------------------------------
15.“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።”
#ያበጃት_ይጠብቃትም_ዘንድ ፦ ስለዚህ ክፍለ ምንባብ ሰቨርያን እንዲህ ይላል «ይሰራና ይጠብቃትም ዘንድ የሚለው ሌባ ሳይኖር አላፊ መንገደኛም ሳይኖር ወይም ሆን ብሎ ክፉ የሚያደርግ ሰውም ሳይኖር ከማን ነው የሚጠብቃት? ከራሱ ነው የሚጠብቃት።ትእዛዙን ካልተላለፈ ገነትን አያጣትም፥ትእዛዙን መጠበቅ ለሰውልጅ ስራ ነው በዚህ ስራም ራሱን ይጠብቃል የተሰጠችውን ገነትንም ይጠብቃል»
ሰውን በመልኩ እንደ ምሳሌው ከፈጠረው በኋላ በኤደን ወደ አዘጋጀለት ልዩ የአትክልት ስፍራ አስገባው።
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
16.“እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤
17.ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።”
የታዛዥነቱ መለኪያ ቀዳሚው ትእዛዝ ይህ ነው ዛፉ መርዛማ ሆኖ ወይም የሆነ ልዩ የዕውቀት ሃይል ኖሮት ሳይሆን ቁጥር 9 እንደተብራራው መልካምና ክፉ የተባሉት የመኖር ሁኔታዎች የሰው ልጅ ለተሰጠው ትእዛዝ ባለው ግብረ መልስ የሚወሰን ነው።ምክንያቱም መልካም ብቻ ነው የሚያውቀው ዛፏን አትንካት ተብሏል ካልነካትም በዚህ መልካምነት ብቻ ይኖራል፥ትእዛዙን ከተላለፈና ዛፏን ቢበላ ግን ክፉን ያውቃል ማለትም በሞት(ከእግዚአብሔር መለየት፥የስጋና የነፍስ መለያየት) መቀጣት መጎስቆልን ያውቃል።ክፉና መልካም የሚያስታውቅ መባሉ ስለዚህ ነው።
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
18.“እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት።”
#የሚመቸውን_ረዳት ፦ ረዳት ባርያ ወይም ተገዢ ሳይሆን በባህርይ በሙላት እርሱን የምታክል ሆና ለዓይኑ ደስ የምታሰኝ ከእርሱ ጋር በደስታ የምትነጋገር በሁሉም ከእርሱ ጋር የምትስማማ ለሁኔታውና ለፍላጎቱ በሙሉ መልስ የምትሰጥ...
#እንፍጠርለት ፦ በምዕራፍ 1፥26 እንዳለው ትንታኔ በተመሳሳይ እዚህ ምንባብም እንጠቀመዋለን። እግዚአብሔር ሌሎች ፍጡራንን እያማከረ ሳይሆን፥ የመፍጠር ውሳኔ ምክረ-ሐሳብ ከራሱ ጋር ብቻ እንጂ ሌሎችን አላማከረምና በራሱ ከራሱጋር ማሰቡንና መወሰኑን የሚያሳይ ነው፥ ልክ እኛ እስኪ ዛሬ ይሄን ላድርግ ይሄን ልስራ ብለን በህሊናችን ከራሳችን ጋር እንደምንመክረው ነው።