በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡
❖ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ
ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
🌿+*" ማር ፊቅጦር "*+🌿
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደማቸውና በገድላቸው ያስጌጡ ብዙ ሰማዕታት አሉ:: ነገር ግን ከኮከብም ኮከብ ይበልጣልና ማን እንደ ጊዮርጊስና እስጢፋኖስ! ከእነርሱ ቀጥለው ከሚጠሩ ሰማዕታት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ቤተ ክርስቲያን "ማር" የምትለው ቅዱስ ፊቅጦር ነው::
እስኪ ከበዛው መዓዛ-ገድሉ ጥቂት እንካፈል:-
+ቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ኅርማኖስ ይባላል:: አረማዊና ጨካኝ ነው:: እናቱ ግን የተመሰገች ቅድስት ማርታ ትባላለች:: ልጇን እንደሚገባ አሳድጋው 20 ዓመት ሲሞላው የአንጾኪያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃና በመንግሥቱ 3ኛ አድርጐ ሾመው::
የድሮዋ አንጾኪያ (ሮም) እንደ ዛሬዋ አሜሪካ ዓለምን የተቆጣጠረች ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ፊቅጦር ደም ግባቱ ያማረ: በጦርነትም ኃይለኛ ስለ ነበር ሁሉ ያከብሩት: ይወዱትም ነበር::
+እርሱ ግን ቀን ቀን ሲጾም: ነዳያንን ሲያበላ ይውል ነበር:: ሌሊት ደግሞ እኩሉን ሲጸልይና ሲሰግድ እኩሉን የእስረኞችን እግር ሲያጥብ ያድር ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆንኮ እርሱ የንጉሡ 3ኛ: የሠራዊትም አለቃ ነው:: በዘመኑ የሚያገድፍ ምግብና የወይን ጠጅ በአፉ ዙሮ አያውቅም::
+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ካደ:: ዘመነ ሰማዕታትም ጀመረ:: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ:: ከ47 ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች በመንኮራኩር ተፈጩ:: በመጋዝ ተተረተሩ:: ለአራዊት ተሰጡ:: በግፍም ተጨፈጨፉ:: ቀባሪ አጥተውም ወደቁ::
በዚሕ ጊዜ ማር ፊቅጦር እናቱን ቅድስት ማርታን በዕንባ ተሰናብቶ ወደ ንጉሡ ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ:: ክፉ አባትም በልጁ ላይ ሞትን መከረ::
ከዚያም ቅዱሱን አፉን በብረት ለጉመው ወደ ምድረ ግብፅ አወረዱት:: መሪያቸው እንዳልነበረ ወታደሮቹ መኩዋንንቱ ሁሉ ተዘባበቱበት:: እርሱ ከምድራዊ ንግሥና ሰማያዊ መንግስትን: በሰዎች ፊት ከመክበር ስለ ክርስቶስ ሲል መናቅን መርጧልና::
ለቀናት: ለወራትና ለዓመታት መኩዋንንቱ እየተፈራረቁ አሰቃዩት:: በርሱ ላይ ያልሞከሩት የስቃይ ዓይነት አልነበረም:: አካሉን ቆራርጠዋል: ዓይኖቹን አውጥተዋል: ምላሱንም ቆርጠዋል:: ሚያዝያ 27 ቀን ግን በሰይፍ አንገቱን ቆርጠውታል:: ስለዚህም እናት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ማክበር ታከብረዋለች::
❖እግዚአብሔርም ለቅዱስ ፊቅጦር እንዲህ አለው:- "እንደ አቅሙ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ስምህን ያከበረ: የብርሃን ልብስ አጐናጽፌ ወደ መንግስተ
ሰማያት አስገባዋለሁ::"
❖ይህች ቀን ማር ፊቅጦር የተወለደባት ናት፡፡ እናቱን ቅድስት ማርታ (ሶፍያንም) እናስባለን፡፡
❖ቸሩ አምላከ ፊቅጦር ሁላችንም ይማረን:: ከቃል ኪዳኑ አሳትፎ ለርስቱ ያብቃን::
✞ ቅዱስ አውሳብዮስ ካልዕ (ጥዑመ ዜና)✞
ቅዱስ አውሳብዮስ በወጣትነቱ ከተባረከች ሚስቱ ጋ በድንግልና የኖረ; በዘመኑ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ; 4,000 አቡነ ዘበሰማያት በአንድ ቀን ያደርስ የነበረ; ስለ ሃይማኖትም በቀስት የተወጋ; በእሳት የቃጠለ; አካሉን ቆራርጠው የጣሉትና እግዚአብሔር ከሞት ያስነሳው ጻድቅና ሰማዕት
ነው:: ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ከነሥጋው ወደ ሰማይ
ተነጥቆ ለ14 ዓመታት ቆይቷል:: ወደ ምድርም ተመልሶ ለ40 ዓመታት በሐዋርያነት ከ85,000 በላይ አሕዛብን ወደ ሃይማኖት መልሷል::
ጌታም በስምህ የተማጸነውን እስከ 7 ትውልድ እምርልሃለሁ ብሎታል::"
❖አባቶቻችን ደግሞ 'ስም አጠራሩ የከበረ ዜና ሕይወቱ ያማረ' ሲሉ ይጠሩታል::
❖ ከበረከቱ ያድለን::
✞ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ
ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አውሳብዮስ ጻድቅ (ጥዑመ ዜና)
2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት (ልደቱ)
3.ቅዱስ ሰርግዮስ ሰማዕት
4.ቅዱስ መፁን ቀሲስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (የቅ/ፋሲለደስ ልጅ)
6.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
7.አባ ክፍላ
8.አባ ኅብስ
=>ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ
=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ : እስከ አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ : ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10-13)
🌹††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር ††† 🌹
👇👇👇
በቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉና ቤተሰብ ይሁኑ
https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar