርቋን ብሯን ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ለድሆች ምጽዋት ያደርገው ዘንድ ለጳጳሱ አደራ ሰጥታ ዐርፋለች ።

#የቅዱስ_ሚካኤል ሥዕሉም ከእቅፏ ወጥቶ በርሮ ማንም ሳይሰቅለው ከቤተ መቅደስ በር ላይ ተሰቅሎ ተገኝቷል ኋላም አብቦ አፍርቶ በአበባው በፍሬው ሕሙማንን የሚፈውስ ሆኗል ይህ የእግዚአብሔር ተአምር ነው ፤ ዛሬም ስለማይመዘገብ ነው እንጂ እግዚአብሔር በመላእክቱ ላይ እያደረ ዘወትር ተአምር ያደርጋል ።

በዚህ መሠረት መጋቤ ብሉይ ሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል በተአምራቱ ዘወትር እንደሚጠብቀን ባሕረ ጥበባት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር  ❝ የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል የቀን እረኛ የሌሊት ጠባቂ ክንፎቹ የእሳት የኾነ #ቅዱስ_ሚካኤል ዘወትር የሚጠብቅ የእውነት ድንኳን ከተማ ነው ። ❞ በማለት ተናግሯል ።

ድንኳን ከቀን ሐሩር ከሌሊት ቁር እንደሚከለሉበት ሁሉ #ቅዱስ_ሚካኤልም በቃል ኪዳኑም የሚታመኑትን ሁሉ ከምሕረት አልባ ከዲያብሎስ ደባ ፤ አጋንንት ድብደባ ፣ ከዚህ ዓለም ፈተና ያድናቸዋልና

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

19 Jun, 04:56


#የባሕራንን_የሞቱን_ጦማር_ቀዶ_ሠርግ_ያደረገ_መልአክ
    

በእስክንድርያ እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያመልኩ ፣ ቅዱስ ሚካኤልንም የሚወዱና ወርኃዊ በዓሉን የሚያከብሩ ደጋጎች ባልና ሚስት ነበሩ ። እነዚህ ባልና ሚስት በየወሩ #በቅዱስ_ሚካኤል በዓል በቅዱስ ሚካኤል ስም ድግስ እየደገሱ ለተራቡ ድሆችና ለጦም አዳሪዎች ሁሉ ያበሉ ይመጸውቱ ነበር ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን የቤቱ አባወራ ጥቂት ታሞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ባልዮው በሞተ ጊዜ ባለቤቱ ፀንሳ ነበር ( እርጉዝ ነበረች ) ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለቤቱ ለመውለድ ደርሳ ምጥ ያዛት ምጡም በጸናባት ጊዜ ከእግዚአብሔር እንዲያማልዳትና ከጭንቋ እንዲያድናት ወደ ቅዱስ ሚካኤል ትለምንና ትማፀን ጀመር በዚያኑ ጊዜ ያለችበት ቤት በድንገት በብርሃን ተሞላ እሷም ከጭንቀቷ ዳነች መልኩ ያማረ ወንድ ልጅ ወለደች ።

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን ባረከው  በጐረቤታቸው አንድ ጨካኝ ምሕረት የሌለው ክፉ ባለጸጋ ሰው ነበር ታዲያ ያ የተወለደው ሕፃን የዚያን ባለጸጋ ሀብትና ንብረት እርሻውንም ሁሉ እንደሚወርስ ቅዱስ ሚካኤል ለእናቱ ነገራት ይህንም ነገር በቤቱ ውስጥ የነበሩት ሁሉ ሰምተው ስለነበር ወሬው ተዛምቶ ባለጸጋው ጆሮ ደረሰ

ባለጸጋውም ይህንን ወሬ በሰማ ጊዜ ሕፃኑን ለመግደል ምክንያት ይፈልግ ጀመር የልጁም ዕድሜ አሥር ዓመት በሆነው ጊዜ ፣ እናቱ ገንዘቧ ሁሉ በማለቁ ከችግር ላይ ወደቀች ያም ርኅራኄ የሌለው ባለጸጋ ይህን ባወቀ ጊዜ ልጅሽ እንዲላላከኝ ስጭኝ በምቾትና በድሎት አኖረዋለሁ ! ትምህርትም አስተምረዋለሁ በአጠቃላይ እንደ ልጄ አድርጌ አሳድገዋለሁ ላንቺም በቂ ገንዘብ ( አንድ ወቄት ወርቅ ) እሰጥሻለሁ ›› አላት ።

ሴትየዋም ይህን በሰማች ጊዜ ስለ ችግሯ ደስ ብሏት ልጇን ሰጠችው ። ያም ባለጸጋ ልጁን የወሰደው ለማሳደግ ሳይሆን እንዳይወርሰው ለመግደል ነበር ለእርሷ ኻያ ወቄት ወርቅ ሰጥቶ ሕፃኑን ላሳድገው ብሎ ወሰደው ወስዶም በሳጥን ከቶ ከባሕር ጣለው ማዕበል እየገፋ ወስዶ ከወደቡ አደረሰው አንድ በግ ጠባቂ አግኝቶ ወርቅ መስሎት ከቤቱ ወስዶ ቢከፍተው መልከ መልካም ብላቴና ሆኖ አገኘው ።

ልጅ ይሻ ነበርና ደስ አለው ከበላው እያበላ ከጠጣው እያጠጣ አሳደገው  ከብዙ ዓመት በኋላ ያ ባለጸጋ ለንግድ ሲሄድ መሽቶበት ከእነዚህ ቤት አደረ ባሕራን ባሕራን እያለ ሲጠራው ሰምቶ #ባሕራን ማለት ምን ማለት ነው ? አለው ፤ ከባሕር የተገኘ ማለት ነው ብሎ አለው ለምን እንደዚህ አልከው ? አለው ከባሕር ስላገኘሁት ነው አለው መቼ አገኘኸው ?አለው ወሩን አስታውሶ ቀኑን ጠቅሶ ሲነግረው እሱ ከጣለበት ጊዜ አንድ ሆኖ ቢያገኘው ለካ አልሞተም ብሎ ሲነጋ እባክህ ወዳጄ አንድ ነገር ላስቸግርህ ከቤት የረሳሁት ዕቃ ነበር የድካሙን ዋጋ ለአንተ እሰጣለሁ ልጅህን ልላከው ፍቀድልኝ አለው እሺ አለው ።

ደብዳቤ ጽፎ ❝ ይህ ልጅ እንደ ደረሰ ግደሉት ❞ ብሎ አትሞ ምልክቱን ነግሮ ስንቁን አሲዞ እንደ ይሁዳ በሽንገላ ስሞ ሰደደው ባሕራንም ዘጠኝ ቀን ተጉዞ የአንድ ቀን ጎዳና ሲቀረው ቅዱስ ሚካኤል በአምሳለ ሊቀ ሐራ በፈረስ ተቀምጦ መላእክትን እንደ ሠራዊት አስከትሎ ከመንገድ ተገናኘው አንተ ልጅ ወዴት ትሄዳለህ አለው እንዲህ ካለ ቦታ መልእክት ላደርስ እየሄድኩ ነው አለው ።

እስኪ መልእክቱን አሳየኝ አለው ፤ ጌታዬ ለማንም አታሳይ ብሎኛል አለው ያም ባይሆን እንደተጠቀለለ አሳየኝ አለው ደብዳቤው እንደታጠፈ እፍ ቢልበት የሞቱን ትእዛዝ አጥፍቶ የሕይወት ትእዛዝ ጽፎበታል ያንጊዜ ይዞ ሄደ ፤ ለቤቱ ሹም ሰጠው ገልጦ ቢያነበው "ልጄን ዳሩለት ሀብት ንብረቴን አውርሱት ባሮቼ ይገዙለት ይህ ቃል የእኔ ለመሆነ ምልክቱ እንዲህ ነው ❞ የሚል አነበበ በጌታውም ማኅተም ታትሟልና ሁሉም ነገር ተደረገለት ባለጸጋው ከንግድ ሲመለስ የዘፈን የጨዋታ ድምፅ ሰምቶ አሽከሩን አግኝቶ ይህ ሁሉ ዘፈን ጨዋታ ምን ተገኝቶ ነው ? ብሎ ጠየቀ የላከው ሰው ልጅህን አግብቶ ሀብትህን ወርሶ ይኸው አርባ ቀን ሙሉ ይዘፈናል አለው ደንግጦ ከፈረሱ ወድቆ ሞተ ።

ባሕራንም ይህ ሁሉ #በቅዱስ_ሚካኤል ተራዳኢነት የተደረገለት መሆኑን አምኖ ማዕርገ ቅስና ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያን አሳንጾ ዕድሜውን በሙሉ በቅን ልቡና በትሑት ሰብእና ሲያገለግል ኖሯል ።
        #ከገናናው_መልአክ_ከቅዱስ_ሚካኤል_አምላከ_ቅዱሳን_ረድኤት_በረከትን_ይስጠን

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

19 Jun, 04:54


እንኳን ለመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አመታዊ በዓል አደረሳችሁ!!

+  መልአኩ ነው +

       ሰዓቱ ሌሊት ነው ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚያ ሌሊት መላው የቤተሰባችን አባል አምሽቶ እየተጫወተ ነው፡፡ ከዚህ የቤተሰብ ስብስብ መካከል ሳይገኝ የቀረው አንድ በወኅኒ ቤት የታሰረ ወንድማችን ብቻ ነበር፡፡ ድንገት ግን የጊቢው በር በተደጋጋሚ ተንኳኳና ሁላችንም ጨዋታችንን አቋረጥን፡፡ በሌሊት የሚያንኳኳው ማን ነው ?

ሠራተኛችን ሮጣ ሔደች:: ወዲያው ግን በሩን ሳትከፍተው ተመልሳ እየሮጠች መጣች፡፡ በደስታ ሰክራ ‹‹የታሰረው ልጃችን በር ላይ ቆሟል!›› ብላ ተናገረች፡፡ "በድምፁ አወቅኩት!› እያለች ዘለለች፡፡ ከሁኔታዋ የተነሣ ‹አብደሻል እንዴ!?› አላት ቤተሰቡ ሁሉ፡፡

እስዋ ግን በእርግጠኝነት ተናገረች! በቀን የታሰረው ልጅ በሌሊት ተፈቶ መምጣቱ ፈጽሞ ሊታመንን የማይችል ነገር ነው፡፡ ቤተሰቡ ሁሉ የታሰረው ልጅ መጣ ብሎ አላመነም፡፡ ባይሆን የመንግሥት ወታደሮች የቀረነውን ሊወስዱን ይሆን? ማን ሊሆን ይችላል? ብሎ ተብሰለሰለ:: በመጨረሻም የሁሉም ግምት አንድ ነገር ላይ አረፈ:: ሁሉም ሰው በአንድ ድምፅ አንድ ቃል ተናገረ "መልአኩ ነው!"

  መልአኩ የሰው ስም አይደለም:: ቤተሰቡ የተስማማው "ደጅ የቆመው የታሰረው ልጃችን ሳይሆን እሱን ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተሠጠው ጠባቂ መልአኩ ይሆናል›› ብሎ ነበር፡፡ የበሩ መንኳኳት አሁንም ስላልቆመ ቤተሰቡ ግር ብሎ ወጣና ተቻኩሎ በሩን ከፈተ፡፡ በደጅ የቆመው ግን እንደተባለው የታሰረው ልጅ ራሱ ነበር፡፡ ሁሉም ተደሰተ!!!

      ይህ ገጠመኝ በአሁን ዘመን የተፈጸመ ነው ብዬ ብናገር ማን ያምነኛል? እውነት በሌሊት የቤታችን በር ሲንኳኳ  መልአክ ነው ብለን እንገምታለን? ይህ ቤተሰብ ምን ዓይነት ቤተሰብ ነው?

በብዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ መጀመሪያ የሚመጣው ጥርጣሬ ‹ሌባ ሊገባ ይሆን?› የሚል ስለሚሆን ዱላ ፍለጋ እናማትራለን፡፡ ወይ ደግሞ ሌሊቱ ወደ መንጋቱ እየተቃረበ ከሆነ ‹‹የምን መርዶ ሊያረዱኝ ይሆን? የቱ ዘመዴ ሞቶ ይሆን?› የሚል ጭንቀት ይፈጠራል፡፡

‹የሚያንኳኳው የእግዚአብሔርመልአክ ይሆናል› ብሎ የሚጠረጥር ሰው ግን በዚህ ዘመን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ እንዲህ ብሎ ግምቱን የሚናገር ሰው ከቤተሰባችንመካከል ቢገኝ እንኳን እንደ ዕብድ ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ታዲያ ይህን ገጠመኝ ከየት አመጣኸው ትሉኝ ከሆነ መልሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚል ነው፡፡

      በሐዋርያት ዘመን ሔሮድስ የተባለው ንጉሥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ወኅኒ ቤት ውስጥ ወርውሮት ነበር፡፡ የቀሩት ደቀመዛሙርትና ክርስቲያኖች በዚያ ሰሞን ሲጸልዩ ከርመዋል፡፡ በአንድ ሌሊት በማርቆስ እናት ቤት ውስጥ ተሰብስበው አምሽተው ነበር፡፡ ድንገት የቤቱ በር ሲንኳኳ ሮዴ የምትባል የቤት ሠራተኛ ደጁን ልትከፍት ወጣች፡፡ ማነው ብላ ስትሰማ የቆመው እስረኛው ቅዱስ ጴጥሮስ መሆኑን በድምፁ አወቀች፡፡ ደስታ ግራ ሲያጋባት በሩን መክፈትን ረስታ ወደ ውስጥ ሮጠችና ጴጥሮስ መምጣቱን ተናገረች፡፡ እነርሱ ግን አላመኑአትም፡፡ ጤንነቷን ተጠራጥረው ‹አብደሻል› አሏት፡፡ እርግጠኛ ሆና ተናገረች፡፡ እነርሱ ግን መልሰው ‹‹የቆመው ጴጥሮስ ሳይሆን መልአኩ ነው፡፡›› አሉ፡፡ ይደንቃል የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንዲህ በር ሲንኳኳ ‹መልአክ ነው› ብለው የሚገምቱ መንፈሳዊያን ነበሩ፡፡ (ሐዋ. 12፡12-15)

      ቅዱሳንመላእክት እኛ የሰው ልጆች ከመፈጠራችን ቀድመው የተፈጠሩ ታላቅ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እንዲያውም ምድርና የሰው ልጅ ሲፈጠር ደስ እያላቸው ‹‹እልል›› ይሉ ነበር፡፡ (ኢዮ. 38፡6) ቅዱሳን መላእክትን እግዚአብሔር ለእንዳንዳችን ጠባቂዎች አድርጎ ሠጥቶናል፡፡ ከክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ስለ መላእክት ጠባቂነት ጋር ይህን ያህል እምነት ከነበራቸው እኛም የመላእክቱን ጠባቂነት ማመን ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖችም ምን ያህል ይገባን ይሆን? ቅዱሳን መላእክት በክርስትና ሕይወት ለሚኖርሰው ሁሉ የመላእክት ረዳትነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለሁሉ ብርታት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በሥጋው ወራት በተያዘባት ምሽት ሲጸልይ ‹‹ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ሉቃ. 22፡43) ይህም ቀርበው አገለገሉት‹ለከ ኃይል› እያሉ አመሰገኑት ማለት ሲሆን ለእኛም የመላእክት ርዳታ አያስፈልገኝም እንዳንል የሚያስተምረን ነው፡፡

ቅዱሳን መላእክት በምድር የሚሆነውን ያውቃሉ:: (2 ሳሙ 14:20) በበደላችን ስንጸጸት "ኃጢአትህ ተሠረየችልህ" ይላሉ (ኢሳ 6:7) በክፋታችን ጸንተን ከቀጠልን ደግሞ "ይቅር አይሉም" (ዘጸ 23:20)
ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ቆመው "የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?" ብለው ያማልዳሉ:: (ዘካ 1:12)

ባለንበት ዘመን በዓለም ሁሉ በበሽታ የሚሠቃየው ብዙ ነው::  በሕመም ለሚሠቃየው ሁሉ

"መልአክ ቢገኝለት እየራራለት [ለእግዚአብሔር] ፡— ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው፡ ቢለው፥ ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል" ኢዮ 33:23-25

(ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

08 Jun, 16:36


አበው ይናገሩ

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብር ምን ነበር ምሥጢሩ
የክርስትና ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ
መቃብሩን ክፈቱና አበው ይመስክሩ፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ
ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ፡፡

ነብያት በመጋዝ የተሰነጠቁት
ሐዋርያት ቁልቁል የተዘቀዘቁት
ሰማዕታት በእሳት የተለበለቡት
ቅዱሳን በገዳም ደርቀው የተገኙት
ምሥጢሩ ምን ነበር? አበው ይናገሩት፡፡

ይናገር ዝቋላ ግሸን ላሊበላ
የቅዱሳንን ዐፅም ለምን እንዳልበላ፡፡
ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር
እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡
ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት?
ወይስ ሀብት ንብረት የተሟላ ቤት?
ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት?
እናንተ ገዳማት ምሥጢሩን አውሩት፡፡

ጐበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና
ምግባር ሃይማኖቱ በእጅጉ የቀና፡፡
እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት
ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡
የጊዮርጊስ ወገን የት ነው የማገኘው?
በመሀል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው?
ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው?

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ሰው አማረው
የሃይማኖት ጀግና የትነው የማገኘው?
ልግባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት
ማኅበረ ሥላሴ ከቅዱሳን ቤት?
አክሱም ግሸን ማርያም ከቃል ኪዳን ቦታ
ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ?
ፈሪሐ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ
ቤተ ክርስቲያንን ያልተደፋፈረ፡፡

የት ነው የማገኘው ለሃይማኖቱ ሟች
ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች፡፡
የወገን መመኪያ የከሀዲ መቅሰፍት
ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሣ ቀስቅሱት፡፡

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምሥጢሩ?
የክርስቲያን ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ?
መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ጀግና አማረው
በእምነቱ የፀና የትነው የማገኘው?
ብቅ ይበል እንየው እሱ ማነው ጀግና?

በጐችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ
መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ
የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ
እንደዚያ እንደ ጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ?
የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው
የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?
ምሥጢርን ከምሥጢሩ አንድ አድርጐ ቀምሮ
ወልድ ዋሕድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ
እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ
ከአትናቴዎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር
መሆኗን የሚያምን ማኅደረ እግዚአብሔር
ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን
ትንታግ ምላስም ጭንግፍግፉን
ልሳነ ጤዛ መናፍቅን
ወልደ አርዮስ ዲቃላውን፡፡
በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ
ጀግና ማነው ዝቅ ይበላ፡፡

ነበር ወይ ያን ጊዜ ለሹመት መጓጓት
እስኪ ጎርጎርዮሰ ይምጣና ጠይቁት
ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ
ምሥጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ፡፡

የክርስቶስ ባርያ የአጋንንት መቅሰፍት
ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት
ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት
የጸሎት ገበሬ ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ይነሣ ቀስቅሱት
ይነሣ ጊዮርጊስ ይመስክር ምሥጢር
የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡

ከእናቶቻችንም አሉ ለፍጥረት ያዘኑ
ዲያብሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ፡፡
ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ
መር ብለው የወጡት ከሥጋ ገበያ
ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ፡፡

እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት
ዓላማው ምንድነው የዘመኑ ወጣት፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ
ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡

ምንጭ፡- መለከት 1ኛ ዓመት ቁጥር 6


@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim
@Melikt_weg_gitim


#Join_and_share

መንፈሳዊ ግጥሞች እና ወጎች

19 May, 01:26


ቅዱስ ያሬድ ከዚያ በኋላ ወደ አከሱም ተመልሶ በመደባይ ታብር በተባለ ቦታ ቅዳሴያትን በዜማ አዘጋጅቷል፡፡ ይህ ቦታ ከአከሱም 15 ኪ.ሜ ርቆ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አክሱምን ተሰናብቶ ለመሄድ ወደ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ገባና «ቅድስት ወብጽዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን ማዕርገ ሕይወት» እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን ድርሰቱን ሰተት አድርጎ አዘጋጀው፡፡

ይህንን ድርሰት ሲያዜም አንድ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ብሎ ይታይ ነበር ይባላል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በሰሜንና ወገራ፣ አገውና በጌምድር እየተዘዋወረ አስተምሮ ከሰሜን ተራራዎች ውስጥ እየጾመና እየጸለየ በብሕትውና ለብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ በሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል ባለው በጸለምት ዋሻ ውስጥ በ571 ዓ.ም ግንቦት 11 ቀን ተሠውሯል፡፡

ይህ ቦታ በተለምዶ የሰሜን ተራሮች በሚባለው ወስጥ የሚገኝ ከፍተኛና ብርዳማ ቦታ ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም ሌላ በትምህርት ሂደትም አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ የድጓን፣ የጾመ ድጓን የዝማሬ መዋሥዕትንና የቅዳሴን ትምህርት ከማስተማሩም በላይ ለቅኔ ትምህርትም መሠረት ጥሏል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዓለም የመጀመርው የዜማ ኖታ/ ምልክት/ ባለቤት ነው።

በእውነት የቅዱስ ያሬድን ጸጋ ያብዛልን ረድኤቱ ፣ በረከቱ ፣ ቃል ኪዳኑን ያብዛልን አሜን አሜን።

3,045

subscribers

195

photos

4

videos