ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan) @mahiberekidusan Channel on Telegram

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

@mahiberekidusan


🌷ይህ ቻናል የተከፈተው ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት ተከታይ ሲሆን ዋና አላማውም ምዕመናን በንስሐ ህይወት ተመላልሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድወርሱ የሚያስችል ትምህርት መስጠት ነው፡፡
🌷💚የቅዱሳን ገድላት
🌷💛ስንክሳር
🌷 ቅዱሳን ስዕላት
መንፈሳዊ ትምህርቶችና ጽሑፎች
🎤 ስብከቶች ............ይቀርቡበታል፡፡🌎

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan) (Amharic)

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan) ከሚባለው መጽሐፍ እና ትምህርትና አገልግሎት በሚከተለው ከታች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት የተከታይ እና እምነት እያላና ምዕመናውን መስራቷን ያስችላ፣ ትምህርት ማህበረ ቅዱሳን ያላትን መንግሥት እንዲቆሞ ነው፡፡ የቅዱሳን ገድላትዎን በተለያዩ ጽሑፎችና ትምህርቶች እንዲያከናውናል፡፡ በሚሳተፉበት ውይይት ለሁሉ የትምህርት ጽሑፍ እና ስብከት እና ስብከቶችን ማየት ይኖራል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

29 Jan, 13:55


​​እንኳን ለእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

† #ዕረፍተ_ድንግል †

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::

ዓለም ተፈጥሮ: አዳምና ሔዋን ስተው: መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው: በኃዘን ንስሃ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከ5 ቀን ተኩል (5500 ዘመናት) በሁዋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው::

ከአዳም አንስቶ ለ5500 ዓመታት አበው: ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ:: መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት:: ምሳሌም መሰሉላት:: ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት::
"እምርሑቅሰ ርእይዋ: ወተአምኅዋ" እንዲል::

የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ
- ከአዳም በሴት
- ከያሬድ በሔኖክ
- ከኖኅ በሴም
- ከአብርሃም በይስሐቅ
- ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
- ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::

ከሌዊ ደግሞ በአሮን: አልዓዛር: ፊንሐስ: ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::

አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በ5,485 ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች:: (ኢሳ. 1:9, መኃ. 4:7) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ:: (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ)

ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ3 ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ12 ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች: እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች:: 15 ዓመት በሞላት ጊዜ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::

በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው:: ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር: ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ:: (ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)

ወልደ እግዚአብሔርን ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ጸንሳ: እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14) "ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በገሊላ ለ2 ዓመታት ቆዩ::

አርዌ ሔሮድስ እገድላለሁ ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም: በዕንባና በኃዘን ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ከገሊላ እስከ ኢትዮዽያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን 5 ዓመት ከ6 ወር ሲሆነው: ለድንግል ደግሞ 21 ዓመት ከ3 ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::

በናዝሬትም ለ24 ዓመታት ከ6 ወራት ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች:: እርሷ 45 ዓመት ልጇ 30 ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምሕርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ3 ዓመታት ከ3 ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም እያደረች ትምሕርቱን ሰማች::

የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: (ሉቃ. 2:35) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሳኤውን አየች:: ለ40 ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::

ከልጇ ዕርገት በሁዋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮንም ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ15 ዓመታት ኖረች:: በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ: ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና: ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::

ዕድሜዋ 64 በደረሰ ጊዜ ጥር 21 ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ: ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ::
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ::" እንዲል::

ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት:-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ::
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ::
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::

በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው) እነርሱን ቀጥቶ: እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል:: በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለ205 ቀናት ቆይታለች::

ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ 1 ሱባኤ ጀመሩ:: 2ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል::

በ3ኛው ቀን (ነሐሴ 16) እንደ ልጇ ባለ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሳኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ::

ለ2 ሳምንታት ቆይተው: ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል::

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን: ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን::

#ቅዱስ_ጐርጐርዮስ_ሊቅ

ለዚህ ቅዱስ አባት ብጹዕ መባል ተገብቷል:: ክቡር: ምስጉን: ንዑድ ሰው ነውና:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በቂሣርያ ቀዸዶቅያ የተወለደው ቅዱሱ ሰው ለደሴተ ኑሲስ ብርሃኗ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ: እናቱ ኤሚሊያ: ወንድሞቹ ቅዱሳን "ባስልዮስ: ዼጥሮስ: መክርዮስና መካርዮስ" ይባላሉ::

የተቀደሰች እህቱም ማቅሪና ትባላለች:: ከዚህ የተባረከ ቤተሰብ ለቅድስና ያልበቃ አንድም ሰው የለም:: ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከማር በጣፈጠ ዜና ሕይወቱ እንደ ተጻፈው:-

በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል::
ሥጋውያን ጠቢባንን ያሳፍር ዘንድም የግሪክን ፍልሥፍና በልኩ ተምሯል:: በታላቅ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ መሪነት ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል:: በመንኖ ጥሪት ተመስግኗል::
ተገብቶትም በኑሲስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኗል:: እርሱ ሲሔድ በከተማው የነበሩ ክርስቲያኖች 11 ብቻ የነበሩ ሲሆን እርሱ ሲያርፍ ክርስቶስን የማያመልኩ ሰዎች ቁጥር 11 ብቻ ነበር:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ፍጹም ሊቅ ነበርና ከቁጥር የበዙ ድርሳናትን ደርሷል:: ታላቁን ጉባኤ ቁስጥንጥንያን (በ381 ዓ/ም) መርቷል:: ብዙ መናፍቃንንም አሳፍሯል::

ከንጽሕናው የተነሳ መላእክት ያቅፉት: እመ ብርሃንም ትገለጥለት ነበር:: ለ33 ዓመታት እንደ ሐዋርያት ኑሮ በዚህ ቀን ድንግል ጠራችው:: ቀድሶ አቁርቦ: ሕዝቡን አሰናብቶ: የቤተ መቅደሱን ምሰሶ እንደ ተደገፈ ዐርፎ ተገኝቷል:: በዝማሬና በፍቅር ቀብረውታል::

@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

29 Jan, 13:55


#እንኳን_ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የዕረፍት በዓል አደረሰን ።

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

20 Jan, 17:37


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ አሜን ። 🙏🙏🙏

ቃና ዘገሊላ

ቃና' የሚለው ቃል በሃገራችን ልሳን (በአማርኛ)
የምግብን: የመጠጥን ጥፍጥና ወይም በጐ መዓዛን የሚያመለክት ነው:: ምንአልባትም ከዚህ በዓል ምሥጢር የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ግን ቃና ከገሊላ አውራጃዎች አንዷ ናት:: ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ በዚህች ሥፍራ ተገኝቶ በድንግል እናቱ ምልጃ ታላቅ ተአምርን በዚህች ዕለት ሠርቷል

ተአምር የሚለውን ቃል በቁሙ 'ምልክት' ብሎ
መተርጐም ይቻላል:: መሠረታዊ መልዕክቱ ግን ነጮቹ በልሳናቸው Miracle የሚሉት ዓይነት ነው:: ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ (በላይ):
ከፍጡራንም ችሎታ የላቀ ነገር ሲሠራ (ሲፈጸም) ተአምር ይባላል:: ተአምር የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ነው:: እርሱ ዓለምን ከመፍጠሩ ጀምሮ እያንዳንዷ ተግባሩ ለእኛ ተአምራት ናቸው

ስለዚህም ነው 'ኤልሻዳይ / ከሐሌ ኩሉ / ሁሉን
ቻይ' እያልን የምንጠራው:: እግዚአብሔር ፍጡራኑን ይወዳልና እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ተአምራት ማድረግን ሰጥቷል:: በብሉይ ኪዳን እነ ሙሴ ባሕር ሲከፍሉ: መና ሲያዘንሙ: ውሃ ሲያፈልቁ (ኦሪትን ተመልከት) እነ ኤልያስ ሰማይን ሲለጉሙ: እሳትን ሲያዘንሙ: ሙታንን ሲያስነሱ (1ነገሥትን ተመልከት) እንደ ነበር ይታወቃል

እንዲያውም በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምር መጽሐፍ ነው ብሎ ለመናገርም ያስደፍራል:: በሐዲስ ኪዳንም መድኃኒታችን ብዙ ተአምራትን ሠርቶ ለሐዋርያቱ የተአምራት ጸጋውን ሰጥቷቸዋል:: (ማቴ. 10:8, 17:20, ማር. 16:17, ሉቃ. 10:17, ዮሐ. 14:12) እነርሱም በተሰጣቸው ሥልጣን ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል:: (ሐዋ. 3:6, 5:1, 5:12, 8:6, 9:33-43, 14:8, 19:11)

ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያ በወንጌሉ ምዕራፍ 2 ላይ
እንዳስቀመጠው የቃና ዘገሊላው ተአምር የመጀመሪያው ነው:: "ወዝንቱ ቀዳሜ ተአምር ዘገብረ . . ." እንዲል:: (ዮሐ. 2:11) ያ ማለት ግን ጌታ ከዚያ በፊት ተአምራትን አልሠራም ማለት አይደለም

ይልቁኑ ራሱን ከገለጠና ከተጠመቀ በኋላ የሠራው
የመጀመሪያው ተአምር ነው ሲል ነው እንጂ:: ምክንያቱም መድኃኒታችን እንደ ተጠመቀ ዕለቱኑ ገዳመ ቆረንቶስ ገብቷልና:: (ማቴ. 4:1) አንድም በቃና ሌሎች ተአምራትን የሚሠራ ነውና ይህ
ተአምር በቃና የመጀመሪያው ሆነ

+ትክክለኛው የቃና ዘገሊላ ቀን የካቲት 23 ነው:: ጥር 11 ተጠምቆ: የካቲት 21 ቀን ከጾም ተመልሷል:: ከዚያም የካቲት 23 ቀን ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ሒዷል:: ነገር ግን አበው መንፈስ ቅዱስ እንደ መራቸው የውሃ በዓል
ከውሃ በዓል ጋር ይስማማል ብለው ጥር 12 ቀን አድርገውታል

በቃና ዘገሊላ ሙሽራው ዶኪማስ ሲሆን ባለ ሠርጉ
ደግሞ አባቱ ዮአኪን ነው:: ይህም ለሐዋርያው ቅዱስ ናትናኤል አጐቱ ነው:: የልጁ ጋብቻ የተቀደሰ ይሆን ዘንድም ጌታ ክርስቶስን: ድንግል እናቱንና ባለሟሎቹ ሐዋርያትን ወደ ሠርጉ ጠራ

ምንም እንኳ መድኃኒታችንና እመቤታችን ከድግሱ
የማይበሉ ቢሆኑም (በትሕርምት ኗሪዎች ነበሩና)
ጠሪውን ደስ ለማሰኘት ሠርጉን (ብቻውን) ለመቀደስና የጋብቻን ክቡርነት ለማሳየት አብረው ታደሙ

የሠርጉ ሥነ ሥርዓት ሲጀመር በድንኳኑ ውስጥ ጌታ ከመካከል ተቀመጠ:: ድንግል በቀኙ: ዮሐንስ በግራው
ሲቀመጡ: ሌሎች
ሐዋርያት ግራና ቀኝ ከበው ተቀመጡ:: ሲበላና ሲጠጣ
ድንገት የተደገሰው ምግብና መጠጥ አለቀ::
ደጋሾቹ በጭንቅ ላይ ሳሉም አይጠና ሆዷ ድንግል እመ ብርሃን የሆነውን አወቀች:: እንዴት አወቀች ቢሉ:- በጸጋ: አንድም 'ከልጅሽ አማልጂን' ብለው ቢለምኗት ነው ይሏል:: እመቤታችን በዚያ ጊዜ ወደ ልጇ ቀርባ ቸር ልጇን "ወይንኬ አልቦሙ-ወይኑኮ አልቆባቸዋል" አለችው

+ለጊዜው ወይኑም: ምግቡም ስላለቀባቸው እንዲህ አለች:: በምሥጢሩ ግን ወይን ያለችው ፍቅርን: ቅዱስ ቃሉንና ክቡር ደሙን ነው:: ጌታም ይመልሳል:- "ምንት ብየ ምስሌኪ ኦ ብእሲቶ: ዓዲ ኢበጽሐ ጊዜየ-አንቺ ሆይ! (እናቴ ሆይ!)
ያልሺኚን አላደርግ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ? ነገር
ግን ጊዜው ገና አልደረሰም ብየ ነው እንጂ" አላት::
ምክንያቱም ጌታ:-

የወይን ጋኖቹ እስኪያልቁ ይጠብቅ ነበር:: (አበረከተ ይሉታልና) አንድም ይሁዳ ወጥቶ ነበርና እርሱ እስኪመለስ ነው:: (እኔ ስወጣ ጠብቆ ተአምር ሠራ ብሎ ለክፋቱ ምክንያት እንዳያቀርብ) አንድም "ወይን (ቅዱስ ደሜን) የምሰጠው በቀራንዮ አንባ ነው" ሲል "ጊዜየ ገና ነው" ብሏታል:: አንዳንድ ልቡናቸው የጠፋ ወገኖቻችን ጌታ እመቤታችንን እንዳቃለላት (ሎቱ ስብሐት! ወላቲ ስብሐት!) አስመስለው ይናገራሉ:: ይህንን ስእንኅን ጌታ ባለጌዎቹ እነሱም አያደርጉት:: "አባትህንና እናትህን አክብር" (ዘጸ. 20) ያለ ጌታ እንዴት ለእናቱ ክብርን ይነፍጋል?ልቡና ይስጠን!

ወደ ጉዳያችን ስንመለስ መድኃኒታችን እንዲህ ሲል መለስላት:: ተግባብተዋልና እመ ብርሃን አሳላፊዎቹን "ኩሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ-የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ" አለቻቸው:: (ዮሐ. 2:5) ጌታም በ6ቱ ጋኖች ውሃ አስሞልቶ በተአምራት ወይን አደረጋቸው

+እንጀራውን ወጡን በየሥፍራው ሞላው:: ታላቅ ደስታም ሆነ:: የአሳላፊዎቹ አለቃም (ለአባታችን አብርሃም ምሳሌ ነው) ከወይኑ ጥፍጥና የተነሳ አደነቀ:: በዚህም የድንግል ማርያም አማላጅነት: የመድኃኒታችን ከሃሊነት ታወቀ: ተገለጠ
መልካም በዓል

@mahiberekidusan👈

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

19 Jan, 16:50


"ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጠመቁ ምክንያት ከብሉይ ወደ ሐዲስ፥ ከኦሪት ወደ ወንጌል አሻገረን፤ የመንግሥተ ሰማያትን ደጅ ከፈተልን፤ ወደ ሀገራችን (ወደ ሰማይ) ይጠራን ዘንድ ብቻ ሳይኾን ሊነገር በማይችል ክብር ያከብረን ዘንድም ቅዱስ መንፈሱን ላከልን፡፡"

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
@mahiberekidusan
@mahiberekidusan
@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

19 Jan, 16:38


#በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሐዱ_አምላክ_ዘለዓለም ሥላሴ አሜን።
እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሰን / አደረሳችሁ ።
#በጥምቀት_ዙሪያ_የሚነሱ_ጥያቄዎች_እና_መልሶቻቸው
#ጌታችን_ለምን_ተጠመቀ?
1. ምሥጢርን ለመግለጥ፡-
ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ ግልፅ ሆኗል፡፡ አብ በደመና “የምወደው የምወልደው ልጄ ይህ ነው” በማለቱ አብ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑን ሲያስረዳ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ተቀመጠ ወልድም በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ፡፡ ስለዚህ ምሥጢርን ለመግለጥ ስንል የአንድነት የሦስትነት ምስጢር በጐላ ሁኔታ እንዲታወቅ ተጠመቀ ማለት ነው፡፡ /ማቴ. 3፥16/

2. ትንቢቱን ለመፈፀም፡-
በመዝሙር 46/47/፥16 ላይ “አቤቱ ውሆች አዩህ፣ ውሆችም አይተውህ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሆችም ጮኹ፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት የተነገረውን ትንቢት ለመፈፀም ተጠመቀ፡፡

3. አርአያ ሊሆነን፡-
ተጠምቆ እንድንጠመቅ አደረገን ሥርዓትን ሠራልን ቀድሞ በአርአያውና በአምሳሉ እንደፈጠረን አሁንም አርአያ ምሳሌ ሆነን፡፡ ለዚህም ነው ምሳሌን ከእኔ ተማሩ ያለን፡፡ /ማቴ 11፥29/ ለትምህርት ለአርአያ /ዮሐ. 13፥1-17/

4. የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፡-
አዳምና ሔዋን ፍዳው በፀናባቸው መከራው በበዛባቸው ጊዜ የሚያቃልልላቸው መስሏቸው ዲያብሎሰ ስመ
ግብርናችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ ባላቸው ጊዜ አዳም ገብሩ ለዲያቢሎስ (አዳም የዲያብሎስ የወንድ አገልጋይ) ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ) ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ዲያብሎስም ይህንን ደብዳቤ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖስ አስቀመጠው፡፡ በዮርዳኖስ ያስቀመጠውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ ደምስሶታል፡፡ ይህንን ጽሕፈት ለመደምሰስ ነው ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተፃፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡” ያለው ቆላ 2፥14

#ጌታችን_መች_ተጠመቀ?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/

#ጌታችን_ስለምን_በ30_ዓመት_ተጠመቀ?
በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ.  3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡

ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡

ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ‹‹ይህ ልጄ ነው›› ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/

#ጌታችን_በዮሐንስ_እጅ_ለምን_ተጠመቀ?

ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ ›› ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ጌታ ስሆን በባርያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ›› ሲል ነው፡፡

ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- እርሱ እከብር አይል ክቡር እጸድቅ አይል ጻድቅ ነውና፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_ጌታችንን_በማን_ስም_አጠመቀው?

ጌታችን ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ "ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ ባንተ ሕልው ነው በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ ባንተ ሕልው ነው ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?" ብሎ ቢጠይቀው ጌታም ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለኝ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡

#ዮሐንስ_ጌታን_ሲያጠምቀው_እጁን_ለምን_አልጫነበትም?
- ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ እንዳይባል፡፡
- መለኮትን በእጅ መንካት ስለማይቻል

#ጌታችን_ጥምቀቱን_ለምን_በዮርዳኖስ_አደረገው?
በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ›› /መዝ.113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/

#ጌታችን_ለምን_በውሃ_ተጠመቀ?
እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ሰብዐ ትካትን በንፍር ውሃ ፈርኦንና ሰራዊቱን በኤርትራ ባሕር ካጠፋ በኋላ ሰዎች ውሃ ለመዓት እንጂ ለምሕረት አልተፈጠረም ይሉ ነበርና ለምሕረት እንደተፈጠረ ለማጠየቅ በውሃ ተጠመቀ ( ዘፍ 7÷17፤ ዘጸ 14÷1-29)

አንድም ውሃ እሳትን ያጠፋል እናንተም በውሃ ብትጠመቁ ከገሃነመ እሳት ትድናላችሁ ሲል ነው፡፡

አንድም ውሃ መልክን ያሳያል እናንተም በውሃ ብትጠመቁ መልክዓ ሥላሴን የአምላክን ቸርነት ርህራሔ ታያላችሁ ሲል ነው፡፡

አንድም በማር በወተት ቢጠመቅ ኖሮ እነዚህ ለባለጸጎች እንጂ ለድሆች አይገኝም ውሃ ግን በሁሉ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ጥምቀት የታዘዘ ለሁሉ ነው ሲል ነው፡፡

አንድም ማርና ወተት ቢታጠብበት ያቆሽሻል እንጂ አያነጣም ውሃ ግን እድፍን ያስለቅቃል እናንተም በማየ ገቦ ብትጠመቁ ከኃጢአት ትጠራላችሁ ሲል ነው፡፡

@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

18 Jan, 17:42


ከተራ

ከተራ 'ከበበ' ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡

በጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰቡ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተክላሉ፡፡

ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥሉ ይውላሉ፡፡ የምንጮች ውኃ እንዲጠራቀም ይከተራሉ (ይገድባሉ) ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይኼድ በመገደብ ለመጠመቂያ (ለጥር 11) ዝግጁ የሚያደርጉበት ዕለት ነው፡፡

በተጨማሪ  በአቅራቢያ የሚገኙት ቤተክርስቲያናት ተሰብስበው ከዚኹ ከተቆፈረው ገንዳ ወይም ከተገደበው ጅረት  አጠገብ ባለው ዳስ ወይም ድንኳን ታቦቶቻቸውን ያሳድራሉ ሊቃውንቱም በዚያው እግዚአብሔርን በማኅሌት ሲያመሰግኑ ያድራሉ።

በበዓለ ጥምቀት የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በዋዜማው የመኼዱ ምሳሌ ነው፡፡

ታቦታቱ የጌታችን ምሳሌ ሲኾኑ ካህናቱ የመጥምቁ ዮሐንስ ምሳሌ መዘምራኑና ሕዝቡ ደግሞ ዮሐንስ ያጠመቃቸው ሕዝቦች ምሳሌዎች ናቸው፡፡
@mahiberekidusan
መልካም የከተራ በዓል!

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

07 Jan, 20:04


#እንኳን_ለጌታችን_ለመድኃኒታችን_ለኢየሱስ_ክርስቶስ_የልደት_በዓል_በሰላም_አደረሳችሁ…!

"…ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ? ቃልን ወሰነችው። ልደቱንም ዘር አልቀደመውም። በመወለዱም ድንግልናዋን አልለወጠም። ቃል ከአብ ያለ ድካም ወጣ። ከድንግልም ያለ ህማም ተወለደ። ሰብአሰገል ሰገዱለት። አምላክ ነውና ዕጣን አመጡለት። ንጉሥም ነውና ወርቅ አመጡለት። ስለኛ በፈቃዱ ለተቀበለው መዳኛችን ለሆነው ሞቱም ከርቤ አመጡለት። እርሱ ቸርና ሰውን ወዳጅ የሆነ አንድ እርሱ ብቻ ነው። ቅድስት ሆይ ለምኚልን።

"…ቤዛ ይስሐቅ በግዕ ከኅቱም ዕፀ ሳቤቅ እንደተገኘ፤ ለእስራኤልም በበረሀ ውስጥ ከኅቱም አለት ውኃ እንደ ፈለቀ፤ የተደነቀች የአሮን በትርም እንደለመለመችና እንደ አፈራች፤ በሶምሶንም እጅ ውስጥ ከአህያ መንጋጋ አጥንት ውኃ እንደ ፈሰሰ፤ እንዲሁ የጌታችን ልደት በኅቱም ድንግልና ሆነ። በዕፀ ጳጦስ ውስጥ እሳት እንደ ነደደች ዕፂቱም እንዳልተቃጠለች እንዲሁ የመለኮቱ እሳት ድንግልን አላቃጠላትም። ለእርሱም ከቸር አባቱ ከማሕየዊ መንፈስ ቅዱስ ጋር ጌትነት ክብር ምስጋና ሰጊድ ከርሱ ጋር በትክክልነት ይገባል ለዘላለሙ አሜን።
"በዓለ ገናን ስናከብር በሀዘን በመከራ፣ በጭንቅ፣ በረሃብና በጥም፣ በሰቀቀን፣ በስደት፣ በወኅኒ ቤት፣ በአልጋ ቁራኛ በደዌ ደኛ፣ በፅኑ ህመም ተይዘው፣ በየቤቱ፣ በየጎዳናው፣ በየሆስፒታሉና በፀበል ስፍራዎች ሁሉ ያሉትን፣ ከሞቀ ቤትና ንብረታቸው ተፈናቅለው በየጥሻው የወደቁትን በማሰብ፣ በመንከባከብ፣ በመጠየቅ፣ በመጎብኘትና ማዕድ በማጋራት ይሁን። ሃገራችን ኢትዮጵያንና ጎረቤቶቿን፣ መላውንም ዓለም ሁሉ ሰላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ያድርግልን። አሜን።

@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

07 Jan, 19:08


እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ ፡፡፡

🌼🌞🌼🌞🌼🌞🌼🌞🌼🌞🌼🌞

"እነኾ ለሕዝብ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታን የምሥራች እነግራችዃለኹ እና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የኾነ ተወልዶላችኋል "
                             ሉቃስ ፪፥፲-፲፮
                                                                        

“በአባቱ ፈቃድ ወረደ በማርያም ዘንድ እንግዳ ኾነ። እግዚአብሔር በንጹሕ ድንግልናዋ ተወለደ።
በእንስሳት በረት ተጨመረ፣ የንግሥናውንም እጅ መንሻ ተቀበለ፣ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕጻናት አለቀሰ።”
         ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ 

በጌታ መወለድ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጠራን - የእርሱን አምላክነት እንድንናገር የተመረጥን - ለርስቱ የተለየን ወገን መኾናችን ተረድተን በሕይወትን እንኖር ዘንድ ጨለማውን ያሳለፈልን የቅዱሳን አምላክ ጊዜያቱን ባርኮ የቤተክርስቲያንን ልዕልና ከምዕመናን የመንፈስ ልደት ጋር በጥምረት  የምናይበት - በሰማያዊ ዜግነት የምንከብርበት የተባረከ የበረከት በዓል እንዲያደርግልን እንመኛለን!

ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች   እንኳን አደረሳችኹ ለማለት እንወዳለን! የበረከት በዓል ይኹንልን!

“ተወልደ እምአመቱ ወሰላመ ገብረ በልደቱ፤
ከአገልጋዩ ተወለደ፣ በልደቱም ሰላምን አደረገ”
ቅዱስ ያሬድ

@mahiberekidusan👈

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

28 Dec, 19:11


🕯                    💛                        🕯


† እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፤ አደረሰን።


                         🕊

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ †


" የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።" [መዝ.፴፬፥፯]


    🕊   ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት   🕊


† በቤተ ክርስቲያን ክቡር ከሆኑ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ገብርኤል ብዙ የክብር ስሞች አሉት:: በተለይ ግን:-

†  ሊቀ አርባብ
†  መጋቤ ሐዲስ
†  መልአከ ሰላም
†  ብሥራታዊ
†  ዖፍ አርያማዊ
†  ፍሡሐ ገጽ
†  ቤዛዊ መልአክ
†  ዘአልቦ ሙስና . . . እየተባለ ይጠራል::

በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ስሙ በብዛት ተጠቅሷል:: ስለ ረዳትነቱና አማላጅነቱም ቤተ ክርስቲያን በስሙ ታቦት ቀርጻ : መቅደስ አንጻ በሥርዓት ክብሩን ትገልጻለች::

ከእነዚህም አንዱ ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነደው እቶን አሳት ማዳኑ ታስቦ የሚከበርበት በዓሉ ዛሬ ነው::

"ለዝንቱ ዜናዊ መልአከ ኃይል::
በዛቲ ዕለት ከመ ይትገበር በዓል::
መምሕራን አዘዙ ወሠርዑ በቃል::" እንዲል:: [ አርኬ ]

ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ::

ምንም እንኳ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ: ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ::

አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው::

ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር ስድሳ ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ አርባ ዘጠኝ ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም::

ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳ አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ::
ዳን 3፥17 ጀምሮ ያንብቡ
ቅዱሳኑን ያዳነ ቅዱስ መልአክ እኛንም ያድነን ዘንድ እንደ አባቶቻችን ፦

"አድኅነኒ ዘአድኃንኮሙ በአክናፊከ ምንትው::
አመ ውስተ እሳት ተወድዩ ሠለስቱ እደው::" እያልን እንለምነው:: [ መልክዐ ገብርኤል ]

የቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ቃል ኪዳን አይለየን፡፡
#ሼር

@mahiberekidusan

             🕯              💖               🕯

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

30 Nov, 21:16


#ህዳር_ጽዮን
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን።🙏🙏🙏
"…በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን። መዝ 137፥1 "…መሠረቶቹ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤ ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል። የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል። የሚያውቁኝን ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸዋለሁ፤ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ጢሮስም የኢትዮጵያም ሕዝብ፥ እነዚህ በዚያ ተወለዱ። ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት። እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል። በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል። መዝ 87፥ 1-7

@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

20 Nov, 18:21


​​​​👆 #የቀጠለ

የቅዱስ ሚካኤል አለቅነት በሐዲስ ኪዳንም አንደሚቀጥል ይህ ነቢይ በትንቢቱ “በዚያ ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሣል..” (ዳን.12፡1) በማለት ተናግሮለታል ፡፡

ስለዚህም ቅዱስ ሚካኤል እኛን ከሰይጣን አሽክላና ወጥመድ ይጠብቀንና በጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት ይቆምልን ዘንድ በእኛም ላይ ሹም ነው። ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦችና የርስቱ ወራሾች ነንና፡፡

እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መሾሙ እጅግ ትሑትና ስለመንጎቹ ነፍሱን እንኳ አሳልፎ እስከመስጠት ደርሶ ስለሚወዳቸው ነበር፡፡ (ዘኁል.12፡3፤ዘጸአ.32፡32)በሕዝቡም ላይ እርሱን መሾሙ እንዲሠለጥንባቸው ወይም እንዲገዛቸው ሳይሆን በትምህርቱና በጸሎቱ እነርሱን እንዲያግዛቸው ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለሙሴ ሲመሰክር “እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው”አለ፡፡ (የሐዋ.7፡35)

እንዲሁ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እጅግ ትሑትና ለሠራዊቱ ተቆርቋሪ የሆነ መልአክ በመሆኑ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ተሾመ፡፡ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙ ልክ እንደ ሙሴ በእነርሱ ላይ ሊሠለጥንባቸው ወይም ሊገዛቸው ሳይሆን መላእክትን ሊመራ ፣ እኛን ደግሞ ከሰይጣን ጥቃት ሊጠብቀንና በጸሎቱ ሊራዳን ነው (ይሁዳ.12) ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን መላእክት እኛን እንደሚጠብቁና እንደሚራዱ እንዲሁም ስለእኛ በፊቱ አንደሚቆሙ ሲያስተምረን “ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁል ጊዜ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ” (ማቴ.18፡10) ብሎናል፡፡

እኛን ይጠብቁ ዘንድ የተሰጡን ቅዱሳን መላእክት ስለእኛ እንዲህ የሚቆረቆሩና ስለመዳናችን የሚተጉ ከሆነ በቅድስናው ልቆ የመላእክት አለቃ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ሚካኤል እንዴት ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይበልጥ አይቆም? (ሉቃ.13፡6-9) እንዴትስ በተሰጠው ሥልጣንና ኃይል አይረዳን? (መዝ.33፡7) እርሱ “ስለሕዝብህ ልጆች የሚቆመው” መባሉም እኛን በጸሎቱና በተራዳኢነቱ የጽድቅ ሕይወታችንን በሚገባ እንድናከናውን እንደሚራዳን የሚያሳይ ኃይለ ቃል ነው፡፡

የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ላይ ለዘለዓለሙ ይደርብን አሜን፡፡


💚 @mahiberekidusan 💚
💛 @mahiberekidusan 💛
❤️ @mahiberekidusan❤️

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

20 Nov, 18:20


​​#ሕዳር_ሚካኤል !

#እንኳን_ለመላእክት_አለቃ_ለቅዱስ_ሚካኤል #በዓለ_ሲመት_በሠላም_አደረሰን !

በዓለ ሲመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል (ሕዳር 12)
(አንብባችሁ ስትጨርሱ ለሌሎችም ታሪኩን እንዲያዉቁ #SHARE_SHARE_SHARE
ብታደርጉ ብዙ አተረፋችሁ፡፡)

ቤተ ክርስቲያን ልጆቹዋ የመላእክትን ተራዳኢነት አውቀው እንዲጠቀሙና የመንግሥቱ ወራሾች ለመሆን እንዲበቁ ስትል ለቅዱሳን መላእክት የመታሰቢያ ቀን በመስጠት በእነርሱ የምናገኛቸውን እርዳታዎች እንዲታወሱ ታደርጋለች፡፡

በዚህም መሠረት በህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ህዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው፡፡

እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል። ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2 እንደሆነ አክሲማሮስ በተሰኘው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት
አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ” (ኢያ.5፡13) ይለናል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስ ይዋጋው፣ በጸሎትም ይራዳቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡን “በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት” (ዘጸ.23፡21) ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር፡፡

ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ አያረጋግጥም የሚል ካለ “መልአክ” የተባለው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ ገልጦልን እናገኛለን፡- ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቅዱስ ሚካኤል ስለመሾሙ ሲመሰክር “በእውነት በመጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም
የለም”(ዳን.10፡21) ብሎአል፡፡

ስለዚህም ለኢያሱ የተገለጠውና እስራኤላውያንንም የመራው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን እንረዳለን፡፡

#ይቀጥላል .......
💚 @mahiberekidusan 💚
💛 @mahiberekidusan 💛
❤️ @mahiberekidusan ❤️

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

16 Nov, 09:12


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ አሜን ።
#ኅዳር 7
የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ነው ።
=============================
በዓሉ ስለ ሁለት ምክንያት ይከበራል
.
1. / በቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገር በልዳ በስሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተክርስቲያን የታነፀበት ዕለት ነው::
.
2 /በአንዲት መበለት ቤት በረሃብ እንዲሞት ባሠሩት ጊዜ ቤቷን በበረከት የሞላበት ፣ልጇን የፈወሰበት እና የታሰረበትን የቤቱን ምሰሶ ያለመለመበት መታሰቢያ በዓል ነው።
.

የኢትዮጵያ ገበዝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ በምልጃህ ሀገራችንን ፈውሳት።

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

10 Nov, 19:24


ተፈጸመ ናሁ ማኅሌተ ጽጌ ሥሙር
🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹🌹

"…ድንግል ሆይ…! ርጉም በኾነ በሄሮድስ ዘመን ከርሱ ጋራ ካገር ወደ አገር ስትሸሺ ካንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ረኀቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ጒዳቱን ከርሱ ጋራ የደረሰብሽን ጸዋትወ መከራ ኹሉ አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ከዐይኖችሽ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አሳስቢ፤ ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ፣ መዐትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ፤ ለጻድቃን ያይደለ ለኃጥኣን አሳስቢ ለንጹሓን ያይደለ ለተዳደፉት አሳስቢ።

"…ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ሆይ ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን፤ አእምሮውን ጥበቡን ፍቅርሽን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን፡፡"

"…የእመቤታችንን ፍቅሯን በልቦናችን ጣዕሟን በአንደበታችን ያሳድርብን። ምልጃና ጸሎቷ ረድኤት በረከቷ ከሁላችን ጋር ይሁን። የአሥራት ሀገሯን ኢትዮጵያን በምልጃዋ ትጠብቅልን።

@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

09 Oct, 16:07


መስከረም 29
የቅድስት አርሴማ እናት አትኖስያ ትባላለች ልጅ በማጣት ለረጅም ዘመን ታዝን ታለቅስ ነበር በኃላም እግዚያብሔር ልመናዋን ሰማት ይህችን ክብርት ቅድስት ልጅንም ሰጣት፤ቅድስት አርሴማ ጥር 6 ነው የተወለደችው፤15 ዓመት ሲሆናት ሊያጋቡአት አሰቡ እርሷ ግን ይህን አልወደደችም፤ በደናግል ገዳም ገብታ በተጋድሎ መኖር ጀመረች።
❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️
ከዚህ በኃላ እንዲህ ሆነ ከሃዲው ንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ ሊያገባት ወደደ ቅድስት አርሴማ ግን ከደናግሉ ጋር ሸሽታ ወደ አርማንያ ሄደች በዚያም በበርሃ ለጥቂት ቀናት ተቀመጠች በኃላ ላይ ድርጣድስ የሚባል አገር ገዢ በበርሃ እንደሚኖሩ ሰማ ወታደሮችንም ልኮ አስመጣቸው፤ የቅድስት አርሴማን መልክ በተመለከተ ጊዜ ፈዞ ደንዝዞ ቀረ የፊቷ ውበት እጹብ ድንቅ፤ ግርማዋ የሚያስደነግጥ ልብ የሚያርድ ነበርና፤ስለዚህም ሊያሰቃያት አልደፈረም በእንክብካቤ በሰገነት ላይ አኖራት፤ ሌሎቹን ግን ለጣአት እንዲሰግዱ ገረፋቸው፤ ቅድስት አርሴማ እኔንም አሰቃዩኝ እያለች አምርራ ታለቀስ ነበር። ድርጣድስ ብዙ ጊዜ ሊሸነግላት ሞከረ እርሷ ግን ትዘልፈው ጣኦታቱንም ትረግም ነበር፤ እርሷ ጸንታ ደናግሉን ታጸና ነበር ትመክራቸው ታረጋጋቸው ነበር፤ ድርጣድስ ሽንገላው እንደማያዋጠው በአወቀ ጊዜ ማሰቃየት ጀመረ፤ በመጨረሻም ከብዙ ስቃይ በኃላ መስከረም 29 ቀን አንገቷን ቆረጣት ከእረሷ ጋር 27 ሰማዕታት አብረው ተሰይፈዋል። በአገራችን በስሟ ሰሜን ወሎ ውስጥ ሲሪንቃ ቅድስት አርሴማ የሚያስገርም ገዳም አላት፤በዚህ ገዳም ሰባት ቀን ብቻ ሱባዬ የሚገባ የልቡን መሻት ትፈጽምለታለች፤በመዲናችን አዲስ አበባም የቅድስት አርሰሴማ ቤተክርስቲያኖች አሉ አንዱም አስኮ ቃሎ ተራራ ላይ የሚያስገርም ቤተክርስቲያን አላት ይህንን የቃሎ ተራራ ሲወጡ ዝቋላ አቦ ትዝ ይላል፤ መስከረም 29 በደማቁ ታቦተ ህጉ ወጥቶ ተከብሮ ይውላል። ከሰማዕቷ በረከት ያድለን። ይህም መስከረም 29 ቀን የሰማዕትነት አክሊል የተቀዳጀችበት ዕለት ነው ፡፡ ታህሳስ 6 ፍልሰተ አጽሟ ነው
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ..........
@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

06 Oct, 18:07


ድንግል ሆይ ለጻድቃን ያይደለ ለኃጥኣን አሳስቢ ።

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

06 Oct, 18:06


የቀጠለ.....
ሰውም ሲኖርም ሲሞትም ፈጣሪውን ማስደሰት አለበት እንጅ ያለ ፍሬ ንስሓ መሞት የለበትም፤ "ግበሩኬ እንከ ፍሬ ሠናየ ዘይደልወክሙ ለንስሓ፤ እንግዲህስ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ እንዲል፡፡ (ማቴ.፫፥፰)
 
ወርኃ ጽጌ የእናታችንን ስደት ከተወደደው ልጇ ጋር የምናስብበት ነው። በተለይም ማሕሌተ ጽጌ በተባለው ድርሰት ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል እርሷን በአበባ ጌታችንን በፍሬ፣ እርሷን በፍሬ ጌታን በአበባ እየመለሰ ብሉይን ከሐዲስ አጣጥሞ የተናገረው ምሥጢር ድንቅ ነው። ክርስቶስን በአበባ ሲመስለው ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ቅዱስ ያሬድ በድጓው "ትወፅእ በትር እም ሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እም ጉንዱ" በማለት ድንግል ማርያምን በጉንድ ክርስቶስን በጽጌ መስሎ ይናገራል። እርሷን በአበባ ሲመስልም ከአበባ ፍሬ እንዲገኝ ፍሬ ሕይወት ፍሬ መድኃኒት ክርስቶስ ከእርሷ እንደሚገኝ ለማመልከት ነው። (ኢሳ.፲፩፥፩)
 
ከማሕሌተ ጽጌ አንድ ማሳያ አቅርበን ክርስቶስ ለምን ተሰደደ የሚለውን እንመልከት፤ “በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፊ ዘዐፀዋ፣ እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኀዋ፣ ተፈሥሒ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ፣በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አቲዋ፣ ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ሔዋ፤በአዳምና በሔዋን በደል ሱራፊ የዘጋውን የገነትን በር ከጽጌ ልጅሽ በቀር ማን ከፈተው? አዳምን ከምርኮ የመለስሽው ድንግል! ደስ ይበልሽ  በተአምርሽ ወደ አበባይቱ ምድር ገብታለችና ሔዋን እንደ እንቦሳ ዘለለች።” ሊቁ በዚች ክፍል ብቻ ሐዲስን ከብሉይ እንዴት እንዳገናኘው ልብ ይሏል።
 
በሰውነቱ መሰደድ፣ መራብ፣ መጠማትን ገንዘብ ያደረገው ክርስቶስ እንደ አምላክነቱ ማንም በማይቀርበው ብርሃን የሚኖር ነቢዩ ዕንባቆም እንደተናገረው “እግዚአብሔር ከቴማን፥ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል። ክብሩ ሰማያትን ከድኖአል፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል። ጸዳሉም እንደ ብርሃን ነው፤ ጨረር ከእጁ ወጥቶአል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሯል። ቸነፈር በፊቱ ይሄዳል፥ የእሳትም ነበልባል ከእግሩ ይወጣል። ቆመ፥ ምድርንም አወካት ተመለከተ፥ አሕዛብንም አናወጠ፤ የዘለዓለምም ተራሮች ተቀጠቀጡ፥ የዘለዓለምም ኮረብቶች ቀለጡ፤ መንገዱ ከዘለዓለም ነው” (ዕን ፫፥፴፮)  በማለት የገለጸው አምላክ ለምን ተሰደደ ቢሉ፡-
 
ለካሣ፦ የመጀመርያውን ሰው አዳምን በበደሉ ምክንያት ከገነት አስወጥቶት ነበርና ካሣ ይሆነው ዘንድ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ተሰደደ። በገድለ አዳም ተመዝግቦ እንደምናገኘው አዳም ገነት ከወጣ በኋላ ተራበ ተጠማ ክርስቶስም በግብጽ ምድር ተራበ ተጠማ፣ አዳም ከገነት ሲወጣ ከሔዋን በቀር አብሮት ማንም አልነበረም፤ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ከዳግማዊት ሔዋን ከድንግል ማርያም በቀር ማንም አልነበረውም፤ “ብክዩ ኅዙናን ኀልየክሙ ስደታ፣ ወላህዉ ፍሡሓን ተዘኪረክሙ ብዝኀ ሠናይታ፣ ማርያም ተዓይል ከመ ዖፍ ውስተ አድባረ ግብጽ ባሕቲታ፣ ተአወዩ በኀጢኦታ ሀገረ አቡሃ ኤፍራታ፤ እናንተ ኀዘንተኞች የእመቤታችንን ስደቷን አስባችሁ አልቅሱ፣ እናንተ ደስተኞች የቸርነቷን  ብዛት አስባችሁ አልቅሱ። ድንግል ማርያም እንደ ወፍ በግብፅ ተራራዎች ብቻዋን ትዞራለች የአባቷ የኢያቄም ሀገር የምትሆን ኤፍራታን አጥታ ታለቅሳለችና እናተ ኀዘንተኞች አልቅሱ።” እንዲል (ሰቆቃወ ድንግል)
 
ስደትን ለሰማዕታት ለመባረክ፦ ሰማዕትነት እሳት፣ ስለት ብቻ መቀበል አይደለም ሀገር ጥሎ መሰደድም ሰማዕትነት ነውና። በመዋዕለ ስብከቱ  “በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ” ብሎ የሚያመጣው ነውና። (ማቴ.፲፥፳፫) የስደተኞች ተስፋ ክርስቶስ ገና በእናቱ እቅፍ ሳለ ስደትን ባረከው። “ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን ኢየሱስ ግፉዕ ምስካየ ግፉዓን፤ኢየሱስ በመሰደዱ የስደተኞች ተስፋ፣ በመገፋቱ የግፉዓን መጠጊያ ሆነ” እንዳለ ሊቁ (ሰቆቃወ ድንግል) ለዚህም ነው ዛሬ ቅዱሳን ፍቅሩ አገብሮቸው ከዘመድ ባዳ ከሀገር ምድረ በዳ አሰኝቶ በዱር በጫካ ከአራዊትና ከእንስሳት ጋር እየታገሉ መኖርን የሚመርጡት።
 
ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደው ልጇ ጋር በስደት ሳለች ያጋጠማትን መከራዎች ከሰቆቃወ ድንግል አንዲትን ቃል አንሥተን እንመልከት። ገና የዐሥራ አምስት ዓመት ብላቴና ሳለች ሕፃን ታቅፋ መሰደዷን ተመልክቶ “ምዕረ በዘባንኪ ወምዕረ በገቦኪ ማርያም ብዙኀ በሐዚ ለሕፃን ደከምኪ ሶበኑ የሐውር  በእግሩ ከመ ትጹሪዮ ይበኪ” በማለት አንድ ጊዜ በጀርባዋ አንድ ጊዜ በጎኗ እያለች ልጅ አዝላ በግብጽ በርኃ ስትንከራተት የሚዘክራት ሰው አጥታ ይልቁንም የልጇን የወርቅ ጫማ ሲወስዱባት ምርር ብላ ስታለቅስ፣ ክርስቶስን ታቅፋ ይዛ ዓይኑን እየተመለከተች ስታልቅስ ልብ በሉ። ሊቁ ይህን ተመልክቶ እናንተ የገሊላ ሰዎች እንቦሳይቱ ማርያም ወዴት ሔደች በለቅሶ እከተላት ዘንድ  መንገዷን ነገሩኝ በማለት ይማጸናል። (ሰቆቃወ ድንግል)
 
ዛሬም ሊቃውንቱ ስደቷን እያሰቡ ሌሊቱን በማሕሌት ወደ ግብጽ እየወረዱ ያድራሉ። የቤተ ክርስቲያን ልጆች አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ! በእውኑ ዛሬስ ድንግል ማርያም ከስደት ተመልሳለችን? በልባችን ላይ ያነገስነው ሄሮድስን ወይስ ክርስቶስን? የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬም ድንግል ማርያም ተመልሳ የምታርፍበት የንጹሕ ልቡና ሀገር ያስፈልጋልና ማረፊያ ለመሆን እንዘጋጀ፡፡ ቅድስት ድንግል ወደ ሀገሯ ስትመለስ ከናዝሬት መልካም ሰው ይወጣልን የተባለላት ናዝሬት የተወደደ የተመሰገነ ክርስቶስን አስገኘች። ይህን ሳስብ ዛሬ የእኛ ሀገርም ድንግል ከስደት ከመመለሷ በፊት ያለችዋ ናዝሬት ትመስለኛለች፤ መልካም ሰው ደግ ሰው የለባትምና። "አድኅነኒ እግዚኦ እስመ ኀልቀ ኄር ወውኅደ ሃይማኖት እም እጓለ መሕያው፤ አቤቱ ደግ ሰው አልቋልና አድነኝ ከሰው ልጆችም መተማመን ጠፍቶአልና” እንዳለ ነቢዩ ዳዊት (መዝ.፲፩፥፩)
 
በመጨረሻም በየቀኑ የምትሰደደውን ድንግል ዓመት ጠብቀን ስደቷን ከምናስብ አሳዳጁን ሄሮድስን አስወግደን ዘወትር ሕፃኑንና እናቱን በልባችን ጽላት አንግሠን እንድንኖር አምላካችን ይርዳን።የልባችን ንጉሥ ክርስቶስ ሲሰደድ አብራ ትሰደዳለችና። ድንግል ሆይ "እስከ ማእዜኑ ትሄልዊ በምድረ ነኪር ሀገረኪ ገሊላ እትዊ፤ እስከመቼ ድረስ በባዕድ ሀገር ትኖሪአለሽ? ወደ ሀገርሽ ገሊላ ተመለሽ።” የሰላም መገኛ ሰላማዊት ርግብ ሱላማጢስ ሆይ፥ ሰላምን ትሰጭን ዘንድ ወደ ዐሥራት ሀገርሽ ገሊላ ኢትዮጵያ ተመለሽ።
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
 
 @mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

06 Oct, 18:04


ዘመነ ጽጌ
 
ዘመነ ጽጌ የሚባለው ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ያለው ነው። ይህ ወቅት ዐቢይ የምስጋና ቀናት ያለው ሊቃውንቱ በማሕሌት፣ ምእመናን በፍቅር ሆነው የእናታችን የድንግል ማርያምን ስደት ከተወዳጅ ልጇ ጋር የሚያዘክሩበት ወር ነው። ከማሕሌቱም በተጨማሪ ምንም እንኳን የዐዋጅ ጾም ባይሆንም የእመቤታችን ፍቅር የበዛላቸው በጾም ሆነው የሚያሳልፉት ዐቢይ የምስጋና ወቅት ነው።
 
ጽጌ ማለት ጸገየ አበበ ከሚል የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን አበባ፣ ውበት፣ ደም ግባት ማለት ነው። አበቦች ውብ፣ ማራኪና አስደሳች ከመሆናቸው የተነሣ የሰው ልጆች በሙሉ አበቦችን ይፈልጋሉ። ምድርም በአበቦች አጊጣ ተሸልማ ስትታይ ክረምት ከለበሰችው ልምላሜ ይበልጥ ታስደስታለች። ዘመነ ጽጌ ዝናምና ወጨፎ፣ ዶፍና ጎርፍ፣ መብረቅና ነጎድጓድ የሚፈራረቅበት የክረምት ቀናት አልፎ ምድር በአበቦች የምትሸለምበት፣ ደመናው ከሰማይ ተወግዶ ሰማይ በከዋከብት የሚያሸበርቅበት፣ የሰው ልጆች ይህንን በማየት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ደስ የሚሰኙበት ወር ነው።
 
ወርኃ ጽጌ የዘመናት ባለቤት ዘመነ ክረምቱን አሳልፎ የደስታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ በሆኑ አበቦች ወደ አሸበረቀው ዘመነ ጸደይ ስላደረሰን "ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት ተሠርገወት ምድር በሥነ ጽጌያት፤ ክረምት አለፈ በረከት ተተካ ምድርም በአበቦች አጌጠች” እየተባለ የሚዘመርበት ወቅት ነው። በዚህ ወራት ሰውም ዕድሜው እንደ አበባ አጭር በመሆኑ ሞቱን ማሰብ እንዳለበት ማስገንዘብ ተገቢ ነው። አበባ የሚወድቀው የሚረግፈው ፍሬ ለማፍራት ነው፤ አበባ ሲኖር በመዓዛው፣ ሲረግፍ በፍሬው ያስደስታል።

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

27 Sep, 08:40


በዘመነ አበው መስቀል የመባረኪያ ምልክት እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፤ ዘፍጥረት ላይ ፤ ‹‹ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው›› ‹‹ወአስተሐለፈ እዴሁ ላዕለ ርዕሰ ኤፍሬም ወምናሴ፤ እጆቹን በኤፍሬምና በምናሴ ላይ በመስቀል ምልክት አድርጎ ጭኖ ባረካቸው›› ይላል፡፡ (ዘፍ. ፵፰፥፲፩)፤ ዕብ. ፲፩፥፳፪)

ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህኑ ቀድሶ በሚወጣበት ጊዜ በእጆቹ ይባርካል፤ ይህም የሚያሳየው ቤተ ክርስቲያን መሠረቷ ከላይ በዓለመ መላእክት ከታች ደግሞ በዘመነ አበው ያየነው መስቀል መሆኑን ነው፡፡

መስቀል በብሉይ ኪዳን እንደየሀገሩ ሁኔታ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲፈጸምበት ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፡- ለወንጀለኞች መቅጫነት አገልግሏል፤ ለአርማም ይጠቀሙበት ነበር፡፡

መስቀል በሐዲስ ኪዳን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ፣ ሰው ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ድኅነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ በመስቀሉ ተጣልተው የነበሩ ሰባቱን መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) አስታርቋል፡፡

ደመራ
ደመራ ማለት መጨመር፣መሰብሰብ፣መከመር ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን ያስተባበረ መሆኑን ገልጸው የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ የጌታችን መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ የጌታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች፡፡

በኋላ ግን አንድ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ አካባቢውን ነግሯት ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ብትማፀን የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ አመለከታት፡፡

እርሷም በምልክቱ መሠረት ብታስቆፍር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኘች፤ ከእርሱ መስቀል ጋር ሁለት ወንበዴዎች የተሰቀሉበትን መስቀል አብራ አግኝታው ስለነበር የጌታችን መስቀል ለይታ ያወቀችበት መንገድ ግን ድውያንን በመፈወሱ፣ አንካሳ በማበርታቱ፣ ጎባጣን በማቅናቱ የዕውራንንም ዐይን በማብራቱ ነው፡፡ ስለዚህም በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ንግሥት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው፡፡

እርስዋም መስከረም ፲፯ ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉን አግኝታ አስወጥታ የቤተ ክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል አደረገች፡፡

የጌታ መስቀል ለብዙ ዓመታት በኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት መስቀሉን ለመውሰድ ጠብ ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት::

ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስን መስቀል ለዐራት ከፍለው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት:: የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅድሳት ጋር በግብፅ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት የግብፅ ክርስቲያኖች በአማሌቃውያን ከሚደርስባቸው ተጽዕኖ ነጻ እንዲወጡ በማድረጋቸው የግብፅ ፓትርያርክ የከበሩ ስጦታዎችን ላኩላቸው:: ንጉሥ ዳግማዊ ዳዊት ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገው ወርቅ ሳይሆን ጌታ የተሰቀለበትን መስቀሉን እንደሆነ ገለጹላቸው::

በመሆኑም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግማደ መስቀሉን ከሌሎች ንዋየ ቅድሳት ጋር ለኢትዮጵያ ሰጥታለች:: ይህ ግማደ መስቀል በግሸን ማርያም ገዳም በእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ኢትዮጵያን እየባረከ ይገኛል::

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መስቀልን ከሐዋርያት በተማረችው መሠረት የወርና የዓመት በዓል ሠርታ ታከብረዋለች::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

27 Sep, 08:39


የመስቀል ደመራ በዓል

የመስቀል ነገር በመጀመሪያ የተገለጸው በመላእክት ዓለም ነበር፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሥነ ፍጥረትን በጻፈበት አክሲማሮስ በተባለ መጽሐፉ እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወረባቸው ጊዜ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳችሁ አለ፡፡ ያን ጊዜ በመላእክት ዓለም ረብሻ ሆነ፤ ከፊሉ ዲያብሎስን አምኖ ከእርሱ ጋር ሆነ፤ ቅዱስ ገብርኤል ግን የፈጠረንን እስክናገኝ በያለንበት ጸንተን እንቆይ አለ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ሌሎች መላእክትም አብረው ጸንተው ቆዩ፤ ተጠራጥውም ከሁለቱም ጎን ሳይሆኑ የቀሩ ነበሩ፡፡

ከዚያም በመላእክትና በዲያብሎስ መካከል ጦርነት ተጀመረ፤ በተዋጉ ጊዜ ዲያብሎስ ሁለት ጊዜ አሸነፋቸው፤ ሆኖም መላእክት አምላካቸውን ‹‹ፈቃድህ ነውን?›› ብለው ቢጠይቁት፤ ‹‹ፈቃዴስ አይደለም፤ ድል የምታደርጉበትን ኃይል እንድታውቁት ብዬ ነው እንጂ›› ብሎ በክንፋቸው ላይ የብርሃን መስቀል ቀረጸላቸው፤ በእጃቸው ደግሞ የብርሃን መስቀል አስያዛቸው፤ ሄደውም ዲያብሎስን ቢገጥሙት በመስቀሉ ኃይል ድል ነሥተውታል፡፡ መላእክት ሳጥናኤልን ድል ያደረጉት በመስቀል ኃይል ነው (ራዕ. ፲፪፥፯፣ መዝ. ፶፱፥፬)፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

12 Sep, 07:10


#በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሃዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ አሜን።🙏#​​​​
መስከረም 2
#እንኳን_ለታላቁ_ነቢይና_ሰማዕት_ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና #ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

¤የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

¤እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

¤ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

¤ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል #እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

¤የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

¤እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና #ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

¤ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

¤ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

¤ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

¤ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

¤"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

¤በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

¤ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: #ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

¤ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

<<¤ አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች) ¤>>
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን:: አሜን

ምንጭ - ዝክረ ቅዱሳን
#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
ለወዳጅዎ_ሀተዋህዶ_ልጆች_ሼር ያድርጉ!
💚 @mahiberekidusan 💚
💛 @mahiberekidusan 💛
❤️ @mahiberekidusan ❤️

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

11 Sep, 08:48


#በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሐዱ_አምላክ_ዘለዓለም_ሥላሴ_አሜን ።

#መስከረም_1/2017 ዓ.ም
                          𝐇𝐀𝐏𝐏𝐘 𝐍𝐄𝐖 𝐘𝐄𝐀𝐑

#ሰላም_ጤና_ይስጥልኝ_ክቡራንና_ክቡራት_ውድ_የተዋሕዶ_ልጆች__መንፈሳዊ_ሰላምታችን_በያላችሁበት ይድረሳችሁ ።
#እንኳን_ለ2017_ዓ.ም_የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሰን። አደረሳችሁ ።

ሰላም ለሀገራችን፣ ፍቅርና አንድነት ለህዝባችን፣ ለቤተክርስቲያናችን ፣ ለቤተሰቦቻን ለወገኖቻችን ሁሉ ይሁንልን ።

#እንኳን_ከዘመነ_ዮሐንስ_ወዴ_ዘመነ_ማቴዎስ በሰላም አደረሰን።

እግዚአብሔር የዘመናት የፍጥረታት ጌታ ሁሉንም በጊዜው ውብ አድርጎ ሰርቶታል። እኛ ሰዎች ማስታወስ ያለብን ጉዳይ ያለ አንድ ቅንጣት መልካም ስራ እግዚአብሔር በቸርነቱ እንደሚያኖረን ለንስሐ እድሜ እንደሚጨምርርልን ነው።
መዝሙረኛው ዳዊት በተሰጠው ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር መዝ 64(5)፥11 "በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፤ ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ ።"  በማለት ልዑለ ባህርይ አምላካችን ቅድስት ሥላሴ(እግዚአብሔር )ዘመናትን (ዓመታትን ) እንደሚያቀዳጃቸው ይናገራል ። እግዚአብሔር የምህረት ፣የይቅርታ አምላክ ስለሆነ ሳያጠፋ ጠብቆ ዘመንን ፣ ጊዜን ይሰጠናል ። 🥀🥀🎋

ስለዚህ እድሜ ሲጨመርልን ማድረግ ያለብን ነገር በንስሐ ህይዎት መመላለስ እና መንፈሳዊ ህይወትን ማሳደግና ማጎልበት፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያ ጦርና ጋሻ ሆነን መንፈሳዊ ትጥቅን ታጥቀን ዘብ ልንቆም፣ እናታችንን ቤተ ክርስቲያንን ልናስደስታት ይገባናል ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ቀኖች ክፉ ናቸውና ዘመኑን ዋጁት" ይላል። ዘመን የተሰጠን እኛ ልንኖርበትና ልንጠቀምበት ነው ። እናም ጊዜ ሳይጠቀምብን እኛ ተጠቅመንበት በወቅቱ ማድረግ ያለብንን ለነፍሳችን ስንቅ ወደ አግዚአብሔር የህይወት መጽሐፍ ማስቀመጥ አለብን። መጽሐፍ እንድህ ይላል ። 🌼💐🌻

እግዚአብሔር መሀሪ ነው ብለህ ኃጢአትን አትስራ፤ ቁጣና መአትም ከእርሱ ጋር አንደሆነ እወቅ  ይላል  ።  ስለዚህ ከዘመን ወዴ ዘመን የምንሸጋገረው በእግዚአብሔር ምህረትና ይቅርታ እንጅ በስራችን አይደለም። ስለዚህ ከገባንበት የኃጢአት ፥የበደል አዘቅት ወጥተን እግዚአብሔር ደስ ልናሰኘው ይገባናል ። በቸርቱ ከአመት ወዴ አመት፣ ከጨለማ ወዴ ብርሃን ፣ ከሞት ወደ ህይወት ፣ከገሃነም እሳት ወደ መንግሰተ ሰማያት የመለሰን አምላካችን ፣ፈጣሪያችን በአራቱም ማዕዘናተ ዓለም የተመሰገነ ይሁን። 💚💛❤️
#ዘመኑን #የሰላም_የንስሐ_የጤና_የፍቅር _የትምህርት_የምህረትና የይቅርታ ያድርግልን ።💐🌼🌻
🍶መልካም አድስ ዓመት

መልካም በዓል 🐓🐏🌺🌸🍁🍎🍊🍉
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን 🙏


@mahiberekidusan💚
@mahiberekidusan💛
@mahiberekidusan❤️

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

11 Sep, 08:47


መልካም ዐውደ ዓመት

“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ”  መዝ. ፷፬/፷፭÷፲፩

መጪው ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችንን  በጋራ የምናገለግልበት የስኬት፣ የቸርነት፣ የንስሐና የሰላም እንዲሆንልን እንመኛለን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን
@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

08 Sep, 17:57


#ሩፋኤል ማለት «እግዚአብሔር ፈዋሽ» ነው። ማለት ነው።ሩፋኤል ማለት «ፈታሄ ማኀፀን» ማለት ነው። ሣልሳይ ሊቀ መላእክት ነው። በኃያላት ላይ የተሾመ የመላእክት አለቃ ሩፋኤል ነው። ቅዱስ ሩፋኤል «መራኄ ፍኖት» መንገድ መሪም ይባላል፡፡
ከበሩት ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ።
(ጦቢት 12 ፥13)

ሩፋኤል ግባ ግባ በቤቴ
ታስሬ እንዳልቀር ፍታኝ አባቴ
ስለ ኃጢአቴ ማልደኝ ግባ በቤቴ
ቆሽሻለሁና ግባ በቤቴ
አማላጅነትህ ግባ በቤቴ
ያስምረኛልና ግባ በቤቴ
ጠላቴ እንዲሸሸኝ ግባ በቤቴ
ሁልጊዜ ናና ግባ በቤቴ 🙌🙌🙌

#የሩፋኤል የስራ ማዕረጉ ብዙ ነው
ከሰባቱ ሊቀ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው ሩፋኤል ሰዳዲ ሰይጣን ነው። ሩፋኤል በቁስል ላይ የተሾመ መልኣክ ነው የሚፈውሰን ሩፋኤል በማህጸን ላይ የተሾመ መልአክ ነው ፈታሄ ማህጸን ነው በተለያዩ የዲያብሎስ ሴራ የራሄሎ /ሾተል /መንፈስ የተዘጉ ማህጸኖችን የሚከፍት በተለይ እርጉዝ የሆኑ ሴቶች ድርሳኑን ቢያነቡት ቢታመኑለት ሩፋኤል ታማኝ ጽንስን ሊያጨናግፍ የመጣውን እርኩስ መንፈስ በስልጣኑ እየሰረ ሲኦል ያወርዳል እንዲሁም በተጨነቅን ጊዜ ሰይጣን እንኳን ደንግጦ ከእኛ ርቆ ቢደበቅ የገባበት ቦታ ገብቶ አንጠልጥሎት ወደ ገሃነም የሚያወርድ ጠበቂያችን ነው።
1ሩፋኤል ጽንስ ጠባቂ ነው።
2እርኩሳን መናፍትን የሚያሰር ተዊጊ/ሰዳዲ ሰይጣን ነው።
3በቁስል/በሽታ ላይ የተሾመ መልአክ ነው።
4ጳጉሜ 3የሰው ልጆችን ኃጢአት ያስተሰርያል የኀጢአት መዝገባችንን ይዞ በጌታ ፊት ይቅር በላቸው ይልልናል።
የሩፋኤል እረድኤት በረከቱ ይደርብን በእውነት ይባርከንም አሜን፫🌹🌹🌹

@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

07 Sep, 19:43


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።
# እንኳን_ለኃያሉ፣_ለገናናው_መልአክ_ለቅዱስ _ሩፋኤል_ዓመታዊ በዓል አደረሰን /አደረሳችሁ ።
#ጳጉሜን_3_በዓሉ የሚከበርለት የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ታሪክ]

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
ቅዱስ ሩፋኤል ቊጥሩ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሲኾን፤ ሩፋ ማለት ሐኪም፤ ኤል ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲኾን ሩፋኤል ማለት “እግዚአብሔር ሐኪሜ ነው” ማለት ነው፤ ሄኖክም “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” ይለዋል (መጽሐፈ ሄኖክ 6፥3)::

ይኽ መልአክ በራማ ሰማይ ያሉ ነገደ መናብርትን የሚመራቸው ነው፡፡ ነገደ መናብርት ያላቸው ቅዱስ ሩፋኤል የሚመራቸው በራማ ሰማይ የሚኖሩ ነገደ መላእክት ናቸው፡፡

ቅዱስ ኤጲፋንዮስም በሥነ ፍጥረት መጽሐፉ ላይ “ወለዳግም ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ መናብርት ወሊቆሙ ሩፋኤል እሉ እሙንቱ እለ ይቀልል ሩጸቶሙ እምነፋስ ወእለ ይጸውሩ ወላትወ መብረቅ ወኲናተ እሳት ዘይነድድ ወአንበሮሙ በዳግሚት ሰማይ” ይላል በራማ ሰማይ የሚገኘውን ኹለተኛውን ዐሥሩን ነገድ መናብርት ሲላቸው አለቃቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፤ እነዚኽም ረቂቅ የኾነ የመብረቅ ጋሻ የእሳት ጦር ይዘው ከነፋስ ይልቅ የፈጠኑ ሲኾኑ በራማ በኹለተኛው ክፍል ላይ አስፍሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሚመራው ከዚኽ ነገድ 24ቱ ካህናተ ሰማይ ወጥተዋል፡፡

አባ ጊዮርጊስም በሰዓታቱ ላይ ስለነዚኽ መላእክት ፡-

“ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጽርሐ አርያም ማኅፈዱ
መካነ ትጉሃን ዐጸዱ ካህናተ ሰማይ ቅዉማን በዐውዱ አክሊላቲሆሙ ያወርዱ ቅድመ መንበሩ እንዘ ይሰግዱ ይርዕዱ ወኢይዝብጦሙ ሶበ ይበርቅ ነዱ”

(ጽርሐ አርያም አዳራሹ፤ የትጉሃን መኖሪያ ቦታው የሚኾን እግዚአብሔር ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ተብሎ በአንድነት በሦስትነት ይመሰገናል፤ ካህናተ ሰማይ በዙሪያው ይቆማሉ፤ በዙፋኑ ፊት እየሰገዱ አክሊሎቻቸውን ያወርዳሉ፤ እሳትነቱ (ባሕርዩ) በሚበርቅ፣ ወገግ በሚል ጊዜ እንዳይመታቸው ይንቀጠቀጣሉ) ይላል

ሊቁ እንደጠቀሰው በዕለተ እሑድ ሥሉስ ቅዱስ ሰባቱን ሰማያት ፈጥረዋል፤ ከዚያም ልዑል እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ ሰባቱን ሰማያት ከፈጠረ በኋላ ሊቁ በአክሲማሮስ እንደገለጸው ከቅዱሳን መላእክት መኻከል፡-

“ወእምዝ ነሥአ እግዚአብሔር እምሰራዊተ ሩፋኤል ፳ወ፬ተ ሊቃናተ ወአቀሞሙ ዐውደ መንበሩ፤ ወሰመዮሙ ለእሙንቱ ካህናተ ሰማይ ወወሀቦሙ ማዕጠንታተ ዘእምወርቀ እሳት ወአክሊላተ ብርሃን ዘእምጳዝዮን ወአብትረ ዘከተማሆን መስቀል ወአልበሶሙ አልባሰ ክህነት” እንዲል ከሰራዊተ ሩፋኤል ፳፬ት ሊቃናትን መርጦ በመንበረ ስብሐት በመጋረጃዋ ውስጥ ዙሪያዋን ክንፍ ለክንፍ ገጥሞ አቁሟቸዋል (ሕዝ ፩፥፲፩-፲፪)።

ቊጥራቸውን ኻያ አራት ማድረጉ በኻያ አራቱ ጊዜያት ጸልየው ሌላውንም ራሳቸውንም ጠብቀው ዋጋቸውን ተቀብለው የሚኖሩ በመኾናቸው ሲኾን እነዚኽንም መላእክት “ካህናተ ሰማይ” ሲላቸው የእሳት የወርቅ ጽና ሲያሲዛቸው የብርሃን አክሊል ጳዝዮን የሚባል የብርሃን ዘውድ ደፍቶላቸዋል፤ የብርሃን ዘንግ ማኅተሙ መስቀል የኾነ ሲያሲዛቸው የብርሃን ካባ ላንቃ ሕብሩ መብረቅ የመሰለ አልብሷቸዋል ( ራእ ፬፥፬-፭፤፲-፲፩)።

እነዚኽ ከሰራዊተ ሩፋኤል የወጡ ሰማያውያን ካህናት በአንድ ላይ ባጠኑ ጊዜ ዛሬ በክረምት ጊዜ ጉም ተራራውን እንደሚሸፍነው ከማዕጠንታቸው የሚወጣው ጢስ መልኩ መብረቅ፣ ድምፁ ነጐድጓድ፣ መዐዛው መልካም የኾነና ጽርሐ አርያም፣ መንበረ መንግሥት የተባሉትን የብርሃን ሰማያት የሚሸፍንና የሚጋርድና ከጢሱ ጋር የቅዱሳን ጸሎት ዐብሮ ወደ እግዚአብሔር ፊት ይወጣል።

“ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ኹሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ” እንዳለ ዮሐንስ በራእዩ (ራእ ፰፥፫-፭)፡፡

ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ ላይ “ወቦ ኪሩቤል ይቀውሙ በየማን በአምሳለ ቀሳውስት ወሱራፌል ይቀውሙ በአምሳለ ዲያቆናት ወድኅሬሆሙ ካህናተ ሰማይ ወቦ እልፍ አእላፋት ወትእልፊተ አእላፋት መብረቅ ወነጐድጓድ ወሠረገላሆሙኒ ምሉኣነ አዕይንት” እንዳለ
★ ኪሩቤል በቀኝ ሱራፌል በግራ ከፍ ብለው የሩፋኤል ሰራዊት ካህናተ ሰማይ ክንፍ ለክንፍ ገጥመው በስተኋላቸው ሲታዩ በሰማይ ውዱድ ዙሪያ እልፍ አእላፋት መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ሠረገላ፣ እንደ መስታየት ብሩህ የኾነ ሲኖርበት እነዚኽ ቅዱሳን መላእክትም ሳያቋርጡ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር” እያሉ ፈጣሪያቸውን በአንድነቱ በሦስትነቱ ያመሰግኑታል (ራእ ፬፥፰)፡፡

ይኽ መልአክ ሩፋኤል ጦቢትን የተራዳ መልአክ ነው፤ ይኽ ጦቢት ዐሥሩ ነገድ በ፯፻፳ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲማረኩ ዐብሮ የተማረከ ጻድቅ ሰው ነው፤ ይኽ ሰውን በመርዳት በደግነቱ የታወቀው ጦቢት ከመንገድ ወድቆ የተገኘ በድን ቀብሮ፤ በዚያው ሌሊት ከቅጥሩ አጠገብ ፊቱን ተገልጦ ተኝቶ ሳለ አዕዋፍ ትኩስ ፋንድያ ዐይኑ ላይ ጥለውበት እንደ ብልዝ ያለ ወጥቶበት ዐይኑ ጠፋ፤ ሚስቱም ባለማስተዋል “አይቴ ውእቱ ምጽዋትከ ወጽድቅከ” (በጐነትኽ ምጽዋትኽ ያዳነኽ ወዴት ነው?) በማለት በተናገረችው ጊዜ ዐዝኖ ሞትን ተመኘ (ጦቢ ፪፥፲፬)፡፡

ያን ጊዜ መልአኩ ሩፋኤል ባሎቿ ስለሞቱባት ቤተሰቦቿ ያንቋሽሿት የነበረችውን የራጉኤል ልጅ ሳራን ለማዳን ተልኮ በመምጣት አስቀድሞ በርሷ ላይ ዐድሮ ባሎቿን ይገድልባት የነበረውን ጋኔን አስወጥቶላት የጦቢት ልጅ ጦብያ እንዲያገባት አድርጓል፤ በዚኽም “ፈታሔ ማሕፀን” ተብሏል "ለሰብእ ወለእንስሳ ፈታሔ ማሕፀኖሙ አንተ" እንዲለው፡፡

በኋላም ወደ ጦቢት በመኼድ ረዥም ዘመን የታወረ ዐይኑን አብርቶለት “አነ ውእቱ ሩፋኤል መልአክ አሐዱ እምነ ሰብዐቱ ቅዱሳን መላእክት” (ከሰብዐቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሩፋኤል እኔ ነኝ) ብሏቸው ተሰውሯል (ጦቢ ፲፪፥፲፭)፡፡

በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ተጻፈ
[የቅዱስ ሩፋኤል በረከት ይደርብን]

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች👇
                •➢ ሼር // SHARE
@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

07 Sep, 19:43


ከመልአኩ ከቅዱስ ሩፋኤል ተራዳኢነት፣ ምልጃ እና ጠባቂነት አምላካችን ያድለን። የዓመት ሰው ይበለን። ፈታሔ ማህፀን ቅዱስ ሩፋኤል በህይወታችን ፣ በቤተክርስቲያናችን ፣ በሀገራችን የተደቀነውን መከራና ችግር በኃይሉ ይፍታልን/ ያስወግድልን። አሜን።

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

06 Sep, 19:26


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ዘለዓለም ሥላሴ አሜን።

#​​ጳጉሜን-

ጳጉሜን የሚለው ስያሜዋ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙ ጭማሪ ማለት ነው፡፡ በግእዝ ተውሳክ ማለት ሲሆን ተውሳክ ማለት ተጨማሪ ማለት ነው፡፡ “ወሰከ - ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሌሎች ሀገሮች ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ያደርጓታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጠር 30 ስናደርግ እነርሱ 31 ብለው የሚቆጥሩት ወር አላቸው፡፡ ይኹን እንጂ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡

ጳጉሜን በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን ትመጣለች፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ሉቃስ መጨረሻ በዘመነ ዮሐንስ መግቢያ ጳጉሜን ስድስት ቀን ትሆናለች፡፡ በዚህም ሀገራችን ኢትዮጵያ የአስራ ሦስት ወራት ጸጋ /Thirty months of sunshine/ በመባል ትታወቃለች፡፡ ጳጉሜን ስድስት በምትሆንበትም ጊዜ ጾመ ነቢያት /የገና ጾም/ ህዳር 14 ቀን ይገባና ታህሳስ 28 ቀን ጾሙ ተፈትቶ የልደት በዓል ይከበራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜን ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው። ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዎች ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡

የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፥2-7፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋት በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ 8፥2፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡

ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

የጳጉሜን ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብባትም ወር ነች፡፡ ይህም ጳጉሜን የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና፡፡

#ወስብሐት-ለእግዚአብሔር-ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

💚 @mahiberekidusan 💚
💛 @mahiberekidusan 💛
❤️ @mahiberekidusan ❤️

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

30 Aug, 06:07


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።
#በዓለ_ዕረፍቱ_ለአቡነ_ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ ሃያ አራት  ቀን  በምግባር፣ በሃይማኖት ገድል ትሩፋታቸው የታወቁት አቡነ ተክለ ሃይማኖት  የዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ተክለ ሃይማኖት ማለት ‹‹የሃይማኖት ተክል፣ ተክለ አብ ተክለ ወልድ ተክለ መንፈስ ቅዱስ›› ማለት ነው፡፡ ጻድቁ አባታችን አባ ተክለ ሃይማኖት በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀሪያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን አንድ ሺህ አንድ መቶ ዘጠና ሰባት ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ጻድቁ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ማለትም ‹‹አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት የፈጠራቸውን አምላክ ያመሰገኑ ቅዱስ አባት ናቸው፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ፍሥሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ይኸውም “የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ” ማለት ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከልጅነታቸው ጀምሮ በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ከአቡነ ቄርሎስ (ጌርሎስ) ዲቁናንም ቅስናንም በተለያየ ጊዜ ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ አባታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡
ጻድቁ አባታችን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት መልሰዋል፡፡ ከ፩ ሺህ ፪፻፲፱ እስከ ከ፩ ሺህ ፪፻፳፪ ዓ.ም በተከታታይ ሦስት ዓመት፣ ከ፩ ሺህ ፪፻፳፫ እስከ ፩ ሺህ ፪፻፴፬ ዓ.ም ለ፲፪ ዓመታት በዳሞት በወላይታ ሀገር ሕዝቡን በማስተማር ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፤ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፤ በዚሁ ቦታ ዲያብሎስ ‹‹አምላክ ነኝ›› እያለ ለረጅም ዘመናት ሕዝቡን በማሳት የሚጠቀምበትን ዛፍ በተአምራት ከሥሩ ነቅለው አፍልሰውታል፡፡
ከከ፩ ሺህ ፪፻፴፬ እስከ ፩ ሺህ ፪፻፵፬ ዓ.ም ለ፲ ዓመታት በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ  በወሎ ክፍለ ሀገር በአማራ ሳይንት ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተማር፣ ከ፩ ሺህ ፪፻፵፬ እስከ ፩ ሺህ ፪፻፶፬  ዓ.ም አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ሐይቁን በእግራቸው እንደ ደረቅ መሬት በመርገጥ ወደ ደሴቱ በመግባት የአገልግሎትና የትሩፋት ሥራን ሠርተዋል፤ ከ፩ ሺህ ፪፻፶፬  እስከ ከ፩ ሺህ ፪፻፷፮ ዓ.ም ወደ ትግራይ ሄደው ከአቡነ አረጋዊ ገዳም ደብረ ዳሞ ውሰጥ በጊዜው ከነበሩት አበምኔት ከአባ ዮሐኒ ቆብና አስኬማ ተቀብለው ለ፲፪ ዓመታት በገዳሙ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት  ያመነኮሷቸው እጅግ ብዙዎች ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በአንብሮተ እድ የሾሟቸው ፲፪ቱ ከዋክብትን፣ ፬ ዐይና የተባሉትን እንዲሁም ነጫጭ ርግብ የተባሉትና ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቀጥሎ በደብረ ሊባኖስ የተሾሙት አፍርተዋል፡፡
ከ፩ ሺህ ፪፻፷፮ እስከ ፩ ሺህ ፪፻፷፯ ዓ.ም ለአንድ ዓመት የትግራይን ገዳማት በሙሉ በመጐብኘት ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ግብፅም በመሄድ በዚያ ያሉ ቅዱሳት መካናትን ትሩፋት ሠርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹ዳዳ›› በተባለ ስፍራ ይመለክ የነበረውን ፸፭ ክንድ የሚረዝመውን ዘንዶ በጸሎት ኃይል በመስቀል ምልክት አማትበው ገድለውታል፡፡ ሦስት ሺህ በጣዖት የሚያመልኩ ወንዶችን አስተምረው አጥምቀው አቊርበዋቸዋል፡፡ ከ፩ ሺህ ፪፻፷፯ እስከ ፩ ሺህ ፪፻፹፱ ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በደብረ ሊባኖስ ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ ፷ ጦሮችን (ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ፣ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን ደግሞ በግራ አስተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማምና ሞት፣ ነገረ መስቀልን በማሰብ በተመስጦ ሌትና ቀን ያለማቋረጥ በጾምና በጸሎት በአርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ ከቁመት ብዛት የተነሣ ጥር ፬ ቀን በ፩ ሺህ ፪፻፹፱ ዓ.ም አንድ የእግራቸው ሲሰበር ዕድሜያቸው ፺፪ ዓመት ነበር፡፡ ከ፩ ሺህ ፪፻፹፱ እስከ ፩ ሺህ ፪፻፺፮ ዓ.ም ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው  እንደ ምሰሶ ጸንተው፤ በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነትን ለምነዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያላቸው የመንግሥት ልብስ አለበሳቸው፡፡ በመስቀል ምልክት የተጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትን አቀዳጅቷቸዋል፡፡ ይኸውም ‹‹ስለ ቀናች ሃይማኖትህ፣ ሃይማኖትን ለማስተማር መላዋን ኢትዮጵያን ስለመዞርህ፣ ከአረማውያን ሕዝብ ጋር በሃይማኖት ስትታገል ደምህን ስለማፍሰስህ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ወርደህ ልዩ ልዩ የቅዱሳን ቦታዎች ስለመሳለምህ፣ በሰባት ዓመታት ቊመት አንዱ እግርህ ስለመሰበሩ፣ ስለብዙ ጾም ጸሎት ስግደትህ፣ ስለልብህ ንጽሕናና ቅድስና›› በማለት የሕይወት አክሊላትን ካቀዳጃቸው በኋላ ዝክራቸውን በማዘከር መታሰቢያቸውን የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ፍጹም ዋጋና ፍጹም ክብር እንደሚሰጣቸው ጌታችን ታላቅ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡  በመጨረሻም አባታችን ለ፲ ቀናት ያህል በተስቦ ሕመም ቆይተው ፈጣሪያቸው የገባላቸውን ቃል ኪዳን ለመነኰሳት መንፈሳውያን ልጆቻቸው ከነገሯቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡
ጸሎታቸውና በረከታቸው፣ ረድኤታቸውና ምልጃቸው በመላው ሕዝበ ክርስቲያንና አድሮ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡-ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት

@mahiberekidusan

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

30 Aug, 06:07


እንኳን ለጻድቁ ለአቡነ ተክለ ኃይማኖት የዕረፍት በዓል አደረሰን። የአባታችን በረከት፣ ረድኤታቸው አይለየን።

ማኅበረ ቅዱሳን (Mahibere Kidusan)

21 Aug, 17:23


#በስመ_አብ_ወወልድ_ወመንፈስ_ቅዱስ_አሐዱ_አምላክ_ዘለዓለም_ሥላሴ_አሜን።

#እንኳን_ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም_ጾመ_ፍልሰታ የፍቺ በዓል ና ለእመቤታችን የትንሳኤና የዕርገት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ!

በአጽናፈ  ዓለም የምትኖሩ/የምትገኙ ውድ  የክርስትና እምነት ተከታዮች የተዋህዶ ልጆች ክርስቲያናዊ ሰላምታችን በቅዱስ እግዚአብሔር ስም ይድረሳችሁ፡፡

#የእመቤታችን_ትንሣኤና_ዕርገት_

ነሐሴ 16 ቀን የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ያረገበት ዕለት ነው።
#እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም በዚህ ምድር የኖረችው ስልሳ_አራት ዓመት ነው፡፡ እነዚህ ዓመታት ሲተነተኑ ሦስት ዓመት በወላጆቿ ሐናና ኢያቄም ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አሥራ አምስት ዓመት ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር ነው፡፡
እመቤታችን እመ አምላክ በስዕለት የተወለደች ፣ በጸጋ የተሞላች፣ ባለሟልነትን የተጎናጸፈች፣አምላክን በአጭር ቁመት ፣በጠባብ ደረት የወሰነች፣የመለኮቱ እሳትነት ስጋዋን ሳያቃጥላት አምላክ ፈጣሪዋን ጸንሳ የወለደች ፣ በግብፅ በርሃ በስደት የተንከራተተች፣ በእውነቱ የህይወትን ምግብ አዝላ ስለእኛ የተራበች ፣የተጠማች፣ ከመዓር ከስኳር የሚጥም ጡቶቿን ያጠባችው ልጇ በቀራኒዮ ኮረብታ ተሰቅሎ ሲሞት መሪር እንባን ያለቀሰች፣ ለቅዱሳን ስደትን ለመባረክ ምሳሌ በመሆን የተጓዘች የተንገላታች ... ድንቅ ዘለዓለማዊ እናት ነች። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በቅዳሜ አርጋኖን ሶስቱ ያልተከፈቱ ደጆች ይልና ። ያብራራል ። አንድም በድንግልና መጽነሷን፦ ድንግልናዋን ሳይለውጠው እግዚአብሔር ወልድ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የመጸነሱ፤ በሁለተኛ ደረጃ ክርስቶስን በምትወልድበት ጊዜ የሴቶች ልማድ ሳያገኛት በጥበበ እግዚአብሔር መውለዷ፤ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ከወለደችው በኋላ ማህተመ ድንግልናዋ አልተፈታም። እመቤታችን ዘላለማዊ ድንግል ናት። የስጋ ብቻ ያይደለ የሀሳብም ድንግል ናት።

አጠር ባለ አገላለጽ አምላክን ከመውለዷ በፊት፣ አምላክን በምትወልድበት ጊዜ እና አምላክን ከወለደች በኋላ ፍጹም ዘላለማዊ ድንግል መሆኗን ሊቁ ያስረዳል ።  እመቤታችን ጥር 21 ቀን በ50 ዓ.ም ከዚህ አለም ድካም አርፋ ወደ ልጇ ተጠርታ ሄዳለች።

ወላድተ አምላክ ባረፈችበት ወቅት ቅዱሳን ሐዋርያት ክቡር ሥጋዋን ለማሳረፍ ወደ ጌቴ ሴማኒ ሲሔዱ አይሁድ "ቀድሞ ልጇ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ተመልሶም ይህን ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ በማስተማር ሕዝባችንን ወስደውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷም እንደ ልጇ ተነሳች እያሉ በማስተማር ሊያውኩን አይደለምን? ኑ! ተሰብስበን በእሳት እናቃጥላት" ብለው ክፉ ምክር ተማከሩ፡፡

አይሁድም ከተማከሩ በኋላ ከመካከላቸውም ብርቱ ጉልበተኛ ሰው የሆነው #ታውፋንያ የተባለ ቅድስት ሥጋዋን ከሐዋርያት ነጥቆ ለማስቀረት ክቡር ሥጋዋ ያለበትን የአልጋ ሸንኮር ሲይዝ በመልአከ እግዚአብሔር እጁ ተቆርጣ ከአልጋው ላይ ተንጠልጥላ ቀረች፤ ከዚህ የጥፋቱ ሥራው ተምሮ እመቤታችንን በመለመኑ እመቤታችን የተቆረጠች እጁን መልሳለታለች፡፡

ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የተቀደሰ ሥጋዋን ጌታችን ይወደው የነበረ ተብሎ የተነገረለት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ይዞ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሆነውን ሁሉ ለወንድሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ነገራቸው፡፡ እነሱም የእመቤታችን ሥጋ በክብር ለማሳረፍ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ፡፡

ከሁለተኛ ሱባኤ ቆይታቸው በኋላ በአሥራ አራተኛ ቀናቸው ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ ሰጣቸው፡፡ ሐዋርያትም በዝማሬና በታላቅ ምስጋና በጌቴ ሴማኔ ቀበሯት፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት› › ተብሎ ትንቢት የተናገረውን ሲተረጉሙት ‹‹ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታሳርፈው የመቅደስህ ታቦት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ›› ብለው ያመሰጥሩታል፡፡ /መዝ. 131፥8/፡፡

የእመቤታችንን ቅድስት ሥጋዋን ሐዋርያት ሲቀብሯት በሀገረ ስብከቱ ሕንድ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመናሰረገላ ተጭኖ ሲመለስ እመቤታችን ስታርግ አገኛት። ለማረጓ ምልክት ይሆን ዘንድ ለምልክት እንዲሆነው ሰበኗን (የመግነዟን ጨርቅ) ተቀብሏት ይለያያሉ፡፡ ለወንድሞቹ ለቅዱሳን ሐዋርያት ያየውን ምስጢር/የተመለከተውን ድንቅ ተዓምር/የወላድተ አምላክን ዕርገት ነገራቸው፡፡

እመቤታችን ለበረከት የሰጠችውንም ሰበን አሳያቸውና አካፈላቸው ፤ ሐዋርያት ‹ ‹ዕርገቷን እንዴት እሱ ብቻ ተመልክቶ ለምን እኛ ይቀርብናል› › ብለው በዓመቱ ነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ገቡ፡፡ ነሐሴ 16 ቀን የልባቸው መሻት ተፈጸመላቸው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቀ (ረዳት) ቄስ፣ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ (ዋና ዲያቆን) አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው፡፡

በንጽህና፣ በፍጹም እምነት ፣በትኅትና የያዙት በተስፋ የጠበቁት በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ያቀረቡት ሱባኤም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገቷን ለማየት አበቃቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን መሠረት አድርጋ ከነሐሴ 1-16 ጾመ ፍልሰታ በማለት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ አድርገን እንድንጠቀምበት ሥርዐት ሠራችልን፡፡

በቅዱሳን አበው በነቢያትና በሐዋርያት በቅዱሳን ሁሉ መሠረት ላይ የታነጽን ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች በየዓመቱ ይህን ጾም በሱባኤ በማሳለፍ ከእመቤታችን ጸጋና በረከት ተሳታፊዎች እንሆናለን፤ ሆነናልም፡፡ ለቅዱሳን ሐዋርያት ትንሳኤዋን ፣ ዕርገቷን እንደገለጸችላቸው ለእኛም ምስጢርን ፣ እውቀትን ታድለን ። ትግለጽልን ። የአመት ሰው ይበለን። መልካም በዓል

ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከወላድተ አምላክ በረከት፣ረድኤት ፍቅር፣ምልጃና ጸሎት ተካፋዮች ያድርገን፡፡
                     አሜን!
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን🙏🙏🙏
#ለወዳጅዎ_ዘመድ_ ፣_ለተዋህዶ_ልጆች #ሼር_ያድርጉ!
💚 @mahiberekidusan 💚
💛 @mahiberekidusan 💛
❤️ @mahiberekidusan

2,237

subscribers

382

photos

2

videos