ኅዳር ፮ ቀን የአርያም ንግሥት፣ የፍጥረታት ሁሉ እመቤት፣ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ አረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍንና ቅድስት ሰሎሜን አስከትላ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት የስደት እና የመከራ ዓመታት በኋላ በስተደቡብ የምትገኘው ደብረ ቁስቋም ላይ ያረፉችበት ዕለት ይከበራል፡፡
ደብረ ቁስቋም በደቡብ ግብጽ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ይህ ተራራ የተቀደሰ ተራራ ስለመሆኑ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ታኦፊሎጎስ በድርሳነ ማርያም ‹‹ይህም ከሀገሮቹ ሁሉ ተራሮች የሚበልጥ (የተለየ) ከፍ ያለ ተራራ ነው፡፡ በውስጡ ቅዱስ አግዚአብሔር ያድራል፡፡ ይህንን ተራራ የእግዚአብሔር ልጅ ወዶታል፤ አክብሮታልምና፤ ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ከተቀደሰች እናቱ ጋር አድሮባታልና፡፡ ከመላእክት ቤት ያድር ዘንድ አልወደደም፤ ቢታንያንም አልመረጠም፡፡ ከተራራው ላይ ባለች ገዳም ቤት ውስጥ አደረ እንጂ፤ ነቢዩ ዳዊት የጽዮንን ተራራ ወደደ፤ በአርያምም መቅደሱን ሠራ እንዳለ፡፡››
በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ዮሴፍ በሕልሙ ‹‹ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ›› ባለው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫-፲፭)
በስደቱም ጣዖታተ ግብጽ እየተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በእነርሱም አድረው ሰውን ሲያስቱ የነበሩ አጋንንትም ሲሸሹ ታይተዋል፤ ደግሞም ጌታችን ዳግማዊ አዳም ነውና በምክረ ከይሲ (ዲያብሎስ) ምክንያት ተሰዶ የነበረው ቀዳማዊ አዳምን ለመካስ ተሰደደ፤ በዚህም አጋንንትን ከሰው ልቡና አውጥቶ አሳደደ፡፡
እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር ከመሰደዷ አስቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብጽ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደ ግብጽ ይወርዳል›› ተብሎም በተናገረው መሠረት ትንቢቱ ተፈጽሟል፡፡ (ኢሳ. ፲፱፥፩)
ጌታችን ኢየሱስ በደብረ ቁስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰበሰባቸው፤ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቁርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር በቁስቋም ተራራ ስድስት ወራትን ያረፈች ሲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፮ የእነርሱን ስደትና ወደ ሀገራቸው እስራኤል መመለሳቸውን በማስታወስ ታከብራለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!!
ምንጭ፤ ድርሳነ ማርያም (ትርጉም ፳፻፫ ዓ.ም)
ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር
ፍኖተ ሰላም ሚዲያ