አዳም የሰው ልጆች መነሻ ነው ። አዳም የሰው ዘር ግንድ ነው ። የሰው ልጅ ጉዞ የጀመረው በእርሱ የቀጠለውም ከእርሱ አብራክ በተገኙት ልጆች ነው ። ሔዋንም የተገኘችው ከአዳም ነው ። አዳም የመጀመሪያው አባት ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያዋ እናት የሔዋን እናትዋ ነው ። አዳም በኃጢአት በወደቀ ጊዜ ብልየት ወይም እርጅና አገኘው ። ኃጢአት ያስረጃል ፣ የማሰብን አቅም ፣ የመናገርን ብቃት ፣ የመሥራትን ችሎታ ያሳጣል ። በኃጢአት ብልየት ውስጥ ያለ ጽድቅን በነበር ክፋትን በአሁን ያወራል ። አዳም እውነት የሆነውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደ ውሸት ቆጥሮ ሐሰት የሆነውን የዲያብሎስን ቃል እንደ እውነት ተቀበለ ። በዚህ ምክንያት ሐሰተኛ ሆነ ። ሲፈጠር እውነተኛ ግንድ እንዲሆን ነበር ፣ አሁን ሐሰተኛ ግንድ ሆነ ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ዳግማዊ አዳም ተብሎ ነው ። እርሱ ርስት አስመላሽ ፣ ጠላትን ተበቃይ ነው ። ራሱ እውነት ስለሆነ እውነተኛው የወይን ግንድ ነኝ አለ ። ሐሰተኛው የወይን ግንድ መራራ ፍሬ እንድናፈራ ምክንያት ሆነ ። እውነተኛው የወይን ግንድ ግን ጣፋጩን የጽድቅ ፍሬ ለማፍራት አስቻለን ። ግንዱ አዳም ሞቶ ስለነበር ቅርንጫፎቹ የሰው ልጆችም በሞት ተይዘው ነበር ። በክርስቶስ ስናምን ከአሮጌው አዳም ግንድ ተነጥለን በአዲሱ ግንድ በክርስቶስ ላይ እንተከላለን ። ሕይወቱንም እንካፈላለን ። አዳም ልጆችን ለሞት ወለደ ፣ ክርስቶስ ግን በዳግም ልደት ምእመናንን ለሕይወት ወለደ ። የበደለው ቃየን ቢሆን ኖሮ እኛ እንተርፍ ነበር ። የበደለው ግን ግንድ የሆነው አዳም ነውና መትረፍ አልቻልንም ። ከምንጩ የደፈረሰ አይጠራምና ሁላችንም በዚህ ዕዳ ተያዝን ። ክርስቶስም ማሻሻያ በማድረግ ፣ አሮጌውን ግንድ በማከም ሳይሆን ሌላ ግንድ በመሆን መጣ ፣ በዚህም ፍጹም ድኅነትን አገኘን ። በአዳም ውስጥ የጽድቅ ምኞት እንጂ ፍሬው አልነበረንም ፣ በክርስቶስ ግን ለሰማይ የምንኖርበትን አቅም አገኘን ።
ገበሬው ወይኑን ሁልጊዜ ይገዝረዋል ። ከገበሬው እጅም ስለት አይጠፋም ። እውነተኛው የወይን ግንድ ክርስቶስ ሲሆን ገበሬው እግዚአብሔር አብ ነው ተብሏል (ዮሐ. 15፡1)። እግዚአብሔር አብም ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል ። ልጁ ካልሞተ ዓለም አይድንምና ። ስለትና ወይን አይለያዩም ፣ ክርስቶስና መስቀልም ለአንድ ቀን ተለያይተው አልታዩም ። ወደ ምድር መውረድ ፣ ከድሀ መወለድ ፣ በበረት መገኘት ፣ በግብጽ መሰደድ ፣ በሰው ሁሉ መጠላት ፣ ቤት አልባ መሆን ፣ የድህነት ኑሮ ፣ በባሪያ እጅ መጠመቅ፣ በሐሰት መከሰስ ፣ በመስቀል ላይ መዋል ፣ በተውሶ መቃብር መቀበር ፣ የሐዋርያት ስደት…. ይህ ሁሉ የመስቀል አካል ነው ። ወይን ስለት ካላገኘው አያፈራም ፣ ክርስቶስም መከራ ባይቀበል ኖሮ እኛን ማትረፍ አይችልም ነበር ። የመስቀሉ ትርፎች እኛ ነን !
አዳም እውነተኛነትን አጣ ። በዚህ ምክንያት በምድር ላይ የውሸት ኑሮ ተጀመረ ። አዳም የምድር ገዥና ትልቁ ንጉሥ ነው ። ውሸት በእርሱ ስለ ተገኘ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የምድር መሪዎች የውሸት አውራ ሠራተኛ ሆኑ ። እውነት የላችሁም ያላቸውንም ባላቸው አቅም የሚያጠፉ ሆነው ተገኙ ። እውነት በነገሥታት ጥቃት ውስጥ ያለማቋረጥ ታልፋለች ። በዛሬው ዓለም ፖለቲካ ተብሎ ሲጠራ ትርጉሙን ውሸት ብሎ ሰው ሁሉ እስኪያስብ ድረስ የአስተዳደር ክብር ወድቋል ። በምድር ላይ ከቤተ መንግሥት እስከ ድሀዋ ጎጆ እውነተኛ ኑሮ እየጠፋ ነው ፣ ብቁ መሪዎች ተደርገው የሚታሰቡም ሕዝብን ማታለል የቻሉት ናቸው ። በወርቅ በአልማዝ ተንቆጥቁጦ የሚወጣው ቆንጆ ውስጡ የተበላሸ ነው ። የራሱ መጨነቅ ሳይደንቀው መጨነቁን ሰው እንዳያውቅበት በብልጭልጭ ይሸፍነዋል ። ብዙ ሕዝብ የሚከተላቸው ዘፋኝና ተዋንያን ሰውን ሲያስደስቱ ራሳቸው ግን ኀዘነተኛ ናቸው ። የውሸት ሳቅ እንዳደከማቸው ይታወቃል ። ባደጉ ከተሞች የቀነጨሩ ሰዎች አሉ ። ባማረ ቤት የሚኖሩ ብዙዎቹ የፈራረሱ ናቸው ። ሕንፃውን አቁሞ ትዳሩ የተበተነበት ፣ ልጆቹ የወደቁበት አያሌ ነው ። ሰዎች በተቃራኒው መኖር ከጀመሩ ቆይተዋል ፣ እንደሚወዱን ሲናገሩ እየጠሉን ሊሆን ይችላል ፣ የጠሉን ሲመስለን ደግሞ በጣም እየወደዱን ነው ። ሰው አድራሻ የለሽ ፣ በቃሉ የማይያዝ ከሆነ ሰንብቷል ። ይህ ሁሉ ከሐሰተኛው ግንድ የተወረሰ ጠባይ ነው ። የሚያሳዝነው የውሸት ኖረን የእውነት መሞታችን ነው ።
ወይን ከሌሎቹ ተክሎች ልዩ የሚያደርገው ሕይወቱ ያለው ግንዱ ላይ ነው ። ቅጠሉ በጣም ቢያምርም በቅጠሉ ላይ ሕይወት የለም ፤ ፍሬው በጣም ቢያምርና ቢጣፍጥም ሕይወት በእርሱ ላይ ስለሌለ ወስደን ብንተክለው አይበቅልም ። የወይን ግንድ የቅርንጫፉና የፍሬው የሕይወት መገኛ ነው ። ከግንዱ የተለየ ወይን ይከስማል ። ክርስቶስ እውነተኛው የወይን ግንድ ነው ። ምእመናን ቅርንጫፍ ናቸው ። ከእርሱ ተለይተው መኖር አይችሉም ። በራሳቸው ጉልበት ክርስትናን መፈጸም አይችሉም ። አንዳንድ ተክሎች በፍሬአቸው ይበቅላሉ ፣ ሌሎችም በቅርንጫፋቸው ሊበቅሉ ይችላሉ ። ወይን ግን ግንዱ ላይ ሕይወት ስላለ ያለ ግንዱ አይበቅልም ። ያለ ግንዱ ያለ ክርስቶስ ማመንም ፣ ማፍራትም አንችልም ። በፍሬው ግንዱ ይታወቃል ፣ በአማንያን ኑሮም ክርስቶስ ይሰበካል ።
ከቤተሰቡ በሚመጣው ነገር የሚሰጋ ሰው ብዙ ነው ። ባለሙያዎች ጋ ስንሄድ በቤተሰባችሁ እንዲህ ዓይነት በሽታ ነበረ ወይ ብለው ይጠይቃሉ ። ቤተሰባቸው በሥልጣን ያሳለፈ ከሆነ ብዙዎች አገር ለቀው ይሰደዳሉ ። አገር የገዙ ሰዎች ለልጆቻቸው አገር እንኳ ማውረስ አይችሉም ። በቤተሰባቸው ባዕድ አምልኮ ያዩ የነበሩ ሰዎች በሚገጥማቸው አለመሳካት ሁሉ ያንን ያስባሉ ። ምናልባት ቤተሰባቸው የሚከተለው ሃይማኖት ከዚያ አላስጣላቸውም ብለው ስለሚያስቡም ለመሸሽ ብለው ሃይማኖት ይቀይራሉ ። ስጋቱ ከፍተኛ ነው ። በክርስቶስ ስናምን ግን እንኳን ከቤተሰብ ከአዳም ግንድነት ተነቅለን በሐዲሱ ግንድ በክርስቶስ ላይ እንተከላለን ። ስለዚህ በዘርማንዘር የሚመጣው ዕዳ ሊያገኘን ፣ ክፉም ሊይዘን አይችልም ። ጦርነቱ አብቅቷል ፣ ጠላትም ተሸንፏል ፣ ነገር ግን አሁን በጦርነት ውስጥ እንዳሉ የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። በክርስቶስ ያመነ የቤተሰብ ጣጣ ሊይዘው አይችልም ። ከዚህ በኋላ ለማፍራት ዕድልና አቅም አለውና በጽድቅ መኖር ይገባዋል ።
እውነተኛው የወይን ግንድ አንተ አንተ ክርስቶስ ነህ ። ከእገሌ ተወለድሁ ፣ ዘራችን ከእነ እስክንድር ይመዘዛል ፣ ከነ ቄሣር ይገናኛል ማለት ሐሰት ነው ። እነዚህ ሁሉ የሞትን ሥልጣን ማሸነፍ አቅቷቸው ወድቀዋል ። ታላቅ ቢባሉም ሎቶሪ ወጥቶላቸው ነው ። ታላቅነታቸውን ሲነጠቁም ፍርድ ቤት ቆመው አልተከራከሩም ። የእነርሱ አይደለምና ፀሐዩ ሲጠልቅ አንሰው ወደ ዋሻ ገቡ ። በባሕርይህ ባለሥልጣን ፣ ጌትነት ገንዘብህ የሆነ አንተ ብቻ ኢየሱስ ክርስቶስ ነህ ። የእገሌ ዘር ነኝ ማለት ለኩራት እንጂ ለጥጋብ አይሆንም ። በአያቱ ድሀ ያልነበረ ባለጠጋ ፣ በአያቱ ባለጠጋ ያልነበረ ድሀ የለም ። ሁሉ ሐሰት ነው ፣ አንተ ብቻ እውነት ነህ ። ጌታ ሆይ የውሸት እየኖርን የእውነት መደሰት እንፈልጋለንና እባክህ ከተኛንበት ቀስቅሰን !
ዲ.አ.መ
ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም.