10ቱ ታካሚዎችን መርጃ ልዕልናዎች‼️🙏
እንደ ማህበረሰብ የመረዳዳት እና የመተጋገዝ ባህል ቢኖረንም በካንሰር የተያዙትን ጓደኞቻችንን፣ ዘመዶቻችንን፣ ጎረቤቶቻችንን እንዲሁም በግል የማናቃቸውን ግለሰቦች ለመርዳት ያለን ቁርጠኝነት ግን እምብዛም ነው። ይህንን በድፍረት እንድከትብ ያስገደደኝ በሀገራችን ያለውን ጥቂት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዋቢ በማድረግ ነው። መንግስታዊ ያልሆኑ በካንሰር ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች ቢቆጠሩ በሽታው ካደረሰው ማህበራዊ ቀውስ አንፃር ምንም ነው ሊባል ይቻላል። አለም አቀፍ ጥናቶች እንደተነበዩት በኢትዮጵያ በየአመቱ ቢያንስ 77,000 ሰው በካንሰር እንደሚያዝ ሲሆን ወደ 50,000 ገደማው ደግሞ በየአመቱ በዚህ በሽታ ይሞታል። ለዛሬ ታድያ አንድ ሰው እንደ ግለሰብ እነዚህን የካንሰር ታካሚዎች በቀላሉ ሊረዳባቸው የሚችልባቸውን መንገዶች እንዲህ ሰድሬያቸዋለው።
1) የካንሰር ታካሚዎችን በሚታከሙባቸው ሆስፒታሎች(በተፈቀደ ሰዓት) ወይም በማረፊያ ቦታዎች ለመጎብኘት/ለመጠየቅ መሞከር!!!
የካንሰር ታካሚ የሆኑ ግለሰቦች በህብረተሰቡ በሚደርስባቸው ጫና እራሳቸውን በቀላሉ ከማህበረሰባዊው መስተጋብሮች የሚያገሉ ስለሆነ ለብቸኝነት የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው። እንደ ሀገራችን ባሉ በኢኮኖሚው ዝቅ ባሉ ሀገራቶች ደግሞ ቤተሰብን የማስተዳደር ጫና ስለሚኖር ታካሚዎች ብቻቸውን የመታከም ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ይህን በመረዳት የታካሚዎችን የግለኝተኝነት መብት(Privacy) በማክበር የጥየቃ ፕሮግራም ማዘጋጀት ይቻላል።
2) የካንሰር ታካሚዎችን የሀይማኖት መብት ባከበረ መልኩ የፀሎት እና የስነ ልቦና ማበረታቻ መድረኮችን ማዘጋጀት፤ ይህም ለእነሱ የምንሰጠው ግዜ በውስጣቸው ያለውን የስነ ልቦና ጫና እንዲቀንስ ያደርገዋል።
3) ቁምነገር እና ዋዝን ያዘለ አጭር የሞባይል መልዕክት ለመላክ መሞከር፤ ቀልዶችን በወረቀት ፅፎ መስጠት ወይም ከቻልን በአካል ተገኝተን እያዋዛን መንገር እንዲሁም የፖስት ካርድ ስጦታን መስጠት ቢቻል መልካም ነው።
4) በራስ ተነሳሽነት የታካሚውን ስራ ሊያቀሉ የሚችሉ ነገሮችን ነቅሶ አውጥቶ እነዛን ጉዳዮች መፈፀም። በተለይ የታካሚውን ልጆች መንከባከብ፣ ምግብ አብስሎ መመገብ፣ ፀጉር መስራት እና ንፅህናን መጠበቅ እና የመሳሰሉት
5) ታካሚዎቹን ባገኘናቸው አጋጣሚ ለማቀፍ መሞከር፦ ዕቅፋት በራሱ የሚሰጠው ጥሩ መልዕክት አለ! ብዙ ሰው የማያቀው ነገር ቢኖር የካንሰር ህክምናን ውድነት እና በቀላሉ መገኘት አለመቻሉን ነው። ስለሆነ ከተቻለ ከሞራል ድጋፉ በተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግባቸው የሚችልባቸውን መንገዶች ማፈላለግ እንደ ትልቅ መፍትሄ ተቀምጧል።
6) ደም መለገስ፦ የካንሰር በሽታን ወይም ህክምናውን ተከትሎ የሚመጣን የደም ማነስ ለማዳን ደምን መለገስ ፍቱን አማራጭ ነው። በተለይ በደም ካንሰር ለሚሰቃዩ ጨቅላ ህፃናት በህይወት የመኖር ተስፋቸውን ያለመልማል‼️
7) ሂውመን ሄር ወይም ዊግ መለገስ፦ የካንሰር ህክምናን ተከትሎ የሚመጣ ጊዜያዊ የፀጉር መመለጥ ስለሚኖር ብዙ ታካሚዎች ለስነ-አዕምሮ እንዲሁም ለስነ-ልቦና ጫና ስለሚዳረጉ በተቻለ አቅም የፀጉር ዊጎችን ወይም ተፈጥሯዊ ፀጉሮችን መለገስ ይቻላል።
8) የጡት ማስያዣን መለገስ፦ በጡት ካንሰር ለተያዙ ዕንስቶች እንደ ዋንኛ ህክምና የሚቆጠረው ጡትን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግደው ቀዶ ጥገና እራሱን የቻሉ አሉታዊ ተፅንኦዎች ይኖሩታል። ስለዚህ እንስቷን ሊያግዝ የሚችል በበሽታው ያልተጠቃውን ሌላኛው ጡት ቀዶ ጥገና ከተሰራው የጡት ደረት ጋር የሚያይዝ ጡት ማስያዣ(Bra) መርዳት ይቻላል።
9) የቤተሰብን ደስታ(ልደት፣ ሰርግ......)፣ የትልልቅ ድግሶችን ከፊል ወጪ እንዲሁም አመት በዓሎችን ያማከለ የመረዳጃ ዝግጅት ከታካሚዎች ጋር ሰብሰብ ብሎ ማክበር ይቻላል። ህይወት ሁሌም የራሷ ፈተና ቢኖራትም ለታካሚዎቹ ይህን ማድረግ ከበሽታቸው ውስጣዊ ህመም(መንፈሳዊ) ይፈውሳል።
10) በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ቅጥር ግቢ በመገኘት የታካሚዎችን ችግሮች ለመስማት መሞከር ከዛም የተቻለን ያክል መፍትሄዎቹ ላይ መስራት። በተለይ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ በሐኪም የታዘዙ የህክምና ግልጋሎት መስጫ ዕቃዎችን እንዲሁም የአንድ ቀን የህክምና ወጪያቸውን በመሸፈን ሀሴትን ከታካሚዎች ገር ማድረግ ይቻላል።
ሆስፒታሎችን ከሩቁ ሳይሆን ውስጣቸው ገብተን ከጤና ባለሞያው ጋር በመመካከር ለእውነተኛ ተረጂዎች እውነተኛ ዕርዳታን እናድርግ‼️
ዶ/ር ሚካኤል ሻውል ለማ
በካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር