ዕዳ የተሻረለት ሎሌ ፤
ምነው ዕዳ ይጠይቃል።
ቀንበር ያነሱለት በሬ ፤
እንዴት ቀንበር ይናፍቃል።
ባለወተት የማር ምድር ፤
እየሸተተን መሃዛው፤
የግብፅ ባርነት ሽንኩርት ፤
እንዴት ቀልባችንን ገዛው።
ይገርማል...
የሞተን እባብ ቢቀብሩት
እንደሚቆም አፈር ልሶ፤
አንገታችን ምነው ቀረ
እንደ ሎጥ ሚስት ተመልሶ።
ክብር የተረፈው አምላክ
ለሱ ክብር ቢያስለቅቀን፤
ምነው በጣዖት ቀየርነው
የሰጠንን ወርቅ አድቅቀን።
ያለውን ለሰጠን ወዳጅ
ለምን ትራፊ እንሰጣለን፤
ጊዜ ላይ ላቆመን አምላክ
እንዴት ጊዜን እናጣለን።
እጦት ሲዘን ከእግሮቹ ስር
ቀንም ሌትም እንዳለፋን፤
ቤታችንን ሲጎበኘው
ምነው ከቤቱ ደጅ ጠፋን
እባካችሁ ..!
የአዳም እና ኤዋን ጥፋት ፤
በኛም ዘመን ሳይሠለስ
በእርሱ መንገድ ብቻ እንጓዝ ፤
ከራስ መንገድ እንመለስ
ይብቃን ይብቃን የራስ ተስፋ፤
የራስ ባህር፣ የራስ መረብ
በጉድለት መባዘን ይብቃን ፤
ወደ ሙላቱ እንቅረብ
ሙሉ እንጀራ አይጋግርም ፤
ሰባራ የሸክላ ምጣድ
ክርስቲያን ፍቃዱን እንጂ ፤
አይኖርም የራሱን ፍቃድ።
✍የሱመልስ
✝ @Excellent_youth ✝
✝ @Excellent_youth ✝