በአማራ ክልል የሚገኙ አስሩም የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ይበል እንጂ በክልሉ ያለው አሁናዊ ሁኔታ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራዎች ለመስራት ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት አስቻይ አለመሆኑ ይገለጻል፡፡
የአማራ ክልል ተማሪዎች ማህበር በበኩሉ በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር ባለበት እንደቀጠለ መሆኑ እየታወቀ የትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ይጀምሩ ማለቱ ትክክል አይደለም ውሳኔውን መልሶ እንዲያጤነው ይገባል ሲል ጠይቋል፡፡
የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አግማስ በየነ ተማሪዎቹ ለደህንነታቸው ዋስትና የሚሰጣቸው አካል በሌለበት ሁኔታ ወደ ተመደቡበት ትምህርት ተቋም መሄድ አዳጋች ነዉ ሲሉም አክለዋል፡፡
ከምንም ነገር በላይ የተማሪዎቹን ደህንነት መጠበቅ የሚቀድም በመሆኑ ማህበሩ እንደ ተቋም ከሚኒስቴሩና ከትምህርት ተቋማት ጋር በመነጋገር ውሳኔውን ለማስቀልበስ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ አቶ አግማስ ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሃሙስ ውሳኔውን ያሳለፈው ከክልሉ ኮማንድፖስት፣ የጸጥታ አደረጃጀቶችና የሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ መሆኑን ገልጿል።
ከክልሉ ዩንቨርስቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የባህር ዳር ዩንቨርሲም ተማሪዎቹ ሲመጡ ለደህንነታቸው ሃላፊነት መውሰድ ያለባቸው እራሳቸው ተማሪዎቹ እንደሆኑ በይፋ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ለጥቆማ 👉 @atc_newsbot
➡️ https://t.me/atc_news